በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኤብላ—ተረስታ የነበረችው ጥንታዊት ከተማ

ኤብላ—ተረስታ የነበረችው ጥንታዊት ከተማ

ኤብላ—ተረስታ የነበረችው ጥንታዊት ከተማ

በ1962 የበጋ ወቅት ፓኦሎ ማቲያ የተባለ አንድ ጣሊያናዊ አርኪኦሎጂስት በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ሜዳማ አካባቢዎች ላይ ጥናት ያካሂድ ነበር። በወቅቱ የሶሪያ መካከለኛ ክፍል በአርኪኦሎጂ ረገድ እምብዛም ጠቃሚ እንዳልሆነ ይታሰብ ስለነበር ይህ ወጣት በቦታው ምን ሊያገኝ እንደሚችል እርግጠኛ አልነበረም። ሆኖም ከሁለት ዓመታት በኋላ ከአሌፖ በስተ ደቡብ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቴል ማርዲክ የተከናወነው ቁፋሮ ውጤት ያስገኘ ሲሆን ብዙዎች ይህን ውጤት ‘ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የ20ኛው መቶ ዘመን አርኪኦሎጂያዊ ግኝት’ በማለት ይገልጹታል።

ጥንታዊ ጽሑፎች ኤብላ የተባለች ከተማ እንደነበረች ቢገልጹም ይህቺ ከተማ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙት በርካታ ጉብታዎች መካከል በየትኛው ሥር እንደምትገኝ የሚያውቅ አልነበረም። አንድ ጽሑፍ የአካድ ንጉሥ የነበረው ሳርጎን “ማሬ፣ ያርሙቲ እና ኤብላ” በተባሉት ከተሞች ላይ ስለተቀዳጀው ድል ይዘግባል። በሌላ ጽሑፍ ላይ ደግሞ የሱሜሪያን ንጉሥ የሆነው ጉዳ “ከኢብላ [ኤብላ] ተራሮች” ስላገኛቸው ምርጥ ጣውላዎች ገልጿል። በካርናክ፣ ግብጽ በተገኘና ፈርዖን ቱሞሰ ሣልሳዊ ድል ያደረጋቸውን ጥንታዊ ከተሞች ዝርዝር በያዘ ጽሑፍ ላይም ኤብላ የሚለው ስም ሰፍሯል። አርኪኦሎጂስቶች ኤብላን ለማግኘት ይጥሩ የነበረው ለምን እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል።

በዚህ አካባቢ የተደረጉ ተጨማሪ ቁፋሮዎች ፍሬ አስገኝተዋል። በ1968 አይቢት ሊም የተባለ የኤብላ ንጉሥ ሐውልት ስባሪ ተገኘ። በዚህ ሐውልት ላይ በአካዲያን ቋንቋ የተቀረጸ መሓላ የተገኘ ሲሆን ጽሑፉም ሐውልቱ፣ “በኤብላ ላይ ለምታበራው” ኢሽታር ለተባለችው አምላክ የተሰጠ መሆኑን ይገልጻል። በእርግጥም በአርኪኦሎጂ አማካኝነት “አዲስ ቋንቋ፣ አዲስ ታሪክ እንዲሁም አዲስ ባሕል” እየተገኘ ነበር።

በ1974/75 ደግሞ የኤብላ ስም በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጠቀሰባቸው የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ ጽላቶች የተገኙ ሲሆን ይህም የጥንቷ ኤብላ አሁን ቴል ማርዲክ ከሚባለው ጉብታ በታች እንደነበረች አረጋግጧል። ከዚህም በላይ ከተማይቱ ቢያንስ ለሁለት ጊዜያት በዚያ ቦታ ላይ ተሠርታ እንደነበር በቁፋሮ የተገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ታላቅ ኃይል የነበራት ይህቺ ከተማ በአንድ ወቅት በጠላት ተደመሰሰች። ከጊዜ በኋላ ኤብላ እንደገና የተገነባች ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ከጠፋች በኋላ ግን ለበርካታ ዘመናት ተረሳች።

