ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመንን ተማርን
የሕይወት ታሪክ
ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመንን ተማርን
ናተሊ ሆልቶርፍ እንደተናገረችው
ጊዜው ሰኔ 1945 ነበር። አንድ ቀን ግርጥት ያለ ሰው የቤታችን የፊት በር ላይ ቆሞ እስኪከፈትለት ድረስ በትዕግሥት እየጠበቀ ነው። ትንሿ ልጄ ሩት በድንጋጤ እየጮኸች “እማማ፣ በር ላይ እንግዳ ቆሟል!” አለች። በሩ ላይ የቆመው ሰው ውዱ ባለቤቴ ፌርዲናንት፣ አባቷ መሆኑን በፍጹም አላወቀችም ነበር። ይህ ከመሆኑ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ማለትም ሩት ከተወለደች ከሦስት ቀን በኋላ ፌርዲናንት ከቤት ወጥቶ ሄደ፤ ከዚያም ተይዞ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታሰረ። ሆኖም ያ ሁሉ አልፎ ሩት አባቷን ለማየት በቃች፤ ቤተሰባችንም በድጋሚ አንድ ላይ ተሰባሰበ። እኔና ፌርዲናንት ስላሳለፍነው ጊዜ ብዙ የምናወራው ነገር ነበረን!
ፌርዲናንት በ1909 ኪየል በተባለች የጀርመን ከተማ የተወለደ ሲሆን እኔ ደግሞ በዚያው አገር ድሬዝደን በምትባል ከተማ በ1907 ተወለድኩ። ቤተሰባችን በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚል መጠሪያ ከሚታወቁት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። ከዚያም በ19 ዓመቴ ከኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን የወጣሁ ከመሆኑም ሌላ ሕይወቴን ለይሖዋ ወሰንኩ።
በዚህ ወቅት ፌርዲናንት የመርከበኝነት ሥልጠና ከሚሰጥበት ኮሌጅ ተመርቆ መርከበኛ ሆኖ ነበር። በመርከብ በሚጓዝባቸው ጊዜያት የአምላክን ህልውና በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች በአእምሮው ይመላለሱ ነበር። አንድ ቀን ከጉዞ መልስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነ ወንድሙን ሊጠይቅ ሄደ። በዚህ ጊዜ ከወንድሙ ጋር ባደረገው ውይይት አእምሮውን ይረብሹት ለነበሩት ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ አገኘ። ከዚያም የሉተራን
ቤተ ክርስቲያን አባልነቱን ከመሰረዙም በላይ የመርከበኝነት ሥራውን ለማቆም ወሰነ። በስብከቱ ሥራ በተካፈለበት የመጀመሪያ ቀን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በዚህ ሥራ የመቀጠል ጠንካራ ፍላጎት አደረበት። ፌርዲናንት የዚያኑ ዕለት ምሽት ሕይወቱን ለይሖዋ የወሰነ ሲሆን ከዚያም በነሐሴ 1931 ተጠመቀ።መርከበኛና ሰባኪ
ፌርዲናንት ወደ ኔዘርላንድ ሄዶ በስብከቱ ሥራ ድጋፍ ለመስጠት ኅዳር 1931 በባቡር ተሳፍሮ ወደ እዚያ ተጓዘ። በዚያ አገር ለሚካሄደው የስብከት ሥራ አመራር ለሚሰጠው ወንድም መርከበኛ እንደሆነ ሲነግረው ወንድም በጣም ተደስቶ “አንተማ በጣም ታስፈልገናለህ!” አለው። አንድ የአቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ቡድን ከአገሪቱ በስተ ሰሜን ባለው የባሕር ዳርቻ ላይ ለሚገኙት ነዋሪዎች ምሥራቹን ማዳረስ እንዲችል ወንድሞች ጀልባ ተከራይተው ነበር። ቡድኑ አምስት አባላትን ያቀፈ ቢሆንም አንዳንቸውም ጀልባ መንዳት አይችሉም ነበር። በመሆኑም ፌርዲናንት የጀልባው ተቆጣጣሪ ሆነ።
ከስድስት ወራት በኋላ ፌርዲናንት በደቡብ ኔዘርላንድ በምትገኘው በቲልበርግ አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ጥያቄ ቀረበለት። በዚያን ወቅት እኔም አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ወደ ቲልበርግ ተጓዝኩ፤ እዚያም ከፌርዲናንት ጋር ተገናኘን። ሆኖም ወዲያውኑ በሰሜን ኔዘርላንድ በሚገኘው ግሮኒንገን እንድናገለግል ተመደብን። እዚያ ከሄድን በኋላ በጥቅምት 1932 የተጋባን ሲሆን በርካታ አቅኚዎች በሚኖሩበት አንድ ቤት ውስጥ አገልግሎታችንን ሳናቋርጥ የጫጉላ ጊዜያችንን አሳለፍን!
