በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኞች ናቸው

ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኞች ናቸው

ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኞች ናቸው

‘ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ደስተኞች ናችሁ።’—ማቴዎስ 5:11

1. ኢየሱስ ደስታንና ስደትን በሚመለከት ለተከታዮቹ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷል?

 ኢየሱስ መንግሥቱን እንዲሰብኩ ሐዋርያቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲልካቸው ተቃውሞ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በመንገር አስጠንቅቋቸው ነበር። “ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል” ሲል ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:5-18, 22) ሆኖም ቀደም ብሎ በተራራ ስብከቱ ላይ ሐዋርያቱንም ሆነ በዚያ የተገኙትን ሌሎች ሰዎች እንዲህ ያለው ተቃውሞ ደስታቸውን እንደማያሳጣቸው አረጋግጦላቸው ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቲያን መሆን የሚያስከትለውን ስደት ከደስታ ጋር አጣምሮ ገልጾታል። ይሁን እንጂ፣ ስደት እንዴት ደስታ ሊያስገኝ ይችላል?

ስለ ጽድቅ መሰደድ

2. ኢየሱስና ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገሩት ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት መከራ ነው?

2 ኢየሱስ ‘ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና’ በማለት ደስታ የሚያስገኘውን ስምንተኛ ነጥብ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:10) መከራ በራሱ የሚወደድ ነገር አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል” በማለት ጽፏል። በተጨማሪም “ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል። ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር” ሲል ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 2:20፤ 4:15, 16) ከኢየሱስ አነጋገር መገንዘብ እንደሚቻለው አንድ ሰው ከሚደርስበት መከራ ደስታ ሊያገኝ የሚችለው ስለ ጽድቅ ሲል የሚጸና ከሆነ ብቻ ነው።

3. (ሀ) ስለ ጽድቅ መሰደድ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ስደት በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

3 እውነተኛ ጽድቅ የሚለካው የአምላክን ፈቃድ በማድረግና ትእዛዛቱን በማክበር ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ስለ ጽድቅ መከራ ደርሶበታል ሲባል የአምላክን ትእዛዝ ወይም መመሪያ ላለመጣስ ሲል ሥቃይ ደርሶበታል ማለት ነው። የአይሁድ መሪዎች ሐዋርያትን ያሳደዷቸው በኢየሱስ ስም መስበካቸውን አናቆምም በማለታቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 4:18-20፤ 5:27-29, 40) ታዲያ ይህ ደስታቸውን እንዲያጡ ወይም የስብከት እንቅስቃሴያቸውን እንዲገቱ አድርጓቸዋል? በፍጹም! “ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየዕለቱም በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 5:41, 42) ይህ ስደት ደስታ አስገኝቶላቸዋል፤ እንዲሁም ለስብከቱ ሥራ ያላቸውን ቅንዓት ይበልጥ አቀጣጥሎታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የጥንት ክርስቲያኖች በንጉሠ ነገሥት አምልኮ አንካፈልም በማለታቸው በሮማውያን ስደት ደርሶባቸዋል።

4. ክርስቲያኖች ስደት የሚደርስባቸው በምን ምክንያት ነው?

4 በዘመናችንም የይሖዋ ምሥክሮች ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ መስበካቸውን አናቆምም በማለታቸው ስደት ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርጉ እገዳ ሲጣልባቸው አንድ ላይ መሰብሰባቸውን በማቆም ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ከመጣስ ይልቅ መከራ መቀበል መርጠዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው ወይም ደም አንወስድም በማለታቸው ስደት ደርሶባቸዋል። (ዮሐንስ 17:14፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) ያም ሆኖ ለጽድቅ ሲሉ የወሰዱት ይህ አቋም ውስጣዊ ሰላምና ደስታ አስገኝቶላቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:14

ስለ ክርስቶስ መሰደብ

5. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች የሚሰደዱበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

5 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደስታ እንደሚያስገኝ የጠቀሰው ዘጠነኛው ነጥብ ከስደት ጋር የተያያዘ ነው። ‘ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ደስተኞች ናችሁ’ በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:11) የይሖዋ ሕዝቦች በዋነኝነት የሚሰደዱት የዚህ ክፉ ሥርዓት ክፍል ባለመሆናቸው ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደ ሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለዚሁ ነው” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል” በማለት ተናግሯል።—1 ጴጥሮስ 4:4

6. (ሀ) ቅቡዓን ቀሪዎችና ባልንጀሮቻቸው የሚሰደቡትና የሚሰደዱት ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ዓይነቱ ስደት ደስታችንን ይቀንስብናል?

