በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስምንት ልጆችን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ ፈታኝ ሆኖም አስደሳች ነበር

ስምንት ልጆችን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ ፈታኝ ሆኖም አስደሳች ነበር

የሕይወት ታሪክ

ስምንት ልጆችን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ ፈታኝ ሆኖም አስደሳች ነበር

ጃስሊን ቫለንታይን እንደተናገረችው

በ1989 ባለቤቴ ለሥራ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በወቅቱ ስምንት ልጆቼን የማሳድግበት ገንዘብ እንደሚልክ ቃል ገብቶልኝ ነበር። ሆኖም ስለ እርሱ አንዳች ነገር ሳልሰማ ሳምንታት አለፉ። ወራት አልፈው ወራት ቢተኩም የባለቤቴ ድምጽ ጠፋ። እኔም ‘ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ወደ ቤቱ ይመለሳል’ እያልኩ ራሴን ማጽናናት ያዝኩ።

ቤተሰቤን የማስተዳድርበት ገንዘብ ስላልነበረኝ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሆነብኝ። እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ባደርኩባቸው በእነዚያ ሌሊቶች እውነታውን መቀበል ተስኖኝ ‘እንዴት በቤተሰቡ ላይ ይህን ያህል ይጨክናል?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። ሆኖም ውሎ አድሮ ባለቤቴ ጥሎን የመሄዱን መራራ ሐቅ አምኜ ተቀበልኩ። አሁን ጥሎን ከሄደ 16 ዓመታት አልፈዋል፤ አሁንም ቢሆን ወደ ቤቱ አልተመለሰም። በዚህ ሳቢያ ልጆቼን ለብቻዬ አሳደግሁ። ይህ ደግሞ ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም በይሖዋ መንገድ ሲመላለሱ በማየቴ እጅግ ተደስቻለሁ። ቤተሰባችን ያንን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት እንደተወጣው ከመናገሬ በፊት ስለ አስተዳደጌ ትንሽ ላውጋችሁ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት

የካሪቢያን ደሴት በሆነችው በጃማይካ በ1938 ተወለድኩ። አባቴ የቤተ ክርስቲያን አባል ባይሆንም እንኳ ራሱን ፈሪሃ አምላክ እንዳለው ሰው አድርጎ ይቆጥር ነበር። ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ የመዝሙርን መጽሐፍ እንዳነብለት ይጠይቀኛል። ስለሆነም ብዙም ሳይቆይ አብዛኞቹን መዝሙሮች በቃሌ ያዝኳቸው። እናቴ በአካባቢያችን የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አባል ስለነበረች በቤተ ክርስቲያኑ ወደ ሚደረጉት ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች አልፎ አልፎ ይዛኝ ትሄድ ነበር።

በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አምላክ ጥሩ ሰዎችን ወደ ሰማይ እንደሚወስዳቸውና ክፉ የሆኑትን ደግሞ ለዘላለም በሲኦል እሳት እንደሚያቃጥላቸው ይነገረን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነና ልጆችንም እንደሚያፈቅር አስተምረውናል። በመሆኑም በግራ መጋባት ስሜት ተዋጥኩ፤ አምላክንም በጣም ፈራሁት። ‘አምላክ የሚወደን ከሆነ ታዲያ ሰዎችን ለምን በእሳት ያሠቃያል?’ እያልኩ አስብ ነበር።

ስለ ሲኦል እሳት ባሰብኩ ቁጥር ያቃዠኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የሚያዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ የተልእኮ ትምህርት መካፈል ጀመርኩ። እነርሱም ክፉ ሰዎች ለዘላለም እንደማይሠቃዩ ከዚህ ይልቅ በእሳት ተቃጥለው አመድ እንደሚሆኑ አስተማሩኝ። ይህ ምክንያታዊ ይመስል ስለነበር በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመርኩ። ይሁንና የሚያስተምሩት ትምህርት ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ ሥነ ምግባርን በተመለከተ የነበረኝን የተሳሳተ አመለካከት ሊያስወግድልኝ አልቻለም።

በዚያን ጊዜ ሕዝቡ በአብዛኛው ዝሙት ትክክል እንዳልሆነ ያምን ነበር። ይሁን እንጂ እኔም ሆንኩ ሌሎች በርካታ ሰዎች አንድ ሰው ዝሙት ፈጽሟል የምንለው ከብዙ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት ካደረገ ብቻ ነው። በመሆኑም በሕግ ያልተጋቡ ሁለት ሰዎች ከሌላ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት እስካልፈጸሙ ድረስ አብረው ቢኖሩም እንኳ ኃጢአት እንደሠሩ ተደርጎ አይቆጠርም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ዕብራውያን 13:4) ሕጋዊ ትዳር ሳይኖረኝ የስድስት ልጆች እናት የሆንኩትም በዚህ ምክንያት ነው።

