በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት
በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት
“በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ . . . ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር።”—ዮሐንስ 2:1, 2
1. ኢየሱስ በቃና እንደነበረ የሚገልጸው ዘገባ ምን ያስገነዝበናል?
ኢየሱስም ሆነ እናቱ ማርያም እንዲሁም አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚፈጸሙ ክቡር የሆኑ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ደስታ እንደሚያስገኙ ያውቁ ነበር። እንዲያውም ክርስቶስ በአንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያውን ተአምር በመፈጸም ዝግጅቱ ለየት ያለና አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል። (ዮሐንስ 2:1-11) አንተም፣ ተጋብተው ይሖዋን በደስታ ማምለክ በሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሠርግ ላይ ተገኝተህ በሥነ ሥርዓቱ ተደስተህ ይሆናል። ወይም አንተ ራስህ ሠርግህ እንደዚህ ዓይነት እንዲሆን ትመኝ አሊያም የአንድ ወዳጅህ የሠርግ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን ልትረዳው ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል?
2. መጽሐፍ ቅዱስ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን አስመልክቶ ምን መረጃ ይዟል?
2 ክርስቲያኖች አንድ ወንድና አንዲት ሴት ትዳር ለመመሥረት በሚፈልጉበት ወቅት አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ይገነዘባሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖች ሠርግ ምን ሊመስል እንደሚገባ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። ይህም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የሰዎች ባሕልና መንግሥት የሚያወጣው ሕግ ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከዘመን ዘመን የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ዛሬ እንደምንመለከተው ዓይነት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አልነበረም። በሠርጉ ዕለት ሙሽራው፣ ሙሽራዋን ወደ ራሱ ቤት አሊያም ወደ አባቱ ቤት ይወስዳታል። (ዘፍጥረት 24:67፤ ኢሳይያስ 61:10፤ ማቴዎስ 1:24) ሙሽራው በይፋ የሚወስደው ይህ እርምጃ እንደ ሠርግ ይቆጠራል፤ ዛሬ በአብዛኞቹ ሠርጎች ላይ የምናየው ዓይነት ሥነ ሥርዓት አልነበረም።
3. ኢየሱስ በቃና ለየትኛው ዝግጅት አስተዋጽኦ አድርጓል?
3 በእስራኤላውያን ዘንድ እንደ ሠርግ የሚቆጠረው ይህ ድርጊት ነበር። ከዚያ በኋላ በዮሐንስ 2:1 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ዓይነት ድግስ ይደረግ ይሆናል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ጥቅስ “በቃና ከተማ ሰርግ ነበር” ብለው ተርጉመውታል። ሆኖም በኩረ ጽሑፉ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል በሌሎች ቦታዎች ‘የሰርግ ድግስ’ ወይም ‘የሰርግ ግብዣ’ ተብሎ ይበልጥ ተስማሚ በሆነ መንገድ ተተርጉሟል። a (ማቴዎስ 22:2-10፤ 25:10፤ ሉቃስ 14:8 የ1980 ትርጉም) ከዘገባው በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከአይሁዳውያን ሠርግ ጋር በተያያዘ ተዘጋጅቶ በነበረ አንድ ድግስ ላይ የተገኘ ሲሆን ግብዣው የበለጠ አስደሳች እንዲሆንም አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የነበረ ሠርግ የሚያካትታቸው ነገሮች በዛሬው ጊዜ ከተለመደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የተለዩ እንደሆኑ ልብ ልንል ይገባል።
4. አንዳንድ ክርስቲያኖች የጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ምን ዓይነት እንዲሆን ይመርጡ ይሆናል? ለምንስ?
