በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉም የላቀው ትምህርት አያምልጥህ!

ከሁሉም የላቀው ትምህርት አያምልጥህ!

ከሁሉም የላቀው ትምህርት አያምልጥህ!

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ጨምሮ የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ ነው። (ዘፍጥረት 1:27፤ ራእይ 4:11) ታላቅ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች፣ አዳምና ሔዋንን አስተምሯቸዋል እንዲሁም በዔድን ገነት ውስጥ ለሚኖራቸው ሕይወት አዘጋጅቷቸዋል። እነርሱን በቀጣይነት የማስተማርና የመንከባከብ ዓላማ ነበረው። (ዘፍጥረት 1:28, 29፤ 2:15-17፤ ኢሳይያስ 30:20, 21) ከፊታቸው እንዴት ያለ ጊዜ ይጠብቃቸው እንደነበር አስብ!

ይሁንና እነዚህ ባልና ሚስት ሁሉንም ነገር ወደኋላ አሽቀንጥረው መጣላቸው የሚያሳዝን ነው። አለመታዘዛቸው ለመላው የሰው ዘር ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ውድቀት መንስኤ ሆኗል። (ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮሜ 5:12) መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ከተፈጠረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የነበረውን ትውልድ አስመልክቶ ሲናገር “እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ” ይላል።—ዘፍጥረት 6:5

ይሖዋ የሰው ልብ ሁሌም ወደ ክፋት ያዘነበለ መሆኑን ከተናገረ ወደ 4,500 ዓመታት ገደማ ያለፉ ሲሆን በዛሬው ጊዜ የሰው ልጅ ያለበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የከፋ ሆኗል። ብዙዎች ያለ ምንም እፍረት ይዋሻሉ፣ ይሰርቃሉ ወይም ሌሎችን ያጠቃሉ። በአንድ በኩል ከዕለት ወደ ዕለት ችግሮች እየጨመሩ የመጡ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ለሰው ማዘኑ እየቀረ መጥቷል። የቤተሰብ ክልልን ጨምሮ በአብዛኛው በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት አደጋ ላይ ወድቋል ቢባል ትክክል አይደለም? ነገር ግን አሁን ላሉት ሁኔታዎች ተወቃሹ አምላክ አይደለም። እነዚህ ችግሮች ግድ አይሰጡትም ብለን ማሰብም የለብንም። ይሖዋ ለሰው ልጆች ደኅንነት ምንጊዜም ቢሆን ያስባል። በተጨማሪም ደስተኛ የሆነ ኑሮ ለመኖር የእርሱን መመሪያ ለማግኘት የሚሹትን ለማስተማር ዝግጁ ነው። ከዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በፊት ልጁን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በመላክ ሕይወታቸውን ስኬታማ በሆነ መንገድ መምራት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተማር ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን ከታላቁ አስተማሪ የተማረ በመሆኑ እንከን የማይወጣለት ትምህርት ምን ዓይነት እንደሆነ አሳይቷል።

እውነተኛ ክርስትናና ትምህርት

ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ላይ የተመሠረተውን የሕይወት መንገድ ማለትም እውነተኛውን ክርስትና አቋቁሟል። በእውነተኛ ክርስትና ውስጥ ተግባራችንም ሆነ አስተሳሰባችን ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ፣ ለስሙም ክብርና ምስጋና የሚያመጣ ሊሆን ይገባዋል። (ማቴዎስ 22:37-39፤ ዕብራውያን 10:7) ኢየሱስ ስለዚህ የሕይወት መንገድ ሲያስተምር የአባቱ ድጋፍ አልተለየውም። ከአምላክ ያገኘውን ድጋፍ አስመልክቶ በዮሐንስ 8:29 ላይ “የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም” በማለት ተናግሯል። እውነት ነው፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የአባቱ እርዳታና መመሪያ አልተለየውም ነበር። የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮችም ቢሆኑ የሚያጋጥማቸውን የሕይወት ውጣ ውረድ ያለ መመሪያ እንዲወጡ አልተተዉም። ይሖዋ በልጁ አማካኝነት አስተምሯቸዋል። የኢየሱስን ትምህርቶችና ምሳሌውን መከተላቸው የተሻሉ ሰዎች አድርጓቸዋል። ይህ በዛሬው ጊዜ ባሉት ተከታዮቹ ላይም ይታያል።— “የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ያሳደረው ተጽዕኖ” የሚለውን በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

