ይሖዋ የኑሮ ውጣ ውረዶችን እንድቋቋም ረድቶኛል
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ የኑሮ ውጣ ውረዶችን እንድቋቋም ረድቶኛል
ዴል ኧርዊን እንደተናገረው
“ስምንት ልጆች በቂ ናቸው! አራቱ መንትዮች መሆናቸው ችግሩን እጥፍ ያደርገዋል።” በአራት ሴት ልጆቻችን ላይ አራት መንታ ልጆች ሲጨመሩ በአካባቢያችን የሚታተም አንድ ጋዜጣ በመጀመሪያ ገጹ ላይ እንዲህ የሚል ርዕስ ይዞ ወጣ። ወጣት ሳለሁ ልጅ መውለድ ይቅርና ሚስት የማግባት ሐሳብ እንኳ አልነበረኝም። አሁን ግን የስምንት ልጆች አባት ሆንኩ!
በ1934 መሪባ በተባለች የአውስትራሊያ ከተማ ውስጥ ተወለድኩ። ከቤታችን ሦስት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነበርኩ። በኋላ ላይ ቤተሰባችን ወደ ብሪስባን ተዛወረ። እናቴም እዚያ በሚገኘው የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ታስተምር ነበር።
የአካባቢያችን ጋዜጦች በ1938 መጀመሪያ ላይ፣ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠራው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ወደ አውስትራሊያ እንዳይገባ ሊከለከል እንደሚችል ዘገቡ። እማዬም ጋዜጣው ከወጣ በኋላ ቤታችን የመጣችውን የይሖዋ ምሥክር “ለምን ይከለክሉታል?” ስትል ጠየቀቻት። የይሖዋ ምሥክሯም “ኢየሱስ፣ ሰዎች ተከታዮቹን እንደሚያሳድዷቸው ተናግሮ የለም እንዴ?” ስትል መለሰችላት። ከዚያም እማዬ በእውነተኛና በሐሰተኛ ሃይማኖት መካከል ያሉትን በርካታ ልዩነቶች የሚተነትን ኪዩር የተባለ ቡክሌት ወሰደች። a እማዬ የቡክሌቱ ሐሳብ ስለማረካት በቀጣዩ እሁድ ልጆቿን ይዛ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ሄደች። መጀመሪያ ላይ አባቴ በጣም ይቃወም ነበር፤ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ይጽፍና ለወንድሞች እንድታደርስለት ለእናቴ ይሰጣት ነበር። ከወንድሞችም አንዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ያዘጋጅና ለአባቴ ይልክለታል።
አንድ እሁድ፣ አባቴ የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት እንዳላረካው ለመናገር አብሮን ወደ ስብሰባ ሄደ። ይሁንና አባዬ በጊዜው ጉባኤውን ሲጎበኝ ከነበረው ተጓዥ የበላይ
ተመልካች ጋር ከተወያየ በኋላ አመለካከቱ የተቀየረ ከመሆኑም በላይ በአካባቢያችን ያሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በየሳምንቱ ቤታችን እየመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉም ፈቀደ።ወላጆቼ መስከረም 1938 ተጠመቁ። እኔ፣ ወንድሜና እህቴ ደግሞ ሲድኒ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ በሚገኘው ሃርግሬቭ ፓርክ ውስጥ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ታኅሣሥ 1941 ተጠመቅን። በዚህ ወቅት ሰባት ዓመቴ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከወላጆቼ ጋር በመሆን አዘውትሬ በመስክ አገልግሎት እካፈል ነበር። በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮቹ ተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻዎች ይዘው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የተቀዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለሰዎች ያሰሙ ነበር።
