በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

የኢየሱስን ልደት ለማክበር ታኅሣሥ 25 የተመረጠበት ምክንያት ምን ነበር?

የአምላክ ቃል ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን አይገልጽም። ኢንሳይክሎፒዲያ ኢስፓኒካ “የገና በዓል የሚከበርበት ታኅሣሥ 25 ቀን ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን በትክክል በማስላት የተገኘ ሳይሆን የክረምቱን ማብቃት አስመልክቶ በሮም የሚከበሩትን ክብረ በዓላት ወደ ክርስቲያናዊ በዓልነት ለመለወጥ ተብሎ የተደረገ ነው” ይላል። የጥንቶቹ ሮማውያን ክረምቱ አልፎ ፀሐይዋ የምትወጣበትን ወቅት የሚያከብሩት በድግስ፣ በፈንጠዝያና ስጦታ በመለዋወጥ ነበር።—12/15 ገጽ 4-5

በሐዋርያት ሥራ 7:59 ላይ ያለው ሐሳብ እስጢፋኖስ የጸለየው ወደ ኢየሱስ እንደሆነ ያሳያል?

በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ጸሎት መቅረብ ያለበት ለይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። እስጢፋኖስ ኢየሱስን በራእይ ሲመለከተው “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት” በማለት ልመናውን በቀጥታ ለእርሱ ማቅረብ እንደሚችል ሳይሰማው አይቀርም። ለኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን እንደተሰጠው እስጢፋኖስ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 5:27-29) ስለዚህ እስጢፋኖስ እስከ ትንሣኤ ድረስ ሕይወት እንዲኖረው ያስቻለውን ኃይል እንዲጠብቅለት ኢየሱስን ጠይቆታል ወይም ለምኖታል።—1/1 ገጽ 31

• የአንድ ሰው የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ እንዳልተወሰነ እንዴት እናውቃለን?

አምላክ ለሰው ልጆች ነፃ ምርጫ የሰጣቸው ሲሆን ይህ ደግሞ የወደፊት ዕጣችን አስቀድሞ ተወስኗል ከሚለው እምነት ጋር ይጋጫል። ይሖዋ ገና ከመወለዳችን በፊት በኋላ የምንፈጽመውን ድርጊት ቢወስንና ባደረግነው ነገር ተጠያቂ ቢያደርገን ኖሮ አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ ነው ለማለት ይቸግር ነበር። (ዘዳግም 32:4፤ 1 ዮሐንስ 4:8)—1/15 ገጽ 4-5

• ተአምራት እውነተኛ ክንውኖች ሳይሆኑ ምናባዊ ፈጠራ ናቸው ብሎ መናገሩ ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሳይንቲስቶች ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያላቸው ሳይንሳዊ እውቀት በጣም ውስን እንደሆነ በመገንዘብ አንድን ነገር ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው ብለው መደምደም እንደማይችሉ አምነዋል። ግፋ ቢል ሊሆን መቻሉ ያጠራጥራል ቢሉ ነው።—2/15 ገጽ 5-6

• መስፍኑ ሳምሶን ፍልስጥኤማዊቷን ልጅ እንዲያጋቡት ወላጆቹን የጠየቃቸው ለምን ነበር? (መሳፍንት 14:2)

የሐሰት አማልክት የምታመልክ ሴት ማግባት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ነው። (ዘፀአት 34:11-16) ሆኖም ሳምሶን በፍልስጥኤማዊቷ ሴት ‘ልቡ ተማርኮ’ ወይም ይህቺ ሴት ለእርሱ ተስማሚ እንደሆነች ተሰምቶት ነበረ። ሳምሶን “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር” አጋጣሚ ይፈልግ ስለነበረ ይህቺ ሴት ከዚህ ዓላማ አንጻር ተስማሚ ሆናለታለች። አምላክም በመንፈሱ አማካኝነት ሳምሶንን ይመራው ነበር። (መሳፍንት 13:25፤ 14: 3, 4, 6)—3/15 ገጽ 26

• አንድ ክርስቲያን አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ለሚሰጠው አገልግሎት አንድ ዓይነት ስጦታ ወይም ጉርሻ መስጠት ይችላል?

ሕግ እንዲጥስ፣ ፍርድን እንዲያጣምም ወይም በአድሎአዊነት እኛ ከሌሎች ሰዎች ፊት ለመሆን ወይም በሌሎች ተራ ለመግባት ብለን ለባለ ሥልጣን ጉቦ ወይም ሌላ ስጦታ መስጠት ስህተት ነው። ሆኖም ለአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን በአግባቡ ስለተወጣ፣ ሕጋዊ አገልግሎት ለማግኘት እንዲረዳን ወይም አድልዎ እንዳይፈጸምብን ስንል የምንሰጠው ስጦታ ወይም ጉርሻ ጉቦ ሊባል አይችልም።—4/1 ገጽ 29