በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በዓለም ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

ኢየሱስ በዓለም ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

ኢየሱስ በዓለም ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

“ኢየሱስ ለግለሰቦችም ይሁን በሕዝብ ፊት የተናገረውን በተመለከተ በወንጌሎች ላይ የሰፈረው ዘገባ ከሁለት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊናገረው የሚችለው ብቻ ነው። . . . ያም ቢሆን ግን የሰዎችን ስሜት የሚኮረኩር፣ ለሥራ የሚያንቀሳቅስና ጥልቀት ያለው በመሆኑ በዓለም ላይ የእርሱን ያህል ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው የለም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል” በማለት ኤድገር ጉድስፒድ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ጽፈዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱን ባጠናቀቀበት ወቅት ተከታዮቹ 120 ገደማ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ብቻ ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 1:15) በአሁኑ ጊዜ ግን ከሁለት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ክርስቲያን እንደሆኑ ይናገራሉ። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ኢየሱስ ነቢይ እንደሆነ ያምናሉ። በእርግጥም ትምህርቶቹ በሰው ልጆች ላይ ይህ ነው የማይባል ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ክርስቲያን ያልሆኑ መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ኢየሱስ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ሃይመን ኤኔሎ የተባሉ የአይሁድ እምነት መምህር “በሰው ልጆች ሃይማኖታዊ ታሪክ ውስጥ የኢየሱስን ያህል በጣም የሚወደድ፣ በሰፊው የሚታወቅና ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው የለም” በማለት ጽፈዋል። ኤኔሎ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ኢየሱስ በሰው ልጆች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ያህል እንደሆነ መገመት የሚችል ሰው አለ? ያሳየው ፍቅር፣ የሰጠው ማጽናኛ፣ የሠራቸው መልካም ነገሮችና የሰጣቸው አስደሳች ተስፋዎች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወደር አይገኝላቸውም። ዓለማችን እስከዛሬ ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል የኢየሱስን ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሜት የቀሰቀሰና የማረከ የለም። በታሪክ ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሰው ሆኗል።” የሂንዱ መሪ የሆኑት ሞሃንደስ ኬ ጋንዲም “ከኢየሱስ የተሻለ ለሰው ልጆች ብዙ ነገር ያደረገ ሰው አላውቅም። እንዲያውም የክርስትና ሃይማኖት ስህተት የለበትም” ካሉ በኋላ “ችግሩ ያለው በእናንተ በክርስቲያኖቹ ላይ ነው። ከትምህርቶቻችሁ ውስጥ ጥቂቱን እንኳን በሥራ ላይ አታውሉም” በማለት ተናግረዋል።

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በኢየሱስ ትምህርቶች እንዳልተመሩ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያረጋግጣል። ሲሰል ጆን ካዱ የተባሉ የክርስትና ታሪክ ጸሐፊ “የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች . . . ከ140 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርን በተመለከተ ቀስ በቀስ ልል እየሆነች መምጣቷን አስተውለው ነበር” ብለዋል። አክለውም “ይህን የመሰለው የሥነ ምግባር አቋም መላላት የዓለምን መንገድ ወደ መደገፍ አምርቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሮም ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በአራተኛው መቶ ዘመን ክርስትናን በተቀበለ ጊዜ ይህ የሥነ ምግባር ዝቅጠት በፍጥነት እየተባባሰ ሄደ። ካዱ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን ለማስተዋል አልተቸገሩም፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤተ ክርስቲያን ከቆስጠንጢኖስ ጋር ኅብረት በመፍጠር ታላቅ ክህደት መፈጸሟ በጣም አሳዝኗቸው ነበር።” ከዚያ በኋላ በነበሩት ምዕተ ዓመታት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የክርስቶስን ስም የሚያስነቅፉ በርካታ አሳፋሪ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

አሁን የሚያሳስበን ‘ኢየሱስ በእርግጥ ያስተማረው ምንድን ነው? ትምህርቶቹስ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይገባል?’ የሚለው ጉዳይ ነው።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከኢየሱስ የተሻለ ለሰው ልጆች ብዙ ነገር ያደረገ ሰው አላውቅም።”—ሞሃንደስ ኬ ጋንዲ

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በዓለም ላይ የእርሱን ያህል ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው የለም።”—ኤድገር ጉድስፒድ

[ምንጭ]

Culver Pictures