በርት ሆርተን የተባለው ወንድም እስከ ዛሬ ድረስ ከአእምሮዬ አይጠፋም። በርት ጣሪያው ላይ ትልቅ ድምፅ ማጉያ የተገጠመለት መኪና ነበረው። ከበርት ጋር መሥራት በተለይ በእኔ ዕድሜ ላለ ትንሽ ልጅ አስደሳች ነበር። ለምሳሌ፣ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆነን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ስናጫውት ብዙ ጊዜ የፖሊስ መኪና ሲመጣ እንመለከታለን። በርት የድምፅ መሣሪያውን ቶሎ ብሎ ያጠፋና ራቅ ወዳለ ሌላ ቦታ እንሄዳለን፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ ሸክላ ይከፍታል። ከበርትም ሆነ እንደ በርት ካሉ ታማኝና ደፋር ወንድሞች፣ በይሖዋ ላይ ስለ መታመንና ድፍረት ስለ ማሳየት ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ።—ማቴዎስ 10:16
አሥራ ሁለት ዓመት ከሆነኝ በኋላ ብቻዬን ከትምህርት ቤት ስመለስ የመመሥከር ልማድ ነበረኝ። አንድ ቀን አድስሄድ ተብሎ ከሚጠራ አንድ ቤተሰብ ጋር ተገናኘሁ። ከጊዜ በኋላም ባልና ሚስቱ፣ ስምንት ልጆቻቸውና ብዙ የልጅ ልጆቻቸው እውነትን ተቀብለዋል። ልጅ ብሆንም እንኳ ለዚህ ጥሩ ቤተሰብ እውነትን ለመንገር ስላበቃኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።—ማቴዎስ 21:16
በወጣትነቴ ያገኘኋቸው የአገልግሎት መብቶች
አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ከዚያም በሜይትላንድ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ ተመደብኩ። በ1956 ደግሞ ሲድኒ በሚገኘው የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ። በወቅቱ ከነበርነው 20 ቤቴላውያን መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። ከእነርሱ ጋር መሥራት ትልቅ መብት ነበር!—ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 1:6፤ 5:10
ጁዲ ሄልበርግ ከተባለች በአቅኚነት ከምታገለግል ቆንጆ እህት ጋር በመተዋወቄ ነጠላ ሆኜ ለመቀጠል ባደረግሁት ውሳኔ መጽናት አልቻልኩም። ጁዲ በአንድ ትልቅ ፕሮጀክት ላይ እንድትረዳኝ ተብሎ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በጊዜያዊነት እንድታገለግል ተጠርታ ነበር። ከጁዲ ጋር ስለተዋደድን ከሁለት ዓመት በኋላ ተጋባን። ከተጋባን በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ወንድሞችን ለማበረታታት ሲባል በሳምንት አንድ ጉባኤ መጎብኘትን የሚጠይቅ ነው።
