አንተንም የሚመለከት አከራካሪ ጉዳይ
አንተንም የሚመለከት አከራካሪ ጉዳይ
ከሌሎች ለየት ባለ መንገድ በጣም የምትቀርበው ጓደኛ ወይም የቤተሰብ አባል አለህ? አንድ ሰው፣ ከዚህ ሰው ጋር ያለህ ቀረቤታ በጥቅም ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደሆነ አድርጎ ቢወነጅልህ ምን ይሰማሃል? እንዲህ ማለቱ እንድትቀየም ወይም እንድትቆጣ አያደርግህም? ሰይጣን ዲያብሎስ ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ባላቸው ሰዎች ሁሉ ላይ የሰነዘረውም ክስ ይኸው ነው።
ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት፣ አዳምና ሔዋን የአምላክን ሕግ እንዲጥሱና በዓመጹ እንዲተባበሩት ባደረገ ጊዜ የሆነውን ነገር መለስ ብለህ አስብ። በዚያን ጊዜ የተፈጸመው ነገር፣ ሰዎች ለይሖዋ ታዛዥ የሚሆኑት መታዘዝ ጥቅም የሚያስገኝላቸው እስከሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን ያመላከተ ነበር? (ዘፍጥረት 3:1-6) አዳም ካመጸ ከ2,500 ዓመታት በኋላ ሰይጣን ይህንኑ ጉዳይ እንደገና አንስቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን የውንጀላው ዒላማ ያደረገው ኢዮብ የተባለውን ሰው ነበር። ዲያብሎስ የሰነዘረው ክስ የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ በግልጽ ለማወቅ ስለሚያስችለን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በጥንቃቄ እንመርምረው።
“ጨዋነቴንም [“ታማኝነቴን፣” NW] እስክሞት ድረስ አልጥልም”
ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው” ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን የኢዮብን ቅንነት በመጥፎ ተረጎመው። “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን?” በማለት ይሖዋን ጠየቀው። ከዚያም ዲያብሎስ፣ ይሖዋ ኢዮብን በመጠበቅና በመባረክ ታማኝ እንዲሆንለት አድርጎታል ብሎ በመወንጀል የአምላክንም ሆነ የኢዮብን ስም አጠፋ። “እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል” በማለት ሰይጣን ተከራከረ።—ኢዮብ 1:8-11
ይሖዋ ለእነዚህ ውንጀላዎች መልስ ለመስጠት ሲል ሰይጣን ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት። ዲያብሎስ፣ ኢዮብ አምላክን ማገልገሉን እንዲተው ለማድረግ ሲል በመከራ ላይ መከራ አፈራረቀበት። ከኢዮብ ከብቶች አንዳንዶቹ ተሰረቁ፣ ሌሎቹም ሞቱ፤ ከብት ጠባቂዎቹም ተገደሉ። እንዲሁም የኢዮብ ልጆች ሞቱ። (ኢዮብ 1:12-19) ታዲያ ሰይጣን ተሳካለት? በጭራሽ! ኢዮብ መከራዎቹን ያመጣበት ዲያብሎስ መሆኑን ባያውቅም እንደሚከተለው ብሏል:- “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።”—ኢዮብ 1:21
ከዚያ በኋላ ሰይጣን በአምላክ ፊት በቀረበ ጊዜ ይሖዋ “ያለ ምክንያት እንዳጠፋው ብትወተውተኝም፣ ይኸው ፍጹምነቱን [“ታማኝነቱን፣” NW] እንደ ጠበቀ ነው” አለው። (ኢዮብ 2:1-3) ዋናው ጥያቄ ኢዮብ አቋሙን ሳያላላ በታማኝነት መጽናቱና የጽድቅ መሥፈርቶችን በጥብቅ መከተሉ ነበር። እስካሁን እንዳየነው ኢዮብ የተነሳበትን የታማኝነት ጥያቄ በድል ተወጥቷል። ይሁን እንጂ ዲያብሎስ ተስፋ አልቆረጠም።
ቀጥሎም ሰይጣን ሁሉንም የሰው ዘሮች የሚነካ ነገር ተናገረ። “‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል፤ እስቲ እጅህን ዘርግተህ ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል” በማለት ከሰሰ። (ኢዮብ 2:4, 5) ዲያብሎስ፣ ኢዮብ በሚለው ስም ፈንታ “ሰው” የሚለውን የወል መጠሪያ በመጠቀም የሁሉንም ሰው ታማኝነት አጠያያቂ አደረገው። ይህም ‘ሰው ሕይወቱን ለማዳን ሲል የማያደርገው ነገር የለም። ዕድሉን ከሰጠኸኝ ሁሉንም ሰው ከአንተ ማራቅ እችላለሁ’ ብሎ የተናገረ ያህል ነው። ታዲያ በማንኛውም ሁኔታ ሥር እንዲሁም በየትኛውም ጊዜ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ የሚቀጥል ሰው አይገኝም ይሆን?
