በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሰው ወዳድ ደሴቶች” ላይ የሚኖሩ የአምላክ ወዳጆች

“ሰው ወዳድ ደሴቶች” ላይ የሚኖሩ የአምላክ ወዳጆች

“ሰው ወዳድ ደሴቶች” ላይ የሚኖሩ የአምላክ ወዳጆች

በ1932 አንድ ጀልባ እጅግ በጣም ውድ የሆነ ዘር ወደ ቶንጋ አመጣ። የጀልባው አዛዥ ለቻርልዝ ቬቴ “ሙታን የት ናቸው?” የሚል ርዕስ ያለው ቡክሌት አበረከተለት። ቻርልዝ እውነትን እንዳገኘ ተገነዘበ። ከጊዜ በኋላ ይህንን ቡክሌት ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋው ለመተርጎም ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ። ቡክሌቱ ከታተመ በኋላ 1,000 ቅጂዎች ተላኩለትና ለሰዎች ማሰራጨት ጀመረ። ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚናገረው የእውነት ዘር በቶንጋ ግዛት መሰራጨት የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር።

የቶንጋ ደሴቶች የደቡብ ፓስፊክን አካባቢ በሚያሳየው ካርታ ላይ የዓለም አዲስ ቀን የሚጀምርበት መስመርና የካፕሪኮርን መስመር ከሚገናኙበት ቦታ በስተ ምዕራብ በኩል ይገኛሉ። ትልቁ ደሴት ቶንጋታፑ፣ ኒው ዚላንድ ውስጥ ከሚገኘው ኦክላንድ ከተማ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 2,000 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ይገኛል። ቶንጋ 171 ደሴቶችን ያቀፈ ግዛት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሰው የሚኖርባቸው አርባ አምስቱ ብቻ ናቸው። እነዚህን ራቅ ብለው የሚገኙ ትንንሽ ደሴቶች ፍሬንድሊ አይላንድስ (ሰው ወዳድ ደሴቶች) በማለት የሰየማቸው የ18ኛው ክፍለ ዘመን ታዋቂ ብሪታንያዊ አሳሽ ጄምስ ኩክ ነበር።

ቶንጋ በሦስት ቡድን የተከፈሉ ደሴቶችን ያቀፈ 106,000 ነዋሪዎች ያሉት አገር ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ቶንጋታፑ፣ ሃአፓይ እና ቫቫው ይባላሉ። በአጠቃላይ በአገሩ ካሉት አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሦስቱ የሚገኙት ብዙ ነዋሪዎች ባሉባቸው የቶንጋታፑ ደሴቶች ውስጥ ሲሆን አንዱ በሃአፓይ ሌላው ደግሞ በቫቫው ውስጥ ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ነዋሪዎቹ የአምላክ ወዳጆች እንዲሆኑ ለመርዳት በዋና ከተማዋ ኑኩዋሎፋ አቅራቢያ የሚስዮናውያን ቤትና የትርጉም ቢሮ ከፍተዋል።—ኢሳይያስ 41:8

ቻርልዝ ቬቴ የተጠመቀው በ1964 ቢሆንም ነዋሪዎቹ ከ1930ዎቹ ጀምሮ የይሖዋ ምሥክር ይመስላቸው ነበር። አንዳንዶች በስብከቱ ሥራ አብረውት ይካፈሉ የነበረ ሲሆን በ1966 ሠላሳ ሰው መያዝ የሚችል የመንግሥት አዳራሽ ተገነባ። ቆየት ብሎም በ1970 በኑኩዋሎፋ 20 የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ያሉት ጉባኤ ተቋቋመ።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ “ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ” በማለት የተናገረው ትንቢት በቶንጋ ደሴቶች ላይ በገሃድ መፈጸም ጀመረ። (ኢሳይያስ 42:12) ብዙዎች ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ የሚረዳው የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ሥራ መስፋፋቱን ቀጥሏል። በኑኩዋሎፋ በ2003 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የነበረው ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 407 ሲሆን 5 ተጠማቂዎች ነበሩ። በ2004 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 621 ሰዎች መገኘታቸው ወደፊት ትልቅ እድገት እንደሚኖር ይጠቁማል።