መንፈሳዊ እድገት ማድረግ

በ1965 ቫስሊን ጉዲሰን እና ኢተል ቼምበርስ በአቅራቢያችን በሚገኘው የባዝ ሕዝብ ወደሚኖሩበት አካባቢ መጥተው መኖር ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ አንድ ቀን አባቴን አግኝተው አነጋገሩት። አባቴም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። በዚያን ዕለት ቤት ብሆን ኖሮ እኔንም ያነጋግሩኝ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የነበረኝ ቢሆንም ሐሰተኛ መሆናቸውን ለማጋለጥ ስል ከእነርሱ ጋር ለማጥናት ወሰንኩ።

በጥናታችን ወቅት በርካታ ጥያቄዎችን እጠይቅ ነበር፤ እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ሁሉንም ይመልሱልኛል። በእነርሱ እርዳታ፣ ሙታን ምንም እንደማያውቁና በሲኦል ውስጥ በመሠቃየት ላይ እንዳልሆኑ ተገነዘብኩ። (መክብብ 9:​5, 10) በገነት ውስጥ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋም ተማርኩ። (መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:3, 4) አባቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን ቢያቆምም እንኳ እኔ ግን በአካባቢው በሚደረግ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። ጉባኤው ሰላማዊና ሥርዓትን በጠበቀ መንገድ የሚከናወን መሆኑ ስለ ይሖዋ ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ መንገድ ከፈተልኝ። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ማለትም ወረዳና አውራጃ ስብሰባዎችን ተካፈልኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይበልጥ መተዋወቅ መቻሌ ይሖዋን እርሱ በሚፈልገው መንገድ እንዳመልከው ፍላጎት አሳደረብኝ። ሆኖም እንቅፋት የሚሆን ነገር አልታጣም።

በወቅቱ ከስድስቱ ልጆቼ መካከል የሦስቱ አባት ከሆነው ሰው ጋር በሕግ ሳንጋባ አብረን እንኖር ነበር። አምላክ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን እንደሚያወግዝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተምሬ ስለነበር ሕሊናዬ ይረበሽ ጀመር። (ምሳሌ 5:​15-​20፤ ገላትያ 5:​19) ለእውነት ያለኝ ፍቅር ጥልቀት እያገኘ ሲሄድ ሕይወቴን ከአምላክ መመሪያዎች ጋር ለማስማማት ያለኝ ፍላጎትም የዚያኑ ያህል ጨመረ። በመጨረሻም ውሳኔ ላይ ደረስኩ። አብሮኝ ለሚኖረው ሰው ጋብቻችንን ሕጋዊ ማድረግ አሊያም ግንኙነታችን መቆም እንዳለበት ገለጽኩለት። ይህ ሰው እምነቴን ባይጋራም እንኳ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘሁ ከአምስት ዓመታት በኋላ ማለትም ነሐሴ 15, 1970 በሕግ ተጋባን። በታኅሣሥ ወር 1970 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።

ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት የወጣሁበትን ቀን መቼም አልረሳውም። የፍርሃት ስሜት ስለነበረብኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት እንዴት መጀመር እንደምችል ግራ ገብቶኝ ነበር። እንዲያውም በመጀመሪያ ያነጋገርኩት ሰው ውይይታችን በአጭሩ እንዲቀጭ በማድረጉ ተደስቼ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የፍርሃት ስሜቱ ለቀቀኝ። ከበርካታ ሰዎች ጋር አጠር አጠር ያሉ ውይይቶችን በማድረጌና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማበርከት በመቻሌ በቀኑ መገባደጃ ላይ የነበረኝ ደስታ ወሰን አልነበረውም።

ቤተሰቡ በመንፈሳዊ እንዲጠነክር መርዳት

በ1977 የልጆቹ ቁጥር ስምንት የደረሰ ሲሆን ቤተሰቤ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። (ኢያሱ 24:15) በመሆኑም ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ብርቱ ጥረት አድርጌአለሁ። አንዳንዴ በጣም ከመድከሜ የተነሳ አንደኛው ልጅ ጮክ ብሎ ሲያነብ እኔ ግን በተቀመጥኩበት እንቅልፍ ይወስደኝ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ልጆቼ ይቀሰቅሱኛል። ያም ሆኖ አካላዊ ድካም የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኖብን አያውቅም።

