ጳውሎስ ወደ ቤርያ ያደረገውን ጉዞ እንቃኝ
ጳውሎስ ወደ ቤርያ ያደረገውን ጉዞ እንቃኝ
የሁለቱ ሚስዮናውያን ተልእኮ የተሳካ ሲሆን በጣም ብዙ ሰዎች አማኞች ሆነዋል። በኋላም የሕዝብ ዓመጽ ተቀሰቀሰ። በመሆኑም አዲስ ለተቋቋመው ጉባኤና ለራሳቸው ደኅንነት ሲባል ሁለቱ ሚስዮናውያን በውድቅት ሌሊት አካባቢውን ለቅቀው እንዲሄዱ ተወሰነ። በውሳኔው መሠረት ጳውሎስና ሲላስ በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የመቄዶንያ የወደብ ከተማ ከሆነችው ተሰሎንቄ ሸሹ። ከዚያም ወደሚቀጥለው የስብከት ክልላቸው ወደ ቤርያ አቀኑ።
በዛሬው ጊዜ ቤርያ (የአሁኗ ቬርዬ) ያለችበትን አካባቢ የሚጎበኝ ሰው ልክ እንደ ጥንቶቹ ተጓዦች ከተማዋን ለምለም በሆነው ቬርሚኦ ተራራ ግርጌ በስተ ምሥራቅ ሊመለከታት ይችላል። ቤርያ ከተሰሎንቄ በስተ ደቡብ ምዕራብ 65 ኪሎ ሜትር፣ ከኤጂያን ባሕር ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከጥንት ሄለናውያን (ግሪካውያን) አማልክት መካከል ዋና ዋናዎቹ ይኖሩበታል ተብሎ በአፈ ታሪክ ይነገርለት የነበረው የኦሊምፐስ ተራራ ከተማዋን በደቡብ በኩል ያዋስናታል።
ቤርያ ጳውሎስ የሰበከባትና ብዙዎች ወደ ክርስትና የተለወጡባት ከተማ በመሆኗ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት ትስባለች። (የሐዋርያት ሥራ 17:10-15) እስቲ ጳውሎስ በቤርያ ያደረገውን ቆይታና የከተማዋን ታሪክ መለስ ብለን እንመርምር።
የቤርያ ጥንታዊ ታሪክ
ቤርያ መቼ እንደተቆረቆረች በትክክል የሚያውቅ የለም። የፍርግያ ጎሳዎች እንደሆኑ የሚገመቱት የመጀመሪያዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በመቄዶንያውያን ተባርረዋል። ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ታላቁ እስክንድር ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ መቄዶንያ እንድትበለጽግ ምክንያት ሆነ። በዚህ ጊዜ አስደናቂ ሕንጻዎችና ግንቦች እንዲሁም የድያ፣ የአርጤምስ፣ የአፖሎ፣ የአቴና እና የሌሎች የግሪክ አማልክት ቤተ መቅደሶች ተገንብተዋል።
አንድ የታሪክ መጽሐፍ እንደገለጸው ቤርያ ለብዙ ዘመናት “በአቅራቢያዋ ላሉትም ይሁን በግሪክ ሰሜናዊ ክፍል ለሚገኙ አካባቢዎች እድገት ትልቅ ሚና ተጫውታለች።” ከተማዋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችው በሮም መንግሥት በተገረሰሰው በመቄዶንያ የመጨረሻ ሥርወ መንግሥት ይኸውም በአንቲጎኒዶች ዘመን (306-168 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ነበር።
ሮማውያን ንጉሥ ፊሊፕ አምስተኛን በ197 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድል ባደረጉ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ሲገልጽ “የቀድሞው የኃይል ሚዛን ተዛባ፤ ሮም በምሥራቁ የሜዲትራንያን ክፍል ኃያል መንግሥት ሆነች” ብሏል። በ168 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ ሮማዊ ጄኔራል የመጨረሻው የመቄዶንያ ገዢ በነበረው በፐርሲየስ ላይ ወሳኝ ድል ተቀዳጀ። ዳንኤል 7:6, 7, 23) ከዚያ ጦርነት በኋላ ለሮም ከተንበረከኩት የመጀመሪያዎቹ የመቄዶንያ ከተሞች መካከል ቤርያ ትገኝበታለች።
ጦርነቱ የተካሄደው ከቤርያ በስተ ደቡብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በፒድና ነበር። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ የቆየው ግሪክ በሮም ተተካ። (በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በፖምፒ እና በጁሊየስ ቄሳር መካከል በነበረው ግጭት ምክንያት መቄዶንያ የጦር አውድማ ሆና ነበር። እንዲያውም ፖምፒ ጦሩንና የጦሩን ጠቅላይ መምሪያ ያሰፈረው በቤርያ አቅራቢያ ነበር።
