የሰርዴሱ ሜለቶ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቃ ነበር?
የሰርዴሱ ሜለቶ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቃ ነበር?
እውነተኛ ክርስቲያኖች በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት በየዓመቱ ኒሳን 14 የጌታ እራትን ያከብራሉ። እንዲህ በማድረጋቸውም ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። ኢየሱስ የሞቱ መታሰቢያ የሆነውን ይህን በዓል ያቋቋመው ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የማለፍን በዓል አክብሮ እንደጨረሰ ሲሆን ሕይወቱ ያለፈውም በዚሁ ቀን ነበር።—ሉቃስ 22:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:23-28
በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ አንዳንዶች የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ቀንና የአከባበሩን ሁኔታ መቀየር ጀመሩ። በትንሿ እስያ ግን በዓሉ ኢየሱስ በሞተበት ትክክለኛ ቀን መከበሩን ቀጥሎ ነበር። ይሁንና አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “በሮምና በእስክንድርያ ኢየሱስ ከሞተበት ቀን በኋላ ባለው እሁድ ላይ ትንሣኤውን የማክበር ልማድ” የነበራቸው ሲሆን በዓሉንም የትንሣኤው የማለፍ በዓል ብለው ይጠሩት ነበር። ኩዋርቶዴሲማንስ (የአሥራ አራተኛ ቀን አክባሪዎች) ተብሎ የሚታወቅ ቡድን አባላት የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ኒሳን 14 እንዲከበር ለማድረግ የቻሉትን ያህል ጥረዋል። የሰርዴሱ ሜለቶም ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። ሜለቶ ማን ነው? ለዚህና ለሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ጥብቅና የቆመውስ በምን መልኩ ነበር?
‘ታላቅ ብርሃን አብሪ’
የቂሳሪያው ዩሲቢየስ ኤክለሲያስቲካል ሂስትሪ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንደገለጸው፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማብቂያ አካባቢ የኤፌሶን ነዋሪ የሆነው ፖሊክራተዝ ‘ወንጌሉ እንደሚለውና የክርስትና ሕግ እንደሚያዘው በዓሉ መከበር ያለበት በማለፍ በዓል ላይ ማለትም በአሥራ አራተኛው ቀን መሆን ይኖርበታል፤ ቀኑ ሊፋለስ አይገባውም’ ሲል ወደ ሮም ደብዳቤ ልኮ ነበር። በዚህ ደብዳቤ መሠረት በልድያ ይኖር የነበረው የሰርዴሱ ጳጳስ ሜለቶ፣ በዓሉ ኒሳን 14 መከበሩን ከሚደግፉት መካከል ነበር። ደብዳቤው አክሎም፣ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ሜለቶን ‘በሞት ካንቀላፉት ታላላቅ ብርሃን አብሪዎች’ መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ይገልጻል። ፖሊክራተዝ እንዳለው ከሆነ ሜለቶ ያላገባ፣ “ለመንፈስ ቅዱስ ያደረ እንዲሁም በትንሣኤ ሲነሳ ወደ ሰማይ እንደሚጠራ በመጠባበቅ በሰርዴስ ምድር የተቀበረ ሰው ነው።” ይህም ሲባል ሜለቶ ራእይ 20:1-6
ክርስቶስ እስኪመለስ ድረስ ትንሣኤ አይኖርም ብለው ከሚያምኑት ወገን ነበር ማለት ነው።—ከዚህ አንጻር ሲታይ ሜለቶ ደፋርና ቆራጥ ሰው መሆን ይኖርበታል። ለክርስቲያኖች መከላከያ ለማቅረብ ሲል የጻፈው አፖሎጂ የተባለው መጽሐፉ ከ161 እስከ 180 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮማ ንጉሠ ነገሥት ለነበረው ማርከስ ኦሪሊየስ የተላከ መልእክትን የያዘ የመጀመሪያ ጽሑፉ ነበር። ሜለቶ ለክርስትና ጥብቅና ከመቆም እንዲሁም ክፉና ስግብግብ የሆኑ ሰዎችን ከማውገዝ ወደ ኋላ አላለም። በዚያ ወቅት ክፉና ስግብግብ የሆኑ ሰዎች የክርስቲያኖችን ንብረት ለመዝረፍ ሲሉ የንጉሠ ነገሥቱን ሕግ ከለላ በማድረግ ያሳድዷቸውና በሐሰት ይወነጅሏቸው ነበር።
ሜለቶ፣ ለንጉሠ ነገሥቱ እንደሚከተለው ሲል በድፍረት ጽፎላቸዋል:- “የምንጠይቅዎት አንድ ነገር ብቻ ነው። ለችግሩ ምክንያት የሆኑትን ሰዎች (የክርስቲያኖችን) ሁኔታ እርስዎ ራስዎ ይመርምሩና ሞትና ቅጣት አሊያም ጥበቃና መከላከያ ይገባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ በጽድቅ ይፍረዱ። ሆኖም በአረማዊ ጠላቶቻችን ላይ እንኳ ሊሆን የማይገባው ይህ ድንጋጌና አዲስ አዋጅ የወጣው ከእርስዎ ዘንድ ካልሆነ አሳዳጆቻችን ሕግ ጥሰው ሲዘርፉን ችላ ብለው እንዳያዩ አጥብቀን እንለምንዎታለን።”
ሜለቶ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም ለክርስትና ጥብቅና ቆሟል
ሜለቶ ቅዱሳን ጽሑፎችን የማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ሁሉንም የጽሑፍ ሥራዎቹን ማግኘት ባይቻልም ከጽሑፎቹ ውስጥ የአንዳንዶቹ ርዕሶች ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ይሰጥ እንደነበረ ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መካከል ኦን ክርስቺያን ላይፍ ኤንድ ዘ ፕሮፌትስ (የክርስትና ሕይወትና ነቢያት)፣ ኦን ዘ ፌዝ ኦቭ ማን (የሰው ልጅ እምነት)፣ ኦን ክርኤሽን (ፍጥረት)፣ ኦን ባፕቲዝም ኤንድ ትሩዝ ኤንድ ፌዝ ኤንድ ክራይስትስ በርዝ (ጥምቀት፣ እውነት፣ እምነትና የክርስቶስ ልደት)፣ ኦን ሆስፒታልቲ (እንግዳ ተቀባይነት)፣ ዘ ኪ (የቅዱሳን ጽሑፎች መፍቻ) እንዲሁም ኦን ዘ ዴቭል ኤንድ ዚ አፖካሊፕስ ኦቭ ጆን (ዲያብሎስና የዮሐንስ ራእይ) የሚሉት ይገኙበታል።
ሜለቶ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛ ብዛት ለማወቅ ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደተጠቀሱ ቦታዎች ተጉዟል። ይህን አስመልክቶም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወደ ምሥራቅ ሄጄ በነበረበት ወቅት እነዚህ
ነገሮች በተሰበኩበትና በተግባር በዋሉበት አካባቢ ሆኜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ጠንቅቄ ከተማርኩና እውነታውን ከመዘገብኩ በኋላ ልኬልሃለሁ።” ይህ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር የነህምያና የአስቴር መጻሕፍትን ባያካትትም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ካዘጋጇቸው ተቀባይነት ያገኙ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር መካከል ጥንታዊው ነው።በጥናቱ ላይ ሜለቶ ስለ ኢየሱስ ትንቢት የተነገረባቸውን ጥቅሶች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በመልቀም በቅደም ተከተላቸው ጽፏቸዋል። ኤክስትራክትስ የተሰኘው የሜለቶ መጽሐፍ ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው መሲሕ እንደነበረና የሙሴ ሕግም ሆነ ነቢያት የክርስቶስን ማንነት አስቀድመው ማመልከታቸውን ይገልጻል።
ሜለቶ ለቤዛው ጥብቅና ቆሟል
በታናሿ እስያ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር። ሜለቶ በሚኖርበት በሰርዴስ ይገኙ የነበሩት አይሁዳውያን የዕብራውያንን የማለፍ በዓል የሚያከብሩት ኒሳን 14 ነበር። ሜለቶ የማለፍ በዓል በሕጉ ውስጥ ተቀባይነት እንዳለውና የክርስቲያኖች የጌታ እራት መከበር ያለበት ኒሳን 14 መሆኑን ለማስረዳት ሲል የማለፍ በዓል የተሰኘ ድርሰት ጽፏል።
ሜለቶ ዘፀአት ምዕራፍ 12ን አስመልክቶ አስተያየቱን ከሰነዘረና የማለፍ በዓል ለክርስቶስ መሥዋዕት ጥላ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ክርስቲያኖች የማለፍ በዓልን ማክበራቸው ትርጉም እንደሌለው አስረድቷል። ምክንያቱም አምላክ የሙሴን ሕግ አስወግዶታል። ቀጥሎም የክርስቶስ መሥዋዕት ለምን እንዳስፈለገ ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- አምላክ አዳምን በደስታ እንዲኖር በገነት ውስጥ አስቀመጠው። ሆኖም የመጀመሪያው ሰው መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበላ የተሰጠውን ትእዛዝ ተላለፈ። ስለሆነም ቤዛው አስፈለገ።
ከዚህም በተጨማሪ ሜለቶ፣ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑ የሰው ልጆች ቤዛ በመሆን ከኃጢአትና ከሞት ነጻ እንዲያወጣቸው ወደ ምድር መላኩንና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞቱን አብራርቷል። የሚገርመው፣ ሜለቶ ኢየሱስ የተሰቀለበትን እንጨት ለማመልከት የተጠቀመው “አጣና” የሚል ትርጉም ባለው ዛይሎን የተባለ ግሪክኛ ቃል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 5:30፤ 10:39፤ 13:29
ሜለቶ ከትንሿ እስያ ውጪ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድም በሰፊው ይታወቅ ነበር። ሥራዎቹ በተርቱሊያን፣ በእስክንድርያው ክሌመንትና በኦሪጀን ዘንድ ታዋቂ ነበሩ። ይሁንና የታሪክ ምሑር የሆኑት ራናይሮ ካንታላሚሳ እንደሚከተለው ይላሉ:- “ሜለቶ እየተዳከመና የጽሑፍ ሥራዎቹም ቀስ በቀስ እየጠፉ የሄዱት የማለፍን በዓል እሁድ ዕለት የማክበሩ ልማድ ድል ሲጎናጸፍና ኩዋርቶዴሲማንስ እንደ መናፍቅ መታየት ሲጀምሩ ነው።” ውሎ አድሮ የሜለቶ የጽሑፍ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ጠፉ።
የክህደት ትምህርት ተጽዕኖ አሳድሮበት ነበር?
ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ቀደም ሲል በትንቢት የተነገረለት ክህደት ወደ እውነተኛው ክርስትና መስረግ ጀመረ። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) በግልጽ እንደሚታየው ይህ በሜለቶ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። በጽሑፍ ሥራዎቹ ላይ የሚታየው ውስብስብ የአጻጻፍ ስልት የግሪክ ፍልስፍና እንዲሁም የሮማውያኑ ዓለም ተጽዕኖ ተንጸባርቆባቸዋል። ምናልባትም ሜለቶ ክርስትናን “ፍልስፍናችን” ሲል የጠራው ለዚህ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ስመ ክርስትና ከሮም ግዛት ጋር መዋሃዱን “የስኬት . . . ዓብይ ማስረጃ” እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል።
በእርግጥም ሜለቶ ሐዋርያው ጳውሎስ“በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ልብ አላለውም። በመሆኑም ምንም እንኳ ሜለቶ በተወሰነ ደረጃ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅና የቆመ ቢሆንም በብዙ መልኩ ግን እውነቱን ችላ ብሎታል።—ቈላስይስ 2:8
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ኒሳን 14 የጌታ እራት በዓልን አቋቋመ