‘በጌታ ጠንክሩ’
‘በጌታ ጠንክሩ’
“በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ።”—ኤፌሶን 6:10
1. (ሀ) ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ምን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ውጊያ ተካሂዶ ነበር? (ለ) ዳዊት በውጊያው ድል ሊነሳ የቻለው እንዴት ነበር?
ጊዜው ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ሲሆን በአንድ የጦር አውድማ ላይ ሁለት ተፋላሚዎች ሠራዊቶቻቸውን ወክለው ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል። በዕድሜ ትንሹ ዳዊት የሚባል እረኛ ነው። ፊት ለፊቱ የተለየ ብርታትና ቁመት ያለው ጎልያድ የሚባል ሰው ቆሟል። ይህ ሰው የለበሰው ጥሩር ብቻ እንኳ 57 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን ግዙፍ ጦርና ትልቅ ሰይፍ ይዟል። ዳዊት ምንም ዓይነት የጦር ትጥቅ ያላደረገ ከመሆኑም ሌላ የያዘው ወንጭፍ ብቻ ነው። ግዙፉ ፍልስጥኤማዊ ጎልያድ ሊገጥመው የመጣው እስራኤላዊ አንድ ፍሬ ልጅ መሆኑን ሲመለከት እንደተሰደበ ተሰማው። (1 ሳሙኤል 17:42-44) በሁለቱም ወገን ላሉ ተመልካቾች አሸናፊው ማን እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነበር። ሆኖም ኃያላን ሁልጊዜ በጦርነት ድል ይቀናቸዋል ማለት አይደለም። (መክብብ 9:11) ዳዊት በይሖዋ ብርታት ስለተማመነ በውጊያው አሸናፊ ሊሆን ችሏል። “ሰልፉ የእግዚአብሔር” እንደሆነ ተናግሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚናገረው “ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው።”—1 ሳሙኤል 17:47, 50
2. ክርስቲያኖች በምን ዓይነት ጦርነት ውስጥ ናቸው?
2 ክርስቲያኖች በሥጋዊ ጦርነት አይካፈሉም። ከሰዎች ሁሉ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም በጣም ኃያላን ከሆኑ ጠላቶቻቸው ጋር መንፈሳዊ ውጊያ አለባቸው። (ሮሜ 12:18) ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ የመጨረሻ ምዕራፍ ውስጥ እያንዳንዱን ክርስቲያን ስለሚመለከት አንድ ጦርነት እንዲህ ሲል ጠቅሷል፦ “ተጋድሎአችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው።”—ኤፌሶን 6:12
3. በኤፌሶን 6:10 መሠረት በውጊያው ለማሸነፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 እነዚህ ‘ርኩሳን መንፈሳዊ ሰራዊት’ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የሚፈልጉት ሰይጣንና አጋንንቱ ናቸው። በኃይል ከእኛ በእጅጉ ስለሚበልጡ ከዳዊት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ሲሆን በይሖዋ ብርታት ካልተማመንን በስተቀር ሊሳካልን አይችልም። ጳውሎስ “በጌታና [በይሖዋና] ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ የተገባ ነው። (ኤፌሶን 6:10) ጳውሎስ ይህን ምክር ከሰጠ በኋላ ውጊያውን በአሸናፊነት እንድንወጣ የሚያስችሉንን መንፈሳዊ ዝግጅቶችና ክርስቲያናዊ ባሕርያት ጠቅሷል።—ኤፌሶን 6:11-17
4. በዚህ ርዕስ ሥር የምንመለከታቸው ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
4 እስቲ በመጀመሪያ ጠላቶቻችን ያላቸውን ጥንካሬና የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች በሚመለከት ቅዱሳን ጽሑፎች ምን እንደሚሉ እንመልከት። ከዚያም ራሳችንን ለመከላከል ልንቀይሰው ስለሚገባን ስልት እንመለከታለን። የይሖዋን መመሪያዎች የምንከተል ከሆነ ጠላቶቻችን ሊያሸንፉን እንደማይችሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
ከርኩሳን መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር የምናደርገው ትግል
5. በኤፌሶን 6:12 ላይ ‘ተጋድሎ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሰይጣን የሚጠቀምበትን ዘዴ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ “ተጋድሎአችን . . . በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር” እንደሆነ ተናግሯል። ቀንደኛው ርኩስ መንፈስ ‘የአጋንንንት አለቃ’ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 12:24-26) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ ‘ተጋድሎአችንን’ ከትግል ወይም ከግብግብ ጋር ያመሳስለዋል። በጥንቷ ግሪክ ይካሄድ በነበረው ትግል እያንዳንዱ ተፋላሚ ተጋጣሚው ሚዛኑን እንዲስት በማድረግ መሬት ላይ ለመጣል ይሞክራል። በተመሳሳይም ዲያብሎስ መንፈሳዊ ሚዛናችንን ለማሳት ይፈልጋል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?