4 በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ለማግባት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች አንዳንድ ሕጋዊ ደንቦችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። ተጋቢዎቹ እነዚህን ደንቦች ካሟሉ በኋላ ሕጋዊ ተቀባይነት ባለው በማንኛውም መንገድ መጋባት ይችላሉ። ይህም መንግሥት የማጋባት ሥልጣን በሰጠው አንድ ዳኛ፣ ሹም አሊያም ሃይማኖታዊ ተወካይ አማካኝነት የሚፈጸም ቀለል ያለ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች በዚህ መንገድ ለመጋባት የሚመርጡ ሲሆን በሠርጋቸው ላይ ጥቂት ዘመዶቻቸው ወይም ክርስቲያን ወዳጆቻቸው ሕጋዊ ምሥክር ሆነው እንዲገኙ አሊያም በዚህ አስደሳች ወቅት ተገኝተው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ለመጋበዝ ይፈልጉ ይሆናል። (ኤርምያስ 33:11፤ ዮሐንስ 3:29) ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ሰፊ እቅድ የሚያስፈልገውና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ትልቅ የሠርግ ድግስ ከማዘጋጀት ይልቅ ለቅርብ ወዳጆቻቸው አነስ ያለ ግብዣ ያደርጉ ይሆናል። በዚህ ረገድ የግል ምርጫችን ምንም ይሁን ምን፣ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከእኛ የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል።—ሮሜ 14:3, 4
5. በርካታ ክርስቲያኖች የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ንግግሩስ ምን ይዟል?
5 አብዛኞቹ ክርስቲያን ተጋቢዎች በሠርጋቸው ዕለት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ። b የጋብቻ መሥራች ይሖዋ መሆኑን እንዲሁም ትዳር ስኬታማና አስደሳች እንዲሆን የሚረዳ ምክር በቃሉ ውስጥ እንዳሰፈረ ይገነዘባሉ። (ዘፍጥረት 2:22-24፤ ማርቆስ 10:6-9፤ ኤፌሶን 5:22-33) ከዚህም በላይ አብዛኞቹ ተጋቢዎች ክርስቲያን ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በዚህ ዕለት የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሆኖም ከሕግ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎችና ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም በአካባቢው ልማድ ረገድ ያሉትን በርካታ ልዩነቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? ይህ የጥናት ርዕስ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን ሁኔታዎች ይመረምራል። አንዳንዶቹ አንተ ከምታውቃቸው ወይም በአካባቢህ ከሚከናወኑት ሥርዓቶች በጣም የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ግን በዚህ ርዕስ ውስጥ ለአምላክ አገልጋዮች አስፈላጊ የሆኑና በብዙ ቦታዎች የሚሠሩ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወይም ሁኔታዎችን ልታስተውል ትችላለህ።
ጋብቻ ክቡር እንዲሆን ሕጋዊ መሆን አለበት
6, 7. ከጋብቻ ጋር ለተያያዙ ሕግ ነክ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
6 የጋብቻ መሥራች ይሖዋ ቢሆንም ሰብዓዊ መንግሥታት ተጋቢዎቹ የሚወስዱትን እርምጃ በተወሰነ መልኩ የመቆጣጠር ሥልጣን አላቸው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው። ኢየሱስ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏል። (ማርቆስ 12:17) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።”—ሮሜ 13:1፤ ቲቶ 3:1
7 በብዙ አገሮች ውስጥ አንድ ሰው ለማግባት የሚያስፈልገውን መሥፈርት ያሟላ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ቄሳር ማለትም መንግሥት ሥልጣን የሰጠው አካል ነው። በዚህም የተነሳ በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለማግባት ነጻ የሆኑ ሁለት ክርስቲያኖች ለመጋባት ሲወስኑ ጋብቻን በተመለከተ የወጣውን የአገራቸውን ሕግ ያከብራሉ። ይህም ፈቃድ ማግኘትን፣ ጋብቻ ለማስፈጸም መንግሥት ሥልጣን በሰጠው አካል አማካኝነት መጋባትንና ምናልባትም ይህ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ጋብቻውን ማስመዝገብን ይጨምር ይሆናል። አውግስጦስ ቄሳር ሕዝቡ “እንዲመዘገብ” ባዘዘ ወቅት ማርያምና ዮሴፍ ትእዛዙን አክብረው “ለመመዝገብ” ወደ ቤተልሔም ሄደዋል።—ሉቃስ 2:1-5
8. የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን ልማድ አይከተሉም? ለምንስ?
