እንጀራ ከገበታ እንዳይጠፋ ትልቅ ድርሻ የሚያበረክተው ወፍጮ
እንጀራ ከገበታ እንዳይጠፋ ትልቅ ድርሻ የሚያበረክተው ወፍጮ
እንጀራ የብዙዎች የዕለት ጉርስ ነው። ከገበታ ሲጠፋ ቅር ይላል። አዎን፤ ቁጥራቸውን በውል ከማናውቃቸው ዘመናት በፊት ጀምሮ እንጀራ የአገራችን ዋነኛ ምግብ ሆኖ ቆይቷል። እውነት ነው፣ የሰው ልጅ በየዕለቱ የግድ ከሚያስፈልጉት አንገብጋቢ ነገሮች አንዱ ምግብ ነው።
እንጀራ የሚዘጋጀው ከጤፍ ወይም ከሌሎች የእህል ዓይነቶች ከሚገኝ ዱቄት ሲሆን ዱቄቱን ለማዘጋጀት ደግሞ እነዚህን የእህል ዓይነቶች መፍጨት የግድ ነው። የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን መፍጨት ጥንታዊ የሰው ልጆች ጥበብ ነው። ዘመናዊ መሣሪያዎች ባልነበሩበት ዘመን እህል መፍጨት ምን ያህል አድካሚ ሥራ ሊሆን እንደሚችል ገምት! በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የወፍጮ ድምፅ መሰማቱ በአገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ ሁኔታ እንደሰፈነ ያመለክት የነበረ ሲሆን የዚህ ድምፅ መጥፋት ደግሞ አገሪቱ ባድማ እንደሆነች ያመለክት ነበር።—ኤርምያስ 25:10, 11
እህል መፍጨት ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር ምን ትስስር ነበረው? ሰዎች እህል ለመፍጨት ምን ዓይነት ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል? ዛሬስ እንጀራ ከገበታ እንዳይጠፋ ትልቅ ድርሻ የሚያበረክቱ ምን ዓይነት ወፍጮዎች አሉ?
ወፍጮ ለምን አስፈለገ?
ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለአዳምና ሔዋን “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:29) ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ምግቦች ውስጥ የአገዳና የብር እህሎች ይገኙበታል። እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ አጃ፣ ሲናር፣ ሩዝ፣ ዘንጋዳ፣ ማሽላና በቆሎ የመሳሰሉት የእህል ዓይነቶች ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ናቸው፤ ምክንያቱም ሰውነታችን ወደ ኃይል ሰጪ ግሉኮስነት የሚቀይረውን ንጥረ ነገር ማለትም ካርቦሃይድሬት ይዘዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ግን የሰው ልጅ እነዚህን የእህል ዓይነቶች ጥሬያቸውን ሊመገባቸው አይችልም። ስለሆነም ፈጭቶና አብስሎ መብላት ይኖርበታል። የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን ለማድቀቅ የሚረዳው ቀላሉ መንገድ ደግሞ በሙቀጫ መውቀጥ፣ በድንጋይ ወፍጮ መፍጨት ወይም ሁለቱንም ዘዴዎች አጣምሮ መጠቀም ነው።
በሰው ጉልበት የሚሰሩ ወፍጮዎች
በግብፅ ባሉ ጥንታዊ መቃብሮች ውስጥ የተገኙ ሐውልቶች በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች በአገራችን የተለመደውን ዓይነት የእጅ ወፍጮ ይጠቀሙ እንደነበር ይጠቁማሉ። ወፍጮው ጎድጎድ ብሎ ከፊት በኩል ዘቅዘቅ ያለ ሲሆን ከላይ መጅ አለው። የምትፈጨው ሴት (በአብዛኛው ሴቶች ናቸው) ትንበረከክና ወፍጮውን ከፊቷ አድርጋ መጁን በሁለት እጅዋ በመያዝ በኃይል ተጭና ገፋ መለስ እያደረገች በድንጋዮቹ መሃል ያለውን እህል ትፈጫለች። በጊዜው በጣም ቀላልና ውጤታማ የሆነ ዘዴ ነበር!