ዲያብሎስ ኢዮብን በክፉ በሽታ እንዲያሠቃየው ይሖዋ ፈቀደለት። ኢዮብ ክፉኛ በመሠቃየቱ እንዲሞት እስከ መጸለይ ደርሷል። (ኢዮብ 2:7፤ 14:13) ሆኖም ኢዮብ “ጨዋነቴንም [“ታማኝነቴን፣” NW] እስክሞት ድረስ አልጥልም” ብሎ ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5) ኢዮብ ይህን የተናገረው አምላክን ስለሚወድ በመሆኑ ምንም ነገር ቢመጣ ይህን ፍቅሩን አይለውጠውም። ኢዮብ ታማኝ ሰው መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። “እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 42:10-17) እንደ ኢዮብ ታማኝ የሆኑ ሌሎች ሰዎችስ ነበሩ? በጊዜ ሂደት ምን ታይቷል?
አከራካሪው ጉዳይ መልስ ያገኘው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዕብራውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ ኖኅን፣ አብርሃምን፣ ሣራንና ሙሴን ጨምሮ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ የበርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ስም ዘርዝሯል። ከዚያም ሐዋርያው “ስለ [ሌሎችም] . . . እንዳልተርክ ጊዜ የለኝም” ብሏል። (ዕብራውያን 11:32) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ጳውሎስ ሰማዩን ሸፍኖ ከሚታይ ደመና ጋር በማወዳደር ‘እንደ ደመና ያሉ ብዙ ምስክሮች’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ዕብራውያን 12:1) አዎን፣ ባለፉት ዘመናት ሁሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች የመምረጥ ነጻነታቸውን ተጠቅመው ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ለመሆን መርጠዋል።—ኢያሱ 24:15
ሰይጣን፣ ሰዎችን ከይሖዋ ማራቅ እንደሚችል ላነሳው ግድድር የማያዳግም መልስ የሰጠው የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በሥቃይ ቢሞትም እንኳን ለአምላክ ያለውን ታማኝነት አላላላም። ኢየሱስ ሊሞት ሲያጣጥር “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ!” ብሏል።—ሉቃስ 23:46
በጊዜ ሂደት በግልጽ እንደታየው ዲያብሎስ፣ ሁሉም ሰው እውነተኛውን አምላክ ማገልገሉን እንዲተው ማድረግ አልቻለም። ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ይሖዋን አውቀው ‘በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም ሐሳባቸው ሊወዱት’ ችለዋል። (ማቴዎስ 22:37) ለይሖዋ ያላቸው የማያወላውል ታማኝነት ሰይጣን ያነሳው ክስ ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል። አንተም ብትሆን ታማኝ በመሆን የዲያብሎስን ውሸታምነት ልታረጋግጥ ትችላለህ።
ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አምላክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ታዲያ አንተ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲሁም ‘እውነተኛውን አምላክና የላከውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ’ ጊዜ በመመደብ ነው።—ዮሐንስ 17:3
ሰይጣን ሰው አምላክን ለማገልገል የሚነሳሳበት ምክንያት አጠያያቂ እንደሆነ በመግለጽ የሰዎችን ታማኝነት አጠራጣሪ አድርጎታል። እውቀት አምላክን ለማገልገል እንዲያነሳሳህ ከተፈለገ ወደ ልብህ ጠልቆ መግባት አለበት። ለዚህ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲሁ መረጃ ከመሰብሰብ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልግሃል። በምትማረው ነገር ላይ የማሰላሰልን ልማድ አዳብር። (መዝሙር 143:5) መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በምታነብበት ጊዜ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ጊዜ ወስደህ አሰላስል:- ‘ያነበብኩት ነገር ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? እዚህ ላይ የትኞቹ የይሖዋ ባሕርያት ተገልጸዋል? እኔስ በሕይወቴ ውስጥ እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ የሚያስፈልገኝ በየትኞቹ መንገዶች ነው? አምላክ የሚወዳቸውና የሚጠላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ያገኘሁት እውቀት ስለ አምላክ ያለኝን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?’ በዚህ መንገድ ማሰላሰልህ ለፈጣሪ ፍቅርና አድናቆት እንዲያድርብህ ያደርጋል።
