የጌታ ጸሎት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
የጌታ ጸሎት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ ያስተማረው የጌታ ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማቴዎስ ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ 13 ላይ ይገኛል። ኢየሱስ ይህንን ጸሎት ከማስተማሩ ትንሽ ቀደም ብሎ “አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 6:7 የ1954 ትርጉም
ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ኢየሱስ ጸሎቱን ሲያስተምር ቃል በቃል እንዲደገም አስቦ አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ይህንን ጸሎት መጀመሪያ ሲያስተምር በቦታው ላልነበረ ደቀ መዝሙር በሌላ ጊዜ ደግሞለታል። (ሉቃስ 11:2-4) ሆኖም በማቴዎስና በሉቃስ የወንጌል ዘገባዎች ላይ በሰፈሩት ጸሎቶች ውስጥ የተጠቀመባቸው ቃላት በተወሰነ መጠን ይለያያሉ። ከዚህም በላይ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ከጊዜ በኋላ ባቀረቧቸው ጸሎቶች ላይ የናሙና ጸሎቱን ቃል በቃል አልደገሙትም።
ታዲያ የጌታ ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በዚህ የናሙና ጸሎት አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጸሎት ማቅረብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮናል። ከዚህም በላይ በዚህ ጸሎት ውስጥ በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን። እንግዲያው የጸሎቱን ክፍሎች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።
የአምላክ ስም ማን ነው?
“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።” (ማቴዎስ 6:9) የናሙና ጸሎቱ መክፈቻ የሆኑት እነዚህ ቃላት አምላክን “አባታችን” ብለን በመጥራት ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይረዱናል። አፍቃሪና ስሜቱን የሚረዳለት ወላጅ ያለው አንድ ልጅ በቀላሉ ወደ ወላጆቹ እንደሚቀርብ ሁሉ እኛም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ሊሰማን እንደሚፈልግ እርግጠኞች በመሆን ልንቀርበው እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 65:2
ኢየሱስ ስለ አምላክ ስም መቀደስ እንድንጸልይ አስተምሮናል። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ማን ነው? መጽሐፍ ዘፀአት 6:3 የ1879 እትም፤ መዝሙር 83:18 NW) ይሖዋ የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመልክተህ ታውቃለህ?
ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ (ኤልሻዳይ) ተገለጥሁ። በስሜም እግዚኣ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።” (ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ይገኛል። ያም ሆኖ አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህንን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። በመሆኑም ፈጣሪያችን ስሙን እንዲቀድሰው መለመናችን ተገቢ ነው። (ሕዝቅኤል 36:23) እንደዚህ ካለው ጸሎት ጋር እንደምንስማማ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ወደ አምላክ ስንጸልይ ይሖዋ በሚለው ስሙ በመጠቀም ነው።
ፓትሪሽያ የተባለች ከልጅነቷ ጀምሮ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የነበረች አንዲት ሴት የጌታን ጸሎት በደንብ ታውቀው ነበር። ሆኖም አንዲት የይሖዋ ምሥክር የአምላክን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስታሳያት ምን ተሰማት? “ማመን አቃተኝ!” ትላለች። “ስለዚህ የራሴን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተመለከትሁ፤ ስሙ እዚያም ላይ ነበር። ከዚያም ምሥክሯ ማቴዎስ 6:9, 10ን አሳየችኝና እዚያ ላይ የተጠቀሰው ጸሎት ስለ አምላክ ስም እንደሚናገር አስረዳችኝ። በጣም ከመደሰቴ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታስጠናኝ ጠየቅዃት።”
የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲሆን መጸለይ
“መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:10) የናሙና ጸሎቱ ክፍል የሆነው ይህ ልመና ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች ሰማይ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ የሰፈነበት ቦታ እንደሆነ ያስባሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች ሰማይን ‘የተቀደሰው፣ የተከበረውና ከፍ ያለው’ በማለት ይገልጹታል። (ኢሳይያስ 63:15) የአምላክ ፈቃድ ‘በሰማይ እንደ ሆነ’ በምድርም እንዲሆን የምንጸልየውም ለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ልመና ሊፈጸም ይችላል?
የይሖዋ ነቢይ የነበረው ዳንኤል የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን [ምድራዊ] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) በሰማይ የተቋቋመው ይህ መንግሥት ጽድቅ በሰፈነበት አገዛዝ ሥር ዓለም አቀፋዊ ሰላም ለማምጣት በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል።—2 ጴጥሮስ 3:13
የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በምድር እንዲሆን የምናቀርበው ጸሎት አምላክ ይህን እንደሚያደርግ ያለንን እምነት የሚያሳይ ሲሆን ይህ ልመናችን በእርግጥ ይፈጸማል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ራእይ 21:3-5
ሰማሁ፤ ‘እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።’” ዮሐንስ አክሎም “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ . . . ‘ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ’ አለኝ” ብሏል።—ስለ ሥጋዊ ፍላጎታችን መጸለይ
ኢየሱስ ስንጸልይ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የአምላክ ስምና ፈቃዱ መሆን እንዳለበት አሳይቷል። ሆኖም የናሙና ጸሎቱ ቀጣይ ክፍል ለይሖዋ ሊቀርቡ የሚችሉ የግል ልመናዎችንም ያካትታል።
ከእነዚህ የመጀመሪያው “የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው ነው። (ማቴዎስ 6:11) ይህንን ልመና ስናቀርብ ቁሳዊ ሃብት እንዲሰጠን መጠየቃችን አይደለም። ኢየሱስ ያስተማረው “የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን” ብለን እንድንጸልይ ነው። (ሉቃስ 11:3) አምላክን የምንወድደውና የምንታዘዘው ከሆነ ዕለታዊ ፍላጎቶቻችንን እንደሚያሟላልን ሙሉ በሙሉ በመተማመን ልንጸልይ እንችላለን።
ስለ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከሚገባ በላይ መጨነቅ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ችላ እንድንልና አምላክ የሚጠብቅብንን ሳናሟላ እንድንቀር ሊያደርገን ይችላል። ሆኖም የይሖዋን አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ ከሰጠነው እርሱም እንደ ምግብና ልብስ ስላሉት ቁሳዊ ነገሮች የምናቀርበውን ልመና ሰምቶ ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:26-33) ይሁን እንጂ ሁላችንም ኃጢአተኞችና የአምላክ ይቅርታ የሚያስፈልገን በመሆናችን የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ቀላል አይደለም። (ሮሜ 5:12) የጌታ ጸሎት ስለዚህ ጉዳይም ይናገራል።
ይቅርታ ለማግኘት መጸለይ
“እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን።” (ማቴዎስ 6:12፤ ሉቃስ 11:4) ይሖዋ አምላክ በእርግጥ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል?
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከባድ ኃጢአቶች ቢሠራም ንስሐ የገባ ሲሆን እንደሚከተለው ብሎ በልበ ሙሉነት መጸለይ ችሏል፦ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤ ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም።” (መዝሙር 86:5) ይህ እንዴት የሚያጽናና ሐሳብ ነው! በሰማይ የሚኖረው አባታችን በሠሩት ኃጢአት ተጸጽተው ወደ እርሱ ለሚጸልዩ ሰዎች “ይቅር ባይ” ነው። ዕዳ ሙሉ በሙሉ ሊሠረዝ እንደሚችል ሁሉ ይሖዋ አምላክም ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር ሊለን ይችላል።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:14, 15) ጻድቅ ሰው የነበረው ኢዮብ ሦስቱ ወዳጆቹ ቢበድሉትም ይቅር ብሏቸዋል፤ እንዲያውም የአምላክን ይቅርታ እንዲያገኙ ስለ እነርሱ ጸልዮአል። (ኢዮብ 42:10) የበደሉንን ይቅር የምንል ከሆነ አምላክን የምናስደስት ከመሆኑም በላይ ይቅርታውን ማግኘት እንችላለን።
አምላክ ልመናችንን ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ የእርሱን ሞገስ ለማግኘት እንድንጥር ሊገፋፋን ይገባል። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ የእርሱን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። (ማቴዎስ 26:41) ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ መደምደሚያ ላይ እንደገለጸው በዚህ ረገድም ቢሆን ይሖዋ ሊረዳን ይችላል።
በጽድቅ መንገድ መመላለስ እንድንችል እንዲረዳን መጸለይ
“ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ።” (ማቴዎስ 6:13) ይሖዋ በፈተና እንድንወድቅ ዝም ብሎ አይተወንም፣ በኃጢአት እንድንወድቅም አያደርገንም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” ይላል። (ያዕቆብ 1:13) አምላክ እንድንፈተን ቢፈቅድም ከታላቁ ፈታኝ፣ “ከክፉው” ከሰይጣን ዲያብሎስ ያድነናል።
ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሰይጣን ፍጹም ሰው የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳ ፈትኖታል! የዲያብሎስ ዓላማ ምን ነበር? ኢየሱስን ንጹሕ ከሆነው የይሖዋ አምልኮ ለማራቅ ነበር። (ማቴዎስ 4:1-11) አምላክን ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ሰይጣን አንተንም ሊውጥህ ይፈልጋል!
ዲያብሎስ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም በመጠቀም አምላክ የሚጠላቸውን ድርጊቶች እንድንፈጽም ይፈትነን ይሆናል። (1 ዮሐንስ 5:19) በዚህም ምክንያት በተለይ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ፈተና ሲያጋጥመን እርዳታ ለማግኘት አዘውትረን ወደ አምላክ መጸለይ ይኖርብናል። ይሖዋን በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚገኙት መመሪያዎች መሠረት ካመለክነው ዲያብሎስን መቋቋም እንድንችል በመርዳት ከክፉው ያድነናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
በአምላክ ማመን አስፈላጊ ነው
በሰማይ የሚኖረው አባታችን ስለ እያንዳንዳችን ደህንነት እንደሚያስብ ማወቃችን እንዴት የሚያስደስት ነው! ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን እንዲያስተምረን አድርጓል። ይህን ማወቃችን ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት እንድንጥር እንደሚያነሳሳን አያጠራጥርም። ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።” (ዕብራውያን 11:6) እንደዚህ ያለውን እምነት እንዴት ማዳበር ይቻላል? የአምላክ ቃል “እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው” ይላል። (ሮሜ 10:17) የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን በእውነተኛ እምነት ለማገልገል ከሚፈልግ ከማንኛውም ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ያስደስታቸዋል።
የጌታን ጸሎት በሚመለከት ከላይ የቀረበው ማብራሪያ የጸሎቱን ትርጉም በጥልቀት ለመረዳት እንዳስቻለህ ተስፋ እናደርጋለን። ስለ ይሖዋና “ከልብ ለሚሹት” ስላዘጋጀላቸው በረከቶች ተጨማሪ እውቀት በማግኘት በአምላክ ላይ ያለህን እምነት ማጠንከር ትችላለህ። ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ይበልጥ ተምረህ በሰማይ ከሚኖረው አባትህ ጋር ዘላለማዊ ዝምድና ለመመሥረት እንድትበቃ እንመኝልሃለን።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ።”—ማቴዎስ 6:9-13
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ዲያብሎስን መቋቋም እንድንችልም ይረዳናል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኛም እንደ ኢዮብ የበደሉንን ይቅር የምንል ከሆነ የአምላክን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን