በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ረዳታችን ነው

ይሖዋ ረዳታችን ነው

ይሖዋ ረዳታችን ነው

“ረዳቴ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ይሖዋ ነው።”—መዝሙር 121:2 Nw

1, 2. (ሀ) ሁላችንም አልፎ አልፎ እርዳታ ያስፈልገናል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ዓይነት ረዳት ነው?

 ከእኛ መካከል ፈጽሞ እርዳታ የማይፈልግ ማን አለ? እንደ እውነቱ ከሆነ ከባድ ችግሮችን ለመቋቋም እንዲሁም የደረሰብንን ሐዘን ወይም አስከፊ መከራ በጽናት ለማሳለፍ አልፎ አልፎ ሁላችንም እርዳታ ያስፈልገናል። ሰዎች እርዳታ ሲያስፈልጋቸው አብዛኛውን ጊዜ ወደሚያስብላቸው ወዳጃቸው ይሄዳሉ። እንዲህ ላለው ወዳጃቸው የከበዳቸውን ነገር ማካፈላቸው ሸክሙ እንዲቀላቸው ያደርጋል። ሆኖም ከሰው ልናገኘው የምንችለው እርዳታ ውስን ነው። በተጨማሪም እርዳታ ባስፈለገን ጊዜ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት ሁኔታቸው ላይፈቅድላቸው ይችላል።

2 ይሁንና ገደብ የሌለው ኃይል ያለውና በተለያዩ መንገዶች ሊረዳን የሚችል አካል አለ። ከዚህ በተጨማሪ ይህ አካል ፈጽሞ እንደማይተወን ቃል ገብቶልናል። መዝሙራዊው “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” በማለት በልበ ሙሉነት በተናገረ ጊዜ የዚህን አካል ማንነት ገልጿል። (መዝሙር 121:2 NW) ይህ መዝሙራዊ ይሖዋ እንደሚረዳው እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት መዝሙር 121ን እንመርምር። እንዲህ ማድረጋችን እኛም ይሖዋን ረዳታችን አድርገን በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

አስተማማኝ የእርዳታ ምንጭ

3. መዝሙራዊው ዓይኖቹን ያነሳው ወደ የትኞቹ ተራሮች ሊሆን ይችላል? ለምንስ?

3 መዝሙራዊው መዝሙሩን የጀመረው የይሖዋ ፈጣሪነት በእርሱ እንዲተማመን እንዳደረገው በሚጠቁም ሐሳብ ነበር፦ “ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሳለሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይመጣል? ረዳቴ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ይሖዋ ነው።” (መዝሙር 121:1, 2 NW) መዝሙራዊው ዓይኖቹን ያነሳው ወደ ማንኛውም ተራራ አልነበረም። ይህ መዝሙር በተጻፈበት ወቅት የይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚገኘው በኢየሩሳሌም ነበር። በይሁዳ ተራሮች ጫፍ ላይ ይገኝ የነበረው ይህ ከተማ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይሖዋ የሚኖርበት ቦታ ነበር። (መዝሙር 135:21) መዝሙራዊው ይሖዋ እንዲረዳው በልበ ሙሉነት በመጠባበቅ ዓይኖቹን የይሖዋ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም ተራሮች አንስቶ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ ሊረዳው እንደሚችል ይህን ያህል እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ሰማይንና ምድርን የፈጠረው” እርሱ በመሆኑ ነው። መዝሙራዊው ‘ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ እኔን ከመርዳት ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር የለም!’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።—ኢሳይያስ 40:26

4. መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ምንጊዜም የሕዝቦቹን ፍላጎት በንቃት እንደሚከታተል የገለጸው እንዴት ነው? ይህን ማወቃችን የሚያጽናና ነው የምንለው ለምንድን ነው?