6 የጥንት ክርስቲያኖች በኢየሱስ ስም መስበካቸውን አናቆምም በማለታቸው ስደት እንደደረሰባቸው ቀደም ብለን ተመልክተናል። ክርስቶስ ተከታዮቹን “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል አዟቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙት ታማኝ ቅቡዓን የክርስቶስ ወንድሞች አጋሮቻቸው በሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየታገዙ ይህን ተልእኮ በቅንዓት በመወጣት ላይ ናቸው። (ራእይ 7:9 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም ሰይጣን ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው በያዙት’ በሴቲቱ ማለትም በአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ዘሮች ላይ ጦርነት አውጆአል። (ራእይ 12:9, 17) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን አምላክ ለሚያመጣው አዲስ ዓለም እንቅፋት የሆኑትን ሰብዓዊ መንግሥታት በሚያጠፋው የአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ ስለተሾመው ስለ ኢየሱስ እንመሰክራለን። (ዳንኤል 2:44፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በዚህም ምክንያት እንሰደባለን እንዲሁም እንሰደዳለን። ሆኖም ይህ ሁሉ የሚደርስብን ስለ ክርስቶስ ስም ስንል በመሆኑ ደስ ይለናል።—1 ጴጥሮስ 4:14

7, 8. ተቃዋሚዎች በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ምን የሐሰት ወሬ ያናፍሱባቸው ነበር?

7 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሰዎች በስሙ ምክንያት ‘ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባቸው’ ደስ ሊላቸው እንደሚገባ ገልጾላቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:11) በእርግጥም የጥንት ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከ59-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሮም ውስጥ ታስሮ ሳለ እዚያ የሚኖሩ የአይሁድ መሪዎች ክርስቲያኖችን በሚመለከት “ስለዚህ የእምነት ክፍል በየቦታው ክፉ እንደሚያወሩበት እናውቃለን” ብለውት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:22) ጳውሎስና ሲላስም ‘የቄሣርን ሕግ በመጣስ ዓለምን አውከዋል’ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:6, 7

8 ታሪክ ጸሐፊው ኬኔት ስኮት በጥንቷ የሮማ ግዛት ዘመን ስለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “የተለያየ የሐሰት ክስ ይሰነዘርባቸው ነበር። ክርስቲያኖች በአረማዊ በዓላት ላይ ባለመካፈላቸው ምክንያት አምላክ የለሾች ተብለዋል። በአረማዊ ክብረ በዓላት ላይ፣ ሕዝባዊ በሆኑ የመዝናኛ ዝግጅቶችና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ባለመሳተፋቸው የሰውን ዘር እንደሚጠሉ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። . . . ማታ ማታ ወንዶችም ሴቶችም አንድ ላይ ይሰበሰቡና . . . ልቅ የሆነ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ የሚል ወሬ ይነዛባቸው ነበር። . . . [የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል] አማኞች ብቻ በሚገኙበት ይከበር ስለነበር ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ አንድን ሕፃን መሥዋዕት ካደረጉ በኋላ ደሙን ይጠጣሉ ሥጋውንም ይበላሉ የሚል ወሬ ይናፈስ ነበር።” በተጨማሪም የጥንት ክርስቲያኖች በንጉሠ ነገሥታዊ አምልኮ ስለማይካፈሉ የመንግሥት ጠላት እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር።

9. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይሰነዘርባቸው ለነበረው የሐሰት ክስ ምን ምላሽ ሰጡ? ዛሬስ ሁኔታው ምን ይመስላል?

9 እንዲህ ያሉት የሐሰት ወሬዎች የጥንት ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኳቸውን ከመፈጸም ወደኋላ እንዲሉ አላደረጓቸውም። ከ60-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጳውሎስ ‘ወንጌሉ ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ እንደተሰበከና’ ‘በዓለም ዙሪያ ፍሬ እንዳፈራ’ ለመናገር ችሏል። (ቆላስይስ 1:5, 6, 23) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በሐሰት ይወነጀላሉ። ሆኖም የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩ ሥራ በስፋት እየተካሄደ ሲሆን በዚህ ሥራ ለሚካፈሉ ሰዎችም ከፍተኛ የደስታ ምንጭ ሆኗል።

እንደ ነቢያት በመሰደዳቸው ደስተኞች ናቸው

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ደስታ የሚያስገኘውን ዘጠነኛውን ነጥብ የደመደመው ምን በማለት ነው? (ለ) ነቢያት ስደት የደረሰባቸው ለምን ነበር? ምሳሌ ስጥ።

