በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጥንታዊው የሩሲያ ቤተ መጻሕፍት የተገኘው ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የፈነጠቀው “ግልጽ ብርሃን”

ከጥንታዊው የሩሲያ ቤተ መጻሕፍት የተገኘው ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የፈነጠቀው “ግልጽ ብርሃን”

ከጥንታዊው የሩሲያ ቤተ መጻሕፍት የተገኘው ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የፈነጠቀው “ግልጽ ብርሃን”

ሁለት ምሑራን ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለማግኘት ፍለጋ ላይ ናቸው። ሁለቱም በየግላቸው በረሃ አቋርጠው ዋሻዎችን፣ ገዳማትንና ከቋጥኝ ተፈልፍለው የተሠሩ ጥንታዊ መኖሪያዎችን እያሰሱ ነው። ከዓመታት በኋላ ሁለቱም ሰዎች እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከተገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆኑት ቅጂዎች ወደተቀመጡበት ጥንታዊው የሩሲያ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ሄዱ። እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? ያገኙት ውድ ሀብትስ ሩሲያ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነው?

የአምላክ ቃል ጠበቆች የሆኑት ጥንታዊ ቅዱሳን ጽሑፎች

ከእነዚህ ምሑራን አንደኛውን የምናገኘው ወደ 19ኛው መቶ ዘመን መባቻ ተመልሰን ነው። በዚህ ወቅት አውሮፓ በምሑራዊ አብዮት ትታመስ የነበረ ሲሆን ቀደም ሲል የነበሩ እምነቶችን በጥርጣሬ ዓይን የመመልከት አዝማሚያ እንዲስፋፋ ያደረጉ ሳይንሳዊ እድገቶችና ሥነ ጥበባዊ ግኝቶች መታየት ጀምረው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ተቀባይነት ለማሳጣት ይጥሩ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ሳይበረዝ እንዳለ መቆየቱ አጠራጣሪ መሆኑን መግለጽ ጀምረው ነበር።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅና የቆሙ አንዳንድ ቅን ሰዎች ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያልተገኙ ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች የአምላክን ቃል ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚረዱ አዳዲስ ማስረጃዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማጥፋት ወይም ለማዛባት ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉ የማይካድ ነው፤ ሆኖም በወቅቱ ከነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በፊት የነበሩትን ጥንታዊ ቅዱሳን ጽሑፎች ማግኘት ቢቻል እነዚህ ጽሑፎች የአምላክ ቃል ያልተበረዘ ለመሆኑ ያለ ድምፅ ምሥክርነት መስጠት ይችላሉ። እንደዚህ ያሉት ጥንታዊ ቅጂዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሳሳተ አተረጓጎም የገባባቸውን ጥቂት ቦታዎች ለማግኘትም ይረዳሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት አስመልክቶ የጦፈ ውዝግብ ከተካሄደባቸው አገሮች አንዷ ጀርመን ነች። በዚያ የነበረ አንድ ወጣት ፕሮፌሰር በትምህርቱ ዓለም የነበረውን የተሳካ ሕይወት በመተው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለመፈለግ ተነሳ፤ በዚህ ጉዞው በየትኛውም ዘመን ከተገኙት ሁሉ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት ችሏል። ይህ ሰው ኮንስታንቲን ቮን ቲሸንዶርፍ ይባላል፤ ቲሸንዶርፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችን ሐሳብ አለመቀበሉ የመጽሐፉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠቃሚ ማስረጃ ለማግኘት አስችሎታል። በ1844 ወደ ሲና ምድረ በዳ ባደረገው የመጀመሪያው ጉዞ ያገኘውን ስኬት ለማመን ያዳግታል። ቲሸንዶርፍ በአንድ ገዳም ውስጥ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቱን መልከት ሲያደርግ በግሪክኛ የተተረጎሙትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ ማለትም የሴፕቱጀንት (የሰብዓ ሊቃናት) ትርጉም አገኘ። ይህ ጽሑፍ እስከ ዛሬ ከተገኙት የሰብዓ ሊቃናት ትርጉሞች ሁሉ ጥንታዊው ነው!