4 መዝሙራዊው በመቀጠል ይሖዋ የአገልጋዮቹን ፍላጎት ምንጊዜም በንቃት እንደሚከታተል ገልጿል፦ “እግርህ እንዲ[ን]ሸራተት አይፈቅድም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። እነሆ፤ እስራኤልን የሚጠብቅ፣ አይተኛም፤ አያንቀላፋምም።” (መዝሙር 121:3, 4) አምላክ በእርሱ የሚታመኑ ሰዎች ‘እንዲንሸራተቱ’ ወይም ሊያንሰራሩ በማይችሉበት ሁኔታ እንዲወድቁ አይፈቅድም። (ምሳሌ 24:16) ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ በከፍተኛ ትኩረት በጎቹን እንደሚጠብቅ እረኛ ስለሆነ ነው። ይህን ማወቃችን አያጽናናም? ሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ላለማየት ለቅጽበት እንኳን ዓይኑን አይጨፍንም። ቀንም ሆነ ሌት እነርሱን በንቃት ይጠብቃል።

5. ይሖዋ ‘በቀኝ በኩል’ ይቆማል የተባለው ለምንድን ነው?

5 መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን በታማኝነት እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ስለነበረ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፤ እግዚአብሔር በቀኝህ በኩል ይከልልሃል። ፀሓይ በቀን አያቃጥልህም፤ ጨረቃም በሌሊት ጒዳት አታመጣብህም።” (መዝሙር 121:5, 6) በመካከለኛው ምሥራቅ በእግሩ ለሚጓዝ ሰው ጥላ ያለበት ቦታ አናት ከምትበሳው ፀሐይ ከለላ የሚያገኝበት ማረፊያ ይሆንለታል። ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደ ጥላ በመሆን እንደ ነበልባል ከሚፋጅ ጥፋት ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ ‘በቀኝ በኩል’ እንደሚቆም መገለጹን ልብ በል። በጥንት ዘመን፣ ውጊያ ላይ ያለ አንድ ወታደር በግራ እጁ የሚይዘው ጋሻ የቀኝ እጁን የተወሰነ ክፍል አይሸፍንለትም። ሆኖም አንድ ታማኝ ጓደኛው ከእርሱ በስተ ቀኝ ቆሞ በመዋጋት ከለላ ይሆነዋል። ይሖዋም እንደዚህ ታማኝ ጓደኛ ሁሉ ምንጊዜም አገልጋዮቹን ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ በታማኝነት ከጎናቸው ይቆማል።

6, 7. (ሀ) መዝሙራዊው ይሖዋ ሕዝቦቹን መርዳቱን እንደማያቆም ያረጋገጠልን እንዴት ነው? (ለ) እኛም የመዝሙራዊው ዓይነት ጠንካራ እምነት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ ለሕዝቦቹ እርዳታ መስጠቱን የሚያቆምበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ይህ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ደምድሟል፦ “እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይንከባከባታል። እግዚአብሔር ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መውጣትህንና መግባትህን ይጠብቃል።” (መዝሙር 121:7, 8) በቁጥር 5 ላይ መዝሙራዊው ‘ይሖዋ ይጠብቅሃል’ ሲል በአሁኑ ጊዜ ስለሚያደርግልን ጥበቃ መናገሩ ነበር። በቁጥር 7ና 8 ላይ ደግሞ ይሖዋ ወደፊት ስለሚያደርግልን ጥበቃ ተናግሯል። እውነተኛ አምላኪዎች ወደፊትም ቢሆን የይሖዋ እርዳታ እንደማይለያቸው ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። አገልጋዮቹ የትም ቦታ ቢሆኑ ወይም ምንም ዓይነት አደጋ ቢደቀንባቸው ምንጊዜም የእርዳታ እጁ አይለያቸውም።—ምሳሌ 12:21

7 በእርግጥም የመዝሙር 121 ጸሐፊ፣ ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ አገልጋዮቹን እንደ አሳቢ እረኛ በጥንቃቄ፤ እንደ ትጉ ጠባቂ ደግሞ በንቃት እንደሚጠብቅ ሙሉ እምነት ነበረው። ይሖዋ ስለማይለወጥ እኛም የመዝሙራዊው ዓይነት ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይችላል። (ሚልክያስ 3:6) እንዲህ ሲባል ታዲያ ምንጊዜም አካላዊ ጥበቃ እናገኛለን ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ረዳታችን አድርገን እስከተመለከትነው ድረስ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልብን ከሚችል ከማንኛውም ነገር ይጠብቀናል ማለት ነው። ታዲያ ‘ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?’ ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ከእርሱ እርዳታ የምናገኝባቸውን አራት መንገዶች እስቲ እንመልከት። በዚህ ርዕስ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው እናያለን። በሚቀጥለው ርዕስ ደግሞ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን እንዴት እንደሚረዳ እንመረምራለን።

