የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ያህል ትክክለኛ ነው?
የእስራኤል የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት ካይም ኸርትሳግ እና ጡረታ ቢወጡም በማዕረግ ስማቸው የሚጠሩት የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የከርሰ ምድር ጥናት ፕሮፌሰር ሞርደካይ ጊኮን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ጦርነቶች (እንግሊዝኛ) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:-
“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ጦርነቶች ስለተካሄዱበት የውጊያ ስልት የሚገልጹት ዘገባዎች . . . እንዲሁ የፈጠራ ውጤቶች ሊሆኑ አይችሉም። በመሳፍንት ምዕራፍ 6 እስከ 8 ላይ የሚገኘውን ጌዴዎን በምድያማውያንና በተባባሪዎቻቸው ላይ ስለሰነዘረው ጥቃት የሚገልጸውን ዘገባ ሆመር ኢሊያድ በተባለው መጽሐፉ ላይ ከገለጸው ከትሮጃን ጦርነት ጋር ማወዳደሩ ለዚህ በቂ ማስረጃ ይሆናል። ለሆመር ጽሑፍ በመልክዓ ምድር ረገድ በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል ማንኛውም የባሕር ዳርቻና በቅርብ የሚገኝ የተመሸገ ከተማ ተስማሚ ነው . . . በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የምናገኘው ጌዴዎን ስላካሄደው ወረራ የሚናገረው ዘገባ ግን እንደዚህ ባለ ሁኔታ ሊከናወን የሚችል አይደለም። ሁለቱ ተዋጊ ወገኖች ስለተጠቀሙበት የውጊያ ስልትና በተለያዩ ቦታዎች ስላደረጉት ፍልሚያ እያንዳንዱ ነገር በግልጽ የሰፈረ ከመሆኑም በላይ 60 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ጦርነቱ የተካሄደበት ቦታ የመሬት አቀማመጥ በዝርዝር ተገልጿል። እንደዚህ ያለው ውጊያ ሌላ ቦታ ሊካሄድ አይችልም . . . በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ጦርነቶች ስለተካሄዱበት የውጊያ ስልት የሚገልጸውን ታሪክ ትክክለኝነት አምነን ለመቀበል ተገድደናል።”
አንተም ብትሆን ጌዴዎን ስላካሄደው ወረራ ምርምር ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን ካርታ ከያዘው ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት’ a ከተባለው ብሮሹር ላይ ገጽ 18 እና 19ን ልትጠቀም ትችላለህ። ታሪኩ “በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ኀይላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ” በማለት ይጀምራል። ጌዴዎን በአቅራቢያው የሚገኙት የእስራኤል ነገዶች እንዲረዱት ጠራቸው። ፍልሚያው ከሐሮድ ምንጭ አንስቶ ወደ ሞሬ ኮረብታ ከዚያም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ይወስደናል። ጌዴዎን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ጠላቶቹን በማሳደድ ድል አደረጋቸው።—መሳፍንት 6:33 እስከ 8:12
‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት’ የሚለው ብሮሹር ውስጥ ያለው ካርታ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ቦታዎችና የምድሩን አቀማመጥ ያሳያል። ሌላኛው ካርታ (ገጽ 15) የእስራኤል ነገዶች የሰፈሩበትን ቦታ ያሳያል። እነዚህ ሁለት ካርታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ ለመረዳት ያስችሉሃል።
ሟቹ ፕሮፌሰር ዮሃናን አሃሮኒ የሰጡት የሚከተለው አስተያየት ይህንን ያጎላል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት አገሮች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከታሪኩ ጋር በጣም የተያያዘ በመሆኑ አንዱን ከአንዱ ነጥሎ መረዳት አይቻልም።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Background map: Based on maps copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel