“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ”
“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ”
“ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።”—ምሳሌ 14:15
1, 2. (ሀ) ሎጥ በሰዶም ካጋጠመው ሁኔታ ምን እንማራለን? (ለ) “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው?
ሎጥ የሚፈልገውን አገር እንዲመርጥ አብርሃም በፈቀደለት ጊዜ “እንደ እግዚአብሔር ገነት” የሆነው ውኃማ ምድር ትኩረቱን ሳበው። ሎጥ ለቤተሰቡ ምቹ መኖሪያ ቦታ ያገኘ መስሎት ሳይሆን አይቀርም “የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ” በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። ይሁን እንጂ የአካባቢው ገጽታ አታላይ ነበር፤ ምክንያቱም በአቅራቢያው “ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን” የነበሩት የሰዶም ሰዎች ይኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 13:7-13) ውሎ አድሮ ሎጥና ቤተሰቡ ከባድ ችግር ይደርስባቸው ጀመር። በመጨረሻም እርሱና ሴቶች ልጆቹ በዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገደዱ። (ዘፍጥረት 19:17, 23-26, 30) ሎጥ መጀመሪያ ላይ እጅግ መልካም መስሎ የታየው ነገር የተገላቢጦሽ ሆኖበታል።
2 የሎጥ ገጠመኝ በአሁኑ ጊዜ ላሉት የአምላክ አገልጋዮች ትምህርት ይሰጣል። ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድመን ማሰብና ከላይ በምናያቸው ነገሮች እንዳንታለል መጠንቀቅ ይገባናል። የአምላክ ቃልም “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ ተገቢ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:13 NW) እዚህ ላይ “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “የተረጋጋችሁ ሁኑ” የሚል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ሪቻርድ ሌንስኪ እንደተናገሩት መረጋጋት የተባለው “ነገሮችን በሚገባ አመዛዝኖና ገምግሞ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችል የሰከነና የማይናወጥ የአእምሮ ሁኔታ” ነው። የተረጋጋ የአእምሮ ሁኔታ መያዝ አስፈላጊ የሆነባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች እስቲ እንመልከት።
የምታገኘውን የንግድ አጋጣሚ መመዘን
3. አንድ ዓይነት የንግድ ሥራ እንድንጀምር ግብዣ ሲቀርብልን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
3 አንድ የተከበረ ሰው፣ ምናልባትም እንዳንተው የይሖዋ አምላኪ የሆነ ወንድም አንድ ዓይነት የንግድ ሥራ እንድትጀምር ግብዣ አቀረበልህ እንበል። ስለሚገኘው ስኬት በስሜት በመናገር አጋጣሚው ሳያመልጥህ ቶሎ እርምጃ እንድትወስድ ያበረታታሃል። አንተም በበኩልህ ይህ አጋጣሚ የራስህንም ሆነ የቤተሰብህን ሕይወት እንደሚያሻሽል ማሰብ ትጀምር ይሆናል፤ አልፎ ተርፎም ሁኔታው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ እንደሚያስገኝልህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ምሳሌ 14:15 “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። አንድ ሰው አዲስ ንግድ እንደሚጀምር ሲያስብ የሚፈጠርበት የደስታ ስሜት፣ ብዙውን ጊዜ ሊያጋጥመው የሚችለውን ኪሳራና አደገኛ ሁኔታ አቅልሎ እንዲመለከት እንዲሁም ንግዱ አስተማማኝ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ ቆም ብሎ እንዳያስብ ሊያደርገው ይችላል። (ያዕቆብ 4:13, 14) እንዲህ የመሰለው ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜ የማስተዋል ስሜትህን መጠበቅ ምንኛ አስፈላጊ ነው!
4. አንድ ዓይነት ንግድ ውስጥ እንድንገባ ሐሳብ ቢቀርብልን ‘ርምጃችንን ማስተዋል’ የምንችለው እንዴት ነው?
4 አስተዋይ የሆነ ሰው ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ንግዱን በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ያደርጋል። (ምሳሌ 21:5) እንዲህ ማድረግ በአብዛኛው የኋላ ኋላ ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች ለማስተዋል ይረዳል። እስቲ የሚከተለውን ሊያጋጥም የሚችል ሁኔታ እንመልከት:- አንድ ሰው ሊጀምር ላሰበው ንግድ ገንዘብ እንድታበድረው ፈለገ እንበል፤ ብድር ከሰጠኸው በጣም ብዙ ትርፍ እንደምታገኝ ይነግርሃል። ግብዣው ያጓጓ ይሆናል፤ ነገር ግን ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል? ተበዳሪው ንግዱ ተሳካም አልተሳካ ገንዘቡን ለመመለስ ይስማማል? ወይስ እዳውን የሚከፍለው ከተሳካለት ብቻ ነው? በሌላ አነጋገር ንግዱ ቢከስር ገንዘብህ ሳይመለስ እንዲቀር ፈቃደኛ ነህ? በተጨማሪም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- “ሰውየው ለምን ከግለሰቦች ብድር ይጠይቃል? ባንኮች ይህ የንግድ ሥራ አስተማማኝ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል?” አስቀድመህ ምን ችግር ሊከሰት እንደሚችል መመርመርህ የቀረበልህን ሐሳብ በሚገባ ለመገምገም ያስችልሃል።—ምሳሌ 13:16፤ 22:3
5. (ሀ) ኤርምያስ መሬት በገዛ ጊዜ ምን የጥበብ እርምጃ ወስዷል? (ለ) ማንኛውንም የንግድ ስምምነት ሕጋዊ በሆነ መንገድ በጽሑፍ ማስፈር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ነቢዩ ኤርምያስ ልክ እንደ እርሱ የይሖዋ አምላኪ ከነበረው የአጎቱ ልጅ መሬት በገዛ ጊዜ በምሥክሮች ፊት የሽያጩን ውል በጽሑፍ አስፍሮ ነበር። (ኤርምያስ 32:9-12) ዛሬም ቢሆን ብልህ ሰው፣ ከዘመዶቹና ከእምነት ወንድሞቹም ጋር ቢሆን በጽሑፍ የሰፈረ ሕጋዊ የንግድ ስምምነት ያደርጋል። a ዝርዝር ነገሮችን የያዘና በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ የጽሑፍ ስምምነት መኖሩ አለመግባባትን ለማስወገድ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን ለመጠበቅ ይረዳል። በተቃራኒው ስምምነቱ በጽሑፍ ካልሰፈረ በሽርክና በሚሠሩት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ለሚፈጠረው ችግር መባባስ አንደኛው መንስኤ ይሆናል። እንዲህ ያለው ችግር ሐዘንና የመረረ ጥልን አልፎ ተርፎም በመንፈሳዊ መድከምን ያስከትላል።
6. ከስግብግብነት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?
6 ከዚህም በላይ ከስግብግብነት መራቅ አለብን። (ሉቃስ 12:15) ብዙ ትርፍ አገኛለሁ የሚለው ተስፋ፣ አንድ ሰው አስተማማኝ ያልሆነ የንግድ ሥራ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እንዳያስተውል ዓይኑን ሊጋርድበት ይችላል። በይሖዋ አገልግሎት ውድ መብቶችን አግኝተው የነበሩ ክርስቲያኖችም ሳይቀሩ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል። የአምላክ ቃል “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ዕብራውያን 13:5) አንድ ክርስቲያን ስለቀረበለት የንግድ አጋጣሚ ሲያስብ ‘እንዲህ ባለው ንግድ ውስጥ መግባቴ የግድ አስፈላጊ ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ያተኮረ ያልተወሳሰበ ኑሮ መምራታችን ‘ከክፋት ሁሉ’ ይጠብቀናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-10
ያላገቡ ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ
7. (ሀ) በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ምን ፈተና ያጋጥማቸዋል? (ለ) የትዳር ጓደኛ ምርጫ ለይሖዋ ታማኝ ከመሆን ጋር ምን ግንኙነት አለው?
7 ማግባት እየፈለጉ ተስማሚ ተጓዳኝ ያላገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች አሉ። በአንዳንድ አገሮች ያለው ማኅበረሰብ ያላገቡ ሰዎች እንዲያገቡ ከፍተኛ ጫና ያደርግባቸዋል። ሆኖም የትዳር ጓደኛ ሊሆን የሚችል ተመሳሳይ እምነት ያለው ሰው የማግኘቱ አጋጣሚ ጠባብ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 13:12) እንደዚያም ሆኖ ክርስቲያኖች ጋብቻ “በጌታ” ብቻ መሆን እንዳለበት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መታዘዝ ለይሖዋ ታማኝ የመሆን ጉዳይ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ያላገቡ ክርስቲያኖች የሚደረግባቸውን ጫናም ሆነ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመቋቋም የማስተዋል ስሜታቸውን መጠበቅ አለባቸው።
8. ሱላማጢሷ ልጃገረድ ምን ግፊት ተደርጎባት ነበር? ዛሬ ያሉት ክርስቲያን ሴቶችስ ምን ተመሳሳይ ፈተና ያጋጥማቸዋል?
8 ንጉሥ ሰሎሞን፣ ሱላማጢስ ተብላ በተጠራች ተራ የገጠር ልጃገረድ ተማርኮ እንደነበር በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል። አንድ ወጣት ፍቅረኛ የነበራት ቢሆንም በሀብቱ፣ በክብሩና በግርማ ሞገሱ አባብሏታል። (ማሕልየ መሓልይ 1:9-11፤ 3:7-10፤ 6:8-10, 13) ክርስቲያን ከሆንሽ አንድ ሰው በማትፈልጊው መንገድ ዓይኑን ጥሎብሽ ይሆናል። ምናልባትም ይህ ሰው አብሮሽ የሚሠራ ወይም በመሥሪያ ቤቱ ሥልጣን ያለው ሊሆን ይችላል፣ ያሞግስሽ፣ መልካም ነገሮች ያደርግልሽና ከአንቺ ጋር የሚሆንበትን አጋጣሚ ይፈላልግ ይሆናል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች እንዳትታለይ ተጠንቀቂ። አንድ ሰው እንደዚህ ማድረጉ ሁልጊዜ አፍቅሮ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም ፈልጎ ነው ባያስብለውም በአብዛኛው ከዚህ የተለየ ምክንያት አይኖረውም። እንደ ሱላማጢሷ ልጃገረድ አንቺም “ቅጥር” ሁኚ። (ማሕልየ መሓልይ 8:4, 10) የሚያሳይሽን የፍቅር መግለጫዎች በጥብቅ ተቃወሚ። በመሥሪያ ቤቱ እንደተቀጠርሽ ለሥራ ባልደረቦችሽ የይሖዋ ምሥክር መሆንሽን መግለጽሽ ጥሩ ነው፤ እንዲሁም ባገኘሽው አጋጣሚ ሁሉ መሥክሪላቸው። እንዲህ ማድረግሽ ጥበቃ ይሆንልሻል።
9. ከማያውቁት ሰው ጋር በኢንተርኔት ወዳጅነት መመሥረት ምን አደጋ አለው? (በገጽ 25 ላይ ያለውንም ሣጥን ተመልከት።)
9 የትዳር ጓደኛ ፈላጊዎችን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ የኢንተርኔት ድረ ገጾች ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል። አንዳንዶች እነዚህ ድረ ገጾች፣ በሌላ በምንም መንገድ የማያገኟቸውን ሰዎች የሚተዋወቁባቸው ዘዴዎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከማያውቁት ሰው ጋር በጭፍን መወዳጀት ከባድ አደጋ አለው። በኢንተርኔት የሚነገረው ነገር እውነት ይሁን ውሸት ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። (መዝሙር 26:4) የይሖዋ አገልጋይ ነኝ የሚል ሁሉ በእርግጥ የይሖዋ አገልጋይ አይደለም። ከዚህም በላይ በኢንተርኔት የሚመሠረት ወዳጅነት በፍጥነት ሊጠናከር ይችላል፤ ይህ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታ እንዲዛባ ምክንያት ይሆናል። (ምሳሌ 28:26) ብዙም ከማያውቁት ሰው ጋር በኢንተርኔትም ሆነ በሌላ መንገድ የጠበቀ ግንኙነት መመሥረት ተገቢ አይደለም።—1 ቆሮንቶስ 15:33
10. ያላገቡ ክርስቲያኖችን እንዴት ማበረታታት እንችላለን?
10 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ‘እጅግ የሚራራ’ አምላክ ነው። (ያዕቆብ 5:11) በሁኔታዎች አስገዳጅነት ትዳር ያልመሠረቱ ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንዲቆርጡ እንደሚያደርጓቸው በሚገባ ያውቃል፤ ለታማኝነታቸው ከፍተኛ አድናቆት አለው። ሌሎቻችን እነዚህን ሰዎች እንዴት ማበረታታት እንችላለን? ለታዛዥነታቸውና ለሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አዘውትረን ልናመሰግናቸው ይገባል። (መሳፍንት 11:39, 40 NW) እንዲሁም የሚያንጹ ዝግጅቶች በምናደርግበት ጊዜ ልንጋብዛቸው እንችላለን። በቅርቡ እንዲህ አድርገሃል? በተጨማሪ መንፈሳዊ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁና እርሱን በማገልገል እንዲደሰቱ እንዲረዳቸው ይሖዋን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። ታማኝ ለሆኑት ለእነዚህ ሰዎች ከልብ በማሰብ ልክ እንደ ይሖዋ አድናቆት እንዳለን እናሳይ።—መዝሙር 37:28
የጤና እክል ሲያጋጥም
11. ከባድ የጤና ችግሮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ይፈጥራሉ?
11 በራሳችንም ሆነ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ከባድ የጤና ችግር ቢደርስ በጣም እናዝናለን። (ኢሳይያስ ) ቢሆንም ውጤታማ ሕክምና ለማግኘት በምንጥርበት ጊዜ የቅዱሳን ጽሑፎችን መመሪያ እንዳንጥስ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች ከደም መራቅ እንደሚገባ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በጥንቃቄ ያከብራሉ፤ እንዲሁም መናፍስታዊ ድርጊቶችን ከሚያካትት ምርመራ ወይም ሕክምና ይርቃሉ። ( 38:1-3የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ገላትያ 5:19-21) ነገር ግን የሕክምና እውቀት የሌላቸው ሰዎች የሕክምና አማራጮችን የመገምገሙ ጉዳይ ግራ ሊያጋባቸውና ሊከብዳቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ የማስተዋል ስሜታችንን ለመጠበቅ ምን ይረዳናል?
12. አንድ ክርስቲያን ስለ ሕክምና አማራጮች በሚያስብበት ጊዜ ሚዛኑን መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?