ሆኖም ለረዥም ሰዓታት መንበርከክ ሰውነትን ይጎዳል። መጁን ጫፍ ድረስ ገፍቶ እንደገና ወደኋላ መመለስ በጀርባ፣ በክንድ፣ በታፋ፣ በጉልበትና በእግር ጣቶች ላይ ዘፀአት 11:5) a እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው ሲወጡ ይህንን የእጅ ወፍጮ ወደ አገራቸው ይዘው እንደሄዱ አንዳንድ ምሁራን ይገምታሉ።
ሕመም እንዲሰማ ያደርጋል። ቅሪተ አካልን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች በሶርያ በሚገኙ የተስተካከለ ቅርፅ በሌላቸው አጽሞች ላይ ምርምር ካደረጉ በኋላ በግብፅ የነበረው ዓይነት ወፍጮ ይጠቀሙ የነበሩ ወጣት ሴቶች ይህን ሥራ መሥራታቸው የጉልበታቸው ሎሚ ወደ ውስጥ እንዲገባ፣ የአከርካሪያቸው ጫፍ እንዲጎዳና በእግራቸው አውራ ጣት መጋጠሚያ ላይ የቁርጥማት በሽታ እንዲይዛቸው እንዳደረገ መገንዘብ ችለዋል። በጥንቷ ግብፅ በእጅ ወፍጮ መፍጨት የሴት ባሪያዎች ሥራ የነበረ ይመስላል። (ቆየት ብሎም ሁለቱንም ድንጋዮች በመቦርቦር የወፍጮዎችን ቅልጥፍና ማሻሻል ተቻለ። በላይኛው ድንጋይ ላይ የተቦረቦረው ቀዳዳ እህሉ ቀስ በቀስ እየተንቆረቆረ ወደ ወፍጮው እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል ነበር። ከዚያም ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ወይም በአምስተኛው መቶ ዘመን ግሪኮች ቀለል ያለ ወፍጮ ፈለሰፉ። ከላይ ያለው ድንጋይ በቀላሉ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እጀታ የተገጠመለት ነበር። እጀታውን ይዞ በትንሹ በማንቀሳቀስ እህል ማስገቢያ የተሠራለት የላይኛው ድንጋይ ከታችኛው ድንጋይ ጋር እንዲፋጭና እህሉ እንዲደቅ ማድረግ ይቻላል።
ከላይ የተጠቀሱት ወፍጮዎች የራሳቸው የሆነ አንዳንድ ከባድ ችግር ነበረባቸው። የሚሠሩት ወደ ፊትና ወደ ኋላ በማንቀሳቀስ ስለነበር እንስሳትን ማሠራት አይቻልም ነበር። በመሆኑም እነዚህ ወፍጮዎች የሚሠሩት በሰው ጉልበት ብቻ ነበር። ስለዚህ ቆየት ብሎ ተሽከርካሪ የእህል ወፍጮዎች ተፈለሰፉ። በዚህ ጊዜ በእንስሳት ጉልበት መጠቀም ተቻለ።
ተሽከርካሪ ወፍጮዎች ሥራውን አቀለሉት
ተሽከርካሪ የእህል ወፍጮ የተፈለሰፈው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በሜዲትራንያን አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በፍልስጥኤም ምድር ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን እነዚህን የእህል ወፍጮዎች ይጠቀሙ ነበር። ኢየሱስ ‘በአህያ ስለሚሽከረከር’ የድንጋይ ወፍጮ የተናገረው ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል።—ማርቆስ 9:42 NW