8 ሁለት ክርስቲያኖች ሕጋዊ በሆነና ተቀባይነት ባለው መንገድ ትዳር ሲመሠርቱ ይህ ጥምረት በአምላክ ፊት የጸና ይሆናል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶችን በመፈጸም የጋብቻ ሥርዓቱን አይደግሙትም፤ እንዲሁም 25ኛ ወይም 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ሲያከብሩ በድጋሚ የጋብቻ መሐላ አይፈጽሙም። (ማቴዎስ 5:37) (አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ቄስ ተጋቢዎቹን በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ካላጋባቸው ወይም ባልና ሚስት መሆናቸውን በይፋ ካላሳወቀ በስተቀር ጋብቻው ተቀባይነት እንደማይኖረው በመናገር በመንግሥት ሕግ የጸደቀውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አይቀበሉም።) በበርካታ አገሮች ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር የጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንዲያስፈጽም መንግሥት ሥልጣን ይሰጠዋል። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው ሰው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር ካቀረበ በኋላ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ሊያከናውን ይችላል። የመንግሥት አዳራሽ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው እውነተኛ አምልኮ የሚያካሂዱበት ቦታ ሲሆን ይሖዋ ያቋቋመውን የጋብቻ ዝግጅት በተመለከተ ንግግር ለማቅረብ ተስማሚ የሆነ ቦታ ነው።
9. (ሀ) በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚጋቡ ክርስቲያኖች ምን ሊወስኑ ይችላሉ? (ለ) ከሠርጉ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው?
9 በሌሎች አገሮች ደግሞ ተጋቢዎቹ እንደ ማዘጋጃ ቤት ባለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ወይም በክብር መዝገብ ሹም ፊት (የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው አካል) እንዲጋቡ ሕጉ ይደነግጋል። አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች ይህንን ሕጋዊ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ በዚያው ዕለት ወይም በማግሥቱ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ። (እነዚህ ክርስቲያኖች ከዚያ በኋላ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ዘንድ ባልና ሚስት በመሆናቸው በሕግ በተፈራረሙበት ቀንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር በሚቀርብበት ቀን መካከል ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ አያደርጉም።) በማዘጋጃ ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚጋቡ ክርስቲያኖች በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ንግግር እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ከሆነ አስቀድመው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባላት ከሆኑት ሽማግሌዎች ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሽማግሌዎች ተጋቢዎቹ ጥሩ ስም ያላቸው መሆኑን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ሠርጉ የሚከናወንበት ሰዓት በአዳራሹ ከሚደረጉ መደበኛ ስብሰባዎችና ሌሎች ፕሮግራሞች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40) ከዚህም በላይ ተጋቢዎቹ የመንግሥት አዳራሹን ለጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት ከጠየቁ ሽማግሌዎቹ ይህንንም ይመለከታሉ፤ አዳራሹ ለዚህ ዓላማ ጥቅም ላይ እንደሚውል ማስታወቂያ መንገር ያስፈልግ እንደሆነም ይወስናሉ።
10. ጥንዶቹ በሕግ ተጋብተው ከሆነ የጋብቻ ንግግሩ ምን መልክ ይኖረዋል?