ለአምላክ ታማኝ መሆን የሚገባን ከሃይማኖታዊ እምነታችን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ብቻ አይደለም። (1 ነገሥት 9:4) ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆን በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ንጹሕ ሥነ ምግባር መያዝን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ታማኝነትህን መጠበቅህ ምንም የሚያስቀርብህ ነገር አይኖርም። ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ስለሆነ አንተም በሕይወትህ እንድትደሰት ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነህ እንድትኖርና በዚያውም አስደሳች ሕይወት እንዲኖርህ ብሎም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኝ ልታስወግዳቸው የሚገቡ አንዳንድ ተግባሮች ምን እንደሆኑ ተመልከት።
ከጾታ ብልግና ራቅ
ይሖዋ ራሱ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጋብቻን በተመለከተ መሥፈርት ያወጣ ሲሆን እርሱም “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:21-24) ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ስለሆኑ ከትዳር ጓደኛቸው ውጪ ከሌላ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ባለመፈጸም አምላክ በጋብቻ ረገድ ላደረገው ዝግጅት አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 13:4) “መኝታ” የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው በሕግ በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት ነው። ከሁለት አንዳቸው ከጋብቻ ውጪ የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ይህ ድርጊት ምንዝር ነው፤ እንዲህ ማድረጋቸው ደግሞ ከአምላክ ዘንድ ቅጣት ሊያስከትልባቸው ይችላል።—ሚልክያስ 3:5
ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ስለ መፈጸምስ ምን ሊባል ይችላል? ይህም ቢሆን ይሖዋ ካወጣው የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር ይጋጫል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት እንድትርቁ ነው’ በማለት ይናገራል። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ግብረ ሰዶምም ሆነ በዘመዳሞች መካከልና ከእንስሳ ጋር የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት በአምላክ ላይ የሚሠሩ ኃጢአቶች ናቸው። (ዘሌዋውያን 18:6, 23፤ ሮሜ 1:26, 27) አምላክን ማስደሰትና በሕይወቱም እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከሥነ ምግባር ብልግና መራቅ አለበት።
ከጋብቻ በፊት የጾታ ስሜትን የሚያነሳሳ ድርጊት መፈጸምስ? ይህ ተግባርም ቢሆን ይሖዋን ያሳዝናል። (ገላትያ 5:19) አእምሮም ጭምር ከብልግና ሐሳቦች የጸዳ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ኢየሱስ “ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” ብሏል። (ማቴዎስ 5:28) እነዚህ የኢየሱስ ቃላት የብልግና ሥዕሎችን የሚያሳዩ ጽሑፎችን፣ ፊልሞችን፣ ወይም የኢንተርኔት ገጾችን በመመልከት ረገድም ሆነ ስለ ወሲባዊ ድርጊቶች የሚያወሱ ዘገባዎችን በማንበብ እንዲሁም የብልግና ግጥሞችን የያዙ ዘፈኖችን በማዳመጥ በኩል በእኩል ደረጃ ይሠራሉ። እንደነዚህ ካሉት ነገሮች መራቅ አምላክን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ በአንድ ሰው ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ስለ ማሽኮርመምስ ምን ሊባል ይችላል? ማሽኮርመም “ከልብ ያልሆነ የፍቅር መግለጫ ወይም የጾታ ስሜትን የሚያነሳሳ” ባሕርይ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ያገቡ ወንዶችና ሴቶች ከትዳር ጓደኛቸው ውጪ ለሌላ ሰው እንዲህ ዓይነት ትኩረት መስጠታቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት መጣስ ሲሆን ይህ ዓይነቱ ድርጊት ለይሖዋ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። (ኤፌሶን 5:28-33) ያላገቡ ሰዎችም ቢሆኑ እንዲሁ ለመደሰት ብለው ብቻ እርስ በርሳቸው የፍቅር መግለጫዎችን መለዋወጣቸው ምንኛ አግባብነት የጎደለው ድርጊት ነው! እንዲህ ዓይነቱን ማሽኮርመም ሌላኛው ወገን የምር እንደሆነ አድርጎ ቢወስደውስ? ይህ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን ስሜታዊ ሥቃይ አስበው። ማሽኮርመም ወደ ምንዝር ወይም ወደ ዝሙት ሊመራ የሚችል መሆኑም በጥሞና ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን መጠበቁ ለራሱ የሚኖረውን አክብሮት ይጨምርለታል።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
በሌሎች የሕይወት ዘርፎችም አምላክን ማስደሰት