ከመላእክት የሚገኝ እርዳታ

8. መላእክት በምድር ላይ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው የማያስገርመው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት ያገለግሉታል። (ዳንኤል 7:9, 10) እነዚህ መንፈሳዊ ልጆቹ ፈቃዱን በታማኝነት ይፈጽማሉ። (መዝሙር 103:20) ይሖዋ ለሰብዓዊ አገልጋዮቹ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለውና እነርሱን መርዳት እንደሚፈልግ በሚገባ ያውቃሉ። መላእክት ለአምላክ ምድራዊ አገልጋዮች ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው ምንም አያስገርምም። (ሉቃስ 15:10) ስለዚህ መላእክት ይሖዋ ሰዎችን እንዲረዱ የሚጠቀምባቸው በመሆኑ እንደሚደሰቱ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ በጥንት ዘመን ምድራዊ አገልጋዮቹን ለመርዳት በመላእክት የተጠቀመው በምን መንገዶች ነው?

9. መላእክት በምድር ላይ ያሉ ታማኝ አገልጋዮችን እንዲጠብቁ ሥልጣን እንደተሰጣቸው የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

9 አምላክ ታማኝ ሰዎችን እንዲጠብቁና እንዲያድኑ ለመላእክት ሥልጣንና ኃይል የሰጠበት ጊዜ ነበር። ሎጥና ሴቶች ልጆቹ በሰዶምና በጎሞራ ላይ ከመጣው ጥፋት እንዲያመልጡ ሁለት መላእክት ረድተዋቸዋል። (ዘፍጥረት 19:1, 15-17) በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጅተው የነበሩትን 185,000 አሦራውያን ወታደሮች አንድ መልአክ ብቻውን ገድሏቸዋል። (2 ነገሥት 19:35) ዳንኤል የአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ በተጣለበት ጊዜ ይሖዋ “መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ [ዘግቷል።]” (ዳንኤል 6:21, 22) አንድ መልአክ ሐዋርያው ጴጥሮስን ከእስር ቤት አውጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 12:6-11) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች መላእክታዊ ጥበቃ ያገኙባቸውን ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች የያዘ ሲሆን ይህም “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” የሚለውን የመዝሙር 34:7ን ትክክለኛነት ያጠናክራል።

10. ይሖዋ በመልአክ ተጠቅሞ ነቢዩ ዳንኤልን ያበረታታው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ መላእክት ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲያበረታቱና እንዲደግፉ የተጠቀመባቸው ጊዜያትም አሉ። ዳንኤል ምዕራፍ 10 ላይ አንድ ልብ የሚነካ ምሳሌ ተጠቅሶ እናገኛለን። በዚያ ወቅት ዳንኤል ወደ 100 ዓመት ሳይጠጋው አይቀርም። ነቢዩ ኢየሩሳሌም ፈራርሳና ቤተ መቅደሱን መልሶ የመገንባቱ ሥራ ተጓትቶ ስለነበረ ሊሆን ይችላል ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አድሮበት ነበር። እንዲሁም አንድ የሚያስፈራ ራእይ ከተመለከተ በኋላ በጣም ተረብሾ ነበር። (ዳንኤል 10:2, 3, 8) አምላክ ለእርሱ ካለው አሳቢነት የተነሳ የሚያበረታታው መልአክ ላከለት። መልአኩ ዳንኤልን በአምላክ ፊት “እጅግ የተወደድህ” ነህ በማለት ከአንዴም ሁለቴ ነገረው። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? አረጋዊው ነቢይ መልአኩን ‘አበርትተኸኛል’ አለው።—ዳንኤል 10:11, 19

11. መላእክት ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ለመምራት እንዴት እንዳገለገሉ የሚያሳየው አንደኛው ምሳሌ የትኛው ነው?