ከልጆቼ ጋር የመጸለይ ልማድ ነበረኝ። ነፍስ እያወቁ ሲሄዱ እንዴት ራሳቸውን ችለው ወደ ይሖዋ መጸለይ እንደሚችሉ አስተምራቸው ነበር። ከመተኛታቸው በፊት እያንዳንዳቸው መጸለያቸውን አረጋግጥ ነበር። ራሳቸውን ችለው መጸለይ ከማይችሉት ከትንንሽ ልጆቼ ጋር በየተራ አብሬ እጸልያለሁ።

መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ ልጆቹን ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ይዤ መሄዴን ይቃወም ነበር። ይሁንና ጉባኤ በምሄድበት ወቅት ልጆቹን የመንከባከቡ ኃላፊነት እርሱ ላይ እንደሚወድቅ መገንዘቡ ተቃውሞው እንዲለዝብ ምክንያት ሆነ። አመሻሽ ላይ ወጣ ብሎ ከጓደኞቹ ጋር መጫወት ይወድ ነበር፤ ሆኖም ስምንት ልጆችን አንጋግቶ ይዞ መሄዱ አላስደሰተውም! የኋላ ኋላ ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ ልጆቹን በማሰናዳበት ወቅት እርሱም ያግዘኝ ጀመር።

ብዙም ሳይቆይ ልጆቹ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የመገኘትና በመስክ አገልግሎት የመካፈል ልማድ አዳበሩ። ትምህርት ቤታቸው ለእረፍት ሲዘጋ ብዙውን ጊዜያቸውን በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር በማገልገል ያሳልፋሉ። ይህም ልጆቼ ገና ከልጅነታቸው ለጉባኤና ለአገልግሎት ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓል።​—⁠ማቴዎስ 24:14

የፈተና ጊዜያት

ባለቤቴ የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ወደ ሌላ አገር እየሄደ መሥራት ጀመረ። ረዘም ላሉ ጊዜያት ከቤተሰቡ ርቆ ይሰነብት የነበረ ቢሆንም የተለመደ ጊዜውን ጠብቆ ወደ ቤት ይመጣ ነበር። ሆኖም በ1989 ከሄደበት ሳይመለስ ቀረ። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ባለቤቴን ማጣቴ በጣም ጎዳኝ። በርካታ ሌሊቶችን ሳለቅስ እንዲሁም መጽናናትን እንዲሰጠኝና እንድጸና እንዲረዳኝ ይሖዋን በጸሎት ስማጸን ከቆየሁ በኋላ ጸሎቴ ምላሽ እንዳገኘ ተሰማኝ። ኢሳይያስ 54:4ን እና 1 ቆሮንቶስ 7:15ን የመሳሰሉት ጥቅሶች የአእምሮ ሰላም እንዳገኝ እንዲሁም የደረሰብኝን ሁኔታ ተቋቁሜ እንድቀጥል ብርታት ሰጥተውኛል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ዘመዶቼና ወዳጆቼ ስሜታዊ ድጋፍም ሆነ ቁሳዊ እርዳታ አድርገውልኛል። ላደረጉልኝ እርዳታ ይሖዋንና ሕዝቦቹን ላመሰግን እወዳለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም ነበሩብን። በአንድ ወቅት አንዷ ልጄ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ተግባር በመፈጸሟ ምክንያት ከጉባኤ ተወገደች። ሁሉንም ልጆቼን በጣም እወዳቸዋለሁ፤ ይሁንና ከሁሉ ከፍ አድርጌ የምመለከተው ለይሖዋ ታማኝ የመሆኔን ጉዳይ ነበር። በመሆኑም በእነዚያ ወቅቶች እኔም ሆንኩ ሌሎቹ ልጆቼ ከተወገዱ ሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በጥብቅ ተከተልን። (1 ቆሮንቶስ 5:​11, 13) ሆኖም እንዲህ ዓይነት አቋም የያዝነው ለምን እንደሆነ ያልተገነዘቡ ሰዎች በጣም ነቀፉን። ይሁንና ልጃችን ወደ ጉባኤ ከተመለሰች በኋላ ባለቤቷ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ በመከተላችን እጅግ መደነቁን ገልጾልኛል። አሁን እርሱም ሆነ ቤተሰቡ ይሖዋን በማገልገል ላይ ናቸው።