6. ዲያብሎስ እምነታችንን ለመሸርሸር የተለያዩ ዘዴዎችን ሊጠቀም እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመህ አስረዳ።
6 ዲያብሎስ እባብ፣ የሚያገሳ አንበሳ አልፎ ተርፎም የብርሃን መልአክ መስሎ ሊቀርብ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:3, 14፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) በእኛ ላይ ስደት ለመቆስቆስ ወይም እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ሰብዓዊ ወኪሎቹን ሊጠቀም ይችላል። (ራእይ 2:10) ዲያብሎስ መላው ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ስለሚገኝ እኛን ለማጥመድ የዓለምን ምኞቶችና ማራኪ የሚመስሉ ነገሮች ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:26፤ 1 ዮሐንስ 2:16፤ 5:19) እንደ ሔዋን ሁሉ እኛንም ዓለማዊ ወይም የክህደት አስተሳሰቦችን ተጠቅሞ ሊያታልለን ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 2:14
7. አጋንንት ምን የአቅም ገደብ አለባቸው? እኛስ ምን እርዳታ አለን?
7 ሰይጣንና አጋንንቱ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውና የረቀቁ መሣሪያዎች የሚጠቀሙ ቢመስሉም አቅማቸው ውስን ነው። እነዚህ ርኩሳን መናፍስት የሰማዩ አባታችንን የሚያሳዝኑ መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈጽም ሊያስገድዱን አይችሉም። የመምረጥ ነጻነት ያለን ከመሆኑም በላይ አሳባችንንና ድርጊታችንን መቆጣጠር እንችላለን። ከዚህም በላይ የምንዋጋው ብቻችንን አይደለም። እንደ ኤልሳዕ ዘመን ሁሉ በዛሬውም ጊዜ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉ።” (2 ነገሥት 6:16) ለአምላክ የምንገዛና ዲያብሎስን የምንቃወም ከሆነ እርሱ ከእኛ እንደሚሸሽ መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ሰጥቶናል።—ያዕቆብ 4:7
የሰይጣንን ዘዴዎች አትሳቱ
8, 9. ሰይጣን፣ ኢዮብ ጽኑ አቋሙን እንዲያላላ ለማድረግ ምን ፈተናዎች አምጥቶበት ነበር? ዛሬስ ምን መንፈሳዊ አደጋዎች ተጋርጠውብናል?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዋና ዋና ዘዴዎች ስለሚገልጽልን ዕቅዱ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ዲያብሎስ በጻድቁ ኢዮብ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ኪሳራ አድርሶበታል፣ የሚወዳቸውን ሰዎች በሞት ነጥቆታል፣ ከቤተሰቡ ተቃውሞ ቆስቁሶበታል፣ አካላዊ ሥቃይ አምጥቶበታል እንዲሁም ወዳጅ ተብዬዎቹ በሐሰት እንዲወነጅሉት አድርጓል። ኢዮብ ተጨንቆ የነበረ ከመሆኑም በላይ አምላክ እንደተወው ተሰምቶታል። (ኢዮብ 10:1, 2) ሰይጣን በዛሬው ጊዜ እነዚህን ችግሮች በቀጥታ ባያመጣም በርካታ ክርስቲያኖች በእነዚህ ችግሮች የሚነኩ ሲሆን ዲያብሎስ ችግሮቹን የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም ይጠቀምባቸዋል።