10 ኢየሱስ ደስታ የሚያስገኘውን ዘጠነኛውን ነጥብ ያጠቃለለው “ደስ ይበላችሁ . . . ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና” በማለት ነበር። (ማቴዎስ 5:12) ይሖዋ ከሃዲ የሆኑትን እስራኤላውያን ለማስጠንቀቅ የላካቸው ነቢያት ሰሚ ጆሮ አጥተዋል እንዲሁም በተደጋጋሚ ስደት ደርሶባቸዋል። (ኤርምያስ 7:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስ “ከዚህ በላይ ምን ልበል? . . . ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ የለኝም። . . . አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ” በማለት ይህን ሐቅ መሥክሯል።—ዕብራውያን 11:32-38

11 ክፉ ንጉሥ በነበረው በአክዓብና በሚስቱ በኤልዛቤል ዘመን በርካታ የይሖዋ ነቢያት በሰይፍ ተገድለዋል። (1 ነገሥት 18:4, 13፤ 19:10) ነቢዩ ኤርምያስ በእግር ግንድ ታስሮ የነበረ ሲሆን በኋላም ጭቃ በሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። (ኤርምያስ 20:1, 2፤ 38:6) ነቢዩ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። (ዳንኤል 6:16, 17) በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩት እነዚህ ነቢያት ይህ ሁሉ ስደት የደረሰባቸው ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ በመቆማቸው ነው። በብዙዎቹ ነቢያት ላይ ስደት ያደረሱት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ናቸው። ኢየሱስ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ሲል ጠርቷቸዋል።—ማቴዎስ 23:31 የ1954 ትርጉም

12. እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ከጥንቶቹ ነቢያት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የሚደርስብንን ስደት እንደ መብት የምንቆጥረው ለምንድን ነው?

12 በዛሬው ጊዜ የምንገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በቅንዓት ስለምንሰብክ ስደት ይደርስብናል። ጠላቶቻችን “የሰዎችን ሃይማኖት በግድ ያስቀይራሉ” ብለው ይከሱናል፤ ሆኖም ከእኛ በፊት የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ተመሳሳይ ክስ ይቀርብባቸው እንደነበር እናውቃለን። (ኤርምያስ 11:21፤ 20:8, 11) ከጥንቶቹ ታማኝ ነቢያት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የሚደርስብንን ስደት እንደ መብት እንቆጥረዋለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ [“ደስተኞች፣” NW] አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 5:10, 11

ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉ ምክንያቶች

13. (ሀ) ስደት ሲደርስብን ተስፋ የማንቆርጠው ለምንድን ነው? (ለ) እንድንጸና የሚያስችለን ምንድን ነው? ይህስ ምን ያረጋግጥልናል?

13 ስደት ሲደርስብን በፍጹም ተስፋ አንቆርጥም፤ እንዲያውም የነቢያትን፣ የጥንት ክርስቲያኖችንና የራሱን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እየተከተልን እንዳለ ስለሚያስገነዝበን እንጽናናለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቁጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 4:12, 14) እንደነዚህ የመሳሰሉት ጥቅሶች በእጅጉ ያጽናኑናል። ስደት ሲደርስብን መጽናት የምንችለው የይሖዋ መንፈስ በእኛ ላይ ስለሚያድርብንና ስለሚያበረታን ብቻ መሆኑን እናውቃለን። በመሆኑም የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘታችን የይሖዋ በረከት እንዳልተለየን የሚያሳይ ማስረጃ ነው፤ ይህ ደግሞ ያስደስተናል።—መዝሙር 5:12፤ ፊልጵስዩስ 1:27-29

14. ስለ ጽድቅ ብለን በመሰደዳችን የምንደሰትባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

14 ስለ ጽድቅ ብለን ስንሰደድና ተቃውሞ ሲደርስብን ደስ የምንሰኝበት ሌላው ምክንያት በእርግጥ ለአምላክ ያደርን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ስለሚያረጋግጥልን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት [“ለአምላክ ያደሩ ሆነው፣” NW] መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ከሁሉም በላይ ደግሞ የምንደሰተው መከራ ሲደርስብን ታማኝነታችንን መጠበቃችን ይሖዋ ፍጥረታቱ እርሱን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነው ለሚለው የሰይጣን ክስ መልስ መስጠት ስለሚያስችለው ነው። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:3, 4) ይብዛም ይነስም የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ በማበርከታችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል።—ምሳሌ 27:11

ዋጋችሁ ታላቅ ስለሆነ ሐሤት አድርጉ

15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ‘ደስ እንድንሰኝና ሐሤት እንድናደርግ’ ምክንያት የሚሆን ምን ነገር ጠቅሷል? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ምን ሽልማት ይጠብቃቸዋል? አጋሮቻቸው የሆኑት ‘ሌሎች በጎችስ’ ምን ሽልማት ያገኛሉ?