በ1960 የመጀመሪያ ልጃችን ኪም ተወለደች። በአሁኑ ጊዜ በወረዳ ሥራ ላይ ሆነው ልጅ የሚወልዱ ባልና ሚስቶች አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎታቸውን አቋርጠው በአንድ ቦታ ላይ ተረጋግተው ይኖራሉ። የሚደንቀው ግን ጉባኤዎችን መጎብኘታችንን እንድንቀጥል ግብዣ ቀረበልን። በደንብ ከጸለይንበት በኋላ የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን። ከዚያም በቀጣዮቹ ሰባት ወራት ውስጥ በኩዊንስላንድና በአውስትራሊያ ሰሜናዊ ክልል የሚገኙትን በጣም ሩቅ ጉባኤዎች ስንጎበኝ ኪም በክፍለ አገር አውቶቡሶች፣ በአውሮፕላንና በባቡር 13,000 ኪሎ ሜትር ያህል አብራን ተጉዛለች። በወቅቱ የራሳችን መኪና አልነበረንም።
ሁልጊዜም በጉብኝታችን ወቅት የምናርፈው በወንድሞችና እህቶች ቤት ነበር። የአየር ንብረቱ ሞቃታማ ከመሆኑ የተነሳ በዚያን ጊዜ የነበሩት መኝታ ቤቶች በራቸው
ላይ ከሚደረገው መጋረጃ ሌላ መዝጊያ አልነበራቸውም። ይህ ደግሞ ኪም ሌሊት ላይ ስታለቅስ ይበልጥ እንድንጨነቅ ያደርገን ነበር። በመጨረሻም ልጅ የመንከባከብ ኃላፊነታችንንና የወረዳ ሥራችንን አብሮ ማስኬድ በጣም ከባድ ሆነብን። ስለዚህ በብሪዝባን ከተማ መኖር የጀመርን ሲሆን እኔም በሰሌዳ ላይ የሚወጡ የንግድ ማስታወቂያዎችን መሥራት ጀመርኩ። ኪም ከተወለደች ከሁለት ዓመት በኋላ ፔቲና የተባለችው ሁለተኛ ልጃችን ተወለደች።የደረሰብኝን አሳዛኝ ሁኔታ መቋቋም
በ1972 ልጆቻችን የ12 እና የ10 ዓመት ልጆች ሳሉ ጁዲ ሆጅኪንስ ዲዚዝ በተባለው በሽታ ሞተች። ቤተሰባችን ሐዘኑን መቋቋም በጣም ከብዶት ነበር። ይሁንና ጁዲ በታመመችበት ጊዜም ሆነ ካረፈች በኋላ ይሖዋ በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በወንድሞች አማካኝነት አጽናንቶናል። ይህ ሐዘን በገጠመን በጥቂት ጊዜ ውስጥ የወጣው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትም ብርታት ሰጥቶናል። መጽሔቱ የቤተ ዘመድ ሞትን ጨምሮ የሚደርሱብንን ፈተናዎች እንዴት መቋቋም እንደምንችልና ፈተናዎችም እንደ ጽናት፣ እምነትና ታማኝነት ያሉትን አምላካዊ ባሕርያት ለማዳበር እንዴት ሊረዱን እንደሚችሉ የሚያብራራ ርዕሰ ትምህርት ይዟል። b—ያዕቆብ 1:2-4
ጁዲ ከሞተች በኋላ ከልጆቼ ጋር በጣም ተቀራረብን። ሆኖም ልጆቼን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኜ ለማሳደግ ያደረግኩት ጥረት አድካሚ እንደነበር አልክድም። ይሁን እንጂ ሁለቱም ጥሩ ልጆች መሆናቸው እነርሱን ማሳደጉ በተወሰነ መጠን ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።
እንደገና አግብቼ ቤተሰባችን ሰፋ
ከጊዜ በኋላ ሁለተኛ ሚስቴን አገባሁ። ከአዲሷ ባለቤቴ ከሜሪ ጋር የምንመሳሰልባቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። እርሷም ባለቤቷን ያጣችው ሆጅኪንስ ዲዚዝ በተባለው በሽታ ነበር። በተጨማሪም ኮሊንና ጄኒፈር የተባሉ ሁለት ሴት ልጆች ነበሯት። ኮሊን ከፔቲና በሦስት ዓመት ያህል ታንሳለች። ስለዚህ ቤተሰባችን የ14፣ የ12፣ የ9 እና የ7 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አራት ሴት ልጆች ያቀፈ ሆነ።
መጀመሪያ ላይ፣ ልጆቹ የእንጀራ ወላጆቻቸውን መመሪያ ለመቀበል ቀላል እስኪሆንላቸው ድረስ ጥፋት በሚያጠፉበት ጊዜ የየራሳችንን ልጆች እንድንቀጣ ከሜሪ ጋር ተነጋገርን። ለእኔና ለእርሷ ደግሞ ሁለት አስፈላጊ ደንቦችን አወጣን። አንደኛ፣ አለመግባባት ቢፈጠር በልጆቻችን ፊት ላለመነጋር ተስማማን። ሁለተኛ፣ በኤፌሶን 4:26 ላይ በተመከርነው መሠረት ሰዓታት ቢወስድብንም እንኳ እስክንስማማ ድረስ ውይይት ለማድረግ ወሰንን!
የሚገርመው ነገር ሁላችንም እንዲህ ባለው ቤተሰብ ውስጥ መኖርን ተላመድነው። ሆኖም ሐዘናችንን መፋቅ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ፣ ሰኞ ምሽት ለሜሪ “የለቅሶ ምሽት” ነበር። ከቤተሰብ ጥናት በኋላ ልጆቹ ወደ መኝታቸው ሲሄዱ አምቃ የያዘችው ስሜት አብዛኛውን ጊዜ ገንፍሎ ይወጣ ነበር።
ሜሪ፣ ልጅ እንድንወልድ ትፈልግ ነበር። የሚያሳዝነው መጀመሪያ ላይ አስወረዳት። ሜሪ ሁለተኛ ጊዜ ስታረግዝ ግን የሚያስደንቅ ነገር ገጠመን። የአልትራሳውንድ ምርመራው ውጤት በሆዷ ውስጥ አንድ ብቻ ሳይሆን አራት ልጆች መኖራቸውን አሳየ! በጣም ደነገጥኩ። በ47 ዓመቴ የስምንት ልጆች አባት ልሆን ነው! የካቲት 14, 1982 ሜሪ፣ አራቱን ሕፃናት በስምንት ወራቸው በቀዶ ሕክምና ተገላገለች። ልጆቻችን በተወለዱበት ቅደም ተከተል መሠረት ክሊንት (1.6 ኪሎ ግራም)፣
ሲንዲ (1.9 ኪሎ ግራም)፣ ጀርሚ (1.4 ኪሎ ግራም) እና ዳንቲ (1.7 ኪሎ ግራም) ይባላሉ። አንዳቸውም ቢሆኑ ከሌላው ጋር አይመሳሰሉም።ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ የሜሪ ዶክተር አጠገቤ መጥቶ ቁጭ አለ።
“ልጆቹን የመንከባከቡ ጉዳይ አሳስቦሃል?” ሲል ጠየቀኝ።
“በጣም እንጂ፣ እንደዚህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያውቅም” አልኩት።
በዚህ ጊዜ የተናገራቸው አስደናቂ ቃላት አበረታተውኛል።
“ጉባኤህ አይጥልህም። አንተ አስነጥስ እንጂ ሺህ የአፍንጫ ማበሻ ናፕኪን ይቀርብልሃል!” አለኝ።
በዚህ የተዋጣለት ዶክተርና በረዳቶቹ ከፍተኛ እገዛ አራቱ ሕፃናት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ጤንነት ኖሯቸው ወደ ቤት መጡ።
አራቱን መንታዎች ለማሳደግ የገጠመን ተፈታታኝ ሁኔታ
እኔና ሜሪ ነገሮችን ሥርዓት ባለው መልኩ ለማከናወን ስንል የ24 ሰዓት ፕሮግራም አወጣን። ትላልቆቹ ልጆቻችን ሕፃናቱን በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ እገዛ አድርገውልናል። እንዲሁም ዶክተሩ የተናገረው ነገር እውነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንዴ “ሳስነጥስ” ጉባኤያችን ቶሎ ይደርስልኝ ነበር። የረጅም ጊዜ ወዳጄ የሆነው ጆን ማክአርተር የእጅ ሙያ ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችንን እንዲያሰፉልን ቀደም ብሎ ዝግጅት አድርጎ ነበር። እህቶች ደግሞ ሕፃናቱ ከሆስፒታል ከተመለሱ በኋላ በቡድን ተደራጅተው ይንከባከቧቸው ጀመር። ወንድሞችና እህቶች ያደረጉልን ደግነት የክርስቲያናዊ ፍቅር ተግባራዊ መግለጫ ነው።—1 ዮሐንስ 3:18
በአንድ በኩል እነዚህ መንታዎች “የጉባኤው ልጆች” ነበሩ። በወቅቱ ረድተውን የነበሩትን አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች ልጆቹ እስካሁን ድረስ እንደ ቤተሰብ ይመለከቷቸዋል። ሜሪም ብትሆን የተዋጣላት ሚስትና ልጆቿን በሚገባ የምትንከባከብ እናት መሆኗን አስመስክራለች። ከአምላክ ቃልና ከድርጅቱ የተማረችውን ነገር በጥሩ ሁኔታ ተግባራዊ አድርጋለች። ደግሞስ ከዚህ የተሻለ ምክር የት ይገኛል!—መዝሙር 1:2, 3፤ ማቴዎስ 24:45