9 በዚህ የመጨረሻ ዘመን መንፈሳዊ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል። የምንኖረው ከመንፈሳዊ ግቦች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጥበት ዓለም ውስጥ ነው። መገናኛ ብዙኃን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ የጾታ ግንኙነቶች የሐዘን ሳይሆን የደስታ ምንጭ እንደሆኑ አድርገው በተደጋጋሚ ያቀርባሉ። እንዲሁም ብዙዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ‘ለእምነት ካልተጋደልን’ በስተቀር እንዲህ ያለው አስተሳሰብ መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንስት ሊያደርገን ይችላል።—ይሁዳ 3
10-12. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ውስጥ የሰጠው አንደኛው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? (ለ) መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን እንዴት ‘ሊታፈን’ እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።
10 ሰይጣን ስኬታማ ከሆነባቸው ዘዴዎች መካከል ከሁሉ የላቀው በዓለምና ቁሳዊ ግቦችን በማሳደድ ተግባር እንድንዋጥ ማድረግ ነው። ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ ‘የመንግሥቱ ቃል ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ሊታነቅ እንደሚችል’ አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 13:18, 22) ‘ማነቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማፈን” የሚል ትርጉም አለው።
11 በሐሩር ክልል በሚገኙ ደኖች ውስጥ በሌላ ዛፍ ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚያድግ አንድ የዛፍ ዓይነት አለ። ይህ ዛፍ እያደር እየጠነከሩ የሚሄዱ ሥሮችን በማውጣት ሌላኛውን ዛፍ ዙሪያውን ተብትቦ የሚይዘው ከመሆኑም በላይ እላዩ ላይ ይጠመጠምበታል። ከዚያም በበርካታ ሥሮቹ አማካኝነት በአፈሩ ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ይሻማዋል። እንዲሁም ወደ ላይ በማደግና ቅጠሎቹን በማንዠርገግ የፀሐይ ብርሃን እንዳያገኝ ያደርገዋል። በመጨረሻም ዋናው ዛፍ ይሞታል።
12 በተመሳሳይም የዚህ ዓለም ጭንቀትና ባለጠጋ የመሆን ምኞት እንዲሁም የተንደላቀቀ አኗኗር ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ቀስ በቀስ ሊያሟጥጥብን ይችላል። ትኩረታችን በዓለም ጉዳዮች ላይ ስለሚያርፍ ውሎ አድሮ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ችላ ልንልና ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የመቅረት ልማድ ሊጠናወተን ይችላል። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ እንድንራብ ያደርገናል። ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ለቁሳዊ ግቦቻችን ቅድሚያ ልንሰጥና በመጨረሻ በቀላሉ የሰይጣን ሲሳይ ልንሆን እንችላለን።
ጸንተን መቆም ያስፈልገናል
13, 14. ሰይጣን ጥቃት ሲሰነዝርብን ምን አቋም መውሰድ ይኖርብናል?
