በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ቀምሰህ ታውቃለህ?

በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ቀምሰህ ታውቃለህ?

በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ቀምሰህ ታውቃለህ?

በክርስቲያናዊ አገልግሎት ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት በቅንዓት የተካፈሉ ታማኝ እህት ናቸው። ምንም እንኳን በዕድሜ መግፋት ሳቢያ አቅማቸው ቢዳከምም በቅርቡ የተገነባውን የመንግሥት አዳራሽ ለመጎብኘት ቆርጠው ነበር። የአንድን ክርስቲያን ወንድም ክንድ ተደግፈው ወደ አዳራሹ እንደገቡ ግራ ቀኝ ሳይሉ በቀስታ እያዘገሙ ወደ መዋጮ ሣጥኑ አመሩ። ከዚያም ለዚሁ ዓላማ ብለው ሲያጠራቅሙት የነበረውን መጠነኛ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ከተቱ። በግንባታ ሥራው በቀጥታ ለመካፈል አቅማቸው ባይፈቅድላቸውም የበኩላቸውን ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው።

እኚህ ክርስቲያን እህት ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ሁለት ሳንቲሞችን ስትጥል የተመለከታትን “ምስኪን መበለት” ሳያስታውሱህ አይቀሩም። የዚህች መበለት ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር ብዙም አናውቅም፤ ሆኖም በዚያ ዘመን ያለ ባል መኖር አንዲትን ሴት ለከባድ የኢኮኖሚ ችግር ይዳርጋት ነበር። ኢየሱስም የኑሮዋን ሁኔታ በሚገባ ያውቅ ስለነበር አዝኖላታል። ለደቀ መዛሙርቱ ምሳሌ አድርጎ ሲጠቅሳት የሰጠችው ትንሽ ስጦታ “ያላትን ሁሉ” እና “ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ” እንደሚያጠቃልል ተናግሯል።—ማርቆስ 12:41-44

ይህን ያህል ችግረኛ የሆነች ምስኪን መበለት እንዲህ ዓይነቱን መሥዋዕትነት የከፈለችው ለምንድን ነው? በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ አምልኮ ይቀርብለት ለነበረው ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ያደረች ስለነበረች ነው። የምታበረክተው አስተዋጽኦ የቱንም ያህል ውስን ቢሆን ቅዱሱን አምልኮ የመደገፍ ፍላጎት ነበራት። አቅሟ የፈቀደላትን ያህል አስተዋጽኦ በማድረጓም ከልቧ ተደስታ መሆን አለበት።

የይሖዋን ሥራ ለመደገፍ መስጠት

የቁሳቁስም ሆነ የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ ምንጊዜም የእውነተኛው አምልኮ ክፍል የነበረ ሲሆን ታላቅ ደስታም ያስገኛል። (1 ዜና መዋዕል 29:9) በጥንቷ እስራኤል መዋጮዎች ቤተ መቅደሱን ለማስዋብ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ለይሖዋ አምልኮ ሲባል የሚከናወኑትን የተለያዩ ተግባራት ለማካሄድ ይውሉ ነበር። ሕጉ እስራኤላውያን ካገኙት ምርት አንድ አሥረኛ የሚሆነውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉትን ሌዋውያን ለመደገፍ እንዲሰጡ ያዝዝ ነበር። ሌዋውያንም ቢሆን ከተሰጣቸው አስራት ውስጥ አንድ አሥረኛውን ለይሖዋ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘኍልቍ 18:21-29

ምንም እንኳን ክርስቲያኖች የቃል ኪዳኑ ሕግ ከሚፈልግባቸው ብቃቶች ነጻ ቢሆኑም የአምላክ አገልጋዮች እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ቁሳዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚጠይቀው መሠረታዊ ሥርዓት ግን አሁንም አልተለወጠም። (ገላትያ 5:1) ከዚህም በላይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ወንድሞቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት አስተዋጽኦ ለማድረግ በመቻላቸው ይደሰቱ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:45, 46) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን አምላክ መልካም ነገሮችን አትረፍርፎ እንደሰጣቸው ሁሉ እነርሱም ለሌሎች ልግስናን እንዲያሳዩ አሳስቧቸዋል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19፤ 2 ቆሮንቶስ 9:11) አዎን፣ ጳውሎስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ትክክለኛነት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት መናገር ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

