“ምርጥ መደምደሚያ ሆኖልኛል”
“ምርጥ መደምደሚያ ሆኖልኛል”
በስፔን የሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት እውነተኛ አንድነት፣ እንከን የማይወጣለት ሐቀኝነትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ጽኑ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል።” በአምላክ እንደማያምን የሚናገረው ይህ መምህር እንዲህ ያለ አስተያየት እንዲሰጥ ያነሳሳው ምንድን ነው?
ለዚህ አስተያየት መነሻ የሆነው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኖኤሚ የጻፈችው ድርሰት ነው። የዚህ ድርሰት ውጤት ደግሞ በትምህርት ቤቱ ከሚሰጠው የማጠቃለያ ፈተና ጋር አብሮ ይወሰድ ነበር። በዚህ ጊዜ ኖኤሚ “በናዚ አገዛዝ ወቅት የነበሩት ባለ ሦስት ማዕዘን የወይን ጠጅ ምልክቶች” በሚል ርዕስ ድርሰት ለማዘጋጀት ወሰነች።
ይህን ርዕስ የመረጠችበት ምክንያት ምንድን ነው? ኖኤሚ ስታብራራ እንዲህ ብላለች:- “ሥራዬን ለአንድ አስተማሪ ማሳየቴ ስለማይቀር አጋጣሚውን ተጠቅሜ መመሥከር እንደምችል ተሰማኝ። በጀርመን አገር በናዚ ግዛት ሥር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምን ያህል እንደጸኑ የሚገልጸው ታሪክ በጥልቅ ነክቶኝ ነበር። ሌሎችም ይህን ታሪክ ቢያውቁ ልባቸው እንደሚነካ እምነት ነበረኝ።”
የኖኤሚ ሥራ እርሷ ከገመተችው በላይ የብዙ ሰዎችን ልብ ነክቷል። የጻፈችው ድርሰት ጥቅምት 5, 2002 በሳይንስና በኅብረተሰብ መስክ በተደረገ ብሔራዊ ውድድር ላይ ሽልማት አገኘ። በውድድሩ ላይ የቀረቡትን ሽልማቶች ያበረከተው ከታወቁ የስፔን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 20 ፕሮፌሰሮችን ያቀፈ የዳኞች ቡድን ነበር።
ኖኤሚ ሽልማቷን የተረከበችው ከስፔን የትምህርት ሚኒስቴሯ ከፒላር ዜል ካስቲዮ ነበር። ኖኤሚ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል የሚለውን የቪዲዮ ፊልም ለሚኒስቴሯ የሰጠቻቸው ሲሆን እርሳቸውም ስጦታውን በደስታ ተቀብለዋል።
የኖኤሚ የትውልድ ከተማ በሆነችው በማንሬሳ የሚታተም ጋዜጣ ይህቺ ወጣት በትምህርቷ ያገኘችውን አስደሳች ውጤት የዘገበ ከመሆኑም ሌላ የድርሰቷን ይዘት ከልሷል። በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቷ ዳይሬክተር፣ ትምህርት ቤቱ 75ኛ ዓመቱን ሲያከብር በሚያደርገው ዝግጅት ላይ የኖኤሚን ሥራ ለማካተት ስለፈለጉ የድርሰቷ አንድ ቅጂ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ኖኤሚ፣ “እንዲህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ ምርጥ መደምደሚያ ሆኖልኛል” ስትል ተናግራለች። “አስተማሪዬ ሚስተር ሆርሃ ቶማስ ካሎት በሪፖርቴ ላይ የጻፈውን መግቢያ ሳነብ ከመጠን በላይ ተደሰትኩ።”
የመግቢያው ሐሳብ እንዲህ ይላል:- “‘በአምላክ መኖር አላምንም። ሆኖም አምላኪዎቹ እውነተኛ “የጎረቤት ፍቅር” እንዲኖራቸው የሚያነሳሳቸው፣ ከፍተኛ ኃይል ያለው አካል መኖሩን ማመን ብችል ደስ ይለኝ ነበር።’”