የእውነተኛው ክርስትና ልዩ ገጽታ ሰዎች ከውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ አስተሳሰባቸውንና ልባቸውን መንካት የሚችል ትምህርት የያዘ መሆኑ ነው። (ኤፌሶን 4:23, 24) አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ኢየሱስ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ስለመሆን ሲያስተምር “‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” ብሏል። (ማቴዎስ 5:27, 28) ኢየሱስ እንዲህ በማለት ደቀ መዛሙርቱ ልባቸውን ንጹሕ አድርገው መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችንና ምኞቶችን ማስወገድ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። ይህን ካላደረጉ ግን መዘዙ የከፋ እንደሚሆን ነግሯቸዋል። መጥፎ የሆኑ ሐሳቦች አምላክን ደስ የማያሰኙና ሌሎችን የሚጎዱ ድርጊቶችን ወደ መፈጸም የሚመሩ መሆናቸው እውነት አይደለም?

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ምክር ይሰጣል:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ‘በእርግጥ በትምህርት አእምሮን መለወጥ ይቻላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አእምሮን መለወጥ በአምላክ ቃል ላይ የተሰጡትን መሠረታዊ ሥርዓቶችና መመሪያዎች ወደ ውስጥ ማስገባትና በተለያየ አቅጣጫ ማሠራትን ይጠይቃል። ይህንንም ለማድረግ አምላክ በቃሉ አማካኝነት ያቀረበውን ትምህርት መማር ያስፈልጋል።

ለውጥ ለማድረግ ተነሳሱ

የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።” (ዕብራውያን 4:12) አሁንም ድረስ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ዘመን ያለፈበት እንዳልሆነ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። አንድ ሰው አካሄዱን እንዲያስተካክል፣ እውነተኛውን ክርስትና እንዲቀበልና የተሻለ ሰው እንዲሆን ሊያነሳሳው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ጥቅም ቀጥለው ያሉት ምሳሌዎች ያሳያሉ።

በፊተኛው ርዕስ ላይ የጠቀስናት ኤሚልያ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በቤቴ ውስጥ ያለውን ችግር ለማስተካከል በግሌ የማደርገው ጥረት ብቻውን በቂ አልነበረም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር ግን ተስፋ እንዳለኝ የተገነዘብኩ ከመሆኑም ሌላ በአስተሳሰቤ ላይ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ታጋሽ መሆንና በቁጣ የመገንፈል ባሕርዬን ማስወገድ እንዳለብኝ ተማርኩ። ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ አብሮኝ ማጥናት ጀመረ። መጠጥ ለማቆም ተቸግሮ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ሊሳካለት ችሏል። ይህም ትዳራችንን እንደ አዲስ እንድንጀምር አስችሎናል። አሁን ደስተኛ ክርስቲያኖች ከመሆናችንም በተጨማሪ ልጆቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ግሩም መመሪያዎች እያስተማርናቸው ነው።”—ዘዳግም 6:7