11 ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ለመምራት በመላእክት ተጠቅሟል። ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ስለ ክርስቶስ እንዲሰብክ አንድ መልአክ የመራው ሲሆን ግለሰቡም ወዲያውኑ ለመጠመቅ በቅቷል። (የሐዋርያት ሥራ 8:26, 27, 36, 38) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ምሥራቹ ላልተገረዙ አሕዛብ እንዲሰበክ የአምላክ ፈቃድ መሆኑ ታወቀ። አንድ መልአክ ቆርኔሌዎስ ለተባለ ፈሪሃ አምላክ ያለው አሕዛብ በራእይ ተገልጦለት ሐዋርያው ጴጥሮስን እንዲያስጠራው ነገረው። ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ጴጥሮስን ባገኙት ጊዜ “ቆርኔሌዎስ . . . አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስ አብሯቸው የሄደ ሲሆን ያልተገረዙ አሕዛብ ለመጀመሪያ ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ለመሆን በቁ። (የሐዋርያት ሥራ 10:22, 44-48) አንድ መልአክ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ካለው ሰው ጋር እንድትገናኝ ቢረዳህ ምን እንደሚሰማህ አስብ!

በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚገኝ እርዳታ

12, 13. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሊረዳቸው እንደሚችል እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን ነበር? (ለ) መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች ኃይል የሰጣቸው እንዴት ነበር?

12 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለሐዋርያቱ እርዳታ እንደሚያገኙ በመንገር አጽናንቷቸው ነበር። አብ ‘አጽናኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስ’ ይልክላቸዋል። (ዮሐንስ 14:26) ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ ሊረዳቸው እንደሚችል የሚያሳምን አጥጋቢ ምክንያት ነበራቸው። ደግሞም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመርዳት አቻ በሌለው ኃይሉ ማለትም በመንፈስ ቅዱሱ እንዴት እንደተጠቀመ የሚገልጹ ብዙ ምሳሌዎች ይዘዋል።

13 በበርካታ አጋጣሚዎች መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ለመስጠት አገልግሏል። መሳፍንት እስራኤልን ነፃ እንዲያወጡ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (መሳፍንት 3:9, 10፤ 6:34) ይኸው መንፈስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተለያየ ዓይነት ስደት ቢደርስባቸውም በድፍረት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ብርታት ሰጥቷቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 4:31) እነዚህ ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም መቻላቸው የመንፈስ ቅዱስን ተግባር በተጨባጭ አሳይቷል። “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” በወቅቱ በነበረው ዓለም የመንግሥቱን ምሥራች ሊያዳርሱ የቻሉት ከዚህ ሌላ በምን ሊሆን ይችላል?—የሐዋርያት ሥራ 4:13፤ ቆላስይስ 1:23

14. ይሖዋ ለሕዝቦቹ እውቀት ለመስጠት በመንፈስ ቅዱሱ የተጠቀመው እንዴት ነው?

14 በተጨማሪም ይሖዋ መንፈስ ቅዱሱን ለሕዝቦቹ እውቀት ለመስጠት ተጠቅሞበታል። ዮሴፍ ከአምላክ መንፈስ ባገኘው እርዳታ ፈርዖን የተመለከታቸውን ትንቢታዊ ሕልሞች መፍታት ችሏል። (ዘፍጥረት 41:16, 38, 39) ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ትሑት ለሆኑ ሰዎች ዓላማዎቹን ገልጦላቸዋል፤ ለኩሩዎች ግን ሰውሮባቸዋል። (ማቴዎስ 11:25) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ “ለሚወዱት” ስላዘጋጃቸው ነገሮች ሲናገር “እግዚአብሔር . . . ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 2:7-10) አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ በትክክል መረዳት የሚችለው የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ካገኘ ብቻ ነው።

ከአምላክ ቃል የሚገኝ እርዳታ

15, 16. ኢያሱ በጥበብ መመላለስ እንዲችል ምን እንዲያደርግ ተነግሮት ነበር?

15 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የይሖዋ ቃል ‘ለማስተማር የሚጠቅም’ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ አገልጋዮች ‘ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆነው እንዲገኙ’ ያስችላቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የአምላክ ቃል በጥንት ዘመን የኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች በወቅቱ ተጽፈው ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንዴት ጥቅም እንዳገኙ የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎች ይዟል።

16 ቅዱሳን ጽሑፎች ለአምላክ አገልጋዮች አስተማማኝ መመሪያ ለመስጠት አገልግለዋል። ኢያሱ እስራኤላውያንን የመምራት ኃላፊነት በተሰጠው ጊዜ እንዲህ ተብሎ ተነግሮት ነበር፦ “[ሙሴ የጻፈው] ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም።” አምላክ ኢያሱን በተአምር ጥበብ እንደሚሰጠው ቃል እንዳልገባለት ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ኢያሱ በጥበብ መመላለስ የሚችለው ‘የሕጉን መጽሐፍ’ ካነበበና ካሰላሰለበት ነው።—ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:1-3

17. ዳንኤልም ሆነ ንጉሥ ኢዮስያስ በወቅቱ ከነበሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል እርዳታ ያገኙት እንዴት ነበር?