ባገኘው ነገር በደስታ የፈነደቀው ቲሸንዶርፍ ከዚህ ቦታ 43 የብራና ጽሑፎች ወሰደ። በ1853 ተጨማሪ ጽሑፎች እንዳሉ በመተማመን እንደገና ቢመለስም ማግኘት የቻለው ጥቂት ቁርጥራጮችን ብቻ ነበር። የቀሩት የት ደረሱ? ቲሸንዶርፍ የገንዘብ አቅሙ ስለተመናመነ የአንድ ባለጸጋ እርዳታ ለማግኘትና ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለመፈለግ የትውልድ አገሩን ትቶ እንደገና ለመጓዝ ወሰነ። ሆኖም ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት የሩሲያው ዛር እንዲረዳው ጠየቀ።

ንጉሡ በጉዳዩ ተስማማ

የፕሮቴስታንት ምሑር የሆነው ቲሸንዶርፍ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት በተስፋፋባት በዚህች ሰፊ አገር ምን ዓይነት አቀባበል ሊገጥመው እንደሚችል በጣም ሳያሳስበው አልቀረም። ደግነቱ በወቅቱ በሩሲያ ለውጥና ተሐድሶ እየተካሄደ ነበር። ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ትሰጥ የነበረችው ዳግማዊት ንግሥት ካትሪን (ታላቋ ካትሪን በመባልም ትታወቃለች) በ1795 የቅዱስ ፒተርስበርግ ኢምፔሪያል ቤተ መጻሕፍት እንዲመሠረት አድርጋለች። በሩሲያ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እጅግ በጣም ብዙ ጽሑፎች የያዘ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስተናገድ ይችል ነበር።

በአውሮፓ ከሚገኙት ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት መካከል የሚመደበው የኢምፔሪያል ቤተ መጻሕፍት አንድ የሚጎድለው ነገር ነበር። ከተቋቋመ ግማሽ ምዕተ ዓመት ቢያልፍም በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥንታዊ ቅጂዎች ስድስት ብቻ ነበሩ። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች የማጥናትና ቅዱሳን ጽሑፎችን የመተርጎም ፍላጎት ሊያረካ አልቻለም። ዳግማዊት ካትሪን አንዳንድ ምሑራን የዕብራይስጥን ቋንቋ እንዲያጠኑ በአውሮፓ ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልካ ነበር። እነዚህ ምሑራን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በዋና ዋናዎቹ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ኮሌጆች ውስጥ የዕብራይስጥ ትምህርት ይሰጥ ጀመር፤ የሩሲያ ምሑራንም ለመጀመሪያ ጊዜ በጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ተመሥርተው ትክክለኛ የሆነ የሩሲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት ጀመሩ። ይሁን እንጂ የገንዘብ እጥረትና ወግ አጥባቂ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቃውሞ ለሥራቸው እንቅፋት ሆነባቸው። ትክክለኛው የእውነት ብርሃን የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ገና አልበራም ነበር።

ዳግማዊ አሌክሳንደር የተባለው የሩሲያ ዛር፣ ቲሸንዶርፍ ለማከናወን ያሰበው ሥራ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም፤ ወዲያው ለተልእኮው የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ አደረገለት። የቲሸንዶርፍ ሥራ በአንዳንዶች ዘንድ “ቅንዓትና የከረረ ተቃውሞ” እንዲቀሰቀስ ቢያደርግም ወደ ሲና ምድረ በዳ ያደረገውን ጉዞ አጠናቅቆ ሲመለስ ቀሪውን የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቅጂ ይዞ ነበር። a ከጊዜ በኋላ ኮዴክስ ሳይናቲከስ ተብለው የተሰየሙት እነዚህ ጽሑፎች እስከ ዛሬ ድረስ ከተገኙት በጣም ጥንታዊ የሚባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል ናቸው። ቲሸንዶርፍ ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተመለሰ በኋላ ወደ ኢምፔሪያል ዊንተር ቤተ መንግሥት በፍጥነት በመሄድ ዛሩ አዲስ የተገኙትን ጥንታዊ ቅጂዎች ለማሳተም ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥያቄ አቀረበ። ቲሸንዶርፍ እነዚህ ጽሑፎች “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሚደረገው ጥልቅ ጥናት ረገድ ትልቅ ድርሻ ያላቸው” እንደሆኑ የገለጸ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ጥንታዊዎቹ ቅጂዎች በኢምፔሪያል ቤተ መጻሕፍት እንዲቀመጡ ተደርጓል። የሩሲያው ዛር አለምንም ማንገራገር በሐሳቡ ተስማማ፤ ደስታ ያስፈነደቀው ቲሸንዶርፍ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አምላክ በዚህ ዘመን፣ . . . በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ትክክለኛ መልእክት ምን እንደሆነ እንድናውቅ ብሎም የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነተኝነት ማረጋገጥ እንድንችል የተሟላና ግልጽ ብርሃን የፈነጠቀልንን የሳይናቲከስን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጥቶናል።”