ነዋሪዎቹ ቀላል ኑሮ ይመራሉ

ይሁን እንጂ፣ ከዋና ከተማው ውጪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በጣም እንደሚያስፈልጉ ማስተዋል ተችሏል። ለምሳሌ ያህል የሃአፓይ ክፍል በሆኑት 16 ደሴቶች ውስጥ የሚገኙት 8,500 ነዋሪዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይበልጥ መማር ያስፈልጋቸዋል። በአብዛኛው በዝቅተኛ ሥፍራ ላይ የሚገኙት የሃአፓይ ደሴቶች የዘምባባ ዛፍ የሞላባቸውና በነጭ አሸዋ የተሸፈኑ ረዣዥም የውቅያኖስ ዳርቻዎች አሏቸው። የውቅያኖሱ ውኃ ጥርት ያለ ከመሆኑ የተነሳ እስከ 30 ሜትር ጥልቀት ድረስ በደንብ ማየት ይቻላል። በውቅያኖሱ ውስጥ ባሉ የዛጎል አለቶችና በሞቃት አካባቢ በሚገኙ ከመቶ በላይ በሚሆኑ የዓሣ ዝርያዎች መሃል መዋኘት ጥሩ ትዝታ ጥሎ ያልፋል። በአጠቃላይ ሲታይ መንደሮቹ ትንንሾች ናቸው። ቤቶቹ ቀለል ያሉ ቢሆኑም በአካባቢው የሚነሳውን ከባድ አውሎ ነፋስ መቋቋም እንዲችሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው።

የማንጎ እና የሌሎችም ፍራፍሬዎች ዛፎች ለጥላነትም ሆነ ለምግብነት ያገለግላሉ። ነዋሪዎቹ በቀን ውስጥ ምግብ በመሰብሰብና በማዘጋጀት ረጅም ሰዓታት ያጠፋሉ። ከአሳማ ሥጋ በተጨማሪ በውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ነገሮችን መመገብ ይወዳሉ። የደሴቶቹ ነዋሪዎች የሚበሉ ሥራ ሥሮችንና ቅጠላ ቅጠሎችን በራሳቸው ጓሮ ያበቅላሉ። ወፍ ዘራሽ የሆኑ ብርቱካንና ሎሚ የመሳሰሉ ዛፎች በየጫካው ውስጥ ያድጋሉ፤ የኮኮነትና የሙዝ ተክሎችም በብዛት ይገኛሉ። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መድኀኒትነት ባላቸው ዕፅዋት፣ ቅጠላ ቅጠሎች፣ የተክል ቅርፊቶችና ሥራ ሥሮች አማካኝነት የሚሰጥ ባሕላዊ ሕክምናም አላቸው።

የሃአፓይ ደሴቶች ካሏቸው በጣም አስደሳች እሴቶች መካከል ዋነኛው መንፈስን ከሚያድሰው አካባቢ ጋር ተላምዶ የሚኖረው ሕዝቡ ነው። ሰው ወዳድ የሆነው የዚህ ሕዝብ አኗኗር ቀላል ነው። አብዛኞቹ ሴቶች ቅርጫት፣ ታፓ የተባለ ልብስና ምንጣፍ ይሠራሉ። የቶንጋ ሴቶች በዛፎች ጥላ ሥር ቁጭ ብለው እያወሩ፣ እየዘመሩና እየተሳሳቁ ሥራቸውን የማከናወን ልማድ ያላቸው ሲሆን በዚህን ጊዜ ልጆቻቸው አጠገባቸው ይጫወታሉ ወይም ይተኛሉ። ውቅያኖሱ ጸጥ ሲል ባለ ዛጎል ዓሣዎችንና ሌሎች የሚበሉ የባሕር ውስጥ ፍጥረታትን የሚያጠምዱት እንዲሁም ጣፋጭ ሰላጣ የሚሠራባቸውን በባሕር ውስጥ የሚበቅሉ ጠንከር ያሉ ተክሎችን ከአለታማው ጠረፍ የሚሰበስቡት በአብዛኛው ሴቶች ናቸው።

አብዛኞቹ ወንዶች ደግሞ አትክልት በማልማት፣ ዓሣ በማስገር፣ ቅርጻ ቅርጾችንና ጀልባ በመሥራት እንዲሁም መረባቸውን በመጠገን ቀኑን ያሳልፋሉ። ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ጣራ ባላቸው ትንንሽ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች ተሳፍረው ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ፣ ለሕክምናና ለንግድ ልውውጥ ከደሴት ወደ ደሴት ይጓጓዛሉ።

