እንደ ላጋኒ አውና ዛፍ ነህ?
እንደ ላጋኒ አውና ዛፍ ነህ?
በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በፖርት ሞርስብይ ከተማ ዳርቻ ላይ በምትገኝ አንድ መንደር ውስጥ ይሰብኩ የነበሩ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ጨርሰው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነበር። በመንገድ ሲያልፉ ዓይን የሚስብ አንድ ዛፍ ተመለከቱና በዕድሜ ተለቅ ያለው “አሃ፣ ላጋኒ አውና!” አለ። ከዚያም አብሮት ላለው ወንድም እንዲህ አለው:- “የስሙ ትርጉም ‘ዓመታዊ ዛፍ’ ማለት ነው። በሐሩር ክልል ከሚገኙት ሌሎች ዛፎች በተለየ መልኩ ይህ ዛፍ በየዓመቱ ቅጠሉ ሙሉ በመሉ ይረግፍና የደረቀ ይመስላል። ያም ሆኖ ዝናብ መዝነብ ሲጀምር እንደገና ቅጠል ያወጣና አብቦ ወደ ቀድሞ ውበቱ ይመለሳል።”
በተለምዶ ሮያል ፖይንሲያና ተብሎ ከሚጠራው ከላጋኒ አውና ዛፍ አንድ ትምህርት መቅሰም እንችላለን። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ይህ ዛፍ በዓለም ላይ ከሚያብቡ አምስት ውብ ዛፎች መካከል አንዱ ነው። ዛፉ በበጋ ወራት አበቦቹና ቅጠሎቹ የሚረግፉ ቢሆኑም እንኳ ብዙ ውሃ ይዞ ማቆየት ይችላል። ሥሩ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ከመሬት በታች ባሉ ትላልቅ ዓለቶች ላይ ተጠምጥሞ ያድጋል። ኃይለኛ ነፋስ ቢመጣ የሚቋቋመው በዚህ መንገድ ነው። በአጭር አነጋገር አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ያልፋል።
እኛም የእምነታችንን ጥንካሬ የሚፈታተኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። እንድንጸና የሚረዳን ምንድን ነው? እንደ ላጋኒ አውና ዛፍ ሁሉ እኛም ሕይወት ሰጪ የሆነውን የአምላክን ቃል ውኃ መጠጣትና ማጠራቀም እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ‘ዐለታችን’ ከሆነው ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር መጣበቅ ይኖርብናል። (2 ሳሙኤል 22:3) እውነት ነው፣ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ሥር ብንሆን እንኳ ይሖዋ ባዘጋጀልን አጋጣሚዎች በመጠቀም መንፈሳዊ ጥንካሬያችንንና ውበታችንን ጠብቀን ማኖር እንደምንችል ላጋኒ አውና ዛፍ ያስታውሰናል። በዚህ መንገድ የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ይሖዋ ያዘጋጀውን ‘የተስፋ ቃል እንወርሳለን።’—ዕብራውያን 6:12፤ ራእይ 21:4