ተአምራት እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?
ተአምራት እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?
ሰውየው በአንድ መኪና ፈረፋንጎ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ ሲመለከት ትኩረቱ ተሳበ። ጽሑፉ “ተአምራት ይፈጸማሉ፣ ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ መላእክትን ጠይቁ” ይላል። እርሱ ራሱ ሃይማኖተኛ ቢሆንም ምን ለማለት እንደተፈለገ አልገባውም። ሹፌሩ ጽሑፉን የለጠፈው በተአምራት ስለሚያምን ነው? ወይስ በተአምራትም ሆነ በመላእክት እንደማያምን የሚያሳይ የምጸት አባባል ነው?
ማንፍሬድ ባርተል የተባሉ ጀርመናዊ ደራሲ በተናገሩት በሚከተለው ሐሳብ ትስማማ ይሆናል። “ተአምር አንባቢን በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች የሚከፍል ቃል ነው” ብለው ነበር። በተአምራት የሚያምኑ ሰዎች ተአምራት እንደሚፈጸሙ፣ ምናልባትም በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ አይጠራጠሩም። a ለምሳሌ ያህል፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግሪክ ውስጥ ያሉ ምዕመናን ተአምራት በወር አንድ ጊዜ ይፈጸማሉ ብለው እንደሚናገሩ ሪፖርት ተደርጓል። በዚህም የተነሳ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ “ምዕመናን አምላክ፣ ማርያምና ቅዱሳን ሰብዓዊ ባሕርይ እንዳላቸው አድርገው ወደ ማመን እያዘነበሉ ነው። አማኞች ለተአምራት ያላቸው አመለካከት በጣም የተጋነነ መሆን የለበትም” ብለው ለማሳሰብ ተገድደዋል።
በአንዳንድ አገሮች ደግሞ በተአምራት የሚያምኑ ሰዎች ያን ያህል ብዙ አይደሉም። በ2002 በጀርመን የአለንስባክ የምርምር ተቋም ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከአገሪቱ ነዋሪዎች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ተአምራት እውነተኛ ክንውኖች ሳይሆኑ ምናባዊ ፈጠራ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በተአምራት ከሚያምኑት ከአንድ ሦስተኛ የሚያንሱ ሰዎች መካከል ግን ከድንግል ማርያም መልእክት እንደደረሳቸው የሚናገሩ ሦስት ሴቶች ይገኙበታል። እነዚህ ሴቶች ማርያም በመላእክትና በእርግብ ታጅባ ተገለጠችልን ካሉ ከጥቂት ወራት በኋላ ቬስትፋለንፖስት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “እስካሁን ድረስ ወደ 50,000 የሚጠጉ ምዕመናን፣ ከሕመማቸው ለመፈወስ የሚፈልጉ ሰዎችና ስለ ሁኔታው የማወቅ ጉጉት ያደረባቸው ግለሰቦች ሴቶቹ ለተመለከቱት ራእይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተውታል።” ወደ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ማርያም ዳግመኛ ስትገለጥ ለማየት ወደ መንደሯ እንደሚጎርፉ ይጠበቅ ነበር። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ማርያም በ1858 በሉርዴስ፣ ፈረንሳይ እና በ1917 በፋቲማ፣ ፖርቱጋል እንደተገለጠች ይነገራል።
ከክርስትና ውጪ ያሉ ሃይማኖቶችስ?
ሁሉም ሃይማኖቶች ለማለት ይቻላል በተአምራት ያምናሉ። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን የቡድሂዝም፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት መሥራቾች ስለ ተአምራት ያላቸው አመለካከት የተለያየ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ይላል:- “የእነዚህ ሃይማኖቶች አመጣጥ ተአምራትና ከተአምራት ጋር የተያያዙ ታሪኮች በሰው ዘር ሃይማኖታዊ አመለካከት ውስጥ ወሳኝ ቦታ እንደነበራቸው በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ቡድሃ ራሱ አልፎ አልፎ ተአምራት ይፈጽም” እንደነበር ይናገራል። ከጊዜ በኋላ “ቡድሂዝም ወደ ቻይና ሲሻገር ሚስዮናውያኑ ብዙውን ጊዜ ተአምራት የመፈጸም ችሎታቸውን በማሳየት ሰዎችን ለመሳብ ይሞክሩ ነበር።”
ኢንሳይክሎፒዲያው የቡድሂዝም ተከታዮች ይፈጽሟቸዋል ከሚባሉት ተአምራት መካከል በርካታዎቹን ከዘረዘረ በኋላ “ለሃይማኖታቸው የሚቀኑ ታሪክ ጸሐፊዎች የዘገቧቸው እነዚህ ሁሉ ተአምራት እውነተኛ እንደሆኑ መቀበል ሊከብድ ይችላል፤ ሆኖም ለተከታዮቹ ተአምር የመፈጸም
ኃይል ማጎናጸፍ የሚችለውን ቡድሃን ከፍ ከፍ ለማድረግ በቀና አስተሳሰብ የተፈጠሩ ታሪኮች መሆናቸው አያጠራጥርም” በማለት ይደመድማል። ስለ እስልምና ሃይማኖት ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል:- “አብዛኛው ሙስሊም ኅብረተሰብ ጥንትም ሆነ ዛሬ ተአምራት እንደሚፈጸሙ ያምናል። መሐመድ በሕዝብ ፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ተአምራት እንደፈጸመ በትውፊት (ሃዲትዝ) ይነገራል። . . . ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ እንኳ ለእምነቱ ተከታዮች ጥቅም ሲሉ በመቃብራቸው ላይ ተአምራት እንደሚፈጽሙ የሚታመን ሲሆን ሰዎችም የእነርሱን እርዳታ በትጋት ይለምናሉ።”በክርስትና ውስጥ የሚፈጸሙት ተአምራትስ?
