ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?
ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?
አንዲት በጃፓን የሚኖሩ አረጋዊት ሴት ልትጠይቃቸው ቤታቸው ለሄደችው ክርስቲያን አገልጋይ “ሞትን አልፈራም። ከእነዚህ አበቦች መለየቱ ግን ያሳዝነኛል” አሏት። አረጋዊቷ ሴት በጣም የሚያምር የአትክልት ቦታ ስለነበራቸው የምታነጋግራቸው ሴት እንዲህ ያሉበትን ምክንያት ለመረዳት አልከበዳትም። ሞትን እንደማይፈሩ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ተፈጥሮን ከልባቸው የሚያደንቁ ከመሆኑም በላይ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ለዘላለም ለመኖር ይፈልጋሉ።
ለዘላለም መኖር የሚለው አባባል በአእምሮህ ውስጥ ጥያቄዎች ይፈጥርብህ ይሆናል። ብዙ ሰዎች እንዲህ ላለው ሐሳብ ብዙም ቦታ አይሰጡትም። እንዲያውም አንዳንዶች ለዘላለም ለመኖር እንደማይፈልጉ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
ለዘላለም መኖር አሰልቺ ይሆናል?
አንዳንዶች ለዘላለም መኖር አሰልቺ ይሆናል ብለው ያስባሉ። ለዚህም ቀኑን ሙሉ ቴሌቪዥናቸው ላይ ተተክለው ከመዋል በቀር ሌላ ሥራ የሌላቸው ጡረተኞች የሚኖሩትን አታካች ሕይወት በምሳሌነት ይጠቅሱ ይሆናል። አንተም እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለህ ሮበርት ጃስትሮ የተባሉት የከዋክብት ተመራማሪ ለዘላለም መኖር በረከት ወይስ እርግማን እንደሆነ ሲጠየቁ ምን ብለው እንደመለሱ ተመልከት። እንዲህ ብለው ነበር:- “የማወቅ ጉጉትና ፈጽሞ የማይረካ የመማር ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በረከት ይሆናል። ለእነርሱ ለዘላለም እውቀት እየሰበሰቡ የመኖሩ ሐሳብ በጣም የሚያስደስት ነው። ማወቅ ያለባቸውን ነገር ሁሉ እንዳወቁ ለሚሰማቸውና አእምሯቸውን ለዘጉ ሰዎች ግን እርግማን ይሆንባቸዋል። ምክንያቱም ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ምንም ነገር አይኖራቸውም።”
ስለዚህ ለአንተም ለዘላለም መኖር አሰልቺ መሆን አለመሆኑ የተመካው በአመለካከትህ ላይ ነው። “የማወቅ ጉጉትና ፈጽሞ የማይረካ የመማር ፍላጎት” ካለህ በሥነ ጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በምሕንድስና፣ በግብርና ወይም በሌላ የሚያስደስትህ መስክ ምን ነገሮችን ልታከናውን እንደምትችል እስቲ አስበው። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር በተለያዩ ዘርፎች ችሎታህን ለማሻሻል የምትችልበት ግሩም አጋጣሚ ይሰጥሃል።
ከዚህም በላይ ከሌሎች ጋር ለዘላለም እየተዋደዱና እየተፋቀሩ መኖርም ዘላለማዊ ሕይወትን አስደሳች እንደሚያደርገው የታወቀ ነው። በተፈጥሯችን ለሌሎች ፍቅር የማሳየት ችሎታ ያለን ሲሆን ሌሎች እንደሚወዱን ሲሰማንም እንደሰታለን። ከሌሎች ጋር ከልብ በመነጨ ፍቅር መዋደድ በጊዜ ሂደት የማይጠፋ ጥልቅ እርካታ ያስገኛል። ለዘላለም መኖር ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለአምላክም ፍቅር ማዳበር የምንችልበት ሰፊ አጋጣሚ ይሰጠናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው” ብሎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 8:3) የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ ማወቅና በእርሱ መታወቅ መቻል ምንኛ መታደል ነው! ከዚህም በላይ ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያችን ልንማራቸው የምንችላቸው ነገሮች ማለቂያ የላቸውም። ታዲያ ለዘላለም መኖር እንዴት አሰልቺ ሊሆን ይችላል?
ሕይወትን ውድ ያደረገው አጭር መሆኑ ነው?
አንዳንዶች ሕይወትን በጣም ውድ ያደረገው አጭር መሆኑ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሕይወትን ውስን አቅርቦት ካለው ከወርቅ ጋር ያወዳድሩታል። ወርቅ በየቦታው የሚገኝ ነገር ቢሆን ኖሮ ዋጋ አይኖረውም ነበር ይላሉ። ሆኖም ወርቅ የትም የሚገኝ ነገር እንኳን ቢሆን ይህ ውበቱን ፈጽሞ አይቀንሰውም ነበር። ሕይወትም ቢሆን እንዲሁ ነው።
ዘላለማዊ ሕይወትን በሁሉም ሥፍራ ተትረፍርፎ ከሚገኘው አየር ጋር ልናወዳድረው እንችላለን። በብልሽት ምክንያት ከባሕር መውጣት በተሳነው ሰርጓጅ
መርከብ ውስጥ ላሉ መርከበኞች አየር በጣም ውድ ነገር ነው። ከአደጋው ከዳኑ በኋላ ግን አየር እንደልብ በማግኘታቸው ቅር የሚላቸው ይመስልሃል? በፍጹም ቅር አይላቸውም!እኛም እንደነዚህ መርከበኞች ከፊታችን ከተጋረጠብን ሞት ልናመልጥና ለዘላለም የመኖር ተስፋ ልናገኝ እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 6:23) አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አለፍጽምናንና ሞትን የሚያስቀር ሲሆን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል። በፍቅር ተነሳስቶ ላደረገልን ለዚህ ዝግጅት አመስጋኞች መሆን አይኖርብንም?
