በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ

የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ

የክርስትና እምነት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ተዳረሰ

በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ አንድ ወሳኝ ስብሰባ ተካሄደ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ “እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት” ዮሐንስ፣ ጴጥሮስና የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በቦታው እንደነበሩ በስም የተጠቀሱት ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኛው በርናባስ ነበሩ። የስብሰባው አጀንዳ ሰፊው የአገልግሎት ክልል ለስብከቱ ሥራ በሚያመች መንገድ እንዴት ቢከፈል ይሻላል የሚል ነበር። ጳውሎስ “ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድ[ን]ሄድ ተስማሙ” ሲል ገልጿል።—ገላትያ 2:1, 9 a

ይህ ስምምነት ምን ትርጉም ነበረው? ምሥራቹ የሚታወጅበት ክልል በአንድ በኩል አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሕዛብ በሚል የተከፈለ ነበር? ወይስ ስምምነቱ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን የተከተለ ነበር? መልሱን ለማግኘት ስለ ፈላሻዎች ማለትም ከጳለስጢና ምድር ውጪ ይኖሩ ስለነበሩ አይሁድ አንዳንድ ታሪካዊ መረጃ ማግኘት ይኖርብናል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአይሁዳውያን ዓለም

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ምን ያህል አይሁዳውያን ነበሩ? ብዙ ምሑራን የአይሁዳውያን ዓለም ካርታ (እንግሊዝኛ) የተባለው ጽሑፍ ካሰፈረው ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ይመስላል:- “ትክክለኛውን አኃዝ ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ከ70 [ከክርስቶስ ልደት በኋላ] ቀደም ብሎ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በይሁዳ ሁለት ሚሊዮን ተኩል አይሁዳውያን፣ በተቀረው የሮማ ግዛት ደግሞ ከአራት ሚሊዮን በላይ ይገኙ እንደነበር ይገመታል። . . . በሮም ግዛት ውስጥ ከአጠቃላዩ ሕዝብ አንድ አሥረኛ ያህሉ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። አይሁዳውያን በብዛት በሚኖሩባቸው በሮማ ግዛት በስተ ምሥራቅ ባሉ ከተሞች ደግሞ ከነዋሪዎቹ መካከል አንድ አራተኛ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት እነርሱ ነበሩ።”

አይሁዳውያን በብዛት ይኖሩ የነበሩት በስተ ምሥራቅ በሚገኙት በሶርያ፣ በትንሿ እስያ፣ በባቢሎንና በግብፅ ሲሆን በአውሮፓ የነበሩት ቁጥራቸው አነስተኛ ነበር። ታዋቂ የሆኑ አንዳንድ የቀድሞ ዘመን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የኖሩት ከእስራኤል ውጪ ነበር። ከእነርሱም መካከል የቆጵሮሱ በርናባስ፣ የጳንጦስ ተወላጅ የሆኑትና ሮም ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጵርስቅላና አቂላ፣ የእስክንድርያው አጵሎስ እንዲሁም የጠርሴሱ ጳውሎስ ይገኙበታል።—የሐዋርያት ሥራ 4:36፤ 18:2, 24፤ 22:3

ከአገራቸው ፈልሰው የሄዱ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ከትውልድ አገራቸው ጋር የሚያገናኟቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚልኩት ዓመታዊ ግብር ሲሆን ይህም በቤተ መቅደሱ እንቅስቃሴና በዚያ በሚከናወነው አምልኮ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ይህን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ጆን ባርክሌይ እንዲህ ብለዋል:- “የፈላሻ ማኅበረሰቦች ለዚህ ዓላማ የሚሰበሰበውን ገንዘብ (ሃብታም የሆኑ አይሁዳውያን የሚሰጡት ተጨማሪ መዋጮ ታክሎበት) በወቅቱ ይከፍሉ እንደነበር የሚያሳይ አጥጋቢ ማስረጃ አለ።”

ከአገራቸው ጋር የሚያገናኛቸው ሌላው ነገር ታላላቆቹን በዓላት ለማክበር በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞ ነው። በሐዋርያት ሥራ 2:9-11 ላይ የሚገኘው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስለተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል የሚተርከው ዘገባ ይህን ያሳያል። በበዓሉ ላይ የተገኙት አይሁዳውያን ከጳርቴና፣ ከሜድ፣ ከኢላም፣ ከመስጴጦምያ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ፣ ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ ከሊቢያ፣ ከሮም፣ ከቀርጤስ እንዲሁም ከዐረብ አገር የመጡ ነበሩ።