በርካታ ታሪኮች ያሏት አንዲት ከተማ

የጥንት ከተሞች የሚገነቡት ደለላማ በሆኑና ለግብርና በሚያመቹ ሜዳማ አካባቢዎች ነበር፤ በጤግሮስና በኤፍራጥስ ወንዞች መካከል ያለው አካባቢ ለዚህ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የመጀመሪያዎቹ ከተሞች የሚገኙት በመስጴጦሚያ ነበር። (ዘፍጥረት 10:10) ኤብላ የሚለው ስም “ነጭ ዓለት” የሚል ትርጉም እንዳለው ይገመታል፤ ይህም ከተማዋ በተቆረቆረችበት ቦታ ላይ የሚገኘውን በሃ ድንጋይ ያመለክታል። ይህ ቦታ የተመረጠው አካባቢው በበሃ ድንጋይ የተሸፈነ መሆኑ የተፈጥሮ ውኃ መኖሩን ስለሚጠቁም ይመስላል፤ ከትላልቅ ወንዞች ርቆ ለሚገኝ ከተማ እንዲህ ያለው የውኃ አቅርቦት በጣም አስፈላጊ ነበር።

በኤብላ ዝናብ እምብዛም ስለማይጥል በዚህ አካባቢ ማልማት የሚቻለው ጥራጥሬ፣ ወይንና የወይራ ዛፍ ብቻ ነበር። አካባቢው ለከብት እርባታ በተለይም ለበጎች ተስማሚ ነው። ኤብላ፣ በመስጴጦሚያ እና በሜድትራኒያን የባሕር ዳርቻ መካከል ባለው ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኝ መሆኗ ለጣውላ፣ ውድ ለሆኑ ድንጋዮችና ለብረት ንግድ አመቺ እንድትሆን አድርጓታል። ከተማዋ 200,000 ያህል ሕዝብ የሚኖርበትን አካባቢ የምታስተዳድር ሲሆን ከእነዚህም አሥር በመቶ የሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎች ነበሩ።

በቁፋሮ የተገኘ የአንድ ታላቅ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ እንደሚጠቁመው ኤብላ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር። ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚያስገባው በር ርዝመት ከ12-15 ሜትር ይደርሳል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃያል እየሆነ የመጣውን አስተዳደር ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ቤተ መንግሥቱን በየጊዜው ማስፋት አስፈልጎ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ውስብስብ የሆነ የሥልጣን ተዋረድ የነበራቸው ሲሆን ንጉሡና ንግሥቲቱ “በጌቶች” እና “በሽማግሌዎች” ይረዱ ነበር።

በኤብላ ከተማ ፍርስራሽ ውስጥ ከ17,000 የሚበልጡ የሸክላ ጽላቶችና ስብርባሪዎች ተገኝተዋል። እነዚህ ስብርባሪዎች ከእንጨት በተሠሩ መደርደሪያዎች ላይ በጥንቃቄ የተቀመጡ ከ4,000 በላይ ሙሉ ጽላቶች እንደነበሩ ይገመታል። ኤብላ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ታደርግ እንደነበር እነዚህ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ለአብነት ያህል፣ በቁፋሮ ከተገኙት የሁለት ፈርዖኖች ንጉሣዊ ምልክቶች መገንዘብ እንደሚቻለው ከተማዋ ከግብጽ ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት። ጽላቶቹ በአብዛኛው የተጻፉት በሱሜሪያ ቋንቋ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት ነው። አንዳንዶቹ ጽላቶች ግን በኤብላ ቋንቋ (በጣም ጥንታዊ የሆነ ሴማዊ ቋንቋ ነው) የተጻፉ ሲሆን ለእነዚህ ሰነዶች ምስጋና ይግባቸውና ይህን ቋንቋ መፍታት ተችሏል። የምሥራቃዊ እስያን ቋንቋዎች የሚያጠኑ ሰዎች ጥንታዊ የሆነውን ይህን ሴማዊ ቋንቋ ማግኘታቸው አስገርሟቸዋል። አንዳንዶቹ ጽላቶች በሱሜሪያንና በኤብላ ቋንቋ የተጻፉ ቃላትን እንደያዙ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ኤብላ—አሌ ኦሪጂኒ ዴላ ቺቬልታ ኧርባና (ኤብላ—የከተሞች ሥልጣኔ መገኛ) የተባለው መጽሐፍ እነዚህን ጽላቶች “እስካሁን ካወቅናቸው ሁሉ ጥንታዊ የሆኑ መዝገበ ቃላት” በማለት ጠርቷቸዋል።

የኤብላ ተዋጊዎች ጠላቶቻቸውን ሲገድሉ ወይም አንገታቸውን ቀልተው ጭንቅላታቸውን ሲያቀርቡ የሚያሳዩ የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች በቁፋሮ መገኘታቸው ኤብላ ወታደራዊ ኃይል እንደነበራት ይጠቁማል። ይሁን እንጂ አሦርና ባቢሎን ኃያል መንግሥታት ሲሆኑ የኤብላ ድምቀት አከተመለት። በወቅቱ ምን እንደተፈጸመ በትክክል ማወቅ ባይቻልም መጀመሪያ ቀዳማዊ ሳርጎን (በኢሳይያስ 20:1 ላይ የተጠቀሰው ሳርጎን አይደለም) ከዚያም የልጅ ልጁ ናራም ሲን በኤብላ ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ይመስላል። ከአርኪዮሎጂያዊ መረጃዎች መመልከት እንደሚቻለው ውጊያው ጭካኔ የተሞላበትና አረመኔያዊ ነበር።

ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከተማዋ በድጋሚ ያንሰራራች ሲሆን በአካባቢው ገናና እስከ መሆንም ደርሳ ነበር። አዲሷ ኤብላ በጥንቃቄ በተሠራ ንድፍ መሠረት መገንባቷ ግርማ ሰጥቷታል። በታችኛው የከተማዋ ክፍል ኢሽታር ለተባለችው እንስት አምላክ የተለየ ቅዱስ ቦታ ነበር፤ ባቢሎናውያንም ኢሽታርን የመራባት አምላክ እንደሆነች አድርገው ይመለከቷታል። በባቢሎን ፍርስራሾች መካከል ስለተገኘው ስመ ጥር የኢሽታር በር ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። በኤብላ የሚገኘው ግርማ ሞገስ የተላበሰ አስደናቂ ሕንፃ፣ ኤሽታር ለተባለችው አምላክ የተቀደሱ አንበሶች መኖሪያ የነበረ ይመስላል። ይህ ደግሞ ወደ ኤብላ ሃይማኖት ይመራናል።

በኤብላ የነበረው ሃይማኖት

በጥንቶቹ ምሥራቃዊ አካባቢዎች እንደሚደረገው ሁሉ በኤብላም በርካታ አማልክት ነበሩ። ከእነዚህም አንዳንዶቹ በኣል፣ ሃዳድ (በአንዳንድ የሶሪያ ነገሥታት ስሞች ላይ የሚጨመር መጠሪያ) እና ዳጎን ናቸው። (1 ነገሥት 11:23፤ 15:18፤ 2 ነገሥት 17:16) የኤብላ ሰዎች እነዚህን አማልክት በሙሉ ይፈሩ ነበር። ሌላው ቀርቶ የሌሎች ሕዝቦችን አማልክት እንኳ ያከብሩ ነበር። አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች እንደሚያሳዩት በተለይ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት፣ ነገሥታት የነበሩ የቀድሞ አባቶችም እንደ አማልክት ተቆጥረው ይመለኩ ነበር።

የኤብላ ሰዎች በአማልክቶቻቸው ብቻ ተማምነው የሚቀመጡ አልነበሩም። አዲሷ የኤብላ ከተማ ማንኛውንም ጠላት የሚያስፈራ ድርብ የግንብ አጥር ነበራት። የውጨኛው ግንብ ዙሪያ 3 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን እነዚህ አጥሮች አሁንም ድረስ በግልጽ ይታያሉ።

ያም ሆኖ ግን በድጋሚ የተሠራችው የኤብላ ከተማ መውደቋ አልቀረም። ኃያል የነበረችውን ኤብላን በ1600 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የደመሰሷት ኬጢያውያን ሳይሆኑ አይቀርም። አንድ ጥንታዊ ግጥም እንደሚገልጸው ኤብላ “እንደ ሸክላ ዕቃ እንክትክት ብላለች።” ብዙም ሳይቆይ ከተማዋ ከታሪክ ገጾች መፋቅ ጀመረች። በ1098 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን የወረሩ የመስቀል ጦረኞች የጻፉት መዝገብ ጥንት ኤብላ የነበረችበትን ቦታ ይጠቅሳል፤ ጽሑፉ ቦታውን ማርዲክ ብሎ በመጥራት ርቆ የሚገኝ ክልል እንደሆነ ይገልጻል። ኤብላ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ እንደገና እስክትታወስ ድረስ ፈጽማ ተረስታ ኖራለች።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኤብላ እና መጽሐፍ ቅዱስ