12 “አስተዋይ” የሆነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመመርመር “ርምጃውን ያስተውላል።” (ምሳሌ 14:15) የሐኪሞችና የሆስፒታሎች ቁጥር አነስተኛ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ መድኃኒትነት ባላቸው ዕፅዋት ከሚደረግ ባሕላዊ ሕክምና ውጪ ሌላ አማራጭ ላይኖር ይችላል። እንዲህ ያለውን ሕክምና ለማድረግ ካሰብን በሚያዝያ 15, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 26 እስከ 29 ላይ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት እንችላለን። b መጽሔቱ ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች በመጥቀስ ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ጉዳዮች ማጣራት ያስፈልገን ይሆናል:- የባሕል ሐኪሙ መናፍስታዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ይታወቃል? ሕክምናው የሚሰጠው ‘የበሽታና የሞት መንስዔ የአማልክት (ወይም የቀድሞ አባቶች መናፍስት) ቁጣ አሊያም ደግሞ ጠላቶች ማስጠንቆላቸው ነው’ በሚል እምነት ነው? መድኃኒት ሲዘጋጅ ወይም ሲሰጥ እንደ መሥዋዕት ማቅረብ፣ ድግምት አሊያም ደግሞ ሌላ መናፍስታዊ ሥርዓት ይከናወናል? (ዘዳግም 18:10-12) እንዲህ የመሰለ ምርምር ማድረጋችን “ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” የሚለውን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር በሥራ ለማዋል ይረዳናል። c (1 ተሰሎንቄ 5:21) እንዲሁም ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ያደርገናል።
13, 14. (ሀ) አካላዊ ጤንነታችንን በመንከባከብ ረገድ ምክንያታዊነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ከሌሎች ጋር ስለ ጤናም ሆነ ስለ ሕክምና በምንወያይበት ጊዜ ምክንያታዊ መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
13 አካላዊ ጤንነታችንን መንከባከብን ጨምሮ በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ ምክንያታዊ መሆን አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) ለጤንነታችን ሚዛናዊ ትኩረት በመስጠት ላገኘነው ውድ የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። የጤና እክል ሲያጋጥመን ለችግሩ ትኩረት መስጠት ይገባናል። ነገር ግን አምላክ ያዘጋጀው ‘ሕዝቦች የሚፈወሱበት’ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ሙሉ ጤና ማግኘት አይቻልም። (ራእይ 22:1, 2) ይበልጥ የሚያስፈልጉንን መንፈሳዊ ነገሮች ችላ እስክንል ድረስ ለአካላዊ ጤንነታችን እንዳንጨነቅ መጠንቀቅ አለብን።—ማቴዎስ 5:3፤ ፊልጵስዩስ 1:10
14 ከሌሎች ጋር ስለ ጤናም ሆነ ስለ ሕክምና በምንወያይበት ጊዜም ቢሆን ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆን ይገባናል። በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ትምህርት ለማግኘት በምንሰበሰብበት ጊዜ የጭውውታችን ዋነኛ ርዕስ የጤንነትና የሕክምና ጉዳይ መሆን የለበትም። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ሕክምናን የሚመለከት ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች፣ ኅሊናውንና ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ዝምድና ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልገዋል። ስለዚህ የእምነት ወንድማችን የራሳችንን አመለካከት እንዲቀበል ማስገደድ ወይም ኅሊናው የሚሰጠውን መመሪያ ችላ እንዲል ግፊት ማድረግ ፍቅር እንደሚጎድለን የሚያሳይ ይሆናል። የጎለመሱ የጉባኤውን አባላት ምክር መጠየቅ ቢቻልም እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን” ውሳኔ የማድረግን የኃላፊነት “ሸክም ሊሸከም” ይገባዋል፤ ምክንያቱም “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።”—ገላትያ 6:5፤ ሮሜ 14:12, 22, 23
ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ
15. ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ምን ያስከትሉብናል?
15 ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ታማኝ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችን እንኳ የሞኝነት ንግግር እንዲናገሩ ወይም ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲፈጽሙ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። (መክብብ 7:7) በርካታ ችግሮች የተፈራረቁበት ኢዮብ በተወሰነ መጠን ሚዛኑን በመሳቱ አስተሳሰቡ መስተካከል አስፈልጎት ነበር። (ኢዮብ 35:2, 3፤ 40:6-8) “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” የነበረ ቢሆንም በአንድ ወቅት ተቆጥቶ የችኮላ ንግግር ተናግሯል። (ዘኍልቍ 12:3፤ 20:7-12፤ መዝሙር 106:32, 33) ዳዊት፣ ንጉሥ ሳኦል ላይ ጥቃት ከማድረስ በመታቀብ አስደናቂ ራስን የመቆጣጠር ባሕርይ አሳይቷል፤ ሆኖም ናባል በዘለፈውና የላካቸውን ሰዎች ባመናጨቀ ጊዜ በመበሳጨቱ ምክንያት የማመዛዘን ችሎታው ተዛብቶ ነበር። ዳዊት ወደ አእምሮው የተመለሰውና አሳዛኝ ስህተት ከመፈጸም ለጥቂት የዳነው አቢግያ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባቷ ነው።—1 ሳሙኤል 24:2-7፤ 25:9-13, 32, 33
16. የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ የሚጠብቀን ምንድን ነው?