ሴት ልጃችን ኤስተር በ1935 ተወለደች። የገንዘብ አቅማችን በጣም ውስን ቢሆንም በአቅኚነት አገልግሎታችን ለመቀጠል ቆርጠን ነበር። ወደ አንድ መንደር ተዛወርንና አንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። እኔ ሕፃኗን ቤት ቁጭ ብዬ ስጠብቅ ባለቤቴ ለረጅም ሰዓት ያገለግላል። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ እኔ ሳገለግል እርሱ ልጃችንን ይጠብቃል። ኤስተር አድጋ አገልግሎት ይዘናት መውጣት እስከጀመርንበት ጊዜ ድረስ በዚህ መልኩ እናገለግል ነበር።
ብዙም ሳይቆይ በአውሮፓ የፖለቲካው ሁኔታ አስጊ እየሆነ መጣ። በጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት እየደረሰባቸው መሆኑን ስንሰማ እኛም ውሎ አድሮ ችግር እንደሚገጥመን ተገነዘብን። ‘ከባድ ስደት ቢመጣ በጽናት ልንወጣው እንችል ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበን ጀመር። በ1938 የኔዘርላንድ ባለ ሥልጣናት የውጪ ዜጎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን እንዳያሰራጩ የሚከለክል ሕግ አወጡ። የኔዘርላንድ ወንድሞች አገልግሎታችን እንዳይስተጓጎልብን ለመርዳት ሲሉ ለመወያየት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር ሰጡን። አንዳንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቻልን።
በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ የሚደረግበት ጊዜ እየተቃረበ ነበር። ለባቡር መሳፈሪያ የምንከፍለው ገንዘብ ባይኖረንም እንኳን ስብሰባው ላይ ለመገኘት ቆርጠን ነበር። ስለዚህ ትንሿ ልጃችንን ኤስተርን ከመሪው ጋር በተያያዘ የሕፃናት መቀመጫ ላይ አስቀምጠን የሦስት ቀን የብስክሌት ጉዞ ጀመርን። ማታ ማታ በመንገዳችን ላይ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቤት እናድር ነበር። በአገር አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመዝሙር 31:6 ቃላት የሕይወታችን መርህ ሆነው አገልግለውናል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በመገኘታችን በጣም ደስ አለን! ስብሰባው ከፊታችን ለሚጠብቁን ፈተናዎች አዘጋጅቶናል። ከሁሉም በላይ በአምላክ እንድንታመን ተበረታተናል። “በእግዚአብሔር ታመንሁ” የሚሉትናዚዎች ያድኑን ጀመር
ናዚዎች በግንቦት 1940 ኔዘርላንድን ወረሩ። ብዙም ሳይቆይ ጌስታፖዎች ወይም የደኅንነት ፖሊሶች የደረሱንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መልክ እያስያዝን ሳለ በድንገት ወደ ቤታችን መጡ። ከዚያም ፌርዲናንትን ወደ ጌስታፖ ዋና መሥሪያ ቤት ይዘውት ሄዱ። እኔና ኤስተር በየጊዜው እየሄድን እንጠይቀው ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ እኛው ፊት በመስቀለኛ ጥያቄ ያፋጥጡት ብሎም ይደበድቡት ነበር። ፌርዲናንት በታኅሣሥ ወር ላይ ሳናስበው ከእስር የተለቀቀ ቢሆንም ያገኘው ነጻነት ግን በአጭሩ ተቀጨ። አንድ ቀን ወደ ቤት ስንመለስ የጌስታፖ መኪና ቤታችን አቅራቢያ ቆሞ አየን። በዚህ ጊዜ ፌርዲናንት ከአካባቢው ጠፋ፤ እኔና ኤስተር ግን ወደ ቤት ገባን። ጌስታፖዎች ፌርዲናንትን መያዝ ስለፈለጉ አሰፍስፈው እየጠበቁን ነበር። እነርሱ ከሄዱ በኋላ ደግሞ የዚያኑ ዕለት ምሽት የኔዘርላንድ ፖሊሶች መጥተው ለምርመራ ይዘውኝ ሄዱ። በሚቀጥለው ቀን እኔና ኤስተር በቅርቡ የተጠመቁ ኖርደር የሚባሉ ባልና ሚስት ቤት ተደበቅን፤ እነርሱም መጠለያ በመስጠትና እኛን በመሸሸግ ረድተውናል።