የቦታ ርቀት ምሥራቹን ከመስበክ አላገደም

በ2002 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ሊከበር በተቃረበበት ጊዜ ሁለት ሚስዮናውያንና ሁለት አቅኚዎች ይህን የመሰለ ሁኔታ ወደ ሰፈነባቸው ደሴቶች ተጓዙ። የሃአፓይ ነዋሪዎች ቀደም ሲል በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው ጽሑፎች ተበርክተውላቸው ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩም ነበሩ።

እነዚህ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች የሚከተሉት ሦስት ዓላማዎች ነበሯቸው፦ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማበርከት፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በጌታ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ። ሦስቱንም ዓላማዎቻቸውን ከግብ ማድረስ ችለዋል። በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት ውስጥ ዘጠና ሰባት የሚያህሉት ጥሪውን ተቀብለዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በዕለቱ ከባድ ዝናብና ኃይለኛ ነፋስ የነበረ ቢሆንም ጣራ በሌለው ጀልባ ተሳፍረው ወደ በዓሉ ስፍራ ተጉዘዋል። ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ የአየሩ ሁኔታ ለጉዞ የሚመች ስላልነበረ ብዙ ተሰብሳቢዎች በዓሉ በተከበረበት ቦታ አድረው በማግስቱ ጠዋት ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

በመታሰቢያ በዓሉ ላይ ንግግር ያቀረበው ወንድምም ቢሆን ብርቱ ጥረት ማድረግ አስፈልጎታል። “በአንድ ምሽት የራሳችሁ ባልሆነ ቋንቋ የመታሰቢያ በዓል ንግግር ሁለት ጊዜ ማቅረብ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ልነግራችሁ አልችልም” በማለት ተናግሯል። ቀጥሎም “እንዴት እንደተጨነቅኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ነገር ግን ጸሎት በጣም ጠቅሞኛል! መቼ እንደተማርኳቸው እንኳ የማላስታውሳቸውን ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች አቀናብሬ መናገር ቻልኩ” ሲል ገልጿል።

በሃአፓይ ደሴቶች ውስጥ ወንጌላውያኑ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት ሁለት በአካባቢው የሚኖሩ ባልና ሚስቶች ተጠምቀዋል። ከሁለቱ ባሎች መካከል አንደኛው የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙትን ጽሑፍ ለማንበብ ፍላጎት ያደረበት በአካባቢው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ ለመሆን ሥልጠና በመውሰድ ላይ ሳለ ነበር።

ይህ ሰውና ባለቤቱ ድሆች ቢሆኑም እንኳ አባል የነበሩበት ቤተ ክርስቲያን በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ስማቸው ሲጠራ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያዋጡ ነበር። ቀደም ሲል ቤቱ ሄዶ አነጋግሮት የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ባልየው ከመጽሐፍ ቅዱሱ 1 ጢሞቴዎስ 5:8ን ገልጦ እንዲያነብ ጋበዘው። እዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው” ብሎ ጽፏል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የባልየውን ልብ በጥልቅ ነካው። ለቤተ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያዋጣ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ማቅረብ እንዳልቻለ ተገነዘበ። በሚቀጥለው ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ኪሱ ውስጥ ገንዘብ ቢኖረውም እንኳ 1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ ያነበበውን ሐሳብ አስታወሰ። ስሙ ሲጠራ ለቤተሰቡ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልገው ለቄሱ በድፍረት ነገራቸው። በዚህ ምክንያት የቤተ ክርስቲያኑ ሽማግሌዎች ባልና ሚስቱን በተሰብሳቢው ፊት አወገዟቸው፤ እንዲሁም ተግሣጽ ሰጧቸው።

ከዚህ በኋላ ሰውየውና ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጥንተው የምሥራቹ ሰባኪዎች ሆኑ። ባልየው “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቀይሮኛል። አሁን በቤተሰቤ ላይ የጭካኔ ተግባርና ሌሎች መጥፎ ነገሮች አልፈጽምም። እንዲሁም ከልክ በላይ አልጠጣም። የአካባቢዬ ነዋሪዎች እውነት በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ እንዳደርግ እንደረዳኝ ማስተዋል ይችላሉ። እነርሱም እንደ እኔ አንድ ቀን እውነትን እንደሚቀበሉ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል።