የነበረብንን የገንዘብ ችግር መቋቋም

ባለቤቴ ጥሎን በሄደበት ወቅት ቋሚ የገቢ ምንጭ አልነበረኝም፤ እንዲሁም ቤተሰቡ ከእርሱ ሲያገኘው የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ተቋርጦ ነበር። ይህ ሁኔታ በትንሽ ነገር ረክተን እንድንኖር እንዲሁም ከቁሳዊ ሀብት ይልቅ መንፈሳዊ ብልጽግና የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን እንድናውቅ አስችሎናል። ልጆቼም እርስ በርሳቸው መዋደድና መረዳዳት እንዳለባቸው ሲማሩ ይበልጥ ተቀራረቡ። ትላልቆቹ ሥራ ሲይዙ ትንንሾቹን ለመርዳት ፈቃደኞች ነበሩ። ትልቋ ልጄ ማርሴሪ የመጨረሻ ታናሽ እህቷ ኒኮል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንድታጠናቅቅ ረድታታለች። ከዚህም በተጨማሪ ትንሽ ግሮሰሪ ከፍቼ ነበር። ከዚህ የማገኘው መጠነኛ ገቢም የሚያስፈልገንን ቁሳዊ ነገር ለማሟላት አስችሎኛል።

ይሖዋም ቢሆን መቼም ትቶን አያውቅም። በአንድ ወቅት ለአንዲት እህት የገንዘብ አቅማችን ስለማይፈቅድልን ወደ አውራጃ ስብሰባ ለመሄድ እንደማንችል አጫወትኳት። እርሷም “እህት ቫል፣ ስለ አውራጃ ስብሰባ ማስታወቂያ ሲነገር ስትሰሚ ለጉዞ መዘገጃጀት ጀምሪ! ይሖዋ የሚያስፈልግሽን ይሰጥሻል” በማለት መለሰችልኝ። እኔም ምክሯን ተከተልኩ። ልክ እንደተናገረችው ይሖዋ የሚያስፈልገንን ማድረጉን አላቋረጠም። ቤተሰባችን በገንዘብ እጦት ሳቢያ ከትልልቅ ስብሰባዎች አንድም ቀን ቀርቶ አያውቅም።

በ1988 ጊልበርት የተባለው ከባድ አውሎ ነፋስ ጃማይካን መታ፤ እኛም ቤታችንን ጥለን የአደጋ ጊዜ መጠለያ ውስጥ ተሸሸግን። ዝናብ የቀላቀለው አውሎ ነፋስ ጋብ ሲል እንዳልነበረ የሆነውን ቤታችንን ለማየት ወንድ ልጄን ይዤ ሄድኩ። ፍርስራሹን ስበረብር አንድ ውድ ንብረቴን አገኘሁና እርሱን እንኳ ባድን ብዬ አሰብኩ። ሆኖም ወዲያውኑ ነፋሱ መንፈስ ጀመረ፤ እኔ ደግሞ ይህን ንብረቴን ትቶ መሄዱ አልሆንልሽ አለኝ። በዚህ ጊዜ “እማማ፣ ቴሌቪዥኑን ወዲያ ተይው እንጂ፤ የሎጥን ሚስት ሆንሽ እንዴ?” የሚለውን የልጄን ድምጽ ሰማሁ። (ሉቃስ 17:31, 32) ይህ ሁኔታ ወደ ሕሊናዬ እንድመለስ አደረገኝ። ስለዚህ በዝናብ የራሰውን ቴሌቪዥን አስቀምጬ ሕይወታችንን ለማትረፍ ከልጄ ጋር ተያይዘን እሮጥን።

ለቴሌቪዥን ስል ሕይወቴን አደጋ ላይ የጣልኩበትን ያንን ጊዜ ሳስታውሰው አሁንም ቢሆን ይዘገንነኛል። ሆኖም ልጄ ያኔ የተናገረውን ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ትኩረት እንደሚሰጥ የሚጠቁመውን ምክሩን ሳስብ ልቤ በደስታ ይሞላል። ከክርስቲያን ጉባኤ ላገኘው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥልጠና ምስጋና ይግባውና ይደርስብኝ ከነበረው ከባድ አካላዊ ምናልባትም መንፈሳዊ ጉዳት ጠብቆኛል።

አውሎ ነፋሱ የነበረንን ቤትና ንብረት በሙሉ አወደመብን፤ እኛም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጥን። በዚህ ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ደረሱልን። በይሖዋ ላይ በመታመን የደረሰብንን ጉዳት እንድንቋቋምና በአገልግሎት ንቁ ሆነን እንድንቀጥል አበረታቱን፤ እንዲሁም ቤታችንን በድጋሚ ሠሩልን። ከጃማይካና ከውጪ አገር የመጡት እነዚህ ፈቃደኛ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩን ፍቅርና የከፈሉት መሥዋዕትነት ልባችንን በጥልቅ ነክቶታል።

