የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች የተቀደሰውን ኅብስት መብላታቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የአምላክን ሕግ መተላለፍ ቅጣት እንደማያስከትል ያመለክታል?—1 ሳሙኤል 21:1-6
በዘሌዋውያን 24:5-9 መሠረት በየሰንበቱ ከይሖዋ ፊት የሚነሳው ኅብስት ካህናቱ እንዲበሉት ይቀመጥ ነበር። ይህም የሚደረገው ኅብስቶቹ ቅዱስ በመሆናቸው በአምላክ አገልግሎት ለሚካፈሉት ወንዶች ማለትም ለካህናቱ ምግብ እንዲሆኑ ተብሎ ነው። እነዚህን ኅብስቶች ካህን ላልሆነ አገልጋይ መስጠት ወይም እንደ ማንኛውም ምግብ ቆጥሮ መብላት ስህተት ይሆናል። ሆኖም ካህኑ አቢሜሌክ ኅብስቱን ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች መስጠቱ ኃጢአት አይደለም።
ዳዊት ከንጉሡ ልዩ ተልእኮ የተሰጠው ይመስል የነበረ ከመሆኑም በላይ እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ተርበው ነበር። አቢሜሌክ እነዚህ ሰዎች በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ መሆናቸውን ጠይቆ አረጋግጧል። በሕጉ መሠረት እነዚህ ሰዎች ኅብስቱን መብላታቸው ስህተት ቢሆንም ኅብስቱ ከሚውልበት መሠረታዊ ዓላማ ጋር ግን አይጋጭም ነበር። አቢሜሌክ ይህንን ማስተዋሉ ልዩ አስተያየት ለማድረግ አስችሎታል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ፈሪሳውያን የሰንበትን ሕግ በተመለከተ ያላቸው ድርቅ ያለ አመለካከት ተገቢ እንዳልሆነ ለማስረዳት ይህንን ታሪክ እንደ ምሳሌ ጠቅሶታል።—ማቴዎስ 12:1-8
ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል አስቸጋሪ ሁኔታ ካጋጠመን የአምላክን ሕግ መጣስ እንችላለን ማለት አይደለም። እስራኤላውያን ወታደሮች ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚዋጉበት ወቅት የተፈጠረውን አስቸጋሪ የሚመስል ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ንጉሥ ሳኦል “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን እንደመቷቸው’ ይናገራል። ወታደሮቹ በውጊያው ዝለውና ተርበው ስለነበር እንስሳቱን ‘በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት።’ (1 ሳሙኤል 14:24, 31-33) ይሖዋ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ በመጣስ ኃጢአት ሠሩ። ይሖዋ ደም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው ለኃጢአት “ማስተስረያ” ብቻ እንደሆነ ተናግሮ ስለነበር ድርጊታቸው አምላክ ደምን በሚመለከት ካወጣው ሕግ ጋር የሚጋጭ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:10-12፤ ዘፍጥረት 9:3, 4) ይሖዋ ኃጢአት የሠሩት ሰዎች ልዩ መሥዋዕት ካቀረቡ በኋላ ምሕረት አድርጎላቸዋል።—1 ሳሙኤል 14:34, 35
በእርግጥም ይሖዋ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ቢሆን ሕግጋቱን እንድንታዘዝ ይጠብቅብናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና” በማለት ተናግሯል።—1 ዮሐንስ 5:3
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየሰንበቱ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ትኩስ ኅብስቶች ይደረደሩ ነበር