ራስህን ከሌሎች ጋር ታወዳድራለህ?
ራስህን ከሌሎች ጋር ታወዳድራለህ?
በውበቱ፣ በተወዳጅነቱ፣ ነገሮችን በፍጥነት በመረዳት ችሎታው ወይም በትምህርት ቤት ውጤቱ የሚበልጠው ሌላ ሰው ያላጋጠመው ከመካከላችን ማን አለ? ሌሎች ደግሞ ከእኛ የተሻለ ጤና ወይም የሚያረካ ሥራ ይኖራቸው ይሆናል፤ እንዲሁም ይበልጥ የተሳካላቸው ወይም ብዙ ጓደኞች ያሏቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ አንዳንዶች ከእኛ የበለጠ ንብረት፣ ገንዘብና ዘመናዊ መኪና ያላቸው ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ደስተኞች መስለው ይታዩ ይሆናል። ከእነዚህ ነገሮች አንጻር ራሳችንን ከሌሎች ጋር እናወዳድራለን? ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ሊወገድ የማይችል ነገር ነው? ክርስቲያኖች ይህን ባሕርይ ሊያስወግዱት የሚገባቸው ለምንድን ነው? ራሳችንን ከማንም ጋር ሳናወዳድር ደስተኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድረው ለምንና መቼ ነው?
ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ማወዳደራቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ወይም ይህን ስሜታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታሰባል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ከእኩዮቻቸው አንሰው መታየት አይፈልጉም። በተጨማሪም ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር በራስ አለመተማመንን ለመቀነስ እንዲሁም ችሎታችንና አቅማችን ምን ድረስ እንደሆነ ለመገምገም ያስችላል ተብሎ ይታሰባል። ሌሎች ሰዎች የደረሱበትን ደረጃ እንመለከታለን። እነዚህ ሰዎች በብዙ መንገዶች ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉ ከሆነና አንድ የሆነ ደረጃ ላይ ከደረሱ እኛም ተመሳሳይ ግቦች ላይ መድረስ እንደምንችል ሊሰማን ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን የሚያወዳድሩት ከሚመስሏቸው ማለትም አንድ ዓይነት ጾታ፣ ተመሳሳይ ዕድሜ፣ ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ካላቸው እንዲሁም በግል ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ነው። በአብዛኛው በመካከላችን በጣም ሰፊ ልዩነት እንዳለ ከሚሰማን ሰው ጋር ራሳችንን አናወዳድርም። ነገሩን በሌላ መንገድ ለማስረዳት ያህል በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ልጃገረድ አብረዋት ከሚማሩ ልጆች ጋር እንጂ ከታዋቂ ሞዴሊስት ጋር ራሷን አታወዳድርም፤ በተመሳሳይም ሞዴሊስቷ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከምትገኘው ልጃገረድ ጋር ራሷን አታወዳድርም።
ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር የሚያወዳድሩት በምን መስኮች ነው? በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እንደ ጉብዝና፣ ውበት፣ ሀብትና አልባሳት ያሉ ንብረቶች ወይም ተሰጥኦዎች ለውድድር ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድረው ይበልጥ ትኩረት በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ነው። ለምሳሌ ያህል ቴምብር የመሰብሰብ ፍላጎት ከሌለን በስተቀር ብዙ ቴምብር ባጠራቀመ ጓደኛችን አንቀናም።
የውድድር መንፈስ ከደስታ እስከ መንፈስ ጭንቀት፣
ከአድናቆትና ያንን ሰው ለመምሰል ከመፈለግ እስከ ብስጭት ወይም ጥላቻ ድረስ የተለያዩ ስሜቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል። ከእነዚህ ስሜቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ጎጂ ከመሆናቸውም በላይ ከክርስቲያናዊ ባሕርያት ጋር ይጋጫሉ።በፉክክር መንፈስ ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር
ራሳቸውን ከሌሎች ጋር አወዳድረው “በልጠው” ለመገኘት የሚጣጣሩ ብዙ ሰዎች የፉክክር መንፈስ ይታይባቸዋል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከሌሎች ልቀው መታየት ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም ይህን ግባቸውን እስኪያሳኩ ድረስ ደስታ አይኖራቸውም። እንዲህ ባሉ ግለሰቦች መካከል መኖር ደስታ ያሳጣል። ከሌሎች ጋር የሚመሠርቱት ወዳጅነት ከአንገት በላይ ሲሆን ግንኙነታቸውም ቢሆን ውጥረት የነገሠበት ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ትሕትና የሚጎድላቸው ከመሆኑም በላይ አስተሳሰባቸው ሌሎች በቀላሉ የበታችነት ስሜትና እፍረት እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ ባልንጀራን እንደራስ ስለመውደድ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ አያውሉም።—ማቴዎስ 18:1-5፤ ዮሐንስ 13:34, 35
ሌሎች ሰዎች “ያነሱ” ሆነው እንዲሰማቸው ማድረግ ስሜታቸውን ወደ ማቁሰል ያደርሳል። አንዲት ደራሲ እንዳሉት ከሆነ “ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች እኛ እንዲኖረን የምንመኘውን ንብረት አግኝተው ስንመለከት በጣም እናዝናለን።” የፉክክር መንፈስ ቅናትንና ብስጭትን የሚቀሰቅስ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው ባገኘው ንብረት፣ ብልጽግና፣ ሥልጣን፣ ዝና፣ ጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት ነገሮች እንዳንደሰት ያደርጋል። ይህ ደግሞ ማብቂያ ወደሌለው የፉክክር እሽክርክሪት ውስጥ ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ ‘መጎነታተልን’ ወይም መፎካከርን ያወግዛል።—ገላትያ 5:26
የምቀኝነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች የሚቀኑባቸውን ሰዎች የሥራ ክንውን በማንኳሰስ የቆሰለውን ለራስ ጥሩ ግምት የማሳደር ስሜታቸውን ለመፈወስ ይሞክራሉ። እንዲህ ያለው ባሕርይ ያን ያህል ጎጂ ላይመስል ይችላል፤ ሆኖም አንድ ሰው እንዲህ ያለ ባሕርይ እንዳለው አውቆ ማስተካከያ ካላደረገ መጥፎ ድርጊት ወደመፈጸም ሊመራው ይችላል። እስቲ ቅናት መጥፎ ድርጊት ወደመፈጸም ሊያደርስ እንደሚችል የሚያሳዩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እንመልከት።
ይስሐቅ በፍልስጥኤማውያን መካከል ይኖር በነበረበት ጊዜ “ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት።” በዚህም የተነሳ አባቱ አብርሃም ያስቆፈራቸውን የውኃ ጉድጓዶች የደፈኑ ሲሆን ንጉሣቸውም፣ ይስሐቅ አካባቢውን ለቅቆ እንዲሄድ ጠየቀው። (ዘፍጥረት 26:1-3, 12-16) ቅናታቸው እልኸኛ አድርጓቸዋል እንዲሁም የይስሐቅን ንብረት እንዲያጠፉ አነሳስቷቸዋል። ይስሐቅ ባገኘው ብልጽግና እየተደሰተ በመካከላቸው እንዲኖር አልፈለጉም።
ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ዳዊት ታዋቂ እንዲሆን የሚያደርገውን ጀብዱ በጦር ሜዳ ፈጸመ። የእስራኤል ሴቶች “ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገደለ” በማለት ስለፈጸመው ጀብዱ ከፍ ከፍ አደረጉት። ሳኦል በሴቶቹ በእጅጉ የተወደሰ ቢሆንም ይህ ንጽጽር እርሱን ዝቅ እንደሚያደርገው አድርጎ ስለቆጠረው ልቡ ውስጥ ቅናት አቆጠቆጠ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዳዊት ላይ ቂም ያዘበት። ብዙም ሳይቆይ፣ በዳዊት ላይ ካደረጋቸው በርካታ የመግደል ሙከራዎች መካከል አንዱን ፈጸመ። ቅናት በእርግጥም የክፋት ምንጭ ነው!—1 ሳሙኤል 18:6-11
ስለዚህ ትልቅ ተግባር ከፈጸሙ ወይም በአንዳንድ ነገሮች ከሚበልጡን ሰዎች ጋር ራሳችንን በማወዳደር የቅንዓትና የፉክክር ስሜት በውስጣችን እንዳይፈጠር እንጠንቀቅ! ቅንዓትና ፉክክር ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚቃረኑ ጎጂ ስሜቶች ናቸው። እነዚህን አስተሳሰቦች እንዴት መቋቋም እንደምንችል ከማየታችን በፊት እስቲ ሌላ የውድድር መንፈስ የሚቀሰቅስ ነገር እንመልከት።
ራሳችንን በመገምገም መደሰት
‘ጎበዝ ነኝ? ቁመናዬ ማራኪ ነው? ጥሩ ችሎታ አለኝ? ጥሩ ጤንነት አለኝ? ተሰሚነት ያለኝና የምወደድ ሰው ነኝ? ከሆነስ ምን ያህል?’ ከመስተዋት ፊት ቆመን ራሳችንን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ልማድ ላይኖረን ይችላል። ነገር ግን አንዲት ደራሲ እንደገለጹት “ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን እንደሚመጡና ይብዛም ይነስም ለራሳችን አጥጋቢ መልስ እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።” ምን መሥራት እንደሚችል በእርግጠኝነት የማያውቅ ሰው ራሱን ከማንም ጋር ሳያወዳድር ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት የቅናት መንፈስ ሳያድርበት ስለእነዚህ ነገሮች ሊያሰላስል ይችላል። ይህ ሰው