17 የአምላክ ቃል ፈቃዱንና ዓላማውን ለመግለጽም አገልግሏል። ለምሳሌ ያህል ዳንኤል ኢየሩሳሌም ለምን ያህል ጊዜ ባድማ ሆና እንደምትቆይ ከኤርምያስ ትንቢት ላይ ማወቅ ችሎ ነበር። (ኤርምያስ 25:11፤ ዳንኤል 9:2) የይሁዳ ንጉሥ በነበረው በኢዮስያስ ዘመን የተፈጸመውንም ነገር ተመልከት። በዚያ ወቅት ብሔሩ ከይሖዋ ርቆ ነበር፤ ነገሥታቱ ደግሞ ሕጉን ለራሳቸው መገልበጥና በሥራ ላይ ማዋል አቁመው እንደነበረ አንዳንድ ሁኔታዎች ይጠቁማሉ። (ዘዳግም 17:18-20) ይሁንና ቤተ መቅደሱ በእደሳ ላይ በነበረበት ወቅት ‘የሕጉ መጽሐፍ’፣ በሙሴ እጅ የተጻፈው ሳይሆን አይቀርም ተገኘ። መጽሐፉ ከ800 ዓመታት በፊት ተጽፎ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ቅጂ እንደሆነ ይገመታል። ንጉሥ ኢዮስያስ መጽሐፉ ከተነበበለት በኋላ ብሔሩ ከይሖዋ ፈቃድ በጣም እንደራቀ ስለተገነዘበ በመጽሐፉ ላይ የተጻፈውን በተግባር ለማዋል ጥብቅ እርምጃ ወሰደ። (2 ነገሥት 22:8፤ 23:1-7) በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ ሕዝቦች በወቅቱ ከነበሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል እርዳታ እንዳገኙ ከዚህ መረዳት አንችልም?

ከእምነት ባልንጀሮች የሚገኝ እርዳታ

18. አንድ የይሖዋ አገልጋይ ሌላውን በሚረዳበት ጊዜ የእርዳታው ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ ብዙውን ጊዜ አገልጋዮቹን የሚረዳው በእምነት ባልንጀሮቻቸው አማካኝነት ነው። በእርግጥም አንድ የይሖዋ አገልጋይ ሌላውን በሚረዳበት ጊዜ የእርዳታው ምንጭ አምላክ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በጉዳዩ ውስጥ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አለበት። የአምላክ መንፈስ አመራሩን የሚቀበሉ ሰዎች ፍቅርንና በጎነትን ጨምሮ ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎችን እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ አንድ የአምላክ አገልጋይ ሌላውን ለመርዳት በሚነሳሳበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ የሚያከናውነውን ሥራ በተጨባጭ እናያለን። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ነው። (ዘፍጥረት 1:26) ይህም ደግነትንና ርኅራኄን ጨምሮ አምላክ ያሉትን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ እንዳለን ያሳያል። ስለዚህ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ሌላውን በሚረዳበት ጊዜ ዋነኛው የእርዳታ ምንጭ በአምሳሉ የፈጠረን ይሖዋ ነው ማለት ይቻላል።

19. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ይሖዋ በእምነት ባልንጀሮች አማካኝነት እርዳታ የሰጠው እንዴት ነበር?

19 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ አገልጋዮቹን በእምነት ባልንጀሮቻቸው አማካኝነት ይረዳ የነበረው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ በኤርምያስ አማካኝነት ለባሮክ ሕይወቱን እንዲያተርፍ ያስቻለውን ምክር እንደሰጠው ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ለሌላው ምክር እንዲሰጥ ያደርጋል። (ኤርምያስ 45:1-5) በመቄዶንያና በአካይያ የነበሩ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም የነበሩ ችግረኛ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ጉጉት እንዳሳዩ ሁሉ እውነተኛ አምላኪዎችም ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ቁሳዊ እርዳታ ለመስጠት የሚነሳሱባቸው ጊዜያት አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ ልግስና ሰዎች “እግዚአብሔርን ለማመስገን” እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸው ተናግሯል።—2 ቆሮንቶስ 9:11

20, 21. ሐዋርያው ጳውሎስ ከሮም በመጡ ወንድሞች የተጽናናው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር?