በክራይሚያ የተገኙ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች

በመግቢያችን ላይ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን የሚፈልግ ሌላም ምሑር እንዳለ ገልጸን ነበር። ይህ ሰው ማን ነው? ቲሸንዶርፍ ወደ ሩሲያ ከመመለሱ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢምፔሪያል ቤተ መጻሕፍት ለማመን የሚያዳግት ግብዣ ቀርቦለት ነበር። ጉዳዩ የሩሲያውን ዛር ትኩረት የሳበ ከመሆኑም በላይ ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ምሑራን ወደ ሩሲያ ጎረፉ። እነዚህ ምሑራን ከፍተኛ መጠን ያለው የጥንታዊ ጽሑፎችና የሌሎች ነገሮች ስብስብ በፊታቸው ተቀምጦ ሲመለከቱ ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም። የተሰባሰቡት ነገሮች አጠቃላይ ብዛታቸው 2,412 ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 975 ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎችና ጥቅልሎች ይገኙበታል። በእነዚህ መካከል ከአሥረኛው መቶ ዘመን በፊት የተጻፉ 45 የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ተካትተዋል። ጉዳዩን ይበልጥ አስደናቂ ያደረገው ደግሞ እነዚህን ጥንታዊ ጽሑፎች በሙሉ ማለት ይቻላል ያሰባሰቧቸው አንድ የ70 ዓመት አዛውንት መሆናቸው ነው። አብርሃም ፊርኮቪች የተባሉት እኚህ ሰው ቀረዓታዊ ምሑር ናቸው። ይሁን እንጂ ቀረዓታውያን እነማን ነበሩ? b

የሩሲያው ዛር የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮበት ነበር። ሩሲያ ድንበሯን በማስፋት ቀደም ሲል በሌሎች አገሮች ቁጥጥር ሥር የነበሩ ቦታዎችን የግዛቷ ክፍል ስታደርግ አዳዲስ ጎሣዎችም በዚህች አገር ሥር ተጠቃለሉ። በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኝ ክራይሚያ በተባለች ውብ አካባቢ አይሁዳዊ ቢመስሉም የቱርክን ባሕል የሚከተሉና ከታታር ጋር የሚቀራረብ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ቀረዓታውያን የሚባሉት እነዚህ ሰዎች በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን ዝርያ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሆኖም ታልሙድን ስለማይቀበሉና ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ ላይ ትኩረት ስለሚያደርጉ ከረቢዎች ይለያሉ። በክራይሚያ የሚኖሩት ቀረዓታውያን ረቢዎችን ከሚከተሉ አይሁዳውያን የተለዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ለሩሲያው ዛር ለማቅረብ ይፈልጉ ነበር። እነዚህ ሰዎች በእጃቸው የነበሩ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በማሳየት ከባቢሎን ግዞት በኋላ በክራይሚያ መኖር የጀመሩ አይሁዶች ዝርያ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው ነበር።

ፊርኮቪች ጥንታዊ መዛግብትንና የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎችን መፈለግ የጀመሩት በክራይሚያ ከሚገኙ የቹፉት ካል የቋጥኝ ቤቶች ነበር። ቀረዓታውያን ከቋጥኝ ተጠርቦ በወጣ ድንጋይ በሚሠሯቸው በእነዚህ ቤቶች ለብዙ ዘመናት የኖሩ ከመሆኑም በላይ የአምልኮ ሥርዓታቸውን ለማከናወን ይጠቀሙባቸው ነበር። በቀረዓታውያን ዘንድ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሚገኝባቸውን ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ማጥፋት እንደ ርኩስ ተግባር ስለሚቆጠር እነዚህ ጽሑፎች ቢያረጁም እንኳ አይጥሏቸውም። በመሆኑም ያረጁትን የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ገኒዛ (በዕብራይስጥ “መደበቂያ ቦታ” ማለት ነው) ተብሎ በሚጠራ አነስተኛ መጋዘን ውስጥ በጥንቃቄ አስቀምጠዋቸዋል። ቀረዓታውያን ለአምላክ ስም ጥልቅ አክብሮት ስለነበራቸው እነዚህን የብራና ጽሑፎች የሚያወጧቸው ከስንት አንዴ ነበር።