በኢየሩሳሌም የሚገኘው የቤተ መቅደሱ አስተዳደር ከአገራቸው ውጪ ከሚኖሩት አይሁዳውያን ጋር በደብዳቤ ይገናኝ ነበር። በሐዋርያት ሥራ 5:34 ላይ የተጠቀሰው የሕግ አስተማሪ የነበረው ገማልያል ወደ ባቢሎንና ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ደብዳቤ ይልክ እንደነበር ማወቅ ተችሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ59 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ እስረኛ ሆኖ ሮም ሲደርስ ‘የአይሁድ መሪዎች’ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም” በማለት ነግረውታል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከእስራኤል ወደ ሮም በየጊዜው ደብዳቤዎችና ሪፖርቶች ይላኩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 28:17, 21

ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓ ሊቃናት በመባል የሚታወቀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ግሪክኛ ትርጉም ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከእስራኤል ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን ሰብዓ ሊቃናትን የእነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ‘ቅዱስ ጽሑፍ’ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩትና ያነብቡት ነበር ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።” የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለማስተማር ሥራቸው በዚሁ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ይጠቀሙ ነበር።

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የክርስትና እምነት የበላይ አካል አባላት እነዚህን ጉዳዮች በሚገባ ያውቁ ነበር። ምሥራቹ በሶርያና ከዚያም አልፎ እንደ ደማስቆና አንጾኪያ ባሉ ቦታዎች በሚገኙ አይሁዳውያን ዘንድ ቀደም ሲል ተዳርሶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:19, 20፤ 11:19፤ 15:23, 41፤ ገላትያ 1:21) ስለዚህ በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተወያዩት ወደፊት ሥራው እንዴት መከናወን እንዳለበት ነው። የክርስትና እምነት በአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት በመጡ ሰዎች ዘንድ እንዴት እንደተስፋፋ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንመልከት።

የጳውሎስ ጉዞና ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን

ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ የተሰጠው ሥራ ‘በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት [የኢየሱስ ክርስቶስን] ስም መሸከም’ ነበር። b (የሐዋርያት ሥራ 9:15) በኢየሩሳሌም ከተካሄደው ስብሰባ በኋላ ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ከአገራቸው ውጪ ለሚኖሩ አይሁድ ምሥራቹን ማድረሱን ቀጠለ። (በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የአገልግሎት ክልሉን የተከፋፈሉት ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊነት ሥራቸውን በስተ ምዕራብ በኩል ያስፋፉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአገራቸው ለሚኖሩ አይሁድና በምሥራቁ ዓለም ለሚገኙት ሰፋፊ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ምሥራቹን ሰብከዋል።

ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ በሶርያ ከምትገኘው አንጾኪያ ተነስተው ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ ትንሿ እስያን አቋርጠው እስከ ጢሮአዳ ድረስ በስተ ምዕራብ በኩል እንዲሄዱ ተደርገው ነበር። ከዚያም “እግዚአብሔር ወንጌልን [ለመቄዶንያ ሰዎች] እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል” ብለው ስላሰቡ ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ወሰኑ። ከጊዜ በኋላ አቴናን እና ቆሮንቶስን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች የክርስቲያን ጉባኤዎች ተቋቁመዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:40, 41፤ 16:6-10፤ 17:1 እስከ 18:18

በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ማብቂያ ላይ ጳውሎስ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ይበልጥ ርቆ የመሄድና በኢየሩሳሌም በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተመደበለትን የአገልግሎት ክልል የማስፋት ዕቅድ ነበረው። ‘በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ ጓጉቻለሁ’ እንዲሁም “ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 1:15፤ 15:24, 28) ይሁንና በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ፈላሻ አይሁድ ሁኔታስ ምን ይመስል ነበር?

በምሥራቁ የሮም ግዛት የሚገኙ የአይሁድ ማኅበረሰቦች

በአንደኛው መቶ ዘመን የአይሁድ ማኅበረሰብ በብዛት ይገኝባት የነበረችው ግብፅ ስትሆን አብዛኞቹም የሚኖሩት በዋና ከተማዋ በእስክንድርያ ነበር። የንግድና የባሕል ማዕከል የነበረችው ይህች ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን መኖሪያ ከመሆኗም ሌላ ከተማይቱ ውስጥ ብዙ ምኩራቦች ይገኙ ነበር። የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነው አይሁዳዊው ፊሎ በመላዋ ግብፅ በወቅቱ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን አይሁዳውያን እንደነበሩ ተናግሯል። በተጨማሪም በአቅራቢያው በምትገኘው በሊቢያ፣ ቀሬና በምትባለው ከተማና በአካባቢዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር።