10 የጋብቻ ንግግሩን የሚያቀርበው ሽማግሌ ንግግሩ ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ በመንፈሳዊ የሚያጠናክርና ክብር ያለው እንዲሆን ለማድረግ ይጥራል። ተጋቢዎቹ ከላይ እንደተገለጸው አስቀድመው በሕግ ፊት ተጋብተው ከሆነ፣ በቄሳር ሕግ መሠረት ባልና ሚስት መሆናቸውን ንግግሩን የሚያቀርበው ሽማግሌ በግልጽ ይናገራል። በሕግ ፊት በተጋቡበት ወቅት የጋብቻ መሐላ ካልፈጸሙ ንግግሩ በሚቀርብበት ጊዜ ይህንን ለማድረግ ይፈልጉ ይሆናል። c በሌላ በኩል ደግሞ አዲሶቹ ተጋቢዎች በሕግ ፊት ሲጋቡ መሐላ የፈጸሙ ቢሆንም በይሖዋና በጉባኤው ፊት እንደገና የጋብቻ መሐላ መፈጸም ከፈለጉ፣ ቀደም ብለው ‘እንደተጣመሩ’ በሚያሳይ መንገድ መሐላውን ማድረግ ይችላሉ።—ማቴዎስ 19:6፤ 22:21
11. በአንዳንድ ቦታዎች ጋብቻ የሚከናወነው እንዴት ነው? ይህስ በጋብቻ ንግግሩ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
11 በአንዳንድ ቦታዎች ሕጉ፣ ተጋቢዎቹ መንግሥት የማጋባት ሥልጣን በሰጠው አካል ፊትም ሆነ በሌላ በማንኛውም ዓይነት ሥርዓት እንዲጋቡ አይጠብቅባቸው ይሆናል። ጋብቻው የሚፈጸመው ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀውን ቅጽ ሞልተው ሥልጣን ለተሰጠው አካል ሲያቀርቡ ነው። ከዚያም ይህ ቅጽ በመዝገብ ቤት ይቀመጣል። በዚህ ቅጽ ላይ የተመዘገበው ዕለት የጋብቻቸው ቀን ስለሚሆን ከዚያ በኋላ እንደ ባልና ሚስት ይቆጠራሉ። ከላይ እንደተገለጸው በዚህ መንገድ የተጋቡ ጥንዶች ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የጋብቻ ንግግር በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል። ንግግሩን እንዲያቀርብ የተመረጠው በመንፈሳዊ የጎለመሰ ወንድም፣ ጥንዶቹ ጋብቻቸው ስለተመዘገበ ባልና ሚስት መሆናቸውን በሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ ይገልጻል። የጋብቻ መሐላ የሚፈጽሙ ከሆነ አንቀጽ 10ና የግርጌ ማስታወሻው ላይ የሰፈረውን መመሪያ ይከተላሉ። በመንግሥት አዳራሹ የተገኙት ሰዎች የተጋቢዎቹ ደስታ ተካፋይ ከመሆናቸውም በላይ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርቶ ከሚቀርበው ምክር ይጠቀማሉ።—ማሕልየ መሓልይ 3:11
ባሕላዊ ጋብቻና በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ
12. ባሕላዊ ጋብቻ ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ ምን ማድረጉ የተሻለ ነው?
12 በአንዳንድ አገሮች ጋብቻ የሚፈጸመው በባሕላዊ ሥርዓት (ወይም በጎሳው ልማድ) መሠረት ነው። ይህ ዓይነቱ ጋብቻ ሁለት ሰዎች ሳይጋቡ አብረው ከሚኖሩበት ሁኔታ የተለየ ነው፤ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ተቀባይነት ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ጋብቻ እንደሆነ ተደርጎ የማይቆጠረውን ልማድ (common-law marriage) የሚያመለክትም አይደለም። d እዚህ ላይ የተገለጸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባለው የጎሳው ወይም የአካባቢው ባሕል መሠረት የሚከናወን ጋብቻ ነው። ይህም ጥሎሽ መቀበልን ወይም መስጠትን ይጨምር ይሆናል፤ በዚህ መልኩ ጥንዶቹ በሕጉም ሆነ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ባልና ሚስት ይሆናሉ። መንግሥት እንደዚህ ያለውን ባሕላዊ ጋብቻ ተቀባይነት ያለው፣ ሕጋዊና የጸና እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ከዚህ ዓይነቱ ሥርዓት በኋላ ይህንን ባሕላዊ ጋብቻ ማስመዝገብ ይቻላል፤ ባልና ሚስቱ እንዲህ ሲያደርጉ ሕጋዊ የጋብቻ የምሥክር ወረቀት ይሰጣቸዋል። ጋብቻቸው መመዝገቡ፣ ለባልና ሚስቱ ወይም ከጊዜ በኋላ ባሏ ቢሞት ለሚስትየው እንዲሁም ወደፊት ለሚወለዱ ልጆች ጥበቃ ይሆናል። ጉባኤው እንዲህ ባለ ባሕላዊ መንገድ የሚጋቡ ሰዎች በተቻለ ፍጥነት ጋብቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ያሳስባቸዋል። በሙሴ ሕግ ሥር ሰዎች ሲጋቡ እንዲሁም ልጆች ሲወለዱ ይመዘገብ እንደነበረ ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው።—ማቴዎስ 1:1-16
13. ባሕላዊ ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ የጋብቻ ንግግር የሚቀርብ ከሆነ ምን ማድረጉ ተገቢ ነው?