ቤርያ በሮም አገዛዝ ዘመን ያገኘችው ብልጽግና
በፓክስ ሮማና ወይም በሮም የሰላም ዘመን ቤርያን የሚጎበኙ ሰዎች ድንጋይ የተነጠፈባቸውና ዳርና ዳሩ ላይ በየተወሰነ ርቀት የቆሙ ዓምዶች ያሏቸው መንገዶችን መመልከት ይችሉ ነበር። ከተማዋ የሕዝብ መታጠቢያዎች፣ ቲያትር ቤቶች፣ ቤተ መጻሕፍትና የትግል ግጥሚያ ማሳያ ሥፍራዎች ነበሯት። በተጨማሪም ቤርያ በቧንቧ የሚሰራጭ የመጠጥ ውኃና የመሬት ውስጥ የፍሳሽ ማስወገጃ ነበራት። ቤርያ በነጋዴዎች፣ በአርቲስቶችና በአትሌቶች የምትጎበኝ ዝነኛ የንግድ ማዕከል የነበረች ሲሆን የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮችንና ሌሎች ትርኢቶችን ለማየት ብዙ ተመልካቾች ወደ ከተማዋ ይጎርፉ ነበር። የባዕድ አገር ሰዎች የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚፈጽሙበት የአምልኮ ቦታ ማግኘት ይችሉ ነበር። አዎን፣ በመላዋ የሮም ግዛት ያሉ ሃይማኖቶች በዚህች ከተማ ይገኙ ነበር።
በቤርያ ከሚመለኩት አማልክት መካከል በሕይወት የሌሉ የሮም ነገሥታት ይገኙበታል። ንጉሠ ነገሥታትን ማምለክ የመጣው እንደ አምላክ ይታይ ከነበረው የታላቁ
እስክንድር አምልኮ ስለሆነ፣ ይህ ዓይነቱ አምልኮ ለቤርያ ሰዎች እንግዳ ነገር የሆነባቸው አይመስልም። ስለ ግሪካውያን ታሪክ የሚናገር አንድ ምንጭ እንዲህ ብሏል:- “በምሥራቃዊው ግዛት ይኖሩ የነበሩት ሄለናውያን [ግሪካውያን] ለነገሥታቶቻቸው አምልኮ አከል ክብር የመስጠት ልማድ ስለነበራቸው የሮማውያን ነገሥታትን አምልኮ በደስታ ተቀብለውታል። . . . በሳንቲሞቻቸው ላይ ንጉሠ ነገሥቱ አንጸባራቂ ዘውድ የደፋ አምላክ ተደርጎ ተቀርጿል። ለአማልክቶቻቸው እንደሚያደርጉት በጸሎትና በመዝሙር ያወድሱታል።” መሠዊያና ቤተ መቅደስ ተገንብተውለታል፤ መሥዋዕቶችም ይቀርቡለታል። ሌላው ቀርቶ ነገሥታት እንኳ የአትሌቲክስ፣ የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ውድድሮችን በሚጨምሩት የንጉሠ ነገሥት አምልኮ በዓላት ላይ ይገኙ ነበር።ቤርያ የባዕድ አምልኮ ማዕከል የሆነችው ለምንድን ነው? የመቄዶንያ ኮይኖን መቀመጫ ስለነበረች ነው። ኮይኖን ከተለያዩ የመቄዶንያ ከተሞች የመጡ ልዑካን የሚያደርጉትን ስብሰባ የሚያመለክት ነበር። ልዑካኑ በሮማውያን የበላይ ቁጥጥር ሥር ሆነው ከተሞቻቸውንና ክልሎቻቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በየጊዜው በቤርያ ይሰበሰቡ ነበር። ከስብሰባው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ለንጉሠ ነገሥቱ የሚከናወነውን የአምልኮ ሥርዓት በበላይነት መከታተል ይገኝበታል።
ጳውሎስና ሲላስ ከተሰሎንቄ ሸሽተው በሄዱባት ከተማ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር። በወቅቱ ቤርያ በሮማውያን ቁጥጥር ሥር ከዋለች ሁለት መቶ ዓመታት አልፈዋል።
ምሥራቹ በቤርያ ተሰበከ
ጳውሎስ በቤርያ መስበክ የጀመረው በከተማዋ ምኩራብ ውስጥ ነበር። ምን ምላሽ አግኝቶ ይሆን? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንደሚገልጸው በምኩራቡ ውስጥ የነበሩት አይሁዳውያን “ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ነበሩ፤ ምክንያቱም ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” (የሐዋርያት ሥራ 17:10, 11) እነዚህ ሰዎች “አስተዋዮች” ስለነበሩ ወጎቻቸውን የሙጥኝ ብለው አልያዙም። ከዚያ ቀደም ሰምተው የማያውቁት ነገር የተነገራቸው ቢሆንም ተጠራጣሪ አልሆኑም አሊያም በቁጣ አልገነፈሉም። የጳውሎስን መልእክት አንቀበልም ከማለት ይልቅ ልባቸውን ከፍተው ለማንም ሳይወግኑ በጥሞና ያዳምጡት ነበር።