13 ጳውሎስ ‘የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ እንዲቋቋሙ’ የእምነት ባልንጀሮቹን አሳስቧቸው ነበር። (ኤፌሶን 6:11) ዲያብሎስንና አጋንንቱን ማጥፋት እንደማንችል የታወቀ ነው። አምላክ ይህን ኃላፊነት የሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 20:1, 2) ይሁን እንጂ በሰይጣን እንዳንሸነፍ እርሱ እስኪጠፋ ድረስ ጥቃቱን ‘መቋቋም’ ወይም ጸንተን መቆም ይኖርብናል።
14 ሐዋርያው ጴጥሮስም የሰይጣንን ጥቃት የመቋቋምን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል። በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) በእርግጥም፣ ዲያብሎስ እንደሚያገሳ አንበሳ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ጸንቶ ለመቆም የመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ድጋፍ በጣም አስፈላጊ ነው።
15, 16. የእምነት ባልንጀሮቻችን ድጋፍ ጸንተን እንድንቆም ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ተናገር።
15 በአፍሪካ የሣር ምድር ውስጥ ድኩላዎች አንበሳ ሲያገሳ ሲሰሙ ከአደጋ ለማምለጥ አካባቢውን ጥለው ይፈረጥጣሉ። ዝሆኖች የሚወስዱት እርምጃ ግን እርስ በርስ በመረዳዳት ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ኤለፋንትስ—ጀንትል ጃይንትስ ኦቭ አፍሪካ ኤንድ ኤዢያ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ የዝሆን መንጋ አብዛኛውን ጊዜ ራሱን ከጥቃት የሚከላከለው ክብ በመሥራት ነው፤ ትላልቆቹ ፊታቸውን ወደ አደጋው አዙረው ሲቆሙ ትንንሾቹ መሃል ገብተው ይሸሸጋሉ።” ዝሆኖች እንዲህ ባለ ቆራጥነትና ሕብረት ጠላታቸውን ስለሚጋፈጡ ግልገሎቻቸው እንኳ ብዙውን ጊዜ በአንበሶች አይጠቁም።
16 እኛም ሰይጣንና አጋንንቱ አንድ ዓይነት ጥቃት ሲሰነዝሩብን በእምነት ጠንካራ ከሆኑ ወንድሞቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ሕብረት መፍጠር ይኖርብናል። ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት አንዳንድ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ “የብርታት ምንጭ” እንደሆኑለት ተናግሯል። (ቆላስይስ 4:10, 11 NW) “የብርታት ምንጭ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት እንደሚናገረው “ቃሉ በግስ መልክ ሲቀመጥ የመቆጥቆጥ ስሜት የሚያስታግሱ መድኃኒቶችን ያመለክታል።” የጎለመሱ የይሖዋ አምላኪዎች የሚሰጡት ድጋፍ እረፍት እንደሚሰጥ ቅባት ስሜታዊ ወይም አካላዊ ሥቃይን ያስታግሳል።
17. ለአምላክ ታማኝ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
17 ከክርስቲያን ወንድሞቻችን የምናገኘው ማበረታቻ አምላክን በታማኝነት ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ንቁ ናቸው። (ያዕቆብ 5:13-15) ታማኝነታችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዱን ሌሎች ነገሮች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማጥናት እንዲሁም በጉባኤም ሆነ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ናቸው። ከአምላክ ጋር ያለን የጠበቀ ዝምድናም ለእርሱ ታማኝ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል። በእርግጥም፣ ስንበላም ሆነ ስንጠጣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስናደርግ ሁሉን ለአምላክ ክብር ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ መታመናችን እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ጎዳና መከተላችንን ለመቀጠል በጣም አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 37:5
18. አስቸጋሪ ሁኔታዎች ኃይላችንን ቢያሟጥጡብን እንኳ መታከት የማይኖርብን ለምንድን ነው?
