በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሀብት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ዘላቂ ብልጽግና አስገኝቶልናል

ሀብት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ዘላቂ ብልጽግና አስገኝቶልናል

የሕይወት ታሪክ

ሀብት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ዘላቂ ብልጽግና አስገኝቶልናል

ዶሬቲያ ስሚዝ እና ዶራ ዋርድ እንደተናገሩት

የምንፈልገው ሀብት ምን ዓይነት ነበር? ኢየሱስ ‘ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ሲል ባዘዘው ሥራ ላይ በቅንዓት መካፈል በጀመርንበት ወቅት ገና ወጣቶች ነበርን። (ማቴዎስ 28:19) ያደረግነው ጥረት ዘላቂ ብልጽግና ያስገኘልን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንንገራችሁ።

ዶሬቲያ፦ የተወለድኩት አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ በ1915 ሲሆን ለቤተሰባችን ሦስተኛ ልጅ ነኝ። የምንኖረው በዩናይትድ ስቴትስ ሚሺገን ውስጥ በምትገኘው ሆዌል ከተማ አቅራቢያ ነበር። ምንም እንኳ አባቴ ሃይማኖተኛ ሰው ባይሆንም እናቴ ግን ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ነበረች። እናታችን አሥርቱን ትእዛዛት እንድንጠብቅ ለማስተማር ብትሞክርም እኔም ሆንኩ ወንድሜ ዊልስ እንዲሁም እህቴ ቪዮላ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች አለመሆናችን ያስጨንቃት ነበር።

የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ የፕሬስባይቴሪያን ሃይማኖት ተከታይ በመሆን መጠመቅ እንደሚኖርብኝ ወሰነች። በተጠመቅሁበት ቀን የነበረውን ሁኔታ አሁን ድረስ በደንብ አስታውሳለሁ። ከእኔ ጋር እናቶቻቸው የታቀፏቸው ሁለት ሕፃናት ተጠምቀው ነበር። ከእነዚያ ሕፃናት ጋር በመጠመቄ እንደተዋረድኩ ተሰምቶኝ ነበር። ቄሱ ውኃ ወስደው ጭንቅላቴ ላይ በመርጨት ጥቂት ቃላትን ያጉተመተሙ ቢሆንም የተናገሩት ነገር አልገባኝም። እውነቱን ለመናገር፣ ስለ ጥምቀት ከሁለቱ ሕፃናት የተሻለ እውቀት አልነበረኝም!

በ1932 አንድ ቀን አንድ መኪና መጥቶ በራችን ላይ ቆመ። እናቴ በሩን ስትከፍት ሃይማኖታዊ መጻሕፍት የያዙ ሁለት ወጣት ወንዶች ቆመው ነበር። አንደኛው ‘አልበርት ሽሮደር እባላለሁ’ በማለት ራሱን አስተዋወቀና በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎችን ለእናቴ አሳያት። እናቴም መጽሐፎቹን ተቀበለች፤ እነዚህ ጽሑፎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንድታስተውል ረድተዋታል።

ሀብት ለማግኘት የማደርገውን ጥረት ጀመርኩ

ከጊዜ በኋላ ከእህቴ ጋር ለመኖር ወደ ዴትሮይት ከተማ ሄድኩ። እዚያም እህቴን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስጠኗት ከአንዲት አረጋዊ እህት ጋር ተዋወቅሁ። ያደርጉት የነበረው ውይይት እናቴ ጋር በነበርኩበት ወቅት እናዳምጠው የነበረውን ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም አስታወሰኝ። በዚያ ፕሮግራም ላይ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተመሠረተ የ15 ደቂቃ ንግግር ይቀርብ የነበረ ሲሆን ንግግሩን የሚያቀርበው በወቅቱ የሚካሄደውን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ነበር። በ1937 በዴትሮይት የመጀመሪያ ከሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርን። ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ተጠመቅሁ።

በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሚስዮናውያንን የሚያሠለጥን ጊልያድ የተባለ ትምህርት ቤት ኒው ዮርክ በሚገኘው ሳውዝ ላንሲንግ ከተማ ውስጥ እንደሚከፍቱ የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። ከዚህ ትምህርት ቤት የሚመረቁ አንዳንድ ተማሪዎች ውጭ አገር ሄደው የማገልገል አጋጣሚ እንደሚያገኙ ሳውቅ ‘ጊልያድ ገብቼ መሠልጠን አለብኝ!’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም ጊልያድ ለመግባት ግብ አወጣሁ። ወደ ሌሎች አገሮች ሄዶ “ሀብት” ለማግኘት ጥረት ማድረግ ማለትም የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን መፈለግ እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!—ሐጌ 2:6, 7

ቀስ በቀስ ግቤ ላይ ደረስኩ

በሚያዝያ 1942 ሥራዬን ለቀቅሁና ከሌሎች አምስት እህቶች ጋር ኦሃዮ፣ በምትገኘው ፊንድሌይ ከተማ ውስጥ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በወቅቱ ስብሰባዎች በቋሚነት የሚካሄዱበት ጉባኤ ባይኖርም በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች በቡድን ሆነን በማንበብ እርስ በርሳችን እንበረታታ ነበር። በአቅኚነት ማገልገል በጀመርኩበት የመጀመሪያው ወር ላይ 95 መጻሕፍትን ፍላጎት ላላቸው ሰዎች አበርክቼ ነበር! ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ፔንስልቬንያ በምትገኘው ቻምበርዝበርግ ከተማ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚህች ከተማ ከአይዋ የመጣችውን ዶራ ዋርድን ጨምሮ ከአምስት አቅኚዎች ጋር ተገናኘሁ። እኔና ዶራም የአገልግሎት ጓደኛሞች ሆንን። ሁለታችንም የተጠመቅነው በተመሳሳይ ዓመት ውስጥ ከመሆኑም በላይ ጊልያድ ትምህርት ቤት ሠልጥነን ውጭ አገር ሚስዮናዊ ሆነን የማገልገል ፍላጎት ነበረን።

በ1944 መጀመሪያ ላይ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ቀን መጣ! ሁለታችንም በጊልያድ ትምህርት ቤት አራተኛ ክፍል ውስጥ ገብተን እንድንሠለጥን የተጋበዝን መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሰን ሲሆን በዚያው ዓመት ነሐሴ ላይ ተመዘገብን። ታሪኬን ከመቀጠሌ በፊት ግን ሀብት ለማግኘት በማደርገው ጥረት ዶራ የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ የሆነችው እንዴት እንደሆነ ትንገራችሁ።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር የነበረኝ ጉጉት

ዶራ፦ እናቴ የአምላክን ቃል መረዳት እንድትችል ጸሎት የታከለበት ጥረት ታደርግ ነበር። አንድ እሁድ ቀን በሬዲዮ የሚተላለፈውን የጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ንግግር ስታዳምጥ አብሬያት ነበርኩ። ንግግሩ ሲያልቅ “እውነት ይህ ነው!” በማለት በአድናቆት ተናገረች። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ማጥናት ጀመርን። በ1935 የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ የይሖዋ ምሥክር ባቀረበው የጥምቀት ንግግር ላይ ተገኝቼ ነበር። ንግግሩ ራሴን ለይሖዋ እንድወስን ልባዊ ፍላጎት ስላሳደረብኝ ከሦስት ዓመት በኋላ ተጠመቅሁ። ራሴን ወስኜ መጠመቄ ትምህርቴን ለመጨረስ በቀሩኝ ዓመታት ውስጥ ግቦቼን እንዳልዘነጋ ረድቶኛል። አቅኚ ለመሆን ስለጓጓሁ ትምህርቴን ለመጨረስ ቸኩዬ ነበር።

በዚያን ጊዜ በአይዋ፣ ፎርት ዳጅ ከተማ የምንገኝ የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ደረጃ አንድ ላይ እንሰበሰብ ነበር። በወቅቱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቀላል አልነበረም። በዚያ ዘመን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች በጉባኤ ላይ ለመወያየት የሚረዱ ጥያቄዎች አልነበሯቸውም። እያንዳንዳችን ጥያቄዎችን አዘጋጅተን የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን ለሚመራው ወንድም እንድናመጣለት ይነገረን ነበር። ሁልጊዜ ሰኞ ማታ እኔና እናቴ ለእያንዳንዱ አንቀጽ ጥያቄ አውጥተን ጥናቱን ለሚመራው ወንድም አስቀድመን እንሰጠው ነበር።

ተጓዥ የበላይ ተመልካች በየጊዜው ጉባኤያችንን ይጎበኝ ነበር። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አንዱ በ12 ዓመቴ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል እንድጀምር የረዳኝ ጆን ቡዝ ነበር። አሥራ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ የአቅኚነት ማመልከቻ ፎርም መሙላት የምችለው እንዴት እንደሆነ ጠየቅሁትና አሳየኝ። በሌላ ጊዜ እንደምንገናኝና ጓደኝነታችን ለረጅም ጊዜ እንደሚዘልቅ ምንም አልጠረጠርኩም ነበር!

አቅኚ እያለሁ ብዙውን ጊዜ የማገለግለው ዶሬቲ አሮንሰን ከተባለች በ15 ዓመት ከምትበልጠኝ አቅኚ እህት ጋር ነበር። በ1943 በጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ክፍል እንድትሠለጥን እስከተጠራችበት ጊዜ ድረስ የአገልግሎት ጓደኛሞች ነበርን። እርሷ ከተጠራች በኋላ ግን በአቅኚነት ብቻዬን ማገልገሌን ቀጠልኩ።

ተቃውሞ ሊያስቆመን አልቻለም

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ተቀስቅሶ ስለነበር የ1940ዎቹ ዓመታት ለእኛ አስቸጋሪ ነበሩ። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ሰዎች ብዙ ጊዜ የተበላሸ እንቁላል፣ የበሰለ ቲማቲም አንዳንዴም ድንጋይ ጭምር ይወረውሩብን ነበር። ከፍተኛ ተቃውሞ ያጋጠመን ግን መጠበቂያ ግንብ እና ኮንሶሌሽን (አሁን ንቁ! ይባላል) የተባሉትን መጽሔቶች መንገድ ላይ ስናበረክት ነው። ተቃዋሚ ሃይማኖተኞች የገፋፉት አንድ ፖሊስ ከአሁን በኋላ በአደባባይ ስንሰብክ ካገኘን እንደሚያስረን በመናገር አስፈራራን።

መስበካችንን ለማቆም ፈቃደኞች ስላልነበርን ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። ከፖሊስ ጣቢያ ከተለቀቅን በኋላ እንደገና ወደዚያ መንገድ ተመልሰን እነዚያኑ መጽሔቶች ማበርከታችንን ቀጠልን። በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች በሰጡን ምክር መሠረት አቋማችንን ለመግለጽ ኢሳይያስ 61:1, 2ን እንጠቀም ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ወጣት ፖሊስ ሲይዘኝ ከመደንገጤ የተነሳ ጥቅሱን በቃሌ አነበነብኩለት። የሚገርመው ፖሊሱ ወዲያውኑ ፊቱን አዙሮ ጥሎኝ ሄደ! መላእክት እየጠበቁን እንዳለ ተሰማኝ።

የማይረሳ ቀን

በ1941 በሴይንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ በተካሄደው የአምስት ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ በመገኘቴ ተደስቼ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 18 የሆኑ ልጆች በስታዲየሙ ሜዳ ላይ እንዲሰበሰቡ ጠየቀ። በጥሪው መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ተሰበሰቡ። ወንድም ራዘርፎርድ መሐረቡን በማውለብለብ ሰላምታ ሲሰጠን እኛም መሐረባችንን በማውለብለብ ምላሽ ሰጠን። ወንድም ራዘርፎርድ ለአንድ ሰዓት ያህል ንግግር ካቀረበ በኋላ እንዲህ አለ፦ “የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የወሰናችሁና በክርስቶስ ኢየሱስ ከሚመራው ቲኦክራሲያዊ መንግሥት ጎን በመቆም አምላክንና ንጉሡን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ያደረጋችሁ ልጆች እባካችሁ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ።” ከዚያም 15,000 የሚሆኑ ልጆች በአንዴ የተነሱ ሲሆን እኔም አንዷ ነበርኩ! አክሎም፦ “ስለ አምላክ መንግሥትና ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሌሎች ለመናገር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን የምትሉ እባካችሁ አዎን በሉ” አለ። ሁላችንም “አዎን” ብለን ስንመልስ ወዲያውኑ እንደ ነጎድጓድ የሚያስተጋባ ጭብጨባ ተሰማ።

ከዚያም ችልድረን a የተባለ አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። ሁላችንም ተሰልፈን በመድረኩ በኩል በማለፍ ከወንድም ራዘርፎርድ እጅ አንድ አንድ መጽሐፍ ተቀበልን። የሚያስደስት አጋጣሚ ነበር! በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ያንን መጽሐፍ ከተቀበሉት መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ እርሱ ጽድቅ በመናገር ይሖዋን በቅንዓት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።—መዝሙር 148:12, 13

በአቅኚነት ለሦስት ዓመት ብቻዬን ካገለገልኩ በኋላ በቻምበርስበርግ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ሲነገረኝ በጣም ተደስቼ ነበር! በዚያች ከተማ ከዶሬቲያ ጋር የተገናኘሁ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቅርብ ጓደኛሞች ሆንን። ሁለታችንም የወጣትነት ቅንዓትና ጉልበት ነበረን፤ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ አቅማችን የፈቀደልንን ያህል ለመካፈል ከፍተኛ ጉጉት ነበረን። አንድ ላይ ሆነን ዕድሜ ልክ የዘለቀውን ሀብት የማግኘት ጥረታችንን ጀመርን።—መዝሙር 110:3

በልዩ አቅኚነት ማገልገል ከጀመርን ከጥቂት ወራት በኋላ የጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ክፍል ተመራቂ ከነበረው ከአልበርት ማን ጋር ተገናኘን። በወቅቱ ወንድም ማን ወደ ተመደበበት አገር ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበር። በውጭ አገር የማገልገል አጋጣሚ ካገኘን ይህን መብት ከመቀበል ወደኋላ እንዳንል አበረታታን።

በትምህርት ቤት አንድ ላይ ያሳለፍነው ጊዜ

ዶራ እና ዶሬቲያ፦ የሚስዮናዊነት ሥልጠናችንን ስንጀምር ምን ያህል ተደስተን እንደነበር መገመት ትችላላችሁ! ትምህርት ቤቱ በገባን በመጀመሪያው ቀን የመዘገበን ከ12 ዓመት በፊት የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ለዶሬቲያ እናት ያበረከተላት አልበርት ሽሮደር ነበር። ጆን ቡዝም እዚያ ነበር። ወንድም ቡዝ በዚያ ወቅት የጊልያድ ትምህርት ቤት የሚገኝበት የይሖዋ ምሥክሮች እርሻ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ወንድሞች የበላይ አካል አባላት በመሆን አገልግለዋል።

በጊልያድ ትምህርት ቤት ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አጥንተናል። ሥልጠናው ግሩም ነበር። ከሜክሲኮ የመጣውን የመጀመሪያውን የውጭ አገር ተማሪ ጨምሮ በጠቅላላው 104 ተማሪዎች ነበርን። እኛ የስፓንኛ ቋንቋ ለመማር ስንሞክር ይህ ወንድም እንግሊዝኛውን ለማሻሻል ይጣጣር ነበር። ወንድም ናታን ኖር የተመደብንበትን አገር ባሳወቀን ዕለት ምን ያህል ተደስተን እንደነበር በቃላት መግለጽ ያስቸግራል! አብዛኞቹ ተማሪዎች በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ ተመደቡ፤ የእኛ ምድብ ደግሞ ቺሊ ነበር።

በቺሊ ሀብት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት

ቺሊ ለመግባት የይለፍ ፈቃድ ማግኘት ያስፈለገን ሲሆን ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። በመሆኑም በጥር 1945 ከተመረቅን በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ ለአንድ ዓመት ተኩል በአቅኚነት አገልግለናል። የይለፍ ፈቃድ ስናገኝ ወደ ቺሊ በመጓዝ ቀደም ብለው ወደ እዚያ ከሄዱት ዘጠኝ ሚስዮናውያን ጋር ተቀላቀልን። ሰባቱ ከእኛ በፊት በተካሄዱት የጊልያድ ትምህርት ቤት ክፍሎች የተመረቁ ነበሩ።

የቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጎ ስንደርስ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቻችን መጥተው ተቀበሉን። ከእነርሱ መካከል አንዱ የጊልያድ ምሩቅ የሆነውና ከጥቂት ዓመታት በፊት ሚስዮናውያን እንድንሆን ያበረታታን አልበርት ማን ነበር። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሁለተኛው ክፍል ምሩቅ ከሆነው ከወንድም ጆሴፍ ፌራሪ ጋር ወደ ቺሊ የመጣው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። እኛ እዚያ በደረስንበት ወቅት በመላው ቺሊ የነበሩት አስፋፊዎች ብዛት 100 አይሞላም ነበር። በአዲሱ የአገልግሎት ምድባችን ተጨማሪ ሀብት ማለትም ልበ ቅን ሰዎችን ፈልጎ የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ነበረን።

ቺሊ ከደረስን በኋላ ሳንቲያጎ በሚገኘው የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ እየኖርን እንድናገለግል ተመደብን። ሰፊ ከሆነው የሚስዮናውያን ቤተሰብ ጋር አንድ ላይ መኖር ለእኛ አዲስ ነገር ነበር። በስብከቱ ሥራ የሚጠበቅብንን ሰዓት ከማሟላት በተጨማሪ ሁላችንም በሳምንት አንድ ጊዜ ለቤተሰቡ ምግብ እንድናበስል እንመደብ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አስቂኝ ነገሮች ያጋጥሙን ነበር። በአንድ ወቅት ለቤተሰባችን ቁርስ የሚሆን ብስኩት ጋገርን። ምድጃውን ስንከፍተው ግን ደስ የማይል ሽታ ሸተተን። ይህ የሆነው ሊጡ ውስጥ ቤኪንግ ፓውደር የከተትን መስሎን ቤኪንግ ሶዳ በመጨመራችን ነው! እንዲህ ያለውን ስህተት የሠራነው አንድ ሰው በቤኪንግ ፓውደር ዕቃ ውስጥ ቤኪንግ ሶዳ ጨምሮ ስለነበረ ነው።

በጣም የሚያስቀው ግን ስፓንኛ ለመማር ስንሞክር የምንሠራው ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው የአንድ ትልቅ ቤተሰብ አባላት የምንናገረውን ነገር መረዳት ስላልቻሉ ጥናታቸውን ሊያቆሙ ምንም አልቀራቸውም ነበር። ይሁን እንጂ የምንነግራቸውን ጥቅሶች ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እየተመለከቱ እውነትን መማር በመቻላቸው ከቤተሰቡ ውስጥ አምስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በዚያን ወቅት ለአዳዲስ ሚስዮናውያን የሚሰጥ የቋንቋ ትምህርት አልነበረም። የተመደብንበት አገር እንደደረስን አገልግሎታችንን ወዲያውኑ በመጀመር ቋንቋውን ከምንመሰክርላቸው ሰዎች ለመማር ጥረት እናደርግ ነበር።

በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩን ሲሆን አንዳንዶቹ ፈጣን እድገት አድርገዋል፤ ሌሎቹ ግን ከፍተኛ ትዕግሥት የሚጠይቁ ነበሩ። ቴሬሳ ቴሎ የተባለች አንዲት ወጣት እውነትን ስንመሠክርላት በደንብ አዳመጠችንና “እባካችሁ ሌላ ጊዜም መጥታችሁ ተጨማሪ ነገሮችን ንገሩኝ” አለችን። ሆኖም 12 ጊዜ ተመልሰን ብንሄድም ልናገኛት አልቻልንም። በዚህ ሁኔታ ሦስት ዓመት አለፈ። ከዚያም ሳንቲያጎ በሚገኝ ቲያትር ቤት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደዚያ ሄድን። እሁድ ቀን ስብሰባውን ጨርሰን ስንወጣ አንዲት ሴት “ወይዘሪት ዶራ፣ ወይዘሪት ዶራ!” በማለት ተጣራች። ዞር ስንል ቴሬሳ ነበረች። ከመንገዱ ማዶ የምትገኘውን እህቷን ለመጠየቅ እንደመጣችና በቲያትር ቤቱ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማየት ጎራ እንዳለች ነገረችን። ከእርሷ ጋር ዳግመኛ በመገናኘታችን በጣም ተደሰትን! ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ዝግጅት አደረግንና ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች። ቴሬሳ ከጊዜ በኋላ ልዩ አቅኚ የሆነች ሲሆን አሁን በዚህ ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ 45 ዓመት ገደማ ሆኗታል።—መክብብ 11:1

“በአሸዋ” ውስጥ ሀብት አገኘን

በ1959 “የአሸዋ ቦታ” የሚል ትርጉም ባላትና 4,300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የቺሊ የባሕር ጠረፍ በስተደቡብ በኩል የመጨረሻው ጫፍ ላይ በምትገኘው ፑንታ አሬናስ በምትባል ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። ፑንታ አሬናስ ለየት ያለች ከተማ ናት። በበጋ ወራት ቀኑ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ እስከ ምሽቱ 5:30 ድረስ ፀሐይ አትጠልቅም። ይህ ሁኔታ በርካታ ቀናት በአገልግሎት ለማሳለፍ ያስችለናል፤ እንዲህ ሲባል ግን ምንም እንቅፋት የለብንም ማለት አይደለም፤ በበጋ ወቅት ከአንታርክቲክ የሚነሳው ኃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል። የክረምቱ ወራት ቀዝቃዛ ሲሆን ቀኖቹም አጭር ናቸው።

በፑንታ አሬናስ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ከተማዋ ደስ የሚሉ ነገሮች አሏት። በበጋ ወቅት ከምዕራብ አቅጣጫ በሰማዩ ላይ ያለማቋረጥ የሚጓዘው ዝናብ አዘል ደመና ደስ የሚል ትዕይንት ይፈጥራል። አልፎ አልፎ ድንገት ዶፉን ያወርድባችኋል፤ ሆኖም ወዲያውኑ ነፋስ ሲመጣ ሁሉ ነገር ቶሎ ይደርቃል። ከዚህም በላይ ደመናውን ሰንጥቆ የሚያልፈው የፀሐይ ብርሃን ለዓይን የሚማርክ ቀስተ ደመና ይፈጥራል። ፀሐይዋ ብልጭ ድርግም ስትል ቀስተ ደመናው እየታየና እየጠፋ አንዳንድ ጊዜ ለሰዓታት ይቆያል።—ኢዮብ 37:14

በወቅቱ በፑንታ አሬናስ የነበሩት አስፋፊዎች ጥቂት ስለነበሩ በአካባቢው በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ የሚደረጉትን ስብሰባዎች የምንመራው እኛ ነበርን። በእርግጥ ይሖዋ ጥረታችንን ባርኮልናል። ከሠላሳ ሰባት ዓመታት በኋላ ለጥየቃ ወደዚያ ሄደን ነበር። ታዲያ ምን ያገኘን ይመስላችኋል? ጥሩ እድገት እያደረጉ ያሉ ስድስት ጉባኤዎችንና ሦስት የሚያምሩ የመንግሥት አዳራሾችን አግኝተናል። ይሖዋ በእነዚህ አሸዋማ አካባቢዎች መንፈሳዊ ሀብት ፈልገን እንድናገኝ ስለፈቀደልን በጣም ተደስተናል!—ዘካርያስ 4:10

“በሰፊ የባሕር ዳርቻ” ላይ ተጨማሪ ሀብት አገኘን

በፑንታ አሬናስ ለሦስት ዓመት ተኩል ካገለገልን በኋላ ቫልፓራይሶ በተባለች የወደብ ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። ከተማዋ የፓስፊክ ውቅያኖስን በግልጽ ለማየት የሚያስችሉ 41 ኮረብቶችና አንድ ባሕረ ሰላጤ አላት። ከእነዚህ ኮረብቶች መካከል ብዙውን ጊዜ ለአገልግሎት የምንሄደው “ሰፊ የባሕር ዳርቻ” የሚል ትርጉም ወዳለውና ፕላያ አንቻ ወደሚባለው ኮረብታ ነበር። እዚያ በቆየንባቸው 16 ዓመታት ውስጥ ወጣት ክርስቲያን ወንድሞች መንፈሳዊ እድገት አድርገው በመላው ቺሊ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው ሲያገለግሉ መመልከት ችለናል።

ቀጣዩ የሚስዮናዊ ምድባችን ደግሞ ቪና ዴል ማር ነበር። በዚህች ከተማ የሚስዮናዊ ቤታችን በመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት እስከደረሰበት ጊዜ ድረስ ለሦስት ዓመት ተኩል አገልግለናል። ከዚያም ከ40 ዓመት በፊት የሚስዮናዊ አገልግሎታችንን ወደ ጀመርንበት ወደ ሳንቲያጎ ተመለስን። በዚህ ወቅት ነገሮች ሁሉ ተለዋውጠዋል። አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ የተገነባ ሲሆን የቀድሞው የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ በአገሪቱ ለቀሩት ሚስዮናውያን መኖሪያ ሆኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ሕንፃ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሆኗል። በዚያ ወቅትም የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት የማየት አጋጣሚ አግኝተናል። በዕድሜ ከገፋነው ሚስዮናውያን መካከል አምስታችን ቤቴል ገብተን እንድናገለግል ተጋበዝን። በቺሊ በቆየንባቸው ጊዜያት ውስጥ በ15 ቦታዎች ተመድበን አገልግለናል። በእነዚህ ዓመታት የአስፋፊዎቹ ቁጥር ከ100 ተነስቶ ወደ ወደ 70,000 ገደማ ሲደርስ ተመልክተናል! በቺሊ ሀብት በመፈለግ ያሳለፍናቸው 57 ዓመታት ምንኛ አስደሳች ነበሩ!

ይሖዋ በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ እየተጠቀመባቸው ያሉ በርካታ ሰዎችን እንድናገኝ ስለፈቀደልን በጣም እንደባረከን ይሰማናል። እነዚህ ሰዎች በእርግጥም ውድ ሀብት ናቸው። አንድ ላይ ሆነን ይሖዋን በማገልገል ባሳለፍናቸው ከ60 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ንጉሥ ዳዊት “ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት . . . በጎነትህ ምንኛ በዛች!” በማለት ከጻፋቸው ቃላት ጋር በሙሉ ልባችን እንስማማለን።—መዝሙር 31:19

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶሬቲያ በ2002 እንዲሁም በ1943 አገልግሎት ላይ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1942 በፎርት ዳጅ፣ አይዋ መንገድ ላይ ስታገለግል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶራ በ2002

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶሬቲያና ዶራ በ1946 ቺሊ በሚገኘው የመጀመሪያ የሚስዮናዊ ቤታቸው በር ላይ