ከእውነተኛ ክርስትና የሚገኘው ትምህርት ሰውን ከመጥፎ ጠባይና ሥነ ምግባር ከጎደለው አኗኗር ያላቅቃል። ይህንንም ማንዌል a እውነት ሆኖ አግኝቶታል። በ13 ዓመቱ ከቤተሰቡ ተለይቶ ወጥቶ ማሪዋና ማጨስ የጀመረ ሲሆን ቀስ በቀስም ወደ ሄሮይን ተሻገረ። መጠለያና ገንዘብ ለማግኘት ሲል ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽም ነበር። ከጊዜ በኋላ ራሱን ለማስተዳደር ሲል በዝርፊያ ተግባር ተሰማራ። ምንጊዜም ሕይወቱን የሚቆጣጠረው አደንዛዥ ዕፅ ነበር ማለት ይቻላል። ተደባዳቢ መሆኑ በተደጋጋሚ እስር ቤት እንዲገባ አድርጎታል። በአንድ ወቅት አራት ዓመት በእስር ቤት ያሳለፈ ሲሆን እዚያም የጦር መሳሪያ አሻሻጭ ሆኖ ነበር። ማንዌል ካገባ በኋላም ቢሆን የቀድሞ ሕይወቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ ገና አልተላቀቀም ነበር። ስለ ሁኔታው ሲናገር “በዶሮዎች ቤት ውስጥ ለመኖር የተገደድንበት ወቅት ነበር። እንዲያውም ባለቤቴ በእንጨት ምግብ ታበስል እንደነበር እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። የነበርንበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ የገዛ ዘመዶቼ ጥላኝ እንድትሄድ ባለቤቴን ይመክሯት ነበር” ብሏል።

ታዲያ ሕይወቱ እንዲለወጥ ያስቻለው ምንድን ነው? ማንዌል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አንድ የማውቀው ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊነግረን ቤታችን መጣ። እኔም ለሰው ልጆች የሚያስብ አምላክ እንደሌለ ለማሳየት ስል ለመወያየት ፈቃደኛ ሆንኩ። ለዚህ ደግሞ ራሴን ሕያው ማስረጃ አድርጌ አቀረብሁ። የይሖዋ ምሥክሩ የነበረው ትዕግሥትና ትሕትና በጣም ስላስደነቀኝ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድገኝ ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። በስብሰባው ቦታ የነበሩ አንዳንዶች ሁኔታዬን የሚያውቁ ቢሆንም ወዳጃዊ የሆነ አቀባበል አደረጉልኝ። ከእነርሱ እንደ አንዱ እንደሆንሁ እንዲሰማኝ አደረጉ። ይህ ደግሞ በጣም አጽናናኝ። ሌላ ሥራ ለማግኘት ስል ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ያለኝን ንክኪ ለመተው ወሰንኩ። ማጥናት ከጀመርኩ ከአራት ወራት በኋላ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቃቱን አሟላሁ፤ ከዚያም ከአራት ወር በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።”

ለማንዌልና ለቤተሰቡ እውነተኛ ክርስትና ምን አስገኝቶላቸዋል? “መጽሐፍ ቅዱስ ባልማር ኖሮ ከዓመታት በፊት በሞትኩ ነበር። ኢየሱስ ያስተማረው የሕይወት መንገድ ቤተሰቦቼን እንዳተርፍ አስችሎኛል። ሁለቱ ልጆቼ እኔ በወጣትነቴ ባሳለፍኩት የሕይወት ጎዳና መጓዝ አያስፈልጋቸውም። ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና ዛሬ ከባለቤቴ ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላለኝ እኮራለሁ። የድሮ ጓደኞቼ ያደረግሁትን ለውጥ ሲመለከቱ የተደሰቱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አሁን እየተከተልኩት ያለው መንገድ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ይነግሩኛል።”

በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሥነ ምግባር ንጽሕና ከአካላዊ ንጽሕና ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር ነው። በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ በድህነት የተጎሳቆለ ሰፈር ውስጥ የሚኖረው ጆን የዚህን አባባል እውነተኝነት ተረድቶታል። እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ልጃችን ሳምንቱን ሙሉ ሳትታጠብ ትከርማለች፣ ደግሞም አንዳችንም ብንሆን ዞር ብለን አናያትም።” ባለቤቱም ቤታቸው በጣም የተዝረከረከ እንደነበር አምናለች። የክርስትናን ትምህርት መከታተል ከጀመሩ በኋላ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። ጆን የመኪና ሌቦች ከሆኑት ጓደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦ ለቤተሰቡ ይበልጥ ትኩረት ይሰጥ ጀመረ። “ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ሰውነታችንም ሆነ ልብሳችን ንጹሕ መሆን እንዳለበት ተማርን። በ1 ጴጥሮስ 1:16 ላይ ያለውን ይሖዋ አምላክ ቅዱስ እንደሆነ እኛም ቅዱስ እንድንሆን የሚያዘውን ቃል በጣም እወደዋለሁ። አሁን ትንሿ ቤታችንን ንጹሕ አድርገን ለመያዝም ጥረት እናደርጋለን” በማለት ይናገራል።

ከሁሉ የላቀውን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ

እንደ እነዚህ ያሉ ተሞክሮዎች ያልተለመዱ ክስተቶች አይደሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ትምህርት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች ታማኝና ታታሪ ሆነው በመገኘታቸው በአሰሪዎቻቸው ዘንድ የሚወደዱ ናቸው። እንዲሁም ለሰዎች ደኅንነት የሚያስቡ ጥሩ ጎረቤትና ጓደኛ መሆን ችለዋል። መጥፎ ሥነ ምግባርንና የሥጋ ዝንባሌን ለማስወገድ በመቁረጣቸው ለአካላዊ፣ ለአእምሯዊና ለስሜታዊ ጤንነታቸው ከበፊቱ የተሻለ ትኩረት መስጠት ችለዋል። ጥሪታቸውን በማይረባ ነገር ከማጥፋት ይልቅ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚጠቅም ነገር ያደርጉበታል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ቈላስይስ 3:18-23) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈረውን ትምህርት በሥራ ማዋል የሚያስገኘው ጥቅም እውነተኛ ክርስትና ከሁሉ የተሻለ ትምህርት የሚገኝበት የላቀ የሕይወት መንገድ መሆኑን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ሕግ ጋር ተስማምቶ የሚኖርን ሰው አስመልክቶ ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል።—መዝሙር 1:3

ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ እኛን ለማስተማር ፈቃደኛ መሆኑን ማወቃችን የሚያበረታታ ነው። ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” ብሏል። (ኢሳይያስ 48:17) እውነት ነው፣ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና እርሱ ባስተማራቸው ትምህርቶች አማካኝነት መንገዱን አሳይቶናል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት በሚያውቁት ሰዎች ሕይወት ላይ ትምህርቱ ለውጥ ያመጣ ከመሆኑም ሌላ ዛሬም ከእርሱ ትምህርት ጋር ተስማምተው የሚኖሩ የብዙዎች ሕይወት ተለውጧል። ስለ እነዚህ ትምህርቶች ይበልጥ ለማወቅ ለምን ጊዜ አትመድብም? በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ማግኘት እንድትችል ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ያሳደረው ተጽዕኖ

የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ የነበረው ዘኬዎስ ያለውን ሥልጣን ያላግባብ በመጠቀም፣ በማጭበርበርና ከተራው ሕዝብ ገንዘብ በመዝረፍ ሀብታም ለመሆን ችሏል። ይሁን እንጂ የኢየሱስን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን ቀየረ።—ሉቃስ 19:1-10

የጠርሴሱ ሳውል ክርስቲያኖችን ማሳደድ አቁሞ ወደ ክርስትና በመለወጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመባል በቅቷል።—የሐዋርያት ሥራ 22:6-21፤ ፊልጵስዩስ 3:4-9

ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ‘ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች’ የነበሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እውነተኛውን ክርስትና ከተማሩ በኋላ ‘በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የታጠቡ፣ የተቀደሱና የጸደቁ’ ለመሆን ችለዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስኬታማ መሆን የምትችልበትን መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር ትችላለህ