13 በዚህ ዓይነት ባሕላዊ ሥርዓት የተጣመሩት ተጋቢዎች ይህ ሕጋዊ ጋብቻ ሲከናወን ባልና ሚስት ይሆናሉ። ከላይ እንደተገለጸው እንደዚህ ባለው ሕጋዊ መንገድ የተጋቡ ክርስቲያኖች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር ተደርጎላቸው የጋብቻ መሐላ ለመፈጸም ይፈልጉ ይሆናል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ ንግግሩን የሚያቀርበው ወንድም እነዚህ ሰዎች በቄሳር ሕግ መሠረት ቀደም ሲል እንደተጋቡ ይገልጻል። እንዲህ ያለው የጋብቻ ንግግርም የሚቀርበው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሕግ ተቀባይነት ያለው ባሕላዊ ወይም የጎሳ ጋብቻ የሚፈጸመውም ሆነ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ንግግር የሚቀርበው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እነዚህ ሁለት ክንውኖች በተቻለ መጠን በአንድ ቀን ቢደረጉ ይመረጣል። ካልሆነ ግን ቀኑ ብዙም ባይራራቅ ጥሩ ነው፤ ይህ መሆኑ የክርስቲያኖች ጋብቻ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከበረ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
14. ባሕላዊውንም ሆነ በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚደረገውን ጋብቻ መፈጸም በሚቻልባቸው አገሮች አንድ ክርስቲያን ምን ሊያደርግ ይችላል?
14 ባሕላዊ ጋብቻ እንደ ሕጋዊ ጋብቻ በሚቆጠርባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ጋብቻን ለመፈጸም የሚያስችል ተጨማሪ ዝግጅትም አለ። በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸመው ጋብቻ ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው የመንግሥት ተወካይ በተገኘበት ሲሆን ተጋቢዎቹ የጋብቻ መሐላ ይፈጽማሉ፤ እንዲሁም በክብር መዝገብ ላይ ይፈርማሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች በባሕላዊ ሥርዓት ከመጋባት ይልቅ በዚህ መንገድ ለመጋባት ይመርጣሉ። ሁለቱም የጋብቻ ሥርዓቶች ከሕግ አንጻር ተቀባይነት ያላቸው እስከሆኑ ድረስ ሁለቱንም በአንድነት ለመፈጸም የሚያስገድድ ሕግ የለም። የጋብቻ ንግግርንና መሐላን በተመለከተ በአንቀጽ 9 እና 10 ላይ የቀረበው ሐሳብ እዚህ ላይም ይሠራል። ዋናው ነገር ጥንዶቹ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር በሆነ መንገድ መጋባታቸው ነው።—ሉቃስ 20:25፤ 1 ጴጥሮስ 2:13, 14
ጋብቻችሁ ክቡር እንደሆነ ይቀጥል
15, 16. ጋብቻው ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
15 አንድ የፋርስ ንጉሥ በትዳሩ ውስጥ ችግር በገጠመው ወቅት ምሙካ የተባለው የንጉሡ ዋና አማካሪ ‘ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን እንዲያከብሩ’ የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ሰጠ። (አስቴር 1:20) የክርስቲያኖችን ትዳር በተመለከተ ማንኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲህ ያለ አዋጅ ማስነገር አያስፈልገውም፤ ምክንያቱም ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር ይፈልጋሉ። በተመሳሳይም ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸውን ያከብሯቸዋል እንዲሁም ያመሰግኗቸዋል። (ምሳሌ 31:11, 30፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) ትዳራችንን ለማክበር ተጋብተን ረጅም ዓመት መቆየት አያስፈልገንም። እንዲህ ያለው አክብሮት ገና ከመጀመሪያው ይኸውም ጋብቻው ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ መታየት ይኖርበታል።
16 የሠርጉ ቀን ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚገባቸው ባልና ሚስቱ ብቻ አይደሉም። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ የጋብቻ ንግግር የሚያቀርብ ከሆነ ይህም ክብር ባለው መንገድ ሊደረግ ይገባል። ተናጋሪው ፊቱን ወደ ተጋቢዎቹ አዙሮ በእነርሱ ላይ ያተኮረ ንግግር ማቅረብ ይኖርበታል። ተናጋሪው ለተጋቢዎቹ አክብሮት በማሳየት በንግግሩ ላይ ቀልድ ወይም በአካባቢው የተለመደ ተረት አይናገርም። ተጋቢዎቹንም ሆነ አድማጮቹን ሊያሳፍሩ የሚችሉ ስለ ተጋቢዎቹ የግል ሁኔታ የሚገልጹ ሐሳቦች መሰንዘር አይኖርበትም። ከዚህ ይልቅ የጋብቻ መሥራች የሆነውን አምላክና እርሱ የሰጠውን የላቀ ምክር ጎላ አድርጎ በመግለጽ ንግግሩን ሞቅ ባለና በሚያንጽ መንገድ ሊያቀርበው ይገባል። በእርግጥም ሽማግሌው የጋብቻ ንግግሩን በሚያስከብር መንገድ ማቅረቡ የጋብቻው ሥነ ሥርዓት ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
17. የክርስቲያኖች ሠርግ በሕጉ መሠረት የሚከናወነው ለምንድን ነው?