የይሖዋን ፈቃድ ማስቀደም

ሁለተኛዋ ልጄ ሚላን ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ አቅኚ ሆና ስታገለግል ቆይታለች። በኋላም በሌላ ጉባኤ ውስጥ አቅኚ ሆና እንድታገለግል የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች፤ ይህ ደግሞ ሥራዋን መልቀቅ ይጠይቅባት ነበር። ይዛው የነበረው ሥራ ለቤተሰባችን ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም እያንዳንዳችን መንግሥቱን እስካስቀደምን ድረስ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ሙሉ እምነት ነበረን። (ማቴዎስ 6:​33) ቆየት ብሎም ዩአን የተባለው ወንድ ልጄ አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ተጋበዘ። እርሱም ቤተሰቡን በገንዘብ ይደግፍ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ እንዲባርከው በመመኘት ግብዣውን እንዲቀበል አበረታታነው። ልጆቼ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት ሲያደርጉ ፈጽሞ ተቃውሜያቸው አላውቅም። ቤት የቀረነውም ብንሆን ምንም ነገር አልጎደለብንም። ከዚህ ይልቅ ደስታችን ከዕለት ወደ ዕለት ይጨምር አልፎ አልፎም ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ እናደርግ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ልጆቼ ‘በእውነት ሲመላለሱ’ ማየቴ ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል። (3 ዮሐንስ 4) ከሴቶች ልጆቼ ውስጥ አንዷ የሆነችው ሚላን ከባለቤቷ ጋር በመሆን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። ሌላዋ ልጄ አንድሪያ እና ባለቤቷ በልዩ አቅኚነት የሚያገለግሉ ሲሆን አንዳንዴም ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከሚሆነው ባሏ ጋር ጉባኤዎችን ይጎበኛሉ። የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ወንዱ ልጄ ዩአን ከባለቤቱ ጋር በልዩ አቅኚነት በማገልገል ላይ ይገኛል። አቫጋ የተባለችው ሌላኛዋ ሴት ልጄ ደግሞ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ጃማይካ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ታገለግላለች። ጄኒፈርና ኒኮል ከባለቤቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው በየጉባኤያቸው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው። አሁን የምኖረው ከማሪሴሪ ጋር ሲሆን ያለንበት ጉባኤ ፖርት ሞራንት ይባላል። ስምንቱም ልጆቼ ይሖዋን ማገልገላቸውን በመቀጠላቸው በእጅጉ ተባርኬያለሁ።

በዕድሜ መግፋት ሳቢያ አንዳንድ የጤንነት ችግሮች አሉብኝ። ሩማቶይድ አርትራይተስ ከተባለው በሽታ ጋር መታገል ግድ ቢሆንብኝም በአቅኚነት ማገልገሌን አላቋረጥኩም። ይሁንና ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ አቀበታማ በሆነው የመኖሪያ አካባቢያችን መጓዝ ስላስቸገረኝ አገልግሎት መውጣት ያዳግተኝ ጀመር። በዚህ ጊዜ በእግር ከመሄድ ይልቅ በብስክሌት ለመጓዝ ሞከርኩ፤ ይህም የተሻለ ሆኖ አገኘሁት። በመሆኑም አንድ ያገለገለ ብስክሌት ገዛሁና በዚያ መጠቀም ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ ልጆቼ በአርትራይተስ የምትሠቃየው እናታቸው በብስክሌት ስትጓዝ ማየት ከብዷቸው ነበር። ይሁንና እንደ ልቤ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል መቻሌን ሲያዩ እጅግ ተደሰቱ።

የማስጠናቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበሉ ማየቴ ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል። በዚህ በመጨረሻው ዘመንም ሆነ ለዘላለም መላው ቤተሰባችን በታማኝት እንዲጸና ይረዳን ዘንድ ዘወትር ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ስምንት ልጆቼን ሳሳድግ የገጠሙኝን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድቋቋም ለረዳኝ፣ ታላቅና ‘ጸሎት ሰሚ’ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ምስጋናዬና ውዳሴዬ ይድረስ።​—⁠መዝሙር 65:2

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጆቼ፣ ከትዳር ጓደኞቻቸውና ከልጅ ልጆቼ ጋር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቴን ለማከናወን በብስክሌት እጠቀማለሁ