በ1976 ቢብሊካል አርኪኦሎጂስት በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራንን ትኩረት ስቦ ነበር። በኤብላ የተገኙትን ጽላቶች የተረጎማቸው ሰው፣ በጽላቶቹ ላይ ከተጻፉት ነገሮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ ከበርካታ ዘመናት በኋላ የጠቀሳቸው ሰዎችና ቦታዎች ስም ሊገኝ እንደሚችል ገልጾ ነበር። አንዳንዶች ይህ ጸሐፊ ከተናገረው ነገር አልፈው በመሄድ ኤብላ፣ የዘፍጥረት ዘገባ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚያረጋግጥ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ እንደያዘች መጻፍ ጀመሩ። a ሚቸል ዳሁድ የተባሉት የካቶሊክ ቄስ በኤብላ የተገኙ “የሸክላ ጽላቶች መጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ ያደርጉታል” በማለት ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል እኚህ ቄስ ጽላቶቹ “በእስራኤላውያን አምላክ ስም መጠቀም የተጀመረው መቼ እንደሆነ” ግልጽ ያደርጉልናል ብለው ያምናሉ።

በአሁኑ ጊዜ በኤብላ የተገኙት ጽሑፎች ትክክለኛ ጥናት እየተደረገባቸው ነው። ዕብራይስጥም ሆነ የኤብላ ቋንቋ የመጡት ከሴማዊ ቋንቋዎች በመሆኑ የአንዳንድ ከተሞች ወይም ግለሰቦች ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው ጋር ሊመሳሰል ወይም አንድ ዓይነት ሊሆን እንደሚችል አይካድም። ይህ መሆኑ ግን በኤብላ ጽሑፎች ላይ የተገለጹት ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን ወይም ሰዎችን እንደሚያመለክቱ ማስረጃ አይሆንም። በኤብላ የተገኙት ነገሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በሚደረገው ጥናት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ወደፊት የሚታይ ይሆናል። መለኮታዊውን ስም በተመለከተ ግን ቢብሊካል አርኪኦሎጂስት የተባለውን መጽሔት የጻፈው ሰው በኤብላ በተገኙት ጽላቶች ላይ “ያህዌህ” የሚለው ስም መጠቀሱን እንዳልጻፈ ተናግሯል። አንዳንዶች ተብሎ የተተረጎመው በሽብልቅ ቅርጽ የተጻፈ ምልክት የኤብላ ነዋሪዎች ከሚያመልኳቸው በርካታ አማልክት መካከል አንዱን እንደሚያመለክት ሲገልጹ ሌሎች በርካታ ባለሞያዎች ደግሞ የሰዋሰው ምልክት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ ምልክቱ፣ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን አያመለክትም።—ዘዳግም 4:35 NW፤ ኢሳይያስ 45:5 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አርኪኦሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ እንዴት እንደሚደግፍ የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ታላቁ ባሕር

ከነዓን

ሶርያ

አሌፖ

ኤብላ (ቴል ማርዲክ)

የኤፍራጥስ ወንዝ

[ምንጭ]

አርኪኦሎጂስት:- Missione Archeologica Italiana a Ebla - Università degli Studi di Roma ‘La Sapienza’

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ ታላቅ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1750 ገደማ የተሠራ የወርቅ ሐብል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሠዓሊ በኤብላ የነበሩትን የሸክላ ጽላቶች አስመስሎ የሠራው ሥዕል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ ጽላቶች

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግብጻውያን በትረ መንግሥት፣ ከ1750-1700 ከክርስቶስ ልደት በፊት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የኤብላ ተዋጊ የጠላቶቻቸውን ጭንቅላት ይዞ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሽታር ለተባለችው እንስት አምላክ የተቀደሰ ሐውልት

[ምንጭ]

Missione Archeologica Italiana a Ebla - Università degli Studi di Roma ‘La Sapienza’

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከቤተ መንግሥቱ ፍርስራሽ በስተቀር የሁሉም ምሥሎች ምንጭ:- Missione Archeologica Italiana a Ebla - Università degli Studi di Roma ‘La Sapienza’