በዘመናችን ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ልግስና

በዘመናችንም ቢሆን የይሖዋ አገልጋዮች ቁሳዊ ሃብታቸውን እርስ በርስ ለመረዳዳትና የአምላክን ሥራ ለመደገፍ ይጠቀሙበታል። አነስተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው እንኳን አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ‘ታማኝና ልባም ባሪያም’ በመዋጮ የሚገኘውን ይህን ገንዘብ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውል ይሖዋ ኃላፊነት እንደሰጠው ይገነዘባል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) በመዋጮ የሚገኘው ገንዘብ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ለሥራ ማስኬጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ብሎም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለመተርጎምና ለማተም፣ ትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስዮናውያንን አሠልጥኖ ለመላክ፣ በአደጋ ጊዜ እርዳታ ለማቅረብና ለሌሎች በርካታ ጠቃሚ ዓላማዎች ይውላል። እስቲ ከእነዚህ መካከል በአንዱ ይኸውም የአምልኮ ቦታዎችን በመገንባት ላይ እናተኩር።

የይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰምና ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ለመጨዋወት በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ በየሳምንቱ አምስት ስብሰባዎችን ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የገንዘብ ድጋፍ ሳይደረግላቸው የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት የኢኮኖሚ ሁኔታቸው አይፈቅድላቸውም። በመሆኑም በ1999 የይሖዋ ምሥክሮች ከበለጸጉ አገሮች በሚገኘው መዋጮ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ በሆኑ አገሮች የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት አደረጉ። ከዚህም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን ለዚሁ ሥራ ያዋሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም በእነዚህ አገሮች ውስጥ ወደሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ሄደው አዳራሾችን ይሠራሉ። በግንባታው ወቅት በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አዳራሾችን ለመገንባትና ለመጠገን የሚያስፈልገውን ሥልጠና የሚያገኙ ሲሆን ከመንግሥት አዳራሽ ፈንድ የሚገኘው ገንዘብም የግንባታ መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ለመግዛት ያስችላል። በእነዚህ አዳዲስ አዳራሾች ውስጥ የሚሰበሰቡ ወንድሞች የእምነት አጋሮቻቸው ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን መሥዋዕት አድርገው ይህን የመሰለ አዳራሽ ስለሰጧቸው አመስጋኞች ናቸው። እነርሱም በተራቸው የመንግሥት አዳራሹን ለመጠገንና ለግንባታ የወጣውን ወጪ መልሶ ለመተካት በየወሩ ገንዘብ የሚያዋጡ ሲሆን ይህም ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባትም እገዛ ያደርጋል።

የመንግሥት አዳራሾች የሚሠሩት በአካባቢው የተለመዱ የግንባታ ቁሳቁሶችንና ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። እነዚህ አዳራሾች በጣም ያሸበረቁ ባይሆኑም ማራኪ፣ አስፈላጊዎቹን ነገሮች ያሟሉና ምቹ ናቸው። የአዳራሽ ግንባታው ፕሮግራም በ1999 ሲጀመር ወደ 40 የሚጠጉ ውስን የገንዘብ አቅም ያላቸው አገሮች ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ነበሩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በግንባታው ፕሮግራም ውስጥ የታቀፉት አገሮች ቁጥር 116 የደረሰ ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆኑትን ይሸፍናል። ባለፉት አምስት ዓመታት ከ9,000 የሚበልጡ የመንግሥት አዳራሾች በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ተገንብተዋል። ይህም በየቀኑ ከአምስት የበለጡ አዳዲስ አዳራሾች ተሠርተዋል ማለት ነው። አሁንም ቢሆን ግን በእነዚህ 116 አገሮች ውስጥ ተጨማሪ 14,500 የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በይሖዋ በረከትና በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞች በፈቃደኝነትና በልግስና በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል በቂ የገንዘብ አቅም እንደሚኖረን ተስፋ እናደርጋለን።—መዝሙር 127:1

የመንግሥት አዳራሾች እድገቱን ያፋጥናሉ

በመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ረገድ የተደረገው ይህ ከፍተኛ ርብርቦሽ ግንባታው በተካሄደባቸው አገሮች በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? በብዙ አካባቢዎች የመንግሥት አዳራሽ ከተሠራ በኋላ የተሰብሳቢዎች ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ ጨምሯል። ከብሩንዲ የተገኘው የሚከተለው ሪፖርት ይህን ያሳያል፦ “አንድ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቶ ካለቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተሰብሳቢዎች ይሞላል። ለምሳሌ ያህል በአማካይ 100 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች ለነበሩት አንድ ጉባኤ 150 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎችን ዘና ባለ ሁኔታ መያዝ የሚችል የመንግሥት አዳራሽ ተሠርቶ ነበር። የግንባታው ሥራ ሲጠናቀቅ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 250 ደርሷል።”