የአልኮል መጠጦች በብዙ አገሮች ውስጥ እንደ ልብ ይገኛሉ። ታዲያ መጠጣት ስህተት ነው? ቅዱሳን ጽሑፎች ወይን፣ ቢራ ወይም ሌላ ዓይነት የአልኮል መጠጥን በልኩ መጠጣትን አይከለክሉም። (መዝሙር 104:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይሁን እንጂ ከልክ በላይ መጠጣትና መስከር በአምላክ ዓይን ኃጢአት ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) ከልክ በላይ በመጠጣት ጤንነትህን ለመጉዳትና የቤተሰብ ሕይወትህን ለመበጥበጥ እንደማትፈልግ ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 23:20, 21, 29-35
ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:5) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 6:18) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለግህ አትዋሽ። (ምሳሌ 6:16-19፤ ቈላስይስ 3:9, 10) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት ይመክራል።—ኤፌሶን 4:25
የቁማር ጨዋታም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላው ጉዳይ ነው። ቁማር መጫወት በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ቢሆንም በሌሎች ኪሳራ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ስግብግብነትን ያሳያል። “ያለ አግባብ የሚገኝ ጥቅምን” የሚያሳድዱ ሰዎች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አያገኙም። (1 ጢሞቴዎስ 3:8) ይሖዋን ደስ ለማሰኘት የምትፈልግ ከሆነ ሎተሪን፣ ቢንጎንና በፈረስ ግልቢያ መወራረድን ጨምሮ ከማንኛውም ዓይነት ቁማር መራቅ ይኖርብሃል። ይህን ስታደርግ ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችልህ ተጨማሪ ገንዘብ ይኖርሃል።
ስርቆት ማለትም የራስህ ያልሆነውን ነገር መውሰድ ሌላው የስግብግብነት መገለጫ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አትስረቅ” ይላል። (ዘፀአት 20:15) አንድን የተሰረቀ ዕቃ እያወቁ መግዛትም ሆነ ባለቤቱን ሳያስፈቅዱ የሰው ንብረት መውሰድ ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 4:28) የይሖዋ ወዳጆች የሥራ ሰዓታቸውን አላግባብ በመጠቀም ፈንታ ሥራቸውን በሐቀኝነት ያከናውናሉ። ‘በሁሉም መንገድ በሐቀኝነት ለመኖር’ ይፈልጋሉ። (ዕብራውያን 13:18 NW) ንጹሕ ሕሊና አንድ ሰው የአእምሮ ሰላም እንዲኖረው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።
የግልፍተኝነት ባሕርይ ያለውን ሰው አምላክ እንዴት ይመለከተዋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 22:24) ልጓም ያልተበጀለት ቁጣ ብዙውን ጊዜ የዓመጽ ድርጊት ወደ መፈጸም ይመራል። (ዘፍጥረት 4:5-8) ስለ መበቀልም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቍጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።” (ሮሜ 12:17-19) ይህን ምክር ስንከተል ሕይወታችን ይበልጥ ሰላማዊ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ደስታችንን ይጨምርልናል።
አንተም ሊሳካልህ ይችላል
ለአምላክ ታማኝ ሆነህ እንዳትኖር ለማድረግ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ቢደርሱብህም ይህንን በማድረግ ረገድ ሊሳካልህ ይችላል? አዎን፣ ትችላለህ። የአምላክ ቃል “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት ስለሚናገር በተነሳው የታማኝነት ጥያቄ ረገድ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን በተግባር መመስከር እንድትችል አምላክ እንደሚፈልግ እወቅ።—ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም
ይሖዋ በፊቱ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንድትችል እንዲያበረታህ ጸልይ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ስለዚህ የአምላክ ቃል የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ከመጽሐፍ ቅዱስ በምትማረው ነገር ላይ በአድናቆት ማሰላሰልህ ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንድታዳብር የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ እሱን እንድታስደስት ያነሳሳሃል። አንደኛ ዮሐንስ 5:3 “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” በማለት ይናገራል። በአካባቢህ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና በደስታ ይረዱሃል። ከእነሱ ጋር እንድትወያይ አለዚያም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ ፈተና ቢደርስበትም በታማኝነት ጸንቷል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ አምላክ ቃል ያለህን እውቀት ማሳደግህ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያለህን ቁርጠኝነት ያጠናክራል