17 በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ሕጋዊ ጋብቻን በተመለከተ በርካታ ነጥቦችን ሳታስተውል አልቀረህም። አንዳንዶቹ ነጥቦች አንተ በምትኖርበት አካባቢ አይሠሩ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ለአገራቸው ሕግ ማለትም ቄሳር ለሚያወጣቸው ደንቦች አክብሮት እንዳለን የሚያሳዩ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። (ሉቃስ 20:25) ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ . . . ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ” በማለት አሳስቧል። (ሮሜ 13:7) በእርግጥም ክርስቲያኖች አምላክ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ላስቀመጠው ዝግጅት አክብሮት እንዳላቸው ከሠርጉ ቀን ጀምሮ ማሳየታቸው ተገቢ ነው።
18. አንዳንዶች ከጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለማድረግ የሚመርጡት የትኛው ዝግጅት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል? ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሐሳብ የምናገኘው ከየት ነው?
18 አብዛኛውን ጊዜ በክርስቲያኖች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ግብዣ ወይም ድግስ ይኖራል። ኢየሱስ እንዲህ ባለ ግብዣ ላይ ተገኝቶ እንደነበረ አስታውስ። እንዲህ ዓይነት ግብዣ የሚዘጋጅ ከሆነ፣ ዝግጅቱ ለአምላክ ክብር የሚያመጣና ተጋቢዎቹንም ሆነ ክርስቲያን ጉባኤን የሚያስመሰግን እንዲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ምክር የሚረዳን እንዴት ነው? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። e
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b በይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ “በአምላክ ፊት ክብር ያለው ጋብቻ” የሚል ርዕስ ያለው የ30 ደቂቃ የጋብቻ ንግግር ይቀርባል። ንግግሩ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? ከሚለው መጽሐፍና ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ ጠቃሚ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ይዟል። እንዲህ ያለው ንግግር ለተጋቢዎቹም ሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለሚገኙት ሁሉ ጠቃሚ ነው።
c የአገሩ ሕግ ከዚህ የተለየ መመሪያ እስከሌለው ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን የሚያስከብረውን የሚከተለውን የጋብቻ መሐላ ይጠቀማሉ። ሙሽራው እንዲህ ይላል:- “እኔ [የሙሽራው ስም] ሁለታችንም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለክርስቲያን ባሎች በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት አንቺን [የሙሽራዋ ስም] ልወድሽና ልንከባከብሽ ሚስቴ አድርጌ ወስጄሻለሁ።” ሙሽራዋ እንዲህ ትላለች:- “እኔ [የሙሽራዋ ስም] ሁለታችንም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለክርስቲያን ሚስቶች በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት አንተን [የሙሽራው ስም] ልወድህ፣ ልንከባከብህና በጥልቅ ላከብርህ ባሌ አድርጌ ወስጄሃለሁ።”
d የግንቦት 1, 1962 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 287 (እንግሊዝኛ) እንደዚህ ስላለው ጋብቻ ሐሳብ ይሰጣል።
e በተጨማሪም “የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ” የሚለውን በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ከጋብቻ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሕጉም ሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሚሰጡት መመሪያ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው?
• ሁለት ክርስቲያኖች በክብር መዝገብ ሹም ፊት ከተጋቡ ከዚያ ብዙም ሳይቆዩ ምን ለማድረግ ሊወስኑ ይችላሉ?
• የጋብቻ ንግግር የሚቀርበው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሆነው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንት እስራኤላውያን ሠርግ ላይ ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደ ራሱ ወይም ወደ አባቱ ቤት ይወስዳት ነበር
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በባሕላዊ ሥርዓት ከተጋቡ በኋላ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል