ሰብዓዊ ክብር—ብዙውን ጊዜ የሚጣስ መብት
ሰብዓዊ ክብር—ብዙውን ጊዜ የሚጣስ መብት
“በካምፕ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥመው እያንዳንዱ ነገር የሚያዋርድ ብሎም ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነው።”—ማግዳሌና ኩሰሮ ሮይተር፣ ከናዚ የማጎሪያ ካምፕ የተረፉ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አሰቃቂ ግፍ እንደተፈጸመ ባይካድም ይህ ድርጊት በሰብዓዊ ክብር ላይ የደረሰ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው ጥቃት አልነበረም። ያለፉትን ዘመናትም ሆነ አሁን ያለንበትን ጊዜ ብንመረምር የምንደርስበት መደምደሚያ ግልጽ ነው:- ብዙዎች “የሚያዋርድ ብሎም ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ” ግፍ ለዘመናት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የሰዎችን ክብር የሚነኩ ሁኔታዎች በሰው ዘር ታሪክ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው ባለፉት የጭካኔ ድርጊቶች ብቻ ተወስነው አልቀሩም። ሰብዓዊ ክብር በሌሎች በረቀቁ መንገዶችም ሲጣስ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ በመልኩ ወይም በቁመናው ምክንያት የሚፌዝበትን ልጅ አሊያም “የተለየ” ባሕል ስላለው መዘባበቻ የሆነን ስደተኛ እንዲሁም በዜግነቱ ወይም በቆዳው ቀለም ምክንያት መድሎ የሚደረግበትን ግለሰብ አስብ። ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት ሰዎች ምናልባት እንደ ጨዋታ አድርገው ይቆጥሩት ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የችግሩ ሰለባዎች የሚደርስባቸው ሥቃይ እንዲሁም ውርደት የሚያስቅ አይደለም።—ምሳሌ 26:18, 19
ሰብዓዊ ክብር ምንድን ነው?
አንድ መዝገበ ቃላት ክብር የሚለውን ቃል ‘ዋጋ ያለው፣ ላቅ ያለ ወይም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው’ በማለት ይፈታዋል። ስለዚህ ሰብዓዊ ክብር ለራሳችን ያለንን አመለካከትም ሆነ ሌሎች ለእኛ ያላቸውን ግምት ያጠቃልላል። ስለ ራሳችን ባለን ግምት
ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮች ቢኖሩም ሌሎች እኛን የሚያዩበት ወይም የሚይዙበት መንገድ ስለ ማንነታችን ያለንን አመለካከት በእጅጉ ይነካዋል።ይነስም ይብዛ ድሃ፣ ረዳት የለሽና አቅመ ደካማ የሌለበት ማኅበረሰብ የለም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ መገኘቱ ብቻ ለራሱ ያለውን አክብሮት እንዲያጣ አያደርገውም። ግለሰቡ ለራሱ ጥሩ ግምት እንዳይኖረው የሚያደርገው ሌሎች ለእርሱ ያላቸው ስሜትና አመለካከት ነው። በጣም የሚያሳዝነው ግን ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚነፈጋቸው ወይም ሰብዓዊ ክብራቸው የሚረገጠው አስቸጋሪ ሕይወት የሚገፉ ሰዎች ናቸው። አረጋውያን፣ ድሆች፣ የአእምሮ ሕመምተኞች ወይም የአካል ጉዳተኞች “የማትረባ፣” “ዋጋ ቢስ” እና “ወራዳ” እየተባሉ ሲዘለፉ መስማት በጣም የተለመደ ነው።
ሰዎች የሌላውን ክብር የሚያዋርድ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? የሰው ልጆች ክብር አግኝተው መሠረታዊ መብታቸው የሚጠበቅበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን አጥጋቢ መልስ ይዟል።