ክርስትናን ከተቀበሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ስለ ተአምራት ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስና በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች እንዳከናወኗቸው የተገለጹትን ተአምራት እውነተኝነት ይቀበላሉ። ሆኖም አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጅ በነበረው በማርቲን ሉተር አመለካከት ይስማማሉ። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ስለ እርሱ ሲናገር “ሉተርም ሆነ ካልቪን ተአምራት የሚፈጸሙበት ዘመን እንዳበቃና በዛሬው ጊዜ ተአምራት ይፈጸማሉ ብለን መጠበቅ እንደሌለብን ጽፈዋል” ይላል። ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ተአምራት እንዴት እንደሚፈጸሙ ለማብራራት ባትሞክርም” በተአምራት ማመኗን ቀጥላለች ይላል። ይሁን እንጂ “የተማረው የፕሮቴስታንት ኅብረተሰብ አምላክም ሆነ መንፈሳዊው ዓለም ከሰዎች ጋር ግንኙነት እንደማይፈጥሩና በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ያን ያህል የጎላ ተጽዕኖ እንደማያሳድሩ እንዲሁም ክርስትና በአመዛኙ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ሃይማኖት እንደሆነ ያምናል።”
አንዳንድ ቀሳውስትን ጨምሮ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ተአምራት እውነተኝነት ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ በዘፀአት 3:1-5 ላይ በእሳት ስለተያያዘው ቁጥቋጦ የሚናገረውን ዘገባ እንውሰድ። ዋት ዘ ባይብል ሪሊ ሰይስ የተባለው መጽሐፍ ጀርመናዊ የሆኑ በርካታ የሃይማኖት ምሑራን ይህን ዘገባ ቃል በቃል እንደተፈጸመ ተአምር አድርገው እንደማይመለከቱት ይናገራል። ከዚያ ይልቅ “ሙሴ ያለ እረፍት ከሚነዘንዘው የጸጸት ስሜትና እንደ ረመጥ ከሚለበልበው ሕሊናው ጋር የሚያደርገውን ውስጣዊ ትግል የሚያመለክት ምሳሌያዊ አገላለጽ” እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። መጽሐፉ አክሎም “ነበልባሉን የመለኮት መገለጥ በሚፈጥረው የብርሃን ነጸብራቅ በድንገት እንደፈነዱ አበቦች አድርገንም ልንረዳው እንችላለን” ይላል።
እንዲህ ዓይነቱ ማብራሪያ ላያረካህ ይችላል። ታዲያ የትኛውን አመለካከት ትይዛለህ? በጥንት ጊዜያት ተአምራት ተፈጽመዋል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለ? በጊዜያችን ይፈጸማሉ ስለሚባሉት ተአምራትስ ምን ለማለት ይቻላል? መላእክትን መጠየቅ እንደማንችል የታወቀ ስለሆነ መልሱን ከየት ማግኘት እንችላለን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
በጥንት ጊዜያት አምላክ በሰዎች ሊፈጸሙ የማይችሉ ድርጊቶችን ለመፈጸም አልፎ አልፎ ጣልቃ ይገባ እንደነበር የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ማንም ሊያስተባብለው አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በታምራትና በድንቅ፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ እጅግ በሚያስፈራም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ አወጣህ።” (ኤርምያስ 32:21) እስቲ አስበው! በዘመኑ ኃያል የነበረው ብሔር የበኩር ልጆቹን በሞት ያሳጣውን ጨምሮ አሥር መለኮታዊ መቅሰፍቶች ሲወርዱበት እጁን ሰጥቷል። ይህ በእርግጥም ተአምር ነበር!—ዘፀአት ምዕራፍ 7 እስከ 14
ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ አራቱ የወንጌል ዘጋቢዎች ኢየሱስ ያከናወናቸውን 35 የሚያህሉ ተአምራት ጽፈዋል። እንዲያውም ከዘገባቸው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ እነርሱ ከጻፏቸው የበለጡ በርካታ ድንቅ ነገሮችን ፈጽሟል። ታዲያ እነዚህ ተአምራት እውነተኛ ናቸው ወይስ የፈጠራ ታሪኮች? b—ማቴዎስ 9:35፤ ሉቃስ 9:11
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ የእውነት ቃል ከሆነ በውስጡ የተመዘገቡትን ተአምራት እውነተኝነት ለመቀበል የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት አለህ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ጊዜያት ስለተፈጸሙት ፈውሶች፣ ትንሣኤዎችና እነዚያን የመሳሰሉ ተአምራት በግልጽ እንደሚናገር ሁሉ እነዚህ ተአምራት በጊዜያችን እንደማይፈጸሙም በማያሻማ ሁኔታ ይገልጻል። (“በጥንት ዘመናት የተፈጸሙት ተአምራት አሁን የማይፈጸሙት ለምንድን ነው?” የሚለውን በገጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ታዲያ እንዲህ ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት የሚቀበሉ ሰዎችም ጭምር በጊዜያችን ይፈጸማሉ የሚባሉት ተአምራት ተጨባጭ መሠረት እንደሌላቸው ይሰማቸዋል ማለት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ተአምር” የሚለው ቃል በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሠራበት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ በሰፈረው “በታወቁት ሰብዓዊ ወይም ተፈጥሯዊ ኃይሎች ሊፈጸሙ የማይችሉ በመሆናቸው ከተፈጥሮ በላይ በሆኑ ኃይሎች ይፈጸማሉ የሚባሉ በገሃዱ ዓለም ያሉ ክስተቶች” በሚለው ትርጉሙ ነው።
b መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ለማግኘት ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለ መጽሐፍ አንብብ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በጥንት ዘመናት የተፈጸሙት ተአምራት አሁን የማይፈጸሙት ለምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ተአምራቶች ተዘርዝረዋል። (ዘፀአት 7:19-21፤ 1 ነገሥት 17:1-7፤ 18:22-38፤ 2 ነገሥት 5:1-14፤ ማቴዎስ 8:24-27፤ ሉቃስ 17:11-19፤ ዮሐንስ 2:1-11፤ 9:1-7) ከእነዚህ ተአምራት ውስጥ አብዛኞቹ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይቶ ለማሳወቅ የረዱ ሲሆን የአምላክ ድጋፍ እንዳለውም አረጋግጠዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮችም በልሳን መናገርንና በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ሐሳቦችን መረዳትን የመሳሰሉ ተአምራዊ ስጦታዎች ነበሯቸው። (የሐዋርያት ሥራ 2:5-12፤ 1 ቆሮንቶስ 12:28-31) በጊዜው የክርስቲያን ጉባኤ ገና ጨቅላ የነበረ እንደመሆኑ የእነዚህ ተአምራት መኖር አስፈላጊ ነበር። ለምን?
አንዱ ምክንያት በወቅቱ የነበሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ጥቂት መሆናቸው ነው። በአብዛኛው ማንኛውም ዓይነት ጥቅልሎችና መጻሕፍት የሚገኙት ሀብታሞች ጋር ብቻ ነበር። ክርስትና ባልደረሰባቸው አገሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ደራሲው ስለሆነው ስለ ይሖዋ ምንም አይታወቅም ነበር። የክርስትና ትምህርቶች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በቃል ነበር። በመሆኑም ተአምራቶች አምላክ የክርስቲያን ጉባኤን እየተጠቀመበት እንደነበር ለማሳየት አገልግለዋል።
ይሁን እንጂ ጳውሎስ እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች አስፈላጊነታቸው ሲያበቃ እንደሚቀሩ ተናግሯል። “ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል።”—1 ቆሮንቶስ 13:8-10
በዛሬው ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የቃላት ማውጫዎችንና ኢንሳይክሎፒዲያዎችን ማግኘት ይችላሉ። ጥሩ ሥልጠና ያገኙ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መለኮታዊ እውቀት ሌሎችም እንዲማሩ በመርዳት ላይ ናቸው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ የተሾመ አዳኝ መሆኑን ለማሳየት ወይም ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚደግፋቸው ለማረጋገጥ ተአምራት አያስፈልጉም።