ገኒዛ ተብለው የሚጠሩት መጋዘኖች ለዘመናት አቧራ ሲጠጡ የቆዩ ቢሆኑም ፊርኮቪች በዚህ ሳይበገሩ በደንብ ፈተሿቸው። በአንደኛው መጋዘን ውስጥ በ916 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተጻፈውን የታወቀ ቅጂ አገኙ። የኋለኞቹ ነቢያት የፒተርስበርግ ኮዴክስ ተብሎ የሚጠራው ይህ ቅጂ አሁን በእጅ ካሉት በጣም ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች አንዱ ነው።

ፊርኮቪች እጅግ በጣም ብዙ ጥንታዊ ቅጂዎችን ያሰባሰቡ ሲሆን በ1859 ይህንን ስብስብ ለኢምፔሪያል ቤተ መጻሕፍት ለመሸጥ ወሰኑ። በ1862 በዳግማዊ አሌክሳንደር እርዳታ እነዚህ ግኝቶች ለቤተ መጻሕፍቱ በ125,000 ሩብልስ ተገዙ፤ ይህ ገንዘብ በጊዜው በጣም ብዙ ነበር። በወቅቱ የቤተ መጻሕፍቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ባጀት ከ10,000 ሩብልስ የማይበልጥ ነበር! ከተገዙት ጽሑፎች መካከል ዝነኛ የሆነው የሌኒንግራድ ኮዴክስ (B 19A) ይገኝበታል። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በ1008 ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት የተሟሉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ ነው። አንድ ምሑር “በዘመናችን ለተዘጋጁ ለአብዛኞቹ ባለማመሳከሪያ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሞች መሠረት በመሆኑ ይህ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር አቻ የሚገኝለት አይመስልም” ብለዋል። (ሣጥኑን ተመልከት።) በዚያው ዓመት ማለትም በ1862 ቲሸንዶርፍ ያዘጋጀው ኮዴክስ ሳይናቲከስ ለሕትመት የበቃ ሲሆን በዓለም ላይ አድናቆትን አትርፏል።

በዘመናችን የፈነጠቀ መንፈሳዊ ብርሃን

በዛሬው ጊዜ ብሔራዊ የሩሲያ ቤተ መጻሕፍት በመባል የሚታወቀው ቤተ መጻሕፍት በዓለም ላይ ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች በብዛት ከሚገኙባቸው ቦታዎች አንዱ ነው። c ሩሲያ ካሳለፈችው ታሪክ አንጻር በሁለት ክፍለ ዘመናት ውስጥ የቤተ መጻሕፍቱ ስም ሰባት ጊዜ ተለውጧል። ከተሰጡት ስሞች መካከል ሳልቲኮፍ ሽቼደሪን የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የሚለው በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው። ቤተ መጻሕፍቱ በ20ኛው መቶ ዘመን በነበረው ብጥብጥ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም ማለት ባይቻልም በውስጡ የነበሩት ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ግን በሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና ሌኒንግራድ በተከበበችበት ወቅት ከነበረው ውጊያ ተርፈዋል። ከእነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች ምን ጥቅም እናገኛለን?

ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች በዘመናችን ለሚገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አስተማማኝ ምንጭ ሆነዋል። እንዲሁም እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች ያልተበረዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት እንዲችሉ እገዛ አድርገዋል። የሳይናቲከስም ሆነ የሌኒንግራድ ኮዴክስ ቅጂዎች በይሖዋ ምሥክሮች ለተዘጋጀውና በ1961 ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለወጣው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የጎላ ድርሻ አበርክተዋል። ለአብነት ያህል፣ የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የተጠቀመባቸው ቢብሊያ ሄብራይካ ስቱትጋርቴንስያ እና በኪትል የተዘጋጀው ቢብሊያ ሄብራይካ የተባሉ መጻሕፍት በሌኒንግራድ ኮዴክስ ላይ የተመሠረቱ ከመሆናቸውም በላይ በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ 6,828 ጊዜ በሚገኘው የአምላክ ስም (ቴትራግራማተን) ተጠቅመዋል።

በቅዱስ ፒተርስበርግ የሚገኘው ጸጥታ የሰፈነበት ቤተ መጻሕፍትና በውስጡ ያሉት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች (አንዳንዶቹ ሌኒንግራድ የሚለው የከተማው የቀድሞ ስም ተጽፎባቸዋል) ባለውለታዎቻችን መሆናቸውን የሚገነዘቡ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ብዙ አይደሉም። ከማንም በላይ ባለውለታችን ግን መንፈሳዊ ብርሃን የሰጠንና መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ ነው። በዚህም ምክንያት መዝሙራዊው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ” የሚል ልመና አቅርቧል።—መዝሙር 43:3

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ቲሸንዶርፍ ከዚህ በተጨማሪ በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጁ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሙሉ ቅጂ ይዞ ተመልሷል።

b ስለ ቀረዓታውያን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 15, 1995 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “ቀረዓታውያንና እውነትን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ” የሚል ርዕስ ተመልከት።

c አብዛኛው ኮዴክስ ሳይናቲከስ ለብሪቲሽ ሙዚየም ስለተሸጠ በሩሲያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኙት ቁርጥራጮች ብቻ ናቸው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መለኮታዊውን ስም ማወቅና በዚህ ስም መጠቀም

ጥበበኛ የሆነው ይሖዋ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጎልናል። ባለፉት ዘመናት ሁሉ የኖሩት ጸሐፊዎች ያደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከእነዚህ ጸሐፊዎች መካከል ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ የነበሩት ማሶሬቶች የተባሉ ዕብራውያን ጸሐፊዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ በመሥራት ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው። የጥንቱ ዕብራይስጥ የሚጻፈው ያለ አናባቢ ነበር። ይህ ዓይነቱ አጻጻፍ ጊዜ እያለፈና ዕብራይስጥ በአረማይክ ቋንቋ እየተተካ ሲሄድ ትክክለኛው አነባበብ ሊጠፋ የሚችልበትን አጋጣሚ ይከፍታል። ማሶሬቶች የዕብራይስጥ ቃላትን ትክክለኛ አነባበብ ማወቅ እንዲቻል በመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ላይ የሚጨመሩ አናባቢ ምልክቶች አዘጋጁ።

በማሶሬቶች የተዘጋጁት አናባቢ ምልክቶች በሌኒንግራድ ኮዴክስ ላይ ቴትራግራማተንን (የአምላክ ስም የሚጻፍባቸው አራት ተነባቢ ፊደላት) ለማንበብ የሚያስችሉ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ማሶሬቶች ባዘጋጁት አናባቢ ምልክት መሠረት ቴትራግራማተን የሕዋ፣ የሕዊ እና የሖዋ ተብለው ይነበባሉ። በአሁኑ ወቅት “ይሖዋ” የሚለው የአምላክ ስም አነባበብ በሰፊው የታወቀ ነው። መለኮታዊው ስም ሕያውና በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ሆነ በጥንት ዘመን በኖሩ ሌሎች ሰዎች ዘንድ የታወቀ ነበር። በዛሬው ጊዜ ‘ይሖዋ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል እንደሆነ’ የሚቀበሉ ሰዎች የአምላክን ስም የሚያውቁት ከመሆኑም በላይ ይጠቀሙበታል።—መዝሙር 83:18 NW

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኘው የጥንታዊ ጽሑፎች ክፍል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳግማዊት ንግሥት ካትሪን

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮንስታንቲን ቮን ቲሸንዶርፍ (መካከል) እና የሩሲያው ዛር ዳግማዊ አሌክሳንደር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም ፊርኮቪች

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁለቱም ሥዕሎች:- National Library of Russia, St. Petersburg

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳግማዊት ንግሥት ካትሪን:- National Library of Russia, St. Petersburg; ዳግማዊ አሌክሳንደር:- From the book Spamers Illustrierte Weltgeschichte, Leipzig, 1898