ለሥራው የተሰማራ ክዌስት የተባለው ጀልባ

በ2002 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ከተከበረ ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ ሌላ ጀልባ በዋጋ የማይተመን ጭነት ይዞ ሃአፓይ ደረሰ። አሥራ ስምንት ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ጀልባ ከኒው ዚላንድ ተነስቶ እዚያ የደረሰው በርካታ የቶንጋ ደሴቶችን አልፎ ነበር። ጀልባው የያዘው ጋሪ እና ሄቲ የሚባሉ ባልና ሚስትን እንዲሁም ኬቲ የምትባል ልጃቸውን ነበር። ዘጠኝ የቶንጋ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሁለት ሚስዮናውያን፣ ሁለት ጊዜ አብረዋቸው ተጉዘዋል። የቶንጋ ተወላጅ የሆኑት ወንድሞች አንዳንድ የባሕር ውስጥ አለቶችን እንኳን በሰላም ማለፍ እንዲችሉ ረድተዋቸዋል። እነዚህ ጉዞዎች የተደረጉት ለመዝናናት ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር ነበር። እነዚህ ወንድሞች ወደ አሥራ አራት ደሴቶች ለመሄድ በጣም ሰፊ የሆነ የውቅያኖስ ክፍል አካልለዋል። በአንዳንዶቹ ደሴቶች የመንግሥቱ ምሥራች በጭራሽ ተሰብኮ አያውቅም ነበር።

የደሴቶቹ ነዋሪዎች ምን ተሰማቸው? አብዛኛውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ ፊታቸው ላይ ግር የመሰኘት ስሜት ቢነበብባቸውም እንደባሕላቸው ሞቅ ባለ መንፈስ ወንድሞችን ተቀብለዋቸዋል። የጉብኝቱን ዓላማ ከተረዱ በኋላ ደግሞ በጣም አመሰገኑ። ወንድሞችና እህቶች ሕዝቡ የአምላክን ቃል እንደሚያከብርና ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ንቁ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም።—ማቴዎስ 5:3

ወንድሞች ብዙ ጊዜ በሞቃት ሥፍራ በሚበቅሉ ዛፎች ሥር ቁጭ ብለው ዙሪያቸውን የሚከቧቸው ሰዎች ከየአቅጣጫው ለሚያነሷቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ይውላሉ። ከመሸ በኋላ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቱ በቤቶች ውስጥ ይቀጥላል። እንዲያውም የአንዱ ደሴት ነዋሪዎች ወንድሞች ሊሄዱ ሲሉ “አትሂዱብን! እናንተ ከሄዳችሁ ጥያቄዎቻችንን ማን ይመልስልናል?” በማለት እንዲቆዩ ለምነዋቸዋል። አንዲት እህት “እውነትን የተራቡ በግ መሰል ሰዎችን ጥሎ መሄድ ምንጊዜም ቢሆን ይከብዳል። በርካታ የእውነት ዘር ተዘርቷል” በማለት ተናግራለች። ወደ አንድ ደሴት ሲደርሱ የከተማው ሹም ባለቤት አርፈው ስለነበር ሰው ሁሉ የሐዘን ልብስ ለብሶ ተመለከቱ። የከተማው ሹም ወንድሞች አበረታች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይዘው ወደ ደሴቱ ስለመጡ አመሰገኗቸው።

ወደ አንዳንዶቹ ደሴቶች ደርሶ ከጀልባ ላይ መውረድ እንዲህ ቀላል አይደለም። ሄቲ እንዲህ ብላለች፦ “አንዱ ደሴት ምቹ የሆነ መውረጃ አልነበረውም፤ በውቅያኖሱ ዳርቻ ከአንድ ሜትር በላይ ከፍ ብሎ የወጣ ቋጥኝ ነበር። ወደ ዳርቻው መጠጋት የምንችለው አየር በሚሞሉ መንሳፈፊያ ጎማዎቻችን ብቻ ነበር። መጀመሪያ ቦርሳዎቻችንን በደሴቱ ዳርቻ ላይ ላሉ ሰዎች ወርውረን አቀበልን። ከዚያም በመንሳፈፊያው ጎማ ወደ ቋጥኙ ጫፍ ደረስንና በውኃው ግፊት ወደኋላ ከመመለሱ በፊት በፍጥነት እየዘለልን ወረድን።”

