በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአውስትራሊያ ገጠራማ ክልሎች ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ

በአውስትራሊያ ገጠራማ ክልሎች ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

በአውስትራሊያ ገጠራማ ክልሎች ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ

በመካከለኛው አውስትራሊያ የሚገኘው በጣም ሰፊ ገጠራማ ክልል በተለምዶ አውትባክ በመባል ይታወቃል። በዚህ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ገለልተኛ ስፍራዎች አንዳንዶቹ ለ12 ዓመታት ያህል ምሥራቹ ተሰብኮላቸው አያውቅም። ስለሆነም የሰሜናዊው ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በዳርዊን ነዋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች ለመፈለግ ዘጠኝ ቀናት የሚወስድ መጠነ ሰፊ የስብከት ዘመቻ ለማድረግ ተዘጋጁ።—ማቴዎስ 10:11

ወንድሞች ዘመቻው ከመጀመሩ ከአንድ ዓመት በፊት ከ800,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ላለው ክልል ካርታ ማውጣትን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን በማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አደረጉ። ይህ ክልል የኒው ዚላንድን የቆዳ ስፋት ሦስት እጥፍ ያክላል። ይህ ስፍራ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ለመረዳት እንድንችል አንድን የከብት እርባታ ጣቢያ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ከመግቢያው በር አንስቶ እስከ ዋናው ቤት ድረስ ያለው መንገድ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል! ከዚህም በላይ አንዳንዶቹ የከብት እርባታ ጣቢያዎች ቢያንስ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ይራራቃሉ።

በዚህ ዘመቻ 145 የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት የተካፈሉ ሲሆን አንዳንዶቹ የመጡት እንደ ታዝማኒያ ካሉ ሩቅ ቦታዎች ነበር። ጥቂቶቹ ወደ ሥፍራው የተጓዙት ለቆይታቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች፣ የመኪና መለዋወጫዎችና ነዳጅ በጫኑ የመስክ መኪናዎች ነበር። ሌሎች ደግሞ እንደነዚህ ያሉትን ዕቃዎች የጫኑት በተሳቢ መኪና ላይ ነበር። በተጨማሪም ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዞ ተስማሚ የሆነ መኪና የሌላቸው ደግሞ እያንዳንዳቸው ሃያ ሁለት ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት አውቶቡሶች ተከራዩ። በአውቶቡስ የተጓዙት ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸው በይበልጥ ያተኮረው በክልሉ በሚገኙ ትንንሽ ከተማዎች ውስጥ ነበር።

በኃላፊነት ላይ የነበሩት ወንድሞች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በዚህ ባልተለመደ አካባቢ ምሥራቹን እንዴት መስበክ እንደሚቻል መመሪያ ለመስጠት ሲሉ ንግግሮችንና ሠርቶ ማሳያዎችን አዘጋጅተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለአቦርጂኖች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመሥከር የአካባቢውን ልማድና ባሕል ማወቁ በጣም ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም አካባቢያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ላይ የዱር እንስሳትን እንዳይጎዱ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ነበር።

ወንድሞችና እህቶች በዚህ ዘመቻ አስደሳች የሆኑ ብዙ ተሞክሮዎችን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል ወንድሞች በአንድ የአቦርጂኖች መንደር ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ንግግር ለመስጠት ዝግጅት አደረጉ። በዚህ ጊዜ በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያላቸው አንዲት ሴት ራሳቸው እየዞሩ ስለ ዝግጅቱ ለመንደርተኛው ተናገሩ። ከንግግሩ በኋላ በዚያ ተገኝተው ለነበሩ ሰዎች 5 መጻሕፍትና 41 ብሮሹሮች ተበርክቶላቸዋል። በሌላ መንደር ውስጥ ደግሞ ወንድሞች ያረጀና የተቀዳደደ የኪንግ ጄምስ ቨርሽን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የያዘ አንድ አቦርጂን አነጋገሩ። የአምላክን ስም ያውቅ እንደሆነ ሰውየውን ሲጠይቁት አዎን አለና የቆየ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከጃኬት ኪሱ አወጣ። ከዚያም መጽሔቱን በመግለጥ “አንተም ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህን በፍጹም ልብህ . . . ውደድ” የሚለውን ማርቆስ 12:30ን ካነበበ በኋላ “ይህን ጥቅስ በጣም እወደዋለሁ” በማለት ተናገረ። ሰፋ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ካደረጉ በኋላ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎችን አበረከቱለት።

በካርፔንቴሪያ ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ 400,000 ሄክታር ስፋት ያለው የአንድ ከብት እርባታ ጣቢያ ኃላፊ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት አሳየ። ወንድሞች ለዚህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባሉትን ጽሑፎች ሲያሳዩት በክርዮል ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ይዘው እንደሆነ ጠየቃቸው። a ብዙ አቦርጂኖች የክርዮልን ቋንቋ መናገር ቢችሉም የሚያነቡት ጥቂቶች ብቻ ስለነበሩ ይህ ያልተለመደ ጥያቄ ነበር። በኋላ ላይ ምሥክሮቹ በዚህ የከብት እርባታ ጣቢያ ውስጥ የሚሠሩ 50 ሰዎች በሙሉ ክርዮል ማንበብ እንደሚችሉ ተረዱ። ኃላፊው በክርዮል ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ በማግኘቱ የተደሰተ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀጣይ የሆነ ግንኙነት ማድረግ እንዲችል ስልክ ቁጥሩን ሰጣቸው።

ለዘጠኝ ቀናት በቆየው በዚህ መጠነ ሰፊ የስብከት ዘመቻ በጠቅላላው 120 መጽሐፍ ቅዱሶች፣ 770 መጻሕፍት፣ 705 መጽሔቶችና 1,965 ብሮሹሮች ተበርክተዋል። በተጨማሪም 720 ተመላልሶ መጠየቆች የተደረጉ ሲሆን 215 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል።

በእርግጥም በዚህ ሰፊ ክልል ተበታትነው የሚገኙ በርካታ ሰዎች በመጨረሻ ላይ መንፈሳዊ ረሃባቸውን ማሥታገስ ችለዋል።—ማቴዎስ 5:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አውስትራሊያ

ሰሜናዊው ግዛት

ዳርዊን

የካርፐንቴሪያ ባሕረ ሰላጤ

ሲድኒ

ታዝማኒያ