ወዳጅ ዘመዶችህስ ምን ይሆናሉ?
አንዳንድ ሰዎች ‘ወዳጅ ዘመዶቼስ ምን ይሆናሉ? እነርሱ አብረውኝ የማይኖሩ ከሆነ ለዘላለም መኖሬ ምንም ፋይዳ አይኖረውም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረህና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደሚቻል ተምረህ ይሆናል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ 17:3) የቅርብ ዘመዶችህ፣ ወዳጆችህና ሌሎች የምትወዳቸው ሰዎች በአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ ለማግኘት ተስፋ የምታደርገውን ደስታ እንዲጋሩህ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:13
ጓደኞችህና የምትወዳቸው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር የማይፈልጉ ከሆነስ? ይህ ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መማርህንና ከተማርከው ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስህን ቀጥል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንቺ ሴት፤ ባልሽን ታድኚው እንደ ሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ሰው፤ ሚስትህን ታድናት እንደ ሆነ ምን ታውቃለህ?” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:16) ሰዎች በጊዜ ሂደት ሊለወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስትናን ይቃወም የነበረ ሰው ከጊዜ በኋላ ተለውጦ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ለመሆን ችሏል። “ውድ ቤተሰቤ ተቃውሞዬን በጽናት ተቋቁመው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በታማኝነት በመደገፋቸው ትልቅ ውለታ ውለውልኛል” በማለት ተናግሯል።
አምላክ ለአንተና ለወዳጅ ዘመዶችህ ሕይወት በጣም ያስባል። አዎን፣ ይሖዋ ‘ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ (2 ጴጥሮስ 3:9) አንተና የምትወዳቸው ሰዎች ሁሉ ለዘላለም እንድትኖሩ ይፈልጋል። የእርሱ ፍቅር ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች ልታገኝ ከምትችለው ፍቅር በእጅጉ ይበልጣል። (ኢሳይያስ 49:15) ስለዚህ አስቀድመህ ከአምላክ ጋር ያለህን ግንኙነት ለምን አታጠናክርም? ከዚያም ወዳጅ ዘመዶችህም እንዲሁ እንዲያደርጉ መርዳት ትችል ይሆናል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ለዘላለም የመኖር ፍላጎት ባይኖራቸውም ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጋር ተስማምተህ ስትመላለስ ሲመለከቱ አመለካከታቸው ሊለወጥ ይችላል።
በሞት ያጣሃቸው የምትወዳቸው ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አስደሳች ተስፋ እንዳላቸው ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ስለሚናገር ስለ አምላክ ለማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ሰዎች እንኳን ትንሣኤ ያገኛሉ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) እነዚህን ሰዎች በትንሣኤ ማግኘቱ ምንኛ አስደሳች ይሆናል!
የዘላለም ሕይወት አስደሳች ተስፋ ነው
በዚህ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ ደስታና እርካታ ማግኘት ከቻልክ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የበለጠ እንደሚያስደስትህ የተረጋገጠ ነው። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለአንዲት ሴት ለዘላለም መኖር የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ስትነግራት ሴትየዋ “ለዘላለም መኖር አልፈልግም። አሁን የምኖረው የ70ና የ80 ዓመት ሕይወት ይበቃኛል” አለቻት። አብሯቸው የነበረ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “አንቺ ብትሞቺ ልጆችሽ ምን እንደሚሰማቸው አስበሽ ታውቂያለሽ?” በማለት
ጠየቃት። ሴትየዋ ልጆቿ እናታቸውን በማጣታቸው ምን ያህል እንደሚያዝኑ ስታስበው እንባዋ በጉንጮቿ ላይ ኮለል ብሎ ወረደ። “ለመጀመሪያ ጊዜ ምን ያህል ራስ ወዳድ እንደነበርኩ ተገነዘብኩ። አሁን ለዘላለም መኖር እንዲያው በራስ ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮረ ተስፋ ሳይሆን ለሌሎች ብሎ መኖርን እንደሚጨምርም ተገንዝቤአለሁ” ብላለች።አንዳንዶች የእነርሱ መኖር ወይም መሞት ማንንም እንደማይጠቅም ወይም እንደማይጎዳ ይሰማቸዋል። ሆኖም “በሕያውነቴ እምላለሁ፤ . . . ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም” ብሎ የተናገረውን ሕይወት ሰጪያችንን ይሖዋን ግን ያሳስበዋል። (ሕዝቅኤል 33:11) አምላክ ለክፉዎች ሕይወት እንኳን ይህን ያህል የሚጨነቅ ከሆነ እርሱን ለሚወዱት ሰዎች ከዚያ የበለጠ እንደሚያስብላቸው የተረጋገጠ ነው።
የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መቼም እንደማይለየው ሙሉ እምነት ነበረው። በአንድ ወቅት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” ብሎ ነበር። (መዝሙር 27:10) ዳዊት ወላጆቹ እንደሚወዱት ጥርጣሬ አልነበረውም። ሆኖም የቅርብ የሥጋ ዘመዶቹ የሆኑት ወላጆቹ ቢተዉት እንኳን አምላክ ፈጽሞ እንደማይተወው ያውቅ ነበር። ይሖዋ በፍቅርና በአሳቢነት ተነሳስቶ የዘላለም ሕይወትና ከእርሱ ጋር መቼም የማይበጠስ ወዳጅነት የመመሥረት መብት ሰጥቶናል። (ያዕቆብ 2:23) እነዚህን ወደር የለሽ ስጦታዎች በአመስጋኝነት መቀበል አይኖርብንም?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ዘላለማዊ ሕይወትን አስደሳች ያደርገዋል