በ1941 በጥር ወር መገባደጃ ገደማ መኖሪያ ቤት ባለው ጀልባ ላይ የሚኖሩ አንድ አቅኚ ባልና ሚስት ታሰሩ። በሚቀጥለው ቀን አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች (ተጓዥ አገልጋይ) እና ባለቤቴ የባልና ሚስቱን ንብረት ለመሰብሰብ ጀልባው ላይ ወጡ። ይሁንና የጌስታፖ ግብረ አበሮች በድንገት ያዟቸው። በዚህ ጊዜ ፌርዲናንት አምልጧቸው በብስክሌቱ አካባቢውን ጥሎ ሲሸሽ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ግን እስር ቤት ተወሰደ።
ከዚያም በኃላፊነት ቦታ ያሉ ወንድሞች ፌርዲናንትን በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ቦታ እንዲሠራ ጠየቁት። ይህም ወደ ቤት መምጣት የሚችለው በወር ለሦስት ቀናት ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ለእኛ አዲስ ፈታኝ ሁኔታ ቢሆንም አቅኚነቴን አላቋረጥኩም። ጌስታፖዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ማደኑን አጠናክረው ስለቀጠሉ መኖሪያችንን የግድ መቀያየር ነበረብን። እንዲያውም በ1942 ብቻ ሦስት ጊዜ ቤት ቀይረናል። በመጨረሻ በሮተርዳም ተቀመጥን፤ ይህ ከተማ ፌርዲናንት አገልግሎቱን በድብቅ ያከናውን ከነበረበት ቦታ በጣም ይርቃል። በዚህን ጊዜ ሁለተኛ ልጄን ለመውለድ ተቃርቤ ነበር። እዚያ ስንደርስ ሁለት ወንዶች ልጆቻቸው ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተወሰዱባቸው ወንድምና እህት ከምፕ አብረናቸው እንድንኖር ወደ ቤታቸው ወሰዱን።
ጌስታፖዎች እግር በእግር ይከታተሉን ጀመር
ሁለተኛ ልጃችን ሩት ሐምሌ 1943 ላይ ተወለደች። ፌርዲናንት ሩት ከተወለደች በኋላ ለሦስት ቀናት ብቻ አብሮን ቆይቶ ተለይቶን ሄደ፤ ከዚያም ለረጅም ጊዜ አላየነውም። ከሦስት ሳምንታት ገደማ በኋላ አምስተርዳም ውስጥ ተያዘ። ከዚያም ወደ ጌስታፖ ጣቢያ ወሰዱትና ማንነቱን አረጋገጡ። ጌስታፖዎች የስብከት ሥራችንን በተመለከተ መረጃ እንዲሰጥ ለማስገደድ ከባድ ምርመራ ቢያደርጉበትም ፌርዲናንት የነገራቸው ነገር ቢኖር የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዳች ተሳትፎ እንደማያደርግ ብቻ ነበር። ጌስታፖዎች ፌርዲናንት ጀርመናዊ ሆኖ ሳለ ለውትድርና አገልግሎት ራሱን ባለማቅረቡ በጣም ተናደዱ፤ እንደ ከሐዲ ስለሚታይ እንደሚገድሉት ይዝቱበት ነበር።