ይሁን እንጂ፣ ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ያን ያህል ደፋሮች አልነበሩም። ለሁለት ሳምንታት ከተጓዙ በኋላ የጀልባው አዛዥ ወደ ዋናው ደሴት ቶንጋታፑ የሚደረገውን የመልስ ጉዞ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከዚህ በኋላ የ18 ሰዓት ጉዞ ይቀረናል። ሆኖም ከመካከላችን አንዳንዶቹ በባሕር ላይ ሲጓዙ ወደ ላይ ስለሚላቸው ያለማቋረጥ መሄድ አንችልም። ወደ መኖሪያችን መመለሱ የሚያስደስተን ቢሆንም የመንግሥቱን ምሥራች የሰሙ በርካታ ሰዎችን ጥለን መሄዳችን ግን በጣም አሳዝኖናል። በቅዱስ መንፈሱና በመላእክቱ አማካኝነት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እንዲረዳቸው ለይሖዋ በአደራ ሰጥተናቸዋል።”

ተስፋ የሚጣልባቸው ደሴቶች

ከላይ የተጠቀሰው ጀልባ ለጉዞ ከተንቀሳቀሰ ስድስት ወር ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ስቲቨንና ማላኪ የተባሉ ሁለት ልዩ አቅኚዎች በሃአፓይ ደሴቶች ውስጥ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በቅርቡ ከተጠመቁት ሁለት ባልና ሚስቶች ጋር አንድ ላይ በመሆን በደሴቶቹ ውስጥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመሩ። በሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ላይ ሞቅ ያሉ ውይይቶች ይደረጉ የነበረ ሲሆን አስፋፊዎቹም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አድርገው ያስተምራሉ።

ታኅሣሥ 1, 2003 በአጠቃላይ በቶንጋ አምስተኛው፣ በሃአፓይ ደግሞ የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቋመ። በርካታ ልጆች በስብሰባዎቹ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ልጆች በትኩረት ማዳመጥ እንዳለባቸው ተምረዋል። በጸጥታ የሚቀመጡ ከመሆኑም ሌላ አድማጮች ሐሳብ የሚሰጡባቸው ትምህርቶች ሲኖሩ በንቃት ይሳተፋሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “ልጆቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ስለተባለው መጽሐፍ ያላቸው እውቀት ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመትከል ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ እንዳሉ የሚያሳይ ነው” ብሏል። በእነዚህ ደሴቶች ውስጥ ገና ብዙ ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች የመሆን ተስፋ እንዳላቸው በግልጽ ማየት ይቻላል።

ቻርልዝ ቬቴ ከሰባ ዓመታት በፊት ሙታን የት ናቸው? የሚል ርዕስ ያለውን ቡክሌት የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በቶንጋ በተረጎመ ጊዜ የመንግሥቱ ዘር ይህን ያህል በአገሩ ልጆች ልብ ውስጥ ሥር ይሰድዳል ብሎ አልገመተም ነበር። ይሖዋ በእነዚህ ርቀው በሚገኙ ደሴቶች የሚካሄደውን የስብከት ሥራ ስለባረከው ያን ጊዜ ከነበረው ትንሽ ጅምር ተነስቶ አሁን ትልቅ እድገት እያሳየ ነው። በዛሬው ጊዜ ቶንጋ በምሳሌያዊ አነጋገር ወደ ይሖዋ ከተመለሱት የባሕር ደሴቶች መካከል አንዱ ነው ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። (መዝሙር 97:1፤ ኢሳይያስ 51:5) አሁን በእነዚህ “ሰው ወዳድ ደሴቶች” ላይ በርካታ የይሖዋ ወዳጆች አሉ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቻርልዝ ቬቴ በ1983

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታፓ የተባለው ልብስ ሲሠራ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ታፓ የተባለው ልብስ ሲሠራ፦ © Jack Fields/CORBIS; በገጽ 8 እና 9 ላይ ከጀርባ ያለው ስዕል እንዲሁም ዓሣ ሲጠመድ፦ © Fred J. Eckert

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቶንጋ ምሥራቹን ለማሰራጨት ያገለገለው “ክዌስት” የተባለው ጀልባ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኑኩዋሎፋ የሚገኘው የተርጓሚዎች ቡድን