ይህን ያህል ጭማሪ የሚገኘው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎች ተገቢ የመሰብሰቢያ ቦታ የሌላቸውንና በዛፍ ሥር ወይም በሜዳ ላይ የሚሰበሰቡ የመንግሥቱ አስፋፊዎችን የሚያዩአቸው በጥርጣሬ ዓይን ነው። በአንድ አገር ውስጥ የጎሳ ግጭቶችን የሚያስነሱት እንዲህ ያሉ ትናንሽ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንደሆኑ ተደርጎ ስለሚታይ የአገሪቱ ሕግ ሁሉም ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች በአምልኮ ቦታዎች ውስጥ እንዲደረጉ ያዝዛል።

ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማግኘታቸው የአንድ ፓስተር ተከታዮች አለመሆናቸውን ለኅብረተሰቡ ለማሳየት ያስችላል። በዚምባቡዌ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ባለፉት ዓመታት በዚህ አካባቢ የሚገኙ ወንድሞች በግለሰቦች ቤት ውስጥ ይሰበሰቡ የነበረ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች ጉባኤውን የሚጠሩት ስብሰባው በሚደረግበት ቤት ባለቤት ስም ነበር። ወንድሞችንም የአቶ እገሌ ቤተ ክርስቲያን አባላት እያሉ ይጠሯቸው ነበር። አሁን የአካባቢው ሰዎች በእያንዳንዱ አዳራሽ ላይ ‘የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ’ የሚሉ በግልጽ የተጻፉ ምልክቶችን ማየት ስለሚችሉ ይህ አመለካከታቸው ተለውጧል።”

በደስታ የሚሰጡ ለጋሾች

ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) እርግጥ ነው፣ በቀጥታ ለድርጅቱ የሚሰጡ ከፍተኛ መጠን ያላቸው መዋጮዎች ጠቃሚ ናቸው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ለመደገፍ ከሚደረገው መዋጮ ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ካሉት የአስተዋጽኦ ሣጥኖች ነው። ብዙም ይሁኑ ትንሽ ሁሉም መዋጮዎች ጠቃሚ ሲሆኑ ማንም አቅልሎ አይመለከታቸውም። ኢየሱስ ምስኪኗ መበለት ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞችን በመዋጮ ሣጥኑ ውስጥ ስትጥል እንደተመለከታት አስታውስ። ይሖዋና መላእክትም አይተዋታል። ስሟን ባናውቀውም ይሖዋ የራሷን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሰጠችው ስጦታ ለሁልጊዜው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብ አድርጓል።

የምናደርጋቸው መዋጮዎች ከመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች በተጨማሪ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የመንግሥቱን ሥራዎች ለመደገፍ ይውላሉ። በዚህ ረገድ ትብብር ማሳየታችን ደስታ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ‘ብዙ ምስጋና ለይሖዋ ለማቅረብ’ ያስችለናል። (2 ቆሮንቶስ 9:12) በቤኒን የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞቻችን “ከዓለም አቀፋዊው የወንድማማች ማኅበር ላገኘነው የገንዘብ እርዳታ በየዕለቱ እየደጋገምን ይሖዋን በጸሎት እናመሰግነዋለን” በማለት ሪፖርት አድርገዋል። ሁላችንም የመንግሥቱን ሥራ በገንዘብ በመደገፍ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ መቅመስ እንችላለን!

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች

ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።

ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, c/o Office of the Secretary and Treasurer, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገራችሁ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ቼኮች “ለይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ በአደራ የሚሰጥበት ዝግጅት

የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እንዲጠቀምበት በአደራ ገንዘብ መስጠት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሰጪው ገንዘቡ እንዲመለስለት ሲጠይቅ ይመለስለታል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ገንዘብ በስጦታ ከመለገስ በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት:- ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።

የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን መንገዶች ለመጠቆም ነው። ብዙዎች ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከራሳቸው የሕግ ወይም የቀረጥ አማካሪዎች ጋር በመማከር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሥራ ለመደገፍ ከመቻላቸውም በላይ እንዲህ በማድረጋቸው ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ችለዋል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመህ ወይም በአገርህ ለሥራው አመራር ለሚሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል መጠየቅ ትችላለህ።

Charitable Planning Office

Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania

100 Watchtower Drive,

Patterson, New York 12563-9204

ስልክ፦ (845) 306-0707

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀድሞዎቹና አዲሶቹ የመሰብሰቢያ አዳራሾች

ዛምቢያ

ሴንትራል አፍሪካ ሪፑብሊክ