የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን በእርጅና ዘመኑ ለአምላክ ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ትንሣኤ አያገኝም ብለን መደምደም እንችላለን?—1 ነገሥት 11:3-9
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጠኝነት ትንሣኤ የሚያገኙ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን በስም የሚጠቅስ ቢሆንም በመጽሐፉ ላይ ስሙ የተጠቀሰ እያንዳንዱ ግለሰብ ትንሣኤ ማግኘት አለማግኘቱን በተመለከተ ግን በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። (ዕብራውያን 11:1-40) ይሁንና ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሲሞቱ የተባለላቸውን ነገር ሰሎሞን ሲሞት ከተባለለት ነገር ጋር በማነጻጸር አምላክ በእርሱ ላይ ምን እንደሚወስን ፍንጭ ማግኘት እንችላለን።
ቅዱሳን ጽሑፎች የሞቱ ሰዎች እጣ ሁለት ዓይነት ብቻ መሆኑን ይኸውም ለጊዜው ከሕልውና ውጪ መሆን አሊያም ደግሞ የዘላለም ጥፋት እንደሆነ ይናገራሉ። ትንሣኤ አይገባቸውም ተብሎ የተፈረደባቸው ሰዎች የተጣሉት “ገሃነም” ወይም “እሳት ባሕር” ውስጥ ነው። (ማቴዎስ 5:22፤ ማርቆስ 9:47,48፤ ራእይ 20:14) የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች አዳምና ሔዋን፣ ከሃዲው የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በአምላክ የቅጣት ፍርድ የጠፉት በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች እንዲሁም የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። a ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ያላቸው ሰዎች ግን በሚሞቱበት ጊዜ ወደ መቃብር ይኸውም ወደ ሲኦል ይገባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የእነዚህን ሰዎች የወደፊት ተስፋ አስመልክቶ ሲናገር “ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት” ይላል።—ራእይ 20:13
ስለዚህ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተገለጹት የእምነት ሰዎች ትንሣኤ እየተጠባበቁ በመቃብር ወይም በሲኦል ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የሆኑት አብርሃም፣ ሙሴ እና ዳዊት ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች ሲሞቱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነርሱ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ለአብርሃም እንዲህ ብሎታል:- “አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ።” (ዘፍጥረት 15:15) ይሖዋ ሙሴንም “እነሆ፣ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው” ብሎታል። (ዘዳግም 31:16) መጽሐፍ ቅዱስ የሰሎሞን አባት የሆነውን ዳዊትን አስመልክቶ ሲናገር:- “ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ” ይላል። (1 ነገሥት 2:10) ስለዚህ ‘ከአባቶቻቸው ጋር እንዳንቀላፉ‘ የሚናገረው አገላለጽ በሌላ አባባል ግለሰቡ ወደ መቃብር ወይም ወደ ሲኦል መግባቱን ያመለክታል።
ሰሎሞን በሞተበት ወቅትስ የተባለው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰሎሞን በመላው እስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም የነገሠው አርባ ዓመት ነው። ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (1 ነገሥት 11:42, 43) ስለዚህ ሰሎሞን በሲኦል ውስጥ ሆኖ ትንሣኤ እየተጠባበቀ ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይመስላል።
ይህ መደምደሚያ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ‘ከአባቶቻቸው ጋር እንዳንቀላፉ’ የተነገረላቸው ሌሎች ሰዎችም ትንሣኤ የማግኘታቸው አጋጣሚ ክፍት ነው የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። እንዲያውም ከሰሎሞን ቀጥለው የተነሡት ብዙዎቹ ነገሥታት ታማኞች የነበሩ ባይሆኑም እንዲሁ ተብሎላቸዋል። ‘ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን የሚነሡ’ እንደመሆኑ መጠን ይህ ነገር ለማመን የሚከብድ አይደለም። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) እውነት ነው፣ ትንሣኤ የማግኘት አጋጣሚ ያለው ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው “መቃብር ውስጥ” ያሉት ከተነሡ በኋላ ነው። (ዮሐንስ 5:28, 29) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖረ አንድ ሰው ትንሣኤ ያገኛል ወይም አያገኝም የሚል ድርቅ ያለ መልስ ከመስጠት ይልቅ በይሖዋ ፍጹም ውሳኔ በመታመን ነገሩን በትዕግሥት እንጠብቃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሰኔ 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 30-31 ተመልከት።