18 አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ጥቃት የሚሰነዝርብን በመንፈሳዊ በምንዳከምበት ወቅት ነው። አንበሳ የሚያሳድደው የተዳከመን እንስሳ ነው። የቤተሰብ ችግሮች፣ የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ወይም ሕመም መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን ሊያሟጥጥብን ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” በማለት እንደተናገረው አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ከማድረግ አንታክት። (2 ቆሮንቶስ 12:10፤ ገላትያ 6:9፤ 2 ተሰሎንቄ 3:13) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ብርታት ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር የምንል ከሆነ የአምላክ ኃይል ሰብዓዊ ድክመቶቻችንን ይሸፍንልናል ማለቱ ነበር። ዳዊት ጎልያድን ድል ማድረጉ አምላክ ለሕዝቦቹ ብርታት መስጠት እንደሚችልና እንደሚያበረታቸውም ያሳያል። በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ፈታኝ ሁኔታዎች ባጋጠሟቸው ጊዜ አምላክ ብርታት እንደሰጣቸው ሊመሰክሩ ይችላሉ።—ዳንኤል 10:19
19. ይሖዋ አገልጋዮቹን ሊያበረታ እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር።
19 አንድ ባልና ሚስት ከአምላክ ያገኙትን ድጋፍ በሚመለከት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ባለፉት ዓመታት በአንድነት ይሖዋን አገልግለናል። ብዙ በረከቶችን ከማግኘታችንም በላይ በርካታ ግሩም ሕዝቦችን አውቀናል። በተጨማሪም ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት እንድንቋቋም አሠልጥኖናል እንዲሁም አበርትቶናል። እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም አንዳንድ ነገሮች ለምን እንደደረሱብን ያልተረዳንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም እንኳ ይሖዋ ምን ጊዜም ከጎናችን እንደሆነ ተገንዝበናል።”
20. ይሖዋ ምንጊዜም ሕዝቦቹን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
20 ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹን ለመደገፍና ለማበርታት እጁ አጭር አይደለም። (ኢሳይያስ 59:1) መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 145:14) በእርግጥም የሰማዩ አባታችን ይሖዋ ‘ሸክማችንን በየዕለቱ ይሸከምልናል’፤ እንዲሁም የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል።—መዝሙር 68:19
‘የእግዚአብሔር ሙሉ የጦር ዕቃ’ ያስፈልገናል
21. ጳውሎስ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ አስፈላጊ መሆኑን ያጎላው እንዴት ነው?
21 እስከ አሁን ድረስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን አንዳንድ ዘዴዎች እንዲሁም እርሱ የሚሰነዝርብንን ጥቃት መቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ተመልክተናል። አሁን ደግሞ እምነታችንን ከጥቃት እንድንጠብቅ የሚረዳንን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ዝግጅት መመልከት ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሰይጣንን የተንኰል ሥራ እንድንቋቋምና ከርኩሳን መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር ያለብንን ትግል በአሸናፊነት እንድንወጣ የሚያስፈልገንን ወሳኝ ነገር ሁለት ጊዜ ጠቅሷል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። . . . ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና።”—ኤፌሶን 6:11, 13
22, 23. (ሀ) መንፈሳዊ ትጥቃችን ምን ነገሮችን ይጨምራል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
22 አዎን፣ “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” መልበስ ይኖርብናል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የላከውን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት በሮም ወታደር ጥበቃ ሥር የነበረ ሲሆን ይህ ወታደር አንዳንድ ጊዜ የተሟላ የጦር ትጥቅ ሳይለብስ አይቀርም። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ስለሚያስፈልገው መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ እንዲጽፍ የገፋፋው አምላክ ነበር።
23 ከአምላክ በሚገኘው በዚህ የጦር ትጥቅ ውስጥ አንድ ክርስቲያን ሊያፈራቸው የሚገቡ ባሕርያትና ይሖዋ ያደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ይገኙበታል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የዚህን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ክፍሎች አንድ በአንድ እንመረምራለን። እንዲህ ማድረጋችን ላለብን መንፈሳዊ ጦርነት የታጠቅነው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዲሁም ሰይጣን ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ስኬታማ ለመሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልን ግሩም ምሳሌ እንዴት እንደሚረዳን እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ውጊያ አለባቸው?
• ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል አንዳንዶቹን ተናገር።
• ክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚያደርጉልን ድጋፍ የሚያበረታን እንዴት ነው?
• የምንተማመነው ከማን በምናገኘው ብርታት መሆን ይኖርበታል? ለምንስ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ‘ከርኩሳን መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር ትግል አለባቸው’
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዚህ ዓለም ጭንቀት የመንግሥቱን ቃል ሊያንቅ ይችላል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ወንድሞቻችን “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልን ይችላሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ብርታት እንዲሰጥህ ትጸልያለህ?