ክርስቲያን የሆኑ አንዳንድ አይሁዶች ከእነዚህ አካባቢዎች የመጡ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ፣” “ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡት አንዳንዶች ሰዎች” እንዲሁም በሶርያ አንጾኪያ የነበረውን ጉባኤ ይረዳ የነበረው “የቀሬናው ሉክዮስ” በማለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:10፤ 11:19, 20፤ 13:1፤ 18:24) ከዚህ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በግብፅና በአካባቢዋ ስላከናወኑት ሥራ የሚገልጸው ነገር የለም። ይህም ክርስቲያኑ ወንጌላዊ ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሰጠውን ምሥክርነት ሳንጨምር መሆኑ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-39

ጳርቴናን፣ ሜድንና ኢላምን ጨምሮ ባቢሎን አይሁዶች በብዛት የሚገኙባት ሌላዋ አገር ነበረች። አንድ የታሪክ ምሑር “ከአርሜንያ አንስቶ እስከ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ድረስ፣ ጤግሮስና ኤፍራጥስ አካባቢ ያለው ግዛትም ሆነ በስተ ሰሜን ምሥራቅ እስከ ካስፒያን ባሕር ድረስ፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ እስከ ሜድ ድረስ ያለውን ቦታ አይሁዳውያን ይገኙበት ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ብዛታቸው 800,000 ወይም ከዚያ በላይ እንደሚገመት ጠቅሷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ዓመታዊዎቹን በዓላት ለማክበር በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የባቢሎን አይሁዶች ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ እንደነበር ተናግሯል።

ከባቢሎን ከመጡት አይሁዶች መካከል አንዳንዶቹ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ተጠምቀው ይሆን? ይህን ማወቅ አንችልም፤ ሆኖም በዚያን ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ያቀረበውን ንግግር ካዳመጡት መካከል ከመስጴጦምያ የመጡ አይሁዶች ይገኙበት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:9) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከ62 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በባቢሎን እንደነበረ ይታወቃል። የመጀመሪያ ደብዳቤውን ምናልባትም ሁለተኛውንም የጻፈው እዚያ እያለ ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:13) በ49 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን የሚገኙባት ባቢሎን ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለያዕቆብ ተመድባ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

የኢየሩሳሌም ጉባኤና በየአገሩ የሚገኙ አይሁዶች

የአገልግሎት ክልል ድልድል በተካሄደበት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረው ያዕቆብ በኢየሩሳሌም በሚገኝ ጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። (የሐዋርያት ሥራ 12:12, 17፤ 15:13፤ ገላትያ 1:18, 19) በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከተለያዩ አገሮች የመጡ አይሁድ ምሥራቹን ተቀብለው ሲጠመቁ በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን አይቷል።—የሐዋርያት ሥራ 1:14፤ 2:1, 41

በዚያ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ዓመታዊዎቹን በዓላት ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። ከተማዋ በሰዎች ስለምትጨናነቅ እንግዶቹ በአቅራቢያው በሚገኙ መንደሮች ለማረፍ ወይም ድንኳን ውስጥ ለመኖር ይገደዱ ነበር። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ በዓሉን ለማክበር የመጡት ሰዎች ከወዳጆቻቸው ጋር የሚገናኙ ከመሆኑም ሌላ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደው አምልኮና መሥዋዕት ያቀርቡ እንዲሁም የሕጉን መጽሐፍ ይማሩ እንደነበር ገልጿል።

ያዕቆብና በኢየሩሳሌም ጉባኤ የሚገኙ ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህን አጋጣሚዎች በመጠቀም ከሌሎች አገሮች ለመጡ አይሁድ ምሥራቹን ሰብከው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ምናልባትም ሐዋርያቱ ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ “በኢየሩሳሌም በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት” በተነሳበት ወቅት በከፍተኛ ጥንቃቄ ምሥራቹን ሰብከው ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 8:1) ከስደቱ በፊትም ሆነ በኋላ እነዚህ ክርስቲያኖች በቅንዓት በመስበካቸው ቀጣይ እድገት እንደተገኘ ዘገባው ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ 8:4፤ 9:31

ከዚህ ምን እንማራለን?