15 ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደ ጥንቶቹ ነቢያት የሐሰት ወሬ ሲነዛባቸውና ሲሰደዱ ደስ የሚሰኙባቸውን ተጨማሪ ምክንያቶች ጠቅሷል። ኢየሱስ ዘጠነኛውን ደስታ ከጠቀሰ በኋላ ወደ መጨረሻ አካባቢ “በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:12) ሐዋርያው ጳውሎስ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:23) አዎን፣ የምናገኘው ‘ታላቅ ዋጋ’ ሕይወት ነው፤ ሆኖም ለድካማችን እንደ ደሞዝ የሚከፈለን ሳይሆን ነጻ ስጦታ ነው። ኢየሱስ ስለዚህ ዋጋ ሲናገር ‘በሰማይ እንደምንቀበለው’ አድርጎ የገለጸው ከይሖዋ የሚገኝ ስለሆነ ነው።

16 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የማይጠፋ ሕይወት በሚያገኙበት ጊዜ “የሕይወትን አክሊል” ይቀበላሉ። (ያዕቆብ 1:12, 17) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 21:3-5) ሁለቱም ቡድኖች ይህን ሽልማት የሚያገኙት የድካማቸው ዋጋ ስለሆነ አይደለም። ቅቡዓኑም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ይህን ሽልማት የሚያገኙት እንዲያው በይሖዋ ‘የጸጋ ስጦታ’ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።—2 ቆሮንቶስ 9:14, 15

17. ስደት ሲደርስብን ልንደሰትና ‘ሐሤት ልናደርግ’ የምንችለው ለምንድን ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ያስነሳው ጭካኔ የተሞላበት ስደት ይጠብቃቸው ለነበሩት ክርስቲያኖች “በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም” በማለት ጽፎ ነበር። በተጨማሪም “በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ” ብሏል። (ሮሜ 5:3-5፤ 12:12) ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ መከራን በጽናት በመቋቋማችን የምናገኘው ሽልማት ከምንም ነገር የላቀ ነው። በንጉሣችን በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር በመሆን አፍቃሪ አባታችንን ለዘላለም እያገለገልንና እያወደስን መኖር እንደምንችል ስናስብ የሚሰማን ደስታ ወሰን የለውም። ይህም ‘በሐሤት’ እንድንሞላ ያደርገናል።

18. የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየቀረበ ሲመጣ ብሔራት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ይሖዋስ ምን እርምጃ ይወስዳል?

18 አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ይደርስባቸዋል። ኢየሱስ ስለዚህ ሥርዓት ማብቂያ በተናገረው ትንቢት ውስጥ “በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል እውነተኛ ክርስቲያኖችን አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:9) ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን በሄድን መጠን ሰይጣን፣ ብሔራት ለይሖዋ ሕዝቦች ያላቸውን ጥላቻ እንዲገልጹ ይገፋፋቸዋል። (ሕዝቅኤል 38:10-12, 14-16) ይህም ይሖዋ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። ይሖዋ “በዚህም ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦች ፊት ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” በማለት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 38:23) በዚህ መንገድ ታላቅ ስሙን ይቀድሳል፤ ሕዝቦቹንም ከስደት ይታደጋል። በእርግጥም ‘በፈተና የሚጸና ሰው ደስተኛ ነው።’—ያዕቆብ 1:12

19. ታላቁን ‘የይሖዋን ቀን’ እየተጠባበቅን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ታላቁ ‘የይሖዋ ቀን’ በጣም በቀረበበት በዚህ ዘመን ስለ ኢየሱስ ስም ‘ውርደትን ለመቀበል በመብቃታችን’ ደስ ይበለን። (2 ጴጥሮስ 3:10-13፤ የሐዋርያት ሥራ 5:41) ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን ሽልማት እየተጠባበቅን እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ስለ ክርስቶስና ስለ መንግሥቱ ያለማሰለስ ‘መስበካችንንና ማስተማራችንን’ እንቀጥል።—የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ ያዕቆብ 5:11

ለክለሳ ያህል

• ስለ ጽድቅ መሰደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

• ስደት በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

• በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ስደት በጥንት ነቢያት ላይ ከደረሰው ስደት ጋር ተመሳሳይ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

• ስደት ሲደርስብን ‘ደስ ሊለንና ሐሤት ልናደርግ’ የምንችለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

‘ሰዎች ሲሰድቧችሁና ሲያሳድዷችሁ ደስተኞች ናችሁ’

[ምንጭ]

እስረኞች:- Chicago Herald-American