ተቃውሞን በድፍረት መቋቋም
ተቃውሞን በድፍረት መቋቋም
በቁጣ ገንፍሎ የወጣው ሕዝብ የሐዋርያው ጳውሎስን ጓደኞች ጋይዩስንና አርስጥሮኮስን ወደ ኤፌሶን ቲያትር ማሳያ ስፍራ እንዲገቡ አስገደዳቸው። በዚያም የነበረው ሕዝብ ለሁለት ሰዓት ያህል “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት” እያለ ጮኸ። (የሐዋርያት ሥራ 19:28, 29, 34) የጳውሎስ ጓደኞች እንዲህ ያለውን ተቃውሞ በድፍረት መቋቋም ይችሉ ይሆን? በመጀመሪያ ደረጃ ተቃውሞው የተነሳው ለምን ነበር?
ጳውሎስ ለሦስት ዓመት ያህል በኤፌሶን ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መስበክ ችሎ ነበር። ከዚህም የተነሳ በከተማው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጣዖትን ማምለክ ተዉ። (የሐዋርያት ሥራ 19:26፤ 20:31) በኤፌሶን በዋነኝነት ይመለክ የነበረው ጣዖት በብር እየተቀረጸ የሚሸጠው የመራባት ሴት አምላክ የሆነችው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ምስል ሲሆን የዚህች ሴት አምላክ እጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ በከተማው ውስጥ ከፍ ባለ ስፍራ ላይ ይገኝ ነበር። ሰዎች እነዚህን ትንንሽ የቤተ መቅደስ ምስሎች እንደ ክታብ ያንጠለጥሏቸው ወይም በቤታቸው ውስጥ ይሰቅሏቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች እነዚህን ጣዖታት አይገዙም ነበር።—1 ዮሐንስ 5:21
ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ በጳውሎስ አገልግሎት ምክንያት ትርፋማ የነበረው ንግዳቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተሰማው። ይህ ሰው እውነቱን በማዛባትና በማጋነን፣ በመላው ትንሿ እስያ የሚገኙ ሰዎች አርጤምስን ማምለክ ሊያቆሙ ይችላሉ ሲል ሌሎች አንጥረኞችን አሳመነ። በዚህን ጊዜ በጣም የተቆጡት የብር አንጥረኞች አርጤምስን እያወደሱ መጮህ ጀመሩ፤ ይህም ከፍተኛ ረብሻ እንዲቀሰቀስ አደረገ፣ ከተማዋም በሁከት ተሞላች።—የሐዋርያት ሥራ 19:24-29
ከዚያም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች 25,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው ቲያትር ቤት ተሰበሰቡ። ጳውሎስ ከሥርዓት ውጪ ሆኖ ለሚተራመሰው ሕዝብ ንግግር መስጠት ፈልጎ ነበር። ሆኖም ወዳጆቹ የነበሩ አንዳንድ ባለ ሥልጣናት እንደዚያ ማድረግ እንደሌለበት አሳመኑት። በመጨረሻም የከተማይቱ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡ እንዲረጋጋ በማድረጉ ጋይዩስና አርስጥሮኮስ ያለምንም ጉዳት ከሕዝቡ መሃል ሊወጡ ቻሉ።—የሐዋርያት ሥራ 19:35-41
በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ ተቃዋሚዎች ሊያጋጥሟቸው አልፎ ተርፎም የሕዝብ ዓመጽ ሊነሳባቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ የጣዖት አምልኮ፣ የሥነ ምግባር ብልግናና ወንጀል በነገሰባቸው ከተሞች ውስጥ ምሥራቹን ይሰብካሉ። ያም ሆኖ ኤፌሶን ውስጥ ‘በአደባባይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ወደኋላ ያላለውን’ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በድፍረት ይኮርጃሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) እነሱም እንዲሁ ‘የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ መሄዱን’ ሲመለከቱ ይደሰታሉ።—የሐዋርያት ሥራ 19:20
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤፌሶን ቲያትር ማሳያ ስፍራ ፍርስራሽ