ፍጹም ለውጥ ያመጣ ጉብኝት
ፍጹም ለውጥ ያመጣ ጉብኝት
“አምላክ ስለላከልኝ ሁለት ‘መላእክት’ ለቤተሰቤ ለመንገር ጓጉቼ ነበር።” ይህን አስተያየት የጻፉት ሁለት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ያነጋገሯቸው አንድ አረጋዊ ናቸው። እኚህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮቹን ከማግኘታቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለ45 ዓመታት አብረዋቸው የኖሩትን የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት እጅግ አዝነው ነበር። ትልልቅ ልጆቻቸው ያጽናኗቸው ቢሆንም የሚኖሩበት ስፍራ እርሳቸው ካሉበት ቦታ የራቀ ነው። ደግሞም ከጓደኞቻቸውም ሆነ ከጎረቤቶቻቸው መካከል ማንም ሰው መጥቶ አልጠየቃቸውም።
እኚህ ሰው ሁለቱ ወጣቶች ሲያነጋግሯቸው “እኔና አምላክ ከአሁን በኋላ ንግግር የለንም” በማለት መለሱላቸው። ያም ሆኖ ወጣቶቹ ሰውየው ባጋጠማቸው ሁኔታ አብረዋቸው ከማዘናቸውም በላይ እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው? የሚል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትራክት ሰጧቸው። ሰውየው ትራክቱን ማታውኑ አንብበው ተጽናኑ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነዚህ ሁለት ክርስቲያን ሴቶች ወደ ሰውየው ቤት ተመልሰው መጡ። ባለፈው ጊዜ ሲጎበኟቸው ምን ያህል አዝነው እንደነበር መመልከታቸውን ከገለጹላቸው በኋላ እንዴት እንደሆኑ ለመጠየቅ መምጣታቸውን ነገሯቸው። ሰውየው በኋላ ላይ ሲጽፉ “እነዚህ ሁለት እንግዳ ሰዎች ስለ እኔ ማሰባቸውና ስለ ደኅንነቴ መጨነቃቸው በጣም አስደንቆኛል” ብለዋል። ሴቶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ በነገሯቸው ሐሳቦችም ማበረታቻ አገኙ። ከዚያም እነዚህ ወጣቶች ተመልሰው እንደሚመጡ ነገሯቸው። ሰውየው በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ከላይ የሰፈረውን አስተያየት ጽፈው በአቅራቢያቸው ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ለመላክ ተነሳሱ።
እኚህ ሰው አንደኛው ልጃቸው ወዳለበት አካባቢ ከመሄዳቸው በፊት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሲሆን የአንደኛዋ ወጣት ቤተሰብ ደግሞ ምግብ አዘጋጅቶ ጋብዟቸው ነበር። እርሳቸውም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይህን አካባቢ ለቅቄ ልሄድ ነው። ያም ሆኖ እነዚያ ወጣቶችና ቤተ ክርስቲያናችሁ ሁልጊዜም ቢሆን ከልቤ አይጠፉም፤ ደግሞም በጸሎቴ አስታውሳችኋለሁ። አዎን፣ አሁን በደንብ እጸልያለሁ። ፍጹም ተለውጫለሁ። ለዚህ ለውጥ ትልቅ ሚና የተጫወቱት እነዚያ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም ሁልጊዜም ሳመሰግናቸው እኖራለሁ።”