በሮምና በአብዛኛው የሮም ግዛት የነበሩ ነዋሪዎች በእንስሳት ጉልበት የሚሠራ ወፍጮ ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ ወፍጮዎች እስከ አሁን ድረስ በፖምፔ በብዛት ይገኛሉ። የላይኛው ድንጋይ ከአፉ ሰፋ ብሎ ከሥሩ ጠበብ ያለ ቅርፅ ሲኖረው የሚፈጨውን እህል ቀስ በቀስ ወደ ወፍጮው ያወርዳል፤ የስረኛው ድንጋይ ደግሞ ሾጠጥ ያለ ነው። የላይኛው ድንጋይ በስረኛው ድንጋይ ላይ በሚዞርበት ጊዜ እህሉ በሁለቱ ድንጋዮች መሃል እየገባ ይፈጫል። በፖምፔ የሚገኙት ወፍጮዎች የላይኛው ክፍላቸው ከ45 እስከ 90 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ የተለያየ ስፋት አላቸው። ቁመታቸው ከ180 ሴንቲ ሜትር አይበልጥም።
ቀለል ካሉ ተሽከርካሪ የእጅ ወፍጮዎችና በእንስሳት ጉልበት ከሚሠሩት ወፍጮዎች የትኛው ቀድሞ ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚታወቅ ነገር የለም። የሆነ ሆኖ በእጅ የሚሠራ ተሽከርካሪ ወፍጮ ለመፍጨት አመቺ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ መጓጓዝ ይችላል። ይህ ወፍጮ ከሁለት ክብ ድንጋዮች የተሰራ ነው፤ የድንጋዮቹም ስፋት ከ30 እስከ 60 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል። ከሥር የሚሆነው ድንጋይ ከላይ በኩል ትንሽ ጎድጎድ ያለ ሲሆን ከላይ የሚውለው ድንጋይ ደግሞ የታችኛው ገጹ ጎበጥ ያለ ነው። ይህም ከታች ከሚውለው ድንጋይ ጋር ለመግጠም ያስችለዋል። የላይኛው ድንጋይ ለማሽከርከር የሚያስችል የእንጨት እጀታ የተገጠመለት ሲሆን ሁለት ሴቶች ትይዩ ሆነው ይቀመጡና በአንድ እጃቸው እጀታውን ይዘው ያሽከረክሩታል። (ሉቃስ 17:35) አንዷ ሴት የወፍጮውን እጀታ ባልያዘችበት እጅዋ እህል በትንሽ በትንሹ እየቆነጠረች በላይኛው የወፍጮው ድንጋይ ቀዳዳ ውስጥ ስትጨምር ሌላዋ ሴት ደግሞ እየተፈጨ የሚወጣውን ዱቄት በዝርግ ዕቃ ወይም ከወፍጮው ስር በተነጠፈ ጨርቅ ትቀበላለች። ይህ ዓይነቱ ወፍጮ ለወታደሮች፣ ለመርከበኞች ወይም የተሻለ የእህል ወፍጮ ከሚገኝበት አካባቢ ራቅ ላሉ ነዋሪዎች ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው።
በውሃ ወይም በንፋስ ግፊት የሚሠራ ወፍጮ
በ27 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቪትሩቪየስ የተባለ ሮማዊ መሐንዲስ በውሃ የሚሠራ ወፍጮ ለሕዝብ አስተዋወቀ። ወራጅ ውሃ የመንኮራኩሩን መቅዘፊያዎች በሚመታበት ጊዜ መንኮራኩሩ ይሽከረከራል። መንኮራኩሩ ደግሞ ዋናውን ዘንግ ያሽከረክረዋል። ዘንጉም በተራው ከላይ ያለውን የወፍጮ ድንጋይ ያሽከረክረዋል።
ይህ የውሃ ወፍጮ ከሌሎቹ ወፍጮዎች ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ውጤታማ ነው? በእጅ የሚሠራ ወፍጮ በግምት በአንድ ሰዓት ውስጥ 10 ኪሎ ግራም እህል ሲፈጭ በጣም ውጤታማ የሚባለው በእንስሳት ጉልበት የሚሠራ ወፍጮ ደግሞ በአንድ ሰዓት እስከ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን እህል ይፈጫል። ቪትሩቪየስ የፈለሰፈው የውሃ ወፍጮ ግን በአንድ ሰዓት ውስጥ ከ150 እስከ 200 ኪሎ ግራም የሚመዝን እህል መፍጨት ይችላል። ከዚያን ጊዜ በኋላ በነበሩት በርካታ መቶ ዘመናት ባለሙያዎች በቪትሩቪየስ ፈጠራ መነሾነት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ለውጦችና ማሻሻያዎች ማድረግ ችለዋል።
ወፍጮዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያገለግለው ኃይል የሚገኘው ከውሃ ብቻ አልነበረም። በውሃ ግፊት በሚንቀሳቀሱት መንኮራኩሮች ፈንታ የሸራ መቅዘፊያ በመጠቀም በንፋስ ኃይል የሚሠራ ወፍጮ መሥራት ይቻላል። በንፋስ ኃይል የሚሠሩ ወፍጮዎች በአውሮፓ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት በ12ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሳይሆን አይቀርም፤ በቤልጂየም፣ በጀርመን፣ በሆላንድና በሌሎችም ቦታዎች በስፋት ጥቅም ላይ ውለው ነበር። እነዚህ ወፍጮዎች ቀስ በቀስ በእንፋሎት እና በሌሎችም የኃይል ምንጮች በሚሠሩ ወፍጮዎች እየተተኩ መጡ።
“የዕለት እንጀራችን”
ይህን የመሰለ መሻሻል ቢደረግም እንኳን በአንዳንድ ቦታ ያሉ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጥንታዊ የሆኑ ወፍጮዎችን ይጠቀማሉ። የአፍሪካና የኦሺንያ ነዋሪዎች አሁንም በሙቀጫና በዘነዘና ይወቅጣሉ። የሜክሲኮና የመካከለኛው አሜሪካ ነዋሪዎች ለቂጣ የሚሆን በቆሎ በድንጋይ ወፍጮና በመጅ ይፈጫሉ። እንዲሁም በውሃና በንፋስ ግፊት የሚሰሩ ወፍጮዎች በተለያዩ ቦታዎች አሁንም ይሠራባቸዋል።
የበለጸጉ አገሮች ግን በዛሬው ጊዜ እህል ለመፍጨት የሚጠቀሙት እጅግ የረቀቁ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ነው። እነዚህ ዘመናዊ ወፍጮዎች በአነስተኛ ወጪ እህሉን በተለያየ ደረጃ ፈጭተው ያወጣሉ።
ዛሬ እህል መፍጨት እንደ ጥንቱ ጊዜ ከባድ ሥራ አለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆነ ይህ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችንም ሆነ እነዚህን የእህል ዓይነቶች በማዘጋጀት “የዕለት እንጀራችንን” ማግኘት የሚያስችለንን ብልሀት የሰጠን ፈጣሪ ምስጋና ይገባዋል።—ማቴዎስ 6:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሳምሶንና ሌሎች እስራኤላውያን ምርኮኞች እህል የመፍጨት ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። (መሳፍንት 16:21፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 5:13) ሴቶች ደግሞ ምርኮኛ ባይሆኑም እንኳን ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ምግብ ለማዘጋጀት እህል ይፈጩ ነበር።—ኢዮብ 31:10
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ግብፃውያን ይጠቀሙበት የነበረው የእጅ ወፍጮ
[ምንጭ]
Soprintendenza Archeologica per la Toscana, Firenze
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእንስሳት ጉልበት የሚሰራ ወፍጮ በመጠቀም የወይራ ዘይት ያወጡ ነበር
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
From the Self-Pronouncing Edition of the Holy Bible, containing the King James and the Revised versions