አዎን፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አይሁዳውያኑን በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ለማግኘት ልባዊ ጥረት አድርገዋል። ከዚያው ጎን ደግሞ ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች በአውሮፓ ምድር ለአሕዛብ ለመመሥከር ጥረት አድርገዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ተለይቶ ከመሄዱ በፊት “ሕዝቦችን ሁሉ” ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የሰጣቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20

እነርሱ ከተዉት ምሳሌ የይሖዋን መንፈስ ድጋፍ ለማግኘት ምሥራቹን በተደራጀ መልክ የመስበክን አስፈላጊነት እንማራለን። ከዚህ በተጨማሪ፣ በተለይ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ባሉበት ክልል ውስጥ ለአምላክ ቃል አክብሮት ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ማግኘት ውጤት እንዳለው ማየት እንችላለን። ለጉባኤያችሁ ከተመደበው ክልል ውስጥ አንዳንዱ አካባቢ ከሌላው የበለጠ ፍሬ ይገኝበታል? እነዚህን ክልሎች ደጋግሞ መሸፈኑ ጥሩ ሊሆን ይችላል። በአካባቢያችሁ ብዙ ሕዝብ የሚገኝባቸው አንዳንድ ክንውኖች ሲኖሩ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠትና ከመንገድ ወደ መንገድ ለማገልገል ልዩ ጥረት ብታደርጉ ውጤት ማግኘት ትችሉ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚያቀርበውን ዘገባ ከማንበብ በተጨማሪ ከታሪክና ከመልክአ ምድር አቀማመጥ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቃችን በጣም ይጠቅመናል። ብዙ ካርታዎችና ፎቶግራፎች የያዘው “መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ” የተባለው ብሮሹር ግንዛቤያችንን ለማስፋት የሚረዳ አንድ መሣሪያ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ይህ ስብሰባ የተደረገው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካሉ በግርዘት ጉዳይ ላይ ለመወያየት በተሰበሰበበት ወቅት ወይም ከዚያ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 15:6-29

b ይህ ርዕስ ትኩረት የሚያደርገው ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ሆኖ ባከናወነው ሥራ ላይ ሳይሆን ለአይሁድ በሰጠው ምሥክርነት ላይ ነው።—ሮሜ 11:13

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

ሐዋርያው ጳውሎስ ከአገራቸው ውጪ ለሚኖሩ አይሁዶች የሰጠው ትኩረት

በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም ስብሰባ ከመደረጉ በፊት

የሐዋርያት ሥራ 9:19, 20 ደማስቆ — “በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ”

የሐዋርያት ሥራ 9:29 ኢየሩሳሌም — “ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋር እየተነጋገረ”

የሐዋርያት ሥራ 13:5 ስልማና፣ ቆጵሮስ — “በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ”

የሐዋርያት ሥራ 13:14 በጲስድያ ውስጥ ያለችው አንጾኪያ — “ወደ ምኵራብ ገብተው”

የሐዋርያት ሥራ 14:1 ኢቆንዮን — “ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ”

በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም ከተደረገው ስብሰባ በኋላ

የሐዋርያት ሥራ 16:14 ፊልጵስዩስ — “ልድያ . . . እግዚአብሔርን የምታመልክ”

የሐዋርያት ሥራ 17:1 ተሰሎንቄ — “የአይሁድ ምኵራብ”

የሐዋርያት ሥራ 17:10 ቤርያ — “ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ”

የሐዋርያት ሥራ 17:17 አቴና — “በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድ . . . ጋር ይነጋገር ነበር”

የሐዋርያት ሥራ 18:4 ቆሮንቶስ — “በምኵራብ ውስጥ እየተነጋገረ”

የሐዋርያት ሥራ 18:19 ኤፌሶን — “ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር”

የሐዋርያት ሥራ 19:8 ኤፌሶን — “ወደ ምኵራብ እየገባ . . . ሦስት ወር ሙሉ ምንም

ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር”

የሐዋርያት ሥራ 28:17 ሮም — “የአይሁድን መሪዎች በአንድነት ጠራ”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በ33 በጰንጠቆስጤ ዕለት ምሥራቹን የሰሙት ሰዎች ከበርካታ አገሮች የመጡ ነበሩ

እልዋሪቆን

ጣሊያን

ሮም

መቄዶንያ

ግሪክ

አቴና

ቀርጤስ

ቀሬና

ሊቢያ

ቢታንያ

እስያ

ገላትያ

ፍርግያ

ጵንፍልያ

ቆጵሮስ

ግብፅ

ኢትዮጵያ

ጳንጦስ

ቀጰዶቅያ

ኪልቅያ

መስጴጦምያ

ሶርያ

ሰማርያ

ኢየሩሳሌም

ይሁዳ

ሜድ

ባቢሎን

ኢላም

አረብ

ጳርቴና

[የውኃ አካላት]

የሜዲትራንያን ባሕር

ጥቁር ባሕር

ቀይ ባሕር

የፋርስ ባሕረ ሰላጤ