ከትዳር ጓደኛህ ጋር ምን ያህል በግልጽ ትነጋገራለህ?
ከትዳር ጓደኛህ ጋር ምን ያህል በግልጽ ትነጋገራለህ?
“የስድሳ ዓመት አረጋዊ የጻፉት የፍቅር ደብዳቤ።” ከጥቂት ዓመታት በፊት በጃፓን የሚገኝ አንድ ባንክ ያካሄደው ውድድር ጭብጡ ይህ ነበር። በጃፓን አገር በ50ዎቹና በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን “እውነተኛ ስሜት” እንዲገልጹ ተበረታተው ነበር። አንድ ተወዳዳሪ ለሚስቱ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስታነቢው ትስቂ ይሆናል፣ ሆኖም ካልነገርኩሽ እቆጫለሁ፤ የሚሰማኝን ልነግርሽ ፈልጌ ነው:- ስላገባሽኝ በጣም አመሰግንሻለሁ።”
በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙትን አገሮች ጨምሮ በብዙ ባሕሎች ውስጣዊ ስሜትን በግልጽ አውጥቶ መናገር ይወገዛል። ሆኖም በዚህ የፍቅር ደብዳቤ ውድድር ላይ ከ15,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተሳትፈው ነበር። ይህ የፍቅር ደብዳቤ ውድድር በጣም ተወዳጅ በመሆኑ ምክንያት ሌላ ውድድር እንዲዘጋጅ ከመደረጉም በላይ በደብዳቤዎቹ ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ መጻሕፍት ታትመዋል። ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች ለሚወዱት የትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ውስጣዊ ስሜት ለመግለጽ በጣም እንደሚፈልጉ ያመለክታል። ሌሎች ግን ስሜታቸውን ለትዳር ጓደኛቸው ከመግለጽ ይቆጠባሉ። ለምን? ምናልባት ምን እንደሚሰማቸው ለሌሎች ሰዎች፣ ለምሳሌ ለትዳር ጓደኛቸው መናገር ከፍተኛ ጥረትና ችሎታ ስለሚጠይቅባቸው ሊሆን ይችላል።
ጡረታ መውጣትን አስመልክተው መጽሐፍ ያዘጋጁ ሂቶሺ ካቶ የተባሉ አንድ ሰው እንደተናገሩት በጃፓን ከሚኖሩ በዕድሜ የገፉ ባለትዳሮች መካከል፣ የፍቺ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚነሳሱት በአብዛኛው ሚስቶች ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ ለብዙ ዓመታት ታምቆ የተያዘ ሥር የሰደደ ቅሬታ እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም “ባልና ሚስቱ ችግር በሚነሳበት ወቅት ስሜታቸውን አውጥተው አለመነጋገራቸውም ሌላው ምክንያት ነው” ብለዋል።
አንዳንድ ጊዜ ሚስቶች መፋታት የሚፈልጉት ባሎቻቸው ጡረታ እንደወጡ ሲሆን ይህ ደግሞ ለባልየው ያልጠበቀው ነገር ይሆንበታል። ባልና ሚስቱ ለብዙ ዓመታት
ስሜታቸውን አውጥተው ሳይነጋገሩ ቆይተው ሊሆን ይችላል። ስሜታቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም እንኳ ውይይቱን አስደሳች ለማድረግ አልቻሉ ይሆናል። በሚነጋገሩበት ጊዜ ይበልጥ ከመቀራረብ ይልቅ ሁልጊዜ ይጨቃጨቃሉ።የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ስሜቶቻቸውን አስደሳች በሆነ መልኩ መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው? በጣም ጠቃሚ የሆኑት ምክሮች የሚገኙት አንድ የጋብቻ አማካሪ በቅርቡ ባወጣው መጽሐፍ ውስጥ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት ተጠብቆ በኖረ ጥንታዊ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሆነ ስታውቅ ትገረም ይሆናል።