እነዚህ አይሁዳውያን ጳውሎስ ያስተማራቸው ነገር እውነት መሆኑን መገንዘብ የቻሉት አንዴት ነው? የሰሟቸውን ነገሮች ተዓማኒነት ባለው መመዘኛ ስለገመገሙ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄና በትጋት ይመረምሩ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ማቲው ሄንሪ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል:- “ጳውሎስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እየጠቀሰ ምክንያቱን ያስረዳቸውና የሚናገረው ነገር ትክክል መሆኑን ለማሳመን ከብሉይ ኪዳን ይጠቅስላቸው ስለነበር ሐሳቡ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ከራሳቸው
መጽሐፍ ቅዱስ ማየት፣ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መመርመርና ፍሬ ነገሩን ማጤን እንዲሁም ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ማወዳደር ይችሉ ነበር። በዚህ ሁኔታ ጳውሎስ የደረሰበት መደምደሚያ ምክንያታዊና ትክክለኛ፣ የመከራከሪያ ነጥቦቹም አሳማኝ መሆናቸውን ማረጋገጥና ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይችሉ ነበር።”ይህ ለአንድ አፍታ ላይ ላዩን አየት ከማድረግ ፈጽሞ የተለየ ነው። የቤርያ ሰዎች በሰንበት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በትጋት ለማጥናት ጊዜ መድበው ነበር።
ይህ ምን ውጤት እንዳስገኘላቸው አስብ። በቤርያ የሚኖሩ ብዙ አይሁዳውያን መልእክቱን ተቀብለው አማኞች ሆነዋል። ወደ ይሁዲነት የተለወጡትን ጨምሮ በርካታ ግሪካውያንም አማኞች ለመሆን በቅተዋል። ይሁንና ይህ ሁኔታ ከተቃዋሚዎች እይታ አላመለጠም። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ሁኔታውን በሰሙ ጊዜ “ሕዝቡን ለመቀስቀስና ለማነሣሣት” ወዲያውኑ ወደ ቤርያ ሄዱ።—የሐዋርያት ሥራ 17:4, 12, 13
ጳውሎስ ቤርያን ለቅቆ ለመሄድ የተገደደ ቢሆንም መስበኩን አላቆመም። እንዲያውም ወደ አቴና በሚሄድ መርከብ ተሳፈረ። (የሐዋርያት ሥራ 17:14, 15) ሆኖም ጳውሎስ የሚደሰትበት ምክንያት ነበረው። ያከናወነው የስብከት ሥራ በቤርያ ክርስትና እንዲቋቋም አስችሏል። በዛሬው ጊዜም ፍሬ እያፈራ ነው።
አዎን፣ በአሁኑ ጊዜም ‘ሁሉን ነገር ፈትነው’ ጠንካራ መሠረት ያለውንና እውነተኛ የሆነውን ነገር አጥብቀው ‘የያዙ’ ሰዎች በቤርያ (በቬርዬ) ይገኛሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:21) በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ እድገት እያደረጉ ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በማካፈል ልክ እንደ ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ተጠምደዋል። ቅን የሆኑ ሰዎችን በመፈለግ ከቅዱሳን መጻሕፍት ምክንያቱን ያስረዳሉ። ይህን የሚያደርጉት እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይል ለተግባር እንዲያነሳሳቸው ለመርዳት ነው።—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ በከፊል
ሚስያ
ጢሮአዳ
ፊልጵስዩስ
ናጱሌ
መቄዶንያ
አንፊጶል
ተሰሎንቄ
ቤርያ
ግሪክ
አቴና
ቆሮንቶስ
አካይያ
እስያ
ኤፌሶን
ሩድ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላቁ እስክንድር የግሪክ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ የተቀረጸበት የብር ሳንቲም
[ምንጭ]
ሳንቲም:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤርያ (በቬርዬ) ወደሚገኘው የአይሁዳውያን ሰፈር የሚያስገባ በር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኗ ቤርያ (በቬርዬ) የሚገኝ ጥንታዊ ምኩራብ