አራት ሕፃናትን ይዞ ወዲያ ወዲህ ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና የስብከቱ ሥራችን በሳምንቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸው ነገሮች መሆናቸው ቀጥሎ ነበር። በወቅቱ ያገኘነው አንዱ በረከት በደግነት ቤታችን መጥተው የሚያጠኑ ባልና ሚስት የሆኑ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘታችን ነው። ይህ ሁኔታዎችን ቀላል ቢያደርግልንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ሜሪ በጣም ስለሚደክማት እንቅልፍ የወሰደውን ሕፃን እንደታቀፈች እያስጠናን ታንቀላፋ ነበር። በመጨረሻም እነዚህ አራት ባልና ሚስቶች መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆነዋል።
ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የተሰጠ መንፈሳዊ ሥልጠና
እኔ፣ ሜሪና ትላልቆቹ ልጆቻችን ሕፃናቱ ገና መሄድ እንኳ ሳይጀምሩ ይዘናቸው ወደ መስክ አገልግሎት እንወጣ ነበር። በእግራቸው መሄድ ከጀመሩ በኋላ ደግሞ እኔና ሜሪ ሁለት ሁለት አድርገን ስለምንይዛቸው ሸክም አልሆኑብንም። እንዲያውም ወዳጃዊ ስሜት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገር አመቺ አጋጣሚ ይፈጥሩልን ነበር። አንድ ቀን አንድ ሰውዬ “የሰዎች ባሕርይ አስቀድሞ የተወሰነ በመሆኑ ኮከባቸው አንድ ዓይነት የሆኑ ሰዎች ተመሳሳይ ባሕርይ ይኖራቸዋል” አለኝ። እኔም ምንም ሳልከራከረው ረፋዱ ላይ ተመልሼ መምጣት እችል እንደሆነ ጠየቅሁት። እርሱም ባቀረብኩት ሐሳብ ስለተስማማ አራቱን መንታዎች ይዤ ሄድኩ። በመገረም እያያቸው ሳለ በተወለዱበት ቅደም ተከተል እንዲቆሙ አደረግኋቸው። ከዚያም በግልጽ በሚታየው አካላዊ ልዩነታቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ሰፊ በሆነው የባሕርይ ልዩነታቸው ላይ ጭምር አስደሳች ውይይት አደረግን። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ያነሳውን ሐሳብ ውድቅ አደረገበት። “ይህን ጽንሰ ሐሳብ ለአንተ
ማንሳቱ ሞኝነት ነው። ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ያለብኝ አይመስልህም?” አለኝ።መንትዮቹ ገና ሕፃናት ሆነው እንኳ ጥፋት ሲያጠፉ በአንድነት ስንገሥጻቸው ደስ አይላቸውም ነበር፤ ስለዚህ ለየብቻ እንቀጣቸው ጀመር። ሆኖም ማንኛውም ሕግ ለሁሉም እንደሚሠራ ተገንዝበው ነበር። ትምህርት ቤት ከሕሊናቸው ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲገጥማቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጸንተው የሚቆሙ ከመሆኑም በላይ እርስ በርሳቸው ይደጋገፉ ነበር። እነርሱን ወክላ የምትናገረው ሲንዲ ነበረች። ብዙም ሳይቆይ ሰዎች የአራቱ ኅብረት በቀላሉ እንደማይጠቃ ተረዱ!