ፌርዲናንት ለቀጣዮቹ አምስት ወራት በእስር ቤት የቆየ ሲሆን በተደጋጋሚ የሚሰነዘርበትን ትረሸናለህ የሚል ዛቻም በጽናት አሳልፏል። ለይሖዋ ካለው የታማኝነት አቋም ንቅንቅ አላለም። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እርግጥ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲይዝ አይፈቀድለትም ነበር። ሌሎች እስረኞች ግን ማግኘት ይችሉ ስለነበር ፌርዲናንት አብሮት የታሰረውን ሰው ቤተሰቦቹ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲልኩለት እንዲጠይቅ አግባባው፤ ሰውየውም በሐሳቡ በመስማማት መጽሐፍ ቅዱስ አስመጣ። ከበርካታ ዓመታት በኋላም ቢሆን ፌርዲናንት ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሳ ፊቱ በደስታ ይፈካና “ያንን መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘቴ በጣም ነበር የጠቀመኝ!” ይላል።
ፌርዲናንት በጥር 1944 መጀመሪያ ላይ በኔዘርላንድ፣
ቪውኸት ወደሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ በድንገት ተዛወረ። በካምፑ ውስጥ ከነበሩ 46 የይሖዋ ምሥክር እስረኞች ጋር መቀላቀል በመቻሉ ወደዚህ ቦታ መዛወሩ ያልታሰበ በረከት ሆኖለት ነበር። ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወሩን መስማቴ አስደሰተኝ፤ ምክንያቱም በሕይወት መኖሩን ማወቅ የቻልኩት በዚያን ጊዜ ነበር!በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያለማሰለስ መስበክ
በካምፑ ውስጥ ሕይወት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ሥር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ወፍራም ልብስ አለማግኘትና ኃይለኛ ብርድ የዕለት ተዕለት ገጠመኞች ነበሩ። በመሆኑም ፌርዲናንት ኃይለኛ የቶንሲል በሽታ ያዘው። ደጅ ላይ በብርድ ረጅም ሰዓት የሚፈጅ ስም ጥሪ ይደረግ ስለነበር አንድ ቀን ከስም ጥሪው በኋላ ለሕክምና ወደ ክሊኒክ ሄደ። እዚህ ቦታ መተኛት የሚፈቀድላቸው 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ትኩሳት የያዛቸው ሕመምተኞች ብቻ ነበሩ። የፌርዲናንት ሰውነት ትኩሳት 39 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ብቻ ስለነበር በክሊኒኩ እንዲተኛ አልተፈቀደለትም! እንዲያውም ሥራውን እንዲቀጥል ተነገረው። ይሁን እንጂ አብረውት የነበሩ እስረኞች ስላዘኑለት ለጥቂት ጊዜ በሞቃት ቦታ ተደብቆ እንዲያርፍ ያደርጉት ነበር። የሙቀት ወቅት ሲመጣ ከሕመሙ ማገገም ቻለ። በተጨማሪም አንዳንድ ወንድሞች ስንቅ በሚመጣላቸው ጊዜ ከሌሎች ጋር ተካፍለው ይበሉ ስለነበር ፌርዲናንት እንደገና ብርታት እያገኘ መጣ።
ባለቤቴ ከመታሰሩ በፊት ስብከት ዋነኛ ሥራው ነበር፤ በካምፑ ውስጥም ቢሆን ስለ እምነቱ ለሌሎች መናገሩን አላቆመም። የካምፑ ባለ ሥልጣናት ልብሱ ላይ ያለውን የይሖዋ ምሥክር መሆኑን የሚያሳውቀውን ከወይን ጠጅ ጨርቅ የተሠራ ባለ ሦስት ማዕዘን አርማ እያዩ ብዙ ጊዜ ያፌዙበት ነበር። እርሱ ግን አጋጣሚውን ከእነርሱ ጋር ውይይት ለመክፈት ይጠቀምበት ነበር። በመጀመሪያ የወንድሞች የስብከት ክልል አብዛኞቹ እስረኞች የይሖዋ ምሥክሮች በሆኑበት ሕንፃ ውስጥ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ ‘ለሌሎች እስረኞችም መስበክ የምንችለው እንዴት ይሆን?’ እያሉ ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። የካምፑ አስተዳደር ሳያውቀው ለዚህ ችግራቸው መፍትሄ ሰጣቸው። እንዴት?
ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንና 12 መጽሐፍ ቅዱሶችን በድብቅ ማግኘት ችለው ነበር። አንድ ቀን ጠባቂዎቹ ከእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ጥቂቶቹን አገኙ፤ የማን እንደሆኑ ግን ማወቅ አልቻሉም። በዚህን ጊዜ የካምፑ ኃላፊዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ለመበታተን ወሰኑ። ስለዚህ በቅጣት መልክ ወንድሞች የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ እስረኞች ወዳሉባቸው ሌሎች ሕንፃዎች ተላኩ። ከዚህ በተጨማሪ በምግብ ሰዓት እንኳን የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ እስረኞች ጋር መቀመጥ ነበረባቸው። ይህ ዝግጅት ወንድሞች ድሮውንም ሊያከናውኑት ለሚፈልጉት ነገር ማለትም ለሌሎች እስረኞች ለመስበክ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላቸው ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
ሁለት ሴቶች ልጆች ለብቻ ማሳደግ
በዚህ ጊዜ እኔና ሁለት ልጆቼ በሮተርዳም እንኖር ነበር። በ1943/44 የነበረው የክረምት ወቅት ከተለመደው በላይ ከብዶ ነበር። ከቤታችን በስተ ጀርባ የአየር መቃወሚያ መድፍ የሚቆጣጠሩ የጀርመን ወታደሮች ጓድ ይገኝ ነበር። ከቤታችን ፊት ለፊት ደግሞ ጀርመንን የሚወጉት የሕብረ ብሔራቱ ኃይሎች ዋነኛ የቦምብ ዒላማ የሆነው የቫል ወደብ ይገኛል። ሕይወታችንን ለማትረፍ የተደበቅንበት ቦታ የሚያዋጣ አልነበረም። ከዚህም በላይ ምግብ እንደ ልብ አይገኝም ነበር። ስለዚህ ከምንጊዜውም በበለጠ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንዳለብን በሚገባ ተማርን።—ምሳሌ 3:5, 6
የስምንት ዓመቷ ኤስተር ለችግረኞች ሾርባ ወደሚከፋፈልበት ቦታ በመሄድ ጥቂት ቁጥር ያለውን ቤተሰባችንን ለመርዳት የበኩሏን ታደርግ ነበር። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ተራዋ ሲደርስ ሾርባው ያልቃል። አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ ወጥታ ሳለ የነበረችበት ቦታ ከአየር በቦምብ ይደበደብ ጀመር። ድብደባውን ስሰማ በጣም ተሸበርኩ፤ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ኤስተር ምንም ጉዳት ሳይደርስባት እንዲያውም ጥቂት ቀይ ሥር ይዛ በመመለሷ ጭንቀቴ በደስታ እንባ ተተካ። ገና እንደገባች “እንዴት አመለጥሽ?” ብዬ ጠየቅኳት። ረጋ ብላ “አባባ ቦምብ ሲጣል ‘መሬት ላይ ለጥ ብለሽ ተኚ ከዚያም ጸልዪ’ ብሎ እንደነገረኝ አደረግኩና ለመትረፍ ቻልኩ” አለችኝ።