20 በተለይ ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ሌላውን ለማበረታታትና ለማጽናናት ስላደረጉት ጥረት የሚያወሱ ዘገባዎች ልብ የሚነኩ ናቸው። ከሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ጋር የተያያዘ አንድ ምሳሌ ተመልከት። ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም እያመራ በነበረበት ወቅት የአፍያን መንገድ ተብሎ በሚታወቀው የሮማውያን አውራ ጎዳና ላይ ተጉዞ ነበር። የጉዞው የመጨረሻ ክፍል ረግረጋማ በሆነ ረባዳ መሬት ላይ መጓዝ ስለሚጠይቅ አስቸጋሪ ነበር። a የሮም ጉባኤ ወንድሞች ጳውሎስ ወደዚያ እየመጣ መሆኑን ሰምተው ነበር። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? በሞቀ ቤታቸው ቁጭ ብለው የጳውሎስን ወደ ሮም መምጣት ይጠባበቁ ይሆን?

21 ከጳውሎስ ጋር አብሮ ተጉዞ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ሉቃስ “በዚያ [በሮም] የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ፣ እንዲሁም ‘ሦስት ማደሪያ’ እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ገልጾልናል። ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችላለህ? በሮም የሚኖሩ በርካታ ወንድሞች ጳውሎስ እየመጣ መሆኑን ሰምተው ስለነበር እርሱን ለመቀበል ተጉዘዋል። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ከሮም 74 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአፍዩስ ገበያ የሚባለው የታወቀ ጣቢያ ድረስ መጥተው የጠበቁት ሲሆን የቀሩት ደግሞ ከከተማዋ 58 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሦስት ማደሪያ የሚባለው ጣቢያ ድረስ መጥተዋል። ጳውሎስ ሲያያቸው ምን ተሰማው? ሉቃስ “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም” በማለት ዘግቧል። (የሐዋርያት ሥራ 28:15) እስቲ አስበው፣ ጳውሎስ ያንን ሁሉ መንገድ ተጉዘው የመጡትን ወንድሞች ማየቱ በራሱ እንዲበረታታና እንዲጽናና አስችሎታል! ጳውሎስ እንዲህ የመሰለ ድጋፍ በማግኘቱ ያመሰገነው ማንን ነበር? የመጽናኛው ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ነበር።

22. የ2005 የዓመት ጥቅሳችን ምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይስ ምን ይብራራል?

22 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አምላክ ያደረጋቸው ነገሮች እርሱ በእርግጥ ጥሩ ረዳት መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ አቻ የማይገኝለት ረዳት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በመዝሙር 121:2 [NW] ላይ የሚገኙትን “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” የሚሉትን ቃላት የ2005 የዓመት ጥቅስ አድርገው መምረጣቸው ተገቢ ነው። ይሁንና ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚረዳን እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ተመሳሳይ ጉዞ አድርጎ የነበረው ሮማዊው ባለቅኔ ሆራስ (65-68 ከክርስቶስ ልደት በፊት) መንገዱ አስቸጋሪ መሆኑን ጽፏል። ሆራስ፣ አፍዩስ የሚባለው የገበያ ቦታ “በመርከበኞችና ስግብግብ በሆኑ ባለ መጠጥ ቤቶች የተጨናነቀ” እንደሆነ ገልጿል። “አስቸጋሪ ስለሆኑት ትንኞችና እንቁራሪቶች” እንዲሁም “ጣዕሙ ደስ ስለማይለው” ውኃ አማርሮ ተናግሯል።

ታስታውሳለህ?

ይሖዋ

• በመላእክት

• በመንፈስ ቅዱስ

• በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ

• በእምነት ባልንጀሮች አማካኝነት እርዳታ የሰጠው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2005 የዓመት ጥቅስ “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” የሚለው ይሆናል።—መዝሙር 121:2 NW

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ በሮም ያሉ ወንድሞች ለሰጡት እርዳታ አምላክን አመስግኗል