ብዙ ጊዜ እንደሚያጋጥመው እኔና ሜሪ፣ ልጆቹ በጉርምስና ዕድሜያቸው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ መርዳት አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር። አፍቃሪ የሆነው ጉባኤ ያደረገልን ድጋፍና የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ያቀረበልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ባይኖሩ ኖሮ ይህን ኃላፊነታችንን መወጣት እጅግ ሊከብደን እንደሚችል እሙን ነው። ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እንኳ ቋሚ የሆነ የቤተሰብ ጥናትና ግልጽ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት እናደርግ ነበር። ስምንቱም ልጆቻችን ይሖዋን ለማገልገል ስለመረጡ ጥረታችን መና ሆኖ አልቀረም።
ከዕድሜ መግፋት ጋር እየታገሉ መኖር
ባለፉት ዓመታት በርካታ መንፈሳዊ መብቶችን አግኝቻለሁ። የጉባኤ ሽማግሌ፣ የከተማ የበላይ ተመልካችና ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። በተጨማሪም ዶክተሮች ለይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች ያለ ደም ሕክምና እንዲሰጧቸው ትብብር የሚጠይቀው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ሆኜ አገለግላለሁ። ከዚህም ባሻገር ለማጋባት በተሰጠኝ ሕጋዊ ሥልጣን በመጠቀም በ34 ዓመታት ውስጥ የስድስት ሴት ልጆቼን ጨምሮ 350 የጋብቻ ሥርዓቶችን የማስፈጸም መብት አግኝቻለሁ።
መጀመሪያ ጁዲ በኋላም የአሁኗ ባለቤቴ ሜሪ በታማኝነት ላበረከቱልኝ ድጋፍ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። (ምሳሌ 31:10, 30) በጉባኤ ሽማግሌነት የምሰጠውን አገልግሎት ከመደገፋቸውም ባሻገር በስብከቱ ሥራም ግሩም ምሳሌ ሆነዋል። በተጨማሪም በልጆቻችን ልብ ውስጥ መንፈሳዊ እሴቶችን በመቅረጽ ረገድ ረድተውኛል።
በ1996 እጆቼን የሚያንቀጠቅጥና ሚዛኔን እንድስት የሚያደርግ የአእምሮ ችግር አጋጠመኝ። በመሆኑም በሰብዓዊ ሥራዬ መቀጠል አልቻልኩም። የቀድሞውን ያህል መሥራት ባልችልም አሁን ድረስ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ደስታ እያገኘሁ ነው። በበጎ ጎኑ ካየነው ደግሞ ሕመሜ የሌሎች አረጋውያን ችግር ይበልጥ እንዲገባኝ አድርጎኛል።
ስላሳለፍኩት ሕይወት ሳስብ ይሖዋ ሁልጊዜም ከጎናችን ሆኖ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በደስታ እንድንወጣ ስለረዳን አመሰግነዋለሁ። (ኢሳይያስ 41:10) በተጨማሪም እኔና ሜሪ እንዲሁም ስምንት ልጆቻችን፣ ጥሩና ደግ ለሆኑት መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አመስጋኞች ነን። ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ መንገዶች ያሳዩንን ፍቅር በቃላት መግለጽ ያቅተናል።—ዮሐንስ 13:34, 35
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን ግን መታተም አቁሟል።
b የመጋቢት 15, 1972 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 174-180 ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከእማዬ እንዲሁም ከታላቅ ወንድሜ ከጋርዝና ከእህቴ ከዶውን ጋር ሆኜ በ1941 በሲድኒ ወደተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ልንሄድ ስንል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኩዊንስላንድ በወረዳ ሥራ ላይ ሆኜ ከጁዲና ከኪም ጋር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አራቱ መንታዎች ከተወለዱ በኋላ አራቱ ትላልቅ ልጆቻችንና ጉባኤው እርዳታ አበርክተውልናል