አነጋገሬ ጀርመናዊ እንደሆንኩ ስለሚያስታውቅብኝ ምግባችንን ኤስተር መግዛቷ ጥሩ ዘዴ ነበር። ይህን ሁኔታ ያስተዋሉት የጀርመን ወታደሮች ኤስተርን አንዳንድ
ነገሮች ይጠያይቋት ጀመር። ሆኖም አንድም ምስጢር አላወጣችም። ኤስተርን መጽሐፍ ቅዱስ ከማስጠናቴም በላይ ትምህርት ቤት መግባት ስላልቻለች ማንበብ፣ መጻፍና ሌሎች ሙያዎችም ቤት ውስጥ አስተምራት ነበር።ኤስተር በአገልግሎትም ትረዳኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስሄድ ከፊቴ ቀድማ ትሄድና የሚከታተለን ሰው አለመኖሩን ታረጋግጣለች። እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ጋር የምንግባባባቸው ምልክቶች በቦታቸው መቀመጣቸውን ታረጋግጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የማስጠናው ሰው በሸክላ ያለ አበባ በመስኮቱ ደፍ ላይ ካስቀመጠ ወደ ቤት መግባት እንደምችል ማመልከቱ ነበር። በምናጠናበት ጊዜ ደግሞ ኤስተር ከቤት ውጪ ሩትን በጋሪ ወደ ላይና ወደ ታች እየገፋች በማጫወት በአካባቢው የሚከናወነውን ነገር ትከታተል ነበር።
ወደ ዛክሰንሃውዘን ተወሰደ
ፌርዲናንት ምን ገጥሞት ይሆን? በመስከረም 1944 ከሌሎች በርካታ እስረኞች ጋር ወደ አንድ ባቡር ጣቢያ ተወሰዱና ለእነርሱ በተዘጋጁ ፉርጎዎች ውስጥ ሰማንያ ሰማንያ እያደረጉ አጨቋቸው። በየፉርጎው ውስጥ ሁለት ሁለት ባልዲዎች የነበሩ ሲሆን አንደኛው ለመጸዳጃ የሚያገለግል፤ ሌላው ደግሞ የመጠጥ ውኃ የሚቀመጥበት ነበር። በእነዚህ ፉርጎዎች ውስጥ ታጭቀው ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ተጓዙ! ፉርጎዎቹ ቀዳዳ ያላቸው ከመሆኑ በስተቀር ደህና የአየር ማስገቢያ አልነበራቸውም። የሙቀቱ፣ የረሃቡና የጥማቱ ነገር ለመግለጽ ያስቸግራል፤ ግማቱማ እንዲያው ሆድ ይፍጀው።
ባቡሩ አስከፊው የዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ላይ ቆመ። ወንድሞች ይዘዋቸው ከመጡት 12 መጽሐፍ ቅዱሶች በስተቀር እስረኞቹ በሙሉ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ተነጠቁ!
ፌርዲናንትና ሌሎች ስምንት ወንድሞች በዛክሰንሃውዘን ሥር በሚተዳደረው በራተኖ ከተማ በሚገኘው የጦር መሣሪያ የሚመረትበት ካምፕ እንዲሠሩ ተላኩ። ወንድሞች እንደሚገደሉ ብዙ ጊዜ ቢዛትባቸውም እንኳን እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞች አልሆኑም። ባነበቡት ጥቅስ ላይ ቀኑን በሙሉ ሲያሰላስሉ መዋል እንዲችሉ ጠዋት ጠዋት እንደ መዝሙር 18:2 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አብረው በማንበብ ጽኑ አቋማቸውን እንዳያላሉ እርስ በርስ ይበረታቱ ነበር። ይህም በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያስቡ አስችሏቸዋል።
በመጨረሻ የመድፍ ድምፅ ሲያስገመግም የሕብረ ብሔራቱና የሩሲያ ወታደሮች ወደ አካባቢው እየተቃረቡ መሆናቸው ታወቀ። ፌርዲናንትና ሌሎች ወንድሞች ወደ ታሰሩበት ካምፕ ቀድመው የደረሱት የሩሲያ ወታደሮች ነበሩ። ወታደሮቹ ለእስረኞቹ ምግብ ከሰጧቸው በኋላ ካምፑን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዟቸው። ከዚያም ሚያዝያ 1945 ማብቂያ ላይ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው።
በመጨረሻ ቤተሰቡ ተሰባሰበ
ፌርዲናንት ሰኔ 15 ቀን ኔዘርላንድ ደረሰ። በግሮኒንገን የሚገኙ ወንድሞች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉለት። በሕይወት እንዳለንና በአንድ የአገሪቱ ክፍል እንደምንኖር ሰማ፤ ለእኛም ወደ ኔዘርላንድ መመለሱ ተነገረን። እስክናገኘው ድረስ ጊዜው በጣም ረዘመብን። በመጨረሻ አንድ ቀን ትንሿ ልጃችን ሩት “እማማ፣ በር ላይ እንግዳ ቆሟል!” አለችኝ። እንግዳው አባቷና ውዱ ባለቤቴ ነበር!
ወደ ቀድሞ ሕይወታችን ከመመለሳችን በፊት ብዙ ችግሮች መፈታት ነበረባቸው። መኖሪያ ቤት አልነበረንም፤
ትልቁ ችግር ደግሞ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንደገና የማግኘታችን ጉዳይ ነበር። ጀርመናውያን በመሆናችን ምክንያት የኔዘርላንድ ባለ ሥልጣናት ለብዙ ጊዜያት እንደ መጤ ይቆጥሩን ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ተደላድለን መኖርና ስንናፍቀው የነበረውን ይሖዋን በቤተሰብ መልክ የማገልገል አጋጣሚ አገኘን።“በእግዚአብሔር ታመንሁ”
ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት እኔና ፌርዲናንት በእነዚያ ክፉ ቀናት እኛ ያሳለፍነው ዓይነት ችግር ከደረሰባቸው ጓደኞቻችን ጋር ስንገናኝ ይሖዋ ያደረገልንን ፍቅራዊ አመራር እያነሳን እንጫወት ነበር። (መዝሙር 7:1) ባሳለፍናቸው ዓመታት ይሖዋ የመንግሥቱን ምስራች በማስፋፋት ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ስለፈቀደልን በጣም ደስተኞች ነን። እንዲሁም የወጣትነት ዕድሜያችንን በይሖዋ ቅዱስ አገልገሎት በማሳለፋችን በጣም ደስተኞች ነን።—መክብብ 12:1
የናዚ የስደት ዘመን ካለፈ በኋላ ፌርዲናንት ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት እስከ ታኅሣሥ 20, 1995 ድረስ ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት አብረን ይሖዋን አገልግለናል። በቅርቡ 98 ዓመት ይሆነኛል። ልጆቻችን በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት ደጋፊዎቻችን ስለነበሩና እስከ አሁን ድረስ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለስሙ ክብር የሚያመጣ ሥራ ማከናወን በመቻሌ ይሖዋን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ ላደረገልኝ ነገር ሁሉ አመሰግነዋለሁ፤ በሕይወት እስካለሁ ድረስ “በእግዚአብሔር ታመንሁ” የሚለውን መርሄን እንደያዝኩ ለመቀጠል ልባዊ ምኞቴ ነው።—መዝሙር 31:6
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥቅምት 1932 ከፌርዲናንት ጋር
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥራቹን ለመስበክ ያገለገለችው “አልሚና” የምትባለው ጀልባና ተሳፋሪዎቿ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከፌርዲናንትና ከልጆቻችን ጋር ሆኜ