ራሱን እየገመገመ ነው። እንዲህ ማድረግ ምንም ስህተት የለውም። ነገር ግን ማንነታችንን የምንገመግመው ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር መሆን የለበትም።ሁላችንም ብንሆን በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ችሎታችን እንደመልካችን ይለያያል። ምንጊዜም ቢሆን ከእኛ የተሻለ ችሎታ ያላቸው የሚመስሉ ሰዎች ይኖራሉ። ስለዚህ እነዚህን ሰዎች በቅናት ዓይን ከመመልከት ይልቅ ትክክልና ጥሩ የሆነውን መለየት በሚያስችሉን እርግጠኛ የሆኑ የአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ብቃታችንን መመዘን ይገባናል። ይሖዋ እያንዳንዳችን ባለን ነገር ይደሰታል። ከማንም ጋር ሊያወዳድረን አይፈልግም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል” በማለት መክሮናል።—ገላትያ 6:4
ቅናትን መዋጋት
ሁሉም ሰው ፍጽምና ስለሚጎድለው ቅናትን ለመቋቋም የማያቋርጥ ብርቱ ትግል ማድረግ ያስፈልገዋል። “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ማወቅና ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ጳውሎስ ዝንባሌው ወደ ኃጢአት እንደሚያደላ ተገንዝቦ ነበር። ይህን ዝንባሌውን ለመዋጋት ‘ሰውነቱን እየጎሰመ እንዲገዛለት ማድረግ’ ነበረበት። (ሮሜ 12:10፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27) እኛም ከጳውሎስ ተሞክሮ የፉክክር አስተሳሰብን በመልካም ነገሮች መተካት እንዳለብን እንማራለን። ‘ከሆንነው በላይ ራሳችንን ከፍ አድርገን እንዳናስብ’ ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ ይገባናል።—ሮሜ 12:3
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ማሰላሰልም ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አምላክ ወደፊት እንደሚሰጠን ቃል ስለገባልን ገነት እስቲ አስብ። በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው ሰላማዊ ይሆናል፤ እንዲሁም ጥሩ ጤንነት፣ የተትረፈረፈ ምግብ፣ ምቹ መኖሪያ ቤትና አርኪ ሥራ ይኖረዋል። (መዝሙር 46:8, 9፤ 72:7, 8, 16፤ ኢሳይያስ 65:21-23) በዚያን ወቅት ከሌሎች መብለጥ እንዳለበት የሚሰማው ሰው ይኖራል? በፍጹም። ይህ ዝንባሌ እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆን ነገር አይኖርም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በዚያን ጊዜ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጠንም ሁሉም ሰው የሚፈልገውንና የሚችለውን በመሥራት ይደሰታል ብለን ማሰባችን ምክንያታዊ ነው። ምናልባት አንድ ሰው ስለ ከዋክብት ጥናት ያካሂድ ይሆናል፤ ሌላው ደግሞ የሚያምሩ የጨርቃ ጨርቅ ንድፎችን ያወጣ ይሆናል። ታዲያ አንዱ በሌላው ላይ የሚቀናበት ምን ምክንያት ይኖረዋል? ወዳጆቻችን የሚያከናውኑት ተግባር ለተጨማሪ ሥራ የሚያነሳሳን እንጂ ለብስጭት የሚዳርገን አይሆንም። በዚያን ጊዜ እንዲህ ያለው የፉክክር መንፈስ ጊዜ ያለፈበት ይሆናል።
እንዲህ ያለ ሕይወት ለማግኘት የምንመኝ ከሆነ በዚያን ጊዜ የሚኖረውን አስተሳሰብ ከአሁኑ ለማዳበር ጥረት ማድረግ አይገባንም? አሁንም ቢሆን በዙሪያችን ያለው ዓለም ካለበት በርካታ ችግር ነፃ በሆነ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንገኛለን። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የፉክክር መንፈስ የማይኖር መሆኑ ከአሁኑ ይህንን መንፈስ እንድናስወግደው የሚያደርገን በቂ ምክንያት ነው።
ይሁንና ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደራችን ፈጽሞ ስህተት ነው? ወይስ እንዲህ ማድረጉ ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ?
ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ
ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር በአብዛኛው መጥፎ ወይም አሳዛኝ መዘዝ ያስከትላል፤ ሆኖም ሁልጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ይከሰታል ማለት አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ጳውሎስ “በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ” በማለት የሰጠውን ምክር ልብ በል። (ዕብራውያን 6:12) ጥንት ከነበሩት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር የሚመሳሰሉ መልካም ባሕርያትን ለማፍራት መጣጣር ጠቃሚ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ራሳችንን ከእነርሱ ጋር ማወዳደር ያስፈልገናል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን ከእነርሱ የምንኮርጀውንና ማሻሻል የሚገባንን ባሕርይ እንድናውቅ ይረዳናል።
እስቲ ዮናታንን እንመልከት። ዮናታን በዳዊት እንዲቀና የሚያደርገው በቂ ምክንያት ነበረው። የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን በአባቱ እግር እንደሚተካ አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይሖዋ ከእርሱ በ30 ዓመት ገደማ የሚያንሰውን ወጣቱን ዳዊትን መረጠው። ዮናታን በዚህ ምክንያት ቂም ከመያዝ ይልቅ ከዳዊት ጋር ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ወዳጅነት ከመመሥረቱም በተጨማሪ ይሖዋ የሾመው ንጉሥ እንደሆነ በማመን ደግፎታል። ዮናታን ከልቡ መንፈሳዊ ሰው ነበር። (1 ሳሙኤል 19:1-4) ዳዊትን እንደ ተቀናቃኝ አድርጎ ከሚያየው አባቱ በተቃራኒ በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት በመገንዘብ ለአምላክ ፈቃድ ለመገዛት ራሱን አቅርቦ ነበር፤ “እኔ እያለሁ ለምን ዳዊት ተመረጠ?” እያለ በመጠየቅ ፉክክር ውስጥ አልገባም።
ክርስቲያን ወንድሞቻችን እኛን ለማስናቅ ወይም ለመቀናቀን እንደሚፈልጉ አድርገን በማሰብ ፈጽሞ ስጋት ሊሰማን አይገባም። እርስ በርስ መፎካከር ተገቢ አይደለም። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት በፉክክር መንፈሳቸው ሳይሆን በተባባሪነታቸው፣ በአንድነታቸውና በፍቅራቸው ነው። ፍራንቼስኮ አልቤሮኒ የተባሉ ሶሺዮሎጂስት “ፍቅር የቅናት ቀንደኛ ጠላት ነው” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “አንድን ሰው ከወደድነው መልካም የሆነውን እንመኝለታለን፤ እንዲሁም ሲሳካለትና ደስታ ሲያገኝ አብረነው እንደሰታለን” ብለዋል። ስለዚህ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው ለአንድ የኃላፊነት ቦታ ቢመረጥ ፍቅራዊ የሚሆነው በነገሩ መደሰት ነው። ዮናታን የተሰማው እንዲህ ነበር። እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙትን ታማኝ ወንድሞች የምንደግፍ ከሆነ እንባረካለን።
የክርስቲያን ወንድሞቻችን መልካም ምሳሌነት ሊደነቅ የሚገባው ሊሆን ይችላል። በሚዛናዊነት ራሳችንን ከእነርሱ ጋር ማወዳደራችን ጤናማ በሆነ መንገድ እምነታቸውን እንድንኮርጅ ይገፋፋናል። (ዕብራውያን 13:7) ካልተጠነቀቅን ግን እነርሱን ለመምሰል የምናደርገው ጥረት መልኩን ቀይሮ ወደ ፉክክር ሊያመራ ይችላል። በአንድ በምናደንቀው ሰው እንደተበለጥን ተሰምቶን እርሱን ለማጣጣል ወይም ለመተቸት የምንሞክር ከሆነ እርሱን ለመምሰል እየጣርን ሳይሆን እየቀናንበት ሊሆን ይችላል።
ፍጹም ያልሆነ ሰው በሁሉም ዘርፍ የተዋጣለት ምሳሌ እንደሆነ ተደርጎ ሊጠቀስ አይችልም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” ይላል። በተጨማሪም “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 5:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) እንደ ፍቅር፣ አዛኝነትና ትሕትና የመሳሰሉትን የይሖዋና የኢየሱስ ባሕርያት ለመኮረጅ መጣጣር ይገባናል። ጊዜ ወስደን ከእነርሱ ባሕርያት፣ ዓላማዎችና ነገሮችን ከሚያከናውኑበት መንገድ አንጻር ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ሕይወታችን ያማረ እንዲሆን፣ እርግጠኛ መመሪያ እንድናገኝ፣ እንድንረጋጋና ዋስትና ያለው ኑሮ እንድንመራ ያስችለናል፤ እንዲሁም የጎለመስን ክርስቲያኖች እንድንሆን ይረዳናል። (ኤፌሶን 4:13) ትኩረት ሰጥተን የይሖዋንና የክርስቶስን ፍጹም ምሳሌነት ለመኮረጅ የቻልነውን ያህል ጥረት የምናደርግ ከሆነ በእርግጥም ከሌሎች ሰዎች ጋር ራሳችንን አናወዳድርም።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ሳኦል በዳዊት ላይ ቀንቶ ነበር
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮናታን ወጣቱ ዳዊትን እንደ ተቀናቃኝ አድርጎ አልተመለከተውም