16 እኛም የማመዛዘን ችሎታችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም የሚያደርጉ ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ዳዊት እንዳደረገው ሌሎች የሚሰጡንን አስተያየት በቁም ነገር መመልከታችን የችኮላ እርምጃ ወስደን ወደ ኃጢአት እንዳናመራ ይረዳናል። (ምሳሌ 19:2) በተጨማሪም የአምላክ ቃል “ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ” በማለት ይመክረናል። (መዝሙር 4:4) በተቻለ መጠን እስከምንረጋጋ ድረስ እርምጃ ሳንወስድ ወይም ውሳኔ ሳናደርግ ብንቆይ ጥሩ ነው። (ምሳሌ 14:17, 29) ከልብ ወደ ይሖዋ ከጸለይን “ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ [ልባችንንና አሳባችንን] በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይህ ከአምላክ የሚገኝ ሰላም ያረጋጋናል፤ እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
17. የማስተዋል ስሜታችንን ለመጠበቅ በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?
17 መጥፎ ሁኔታዎችን ለማስወገድና በጥበብ ለመመላለስ የቻልነውን ያህል ብንጥርም ሁላችንም እንሳሳታለን። (ያዕቆብ 3:2) ምናልባትም ምንም ሳይታወቀን ጥፋት የሚያስከትልብንን የኃጢአት እርምጃ እንወስድ ይሆናል። (መዝሙር 19:12, 13) ከዚህም በላይ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከይሖዋ ተነጥለን የራሳችንን አካሄድ የመምራት ችሎታም ሆነ መብት የለንም። (ኤርምያስ 10:23) በመሆኑም ይሖዋ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” ብሎ ስላረጋገጠልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (መዝሙር 32:8) አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የንግድ ስምምነትን በጽሑፍ ስለ ማስፈር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት:- መጠበቂያ ግንብ ነሐሴ 1, 1997 ገጽ 30, 31፣ ኅዳር 15, 1986 ገጽ 16, 17 (እንግሊዝኛ) ወይም 11-107 ገጽ 14, 15 (አማርኛ)፣ ንቁ! የካቲት 8, 1983 ከገጽ 13-15 (እንግሊዝኛ)።
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የታኅሣሥ 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ ከ19-22 ተመልከት።
c ይህ ሐሳብ አወዛጋቢ የሆኑ አማራጭ ሕክምናዎችን የማድረግ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ጭምር ይጠቅማል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• አንድ የንግድ ሥራ እንድንጀምር ጥያቄ ሲቀርብልን
• የትዳር ጓደኛ ስንፈልግ
• የጤና እክል ሲያጋጥመን
• ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ
የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እምነት ሊጣልበት ይችላል?
ለትዳር ፈላጊዎች ድረ ገጾችን የሚያዘጋጁ ሰዎች ራሳቸውን ከኃላፊነት ነጻ ለማድረግ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ይሰጣሉ:-
“የተቻለንን ያህል ጥረት ብናደርግም እንኳ እዚህ ላይ የግለሰቡ እውነተኛ ማንነት በትክክል ተገልጿል ብለን ዋስትና መስጠት አንችልም።”
“በድረ ገጹ ውስጥ ያለው ማንኛውም መረጃ ትክክል፣ የተሟላ ወይም ጠቃሚ ነው የሚል ዋስትና አንሰጥም።”
“[በዚህ] ድረ ገጽ ውስጥ የሚገኙት አስተያየቶች፣ ምክሮች፣ ሐሳቦች፣ ግብዣዎች ወይም መረጃዎች አሊያም የድረ ገጹ ሌሎች ገጽታዎች በራሳቸው በግለሰቦቹ የተገለጹ በመሆናቸው . . . ሙሉ እምነት የሚጣልባቸው ላይሆኑ ይችላሉ።”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሴቶች ሱላማጢስ የተባለችውን ልጃገረድ መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ”