በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ቃል አካሄድህን እንዲመራልህ ፍቀድ

የአምላክ ቃል አካሄድህን እንዲመራልህ ፍቀድ

የአምላክ ቃል አካሄድህን እንዲመራልህ ፍቀድ

“ሕግህ [“ቃልህ፣” የ1980 ትርጉም] ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።”—መዝሙር 119:105

1, 2. አብዛኞቹ የሰው ልጆች እውነተኛ ሰላምና ደስታ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሊሳካ ያልቻለው ለምንድን ነው?

 አንድ ሰው አቅጣጫ እንዲጠቁምህ የጠየቅህበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ይህን ያደረግኸው ወደምትሄድበት አካባቢ ብትቃረብም የመጨረሻውን መታጠፊያ ተጠራጥረህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ቦታው ጨርሶ ጠፍቶህ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም በሌላ መንገድ መሄድ አስፈልጎህ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በዚህ ወቅት አካባቢውን የሚያውቅ ሰው የጠቆመህን አቅጣጫ መከተሉ ጥበብ አይመስልህም? እንዲህ ያለው ሰው ወደፈለግህበት ቦታ እንድትደርስ ሊረዳህ ይችላል።

2 በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጆች ያለ ፈጣሪያቸው እርዳታ በሕይወት ጎዳና ላይ ለመጓዝ ሲሞክሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ያለ ፈጣሪ መመሪያ በትክክለኛው አቅጣጫ መጓዝ ይኸውም ወደ እውነተኛ ሰላምና ደስታ የሚመራውን መንገድ ማግኘት በጭራሽ አይችሉም። የሰው ልጆች ይህን መንገድ ማግኘት ያቃታቸው ለምንድን ነው? ከ2,500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኤርምያስ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 10:23) ብቃት ካለው አካል እርዳታ ሳያገኝ አካሄዱን በራሱ ለመምራት የሚሞክር ማንኛውም ሰው እንደማይሳካለት የታወቀ ነው። የሰው ልጅ መመሪያ እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የለውም!

3. ይሖዋ አምላክ፣ ለሰው ልጆች መመሪያ ለመስጠት ከሁሉ የላቀ ብቃት አለው የምንለው ለምንድን ነው? ምን ለማድረግስ ቃል ገብቷል?

3 ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን መመሪያ ለመስጠት ከማንም በላይ የላቀ ብቃት አለው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከማንም በተሻለ መንገድ የሰው ልጆችን አፈጣጠር የሚያውቀው እርሱ ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ የሰው ልጆች አቅጣጫቸውን ስተው ከመንገዳቸው እንዴት ሊወጡ እንደቻሉ በሚገባ ያውቃል። እንደገና ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ የሚያስፈልጋቸው ምን እንደሆነም ያውቃል። በተጨማሪም ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም ለእኛ የሚበጀን ጎዳና የትኛው እንደሆነ ያውቃል። (ኢሳይያስ 48:17) በመሆኑም በመዝሙር 32:8 ላይ ይሖዋ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በማለት በገባው ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን። ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው?

4, 5. የአምላክ ቃል የሚመራን እንዴት ነው?

4 መዝሙራዊው “ሕግህ [“ቃልህ፣” የ1980 ትርጉም] ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” በማለት ለይሖዋ ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 119:105) አምላክ የተናገራቸው ሐሳቦችና ማሳሰቢያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በጎዳናችን ላይ ሊያጋጥሙን የሚችሉ እንቅፋቶችን መወጣት እንድንችል ይረዱናል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን የምናነብና እንዲመራን የምንፈቅድ ከሆነ በኢሳይያስ 30:21 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሕይወታችን ሲፈጸም መመልከት እንችላለን። ጥቅሱ “ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል” ይላል።

5 መዝሙር 119:105 የአምላክ ቃል የሚያከናውናቸውን ተዛማጅነት ያላቸው ሁለት ተግባራት እንደሚጠቁም ልብ በል። በመጀመሪያ፣ የአምላክ ቃል ለእግራችን መብራት በመሆን ያገለግላል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረግ እንድንችል እንዲሁም ይህ ዓለም በሚያመጣው ወጥመድ እንዳንወድቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች አካሄዳችንን ሊመሩልን ይገባል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የአምላክ ማሳሰቢያዎች ለመንገዳችን ብርሃን ይሆኑልናል፤ ይህም ሲባል አምላክ ቃል በገባው ገነት ውስጥ ለዘላለም ከመኖር ተስፋችን ጋር የሚስማሙ ምርጫዎች እንድናደርግ ይረዱናል ማለት ነው። ከፊታችን ያለው ጎዳና በቂ ብርሃን ካለው የያዝነው መንገድ ጥሩ ወይም መጥፎ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ማስተዋል እንችላለን። (ሮሜ 14:21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9፤ ራእይ 22:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት አምላክ የተናገራቸው ሐሳቦች ለእግራችን መብራት፣ ለመንገዳችንም ብርሃን እንዴት እንደሚሆኑ በስፋት እንመልከት።

“ለእግሬ መብራት”

6. የአምላክ መመሪያዎች ለእግራችን መብራት ሊሆኑ የሚችሉት በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ነው?

6 ሁላችንም በየዕለቱ ውሳኔዎች እናደርጋለን። አንዳንዶቹ ውሳኔዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ ቀላል ይመስሉ ይሆናል፤ በሌሎች ጊዜያት ግን ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን፣ ሐቀኝነታችንን ወይም የገለልተኝነት አቋማችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሊገጥሙን ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳችንን ማስለመድ’ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 5:14) የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት በማግኘትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች የመረዳት ችሎታ በማዳበር ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ለማድረግ ሕሊናችንን ማሠልጠን እንችላለን።—ምሳሌ 3:21

7. አንድ ክርስቲያን እምነቱን ከማይጋሩ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሊፈተን የሚችልበትን ሁኔታ ጥቀስ።

7 አንድ ምሳሌ እንመልከት። የይሖዋን ልብ ለማስደሰት ከልብህ ትጥራለህ? (ምሳሌ 27:11) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልትመሰገን ይገባሃል። ሆኖም የሥራ ባልደረቦችህ አንድ የስፖርት ዝግጅት በሚካሄድበት ቦታ ላይ አብረሃቸው እንድትገኝ የመግቢያ ቲኬት ሰጡህ እንበል። እነዚህ ሰዎች በሥራ ቦታ ከአንተ ጋር መሆን ስለሚያስደስታቸው ከሥራ ሰዓት ውጭም አብረሃቸው ጊዜ እንድታሳልፍ ይፈልጋሉ። የሥራ ባልደረቦችህ መጥፎ ሰዎች እንዳልሆኑ ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም በአንዳንድ የሕይወት መስኮች መልካም ሥነ ምግባራዊ አቋም ይኖራቸው ይሆናል። በዚህ ወቅት ምን ታደርጋለህ? ግብዣውን መቀበልህ የሚያስከትለው አደጋ ይኖር ይሆን? የአምላክ ቃል በዚህ ጉዳይ ረገድ ትክክለኛ ውሳኔ እንድታደርግ የሚረዳህ እንዴት ነው?

8. ጓደኝነትን በተመለከተ ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዱን የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

8 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት። በዚህ ወቅት መጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘው “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ይሆናል። ሆኖም ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ለመከተል የእኛን እምነት ከማይጋሩ ሰዎች ፈጽሞ መራቅ ይኖርብናል ማለት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ማለት እንዳልሆነ ያሳዩናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ፣ እምነቱን የማይጋሩትን ጨምሮ ‘ለሁሉም’ ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ክርስትና፣ እምነታችንን የማይጋሩ ሰዎችን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች አሳቢነት እንድናሳይ ይጠይቅብናል። (ሮሜ 10:13-15) ደግሞም የእኛ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች የምንርቅ ከሆነ “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” የሚለውን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?—ገላትያ 6:10

9. ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ሚዛናዊ እንዲሆን የሚረዳን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ነው?

9 ይሁን እንጂ ከሥራ ባልደረባችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግና የዚያ ሰው የቅርብ ጓደኛ መሆን በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በዚህ ጊዜ ልንመለከተው የሚገባ ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) “አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” የሚለው ሐረግ ምን ትርጉም አለው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ሐረግ “አትጣመሩ፣” “ከእነርሱ ጋር አቻ ሆናችሁ ለመሥራት አትሞክሩ” ወይም “ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት አትመሥርቱ” በማለት ተርጉመውታል። ከአንድ የሥራ ባልደረባህ ጋር ያለህ ግንኙነት ተገቢ የማይሆነው ምን ጊዜ ነው? ግንኙነታችሁ መስመሩን ስቶ አግባብ ባልሆነ መንገድ ተጠምደሃል ሊባል የሚችለውስ መቼ ነው? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ አካሄድህን ሊመራልህ ይችላል።

10. (ሀ) ኢየሱስ ወዳጆቹን የመረጠው እንዴት ነበር? (ለ) አንድ ሰው ጓደኝነትን በተመለከተ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንዲያደርግ የትኞቹ ጥያቄዎች ሊረዱት ይችላሉ?

10 የሰው ልጆች ሲፈጠሩ ጀምሮ ለእነርሱ ፍቅር የነበረውን የኢየሱስን ምሳሌ ተመልከት። (ምሳሌ 8:31) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከተከታዮቹ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። (ዮሐንስ 13:1) ሌላው ቀርቶ የተሳሳተ ሃይማኖታዊ አመለካከት የነበረውን ሰው እንኳ ‘ወዶታል።’ (ማርቆስ 10:17-22) ይሁንና ኢየሱስ የቅርብ ወዳጆቹን በመምረጥ ረገድ ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አበጅቶ ነበር። የአባቱን ፈቃድ የመፈጸም ልባዊ ፍላጎት ከሌላቸው ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አልነበረውም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “የማዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:14) እርግጥ ነው፣ ከአንድ የሥራ ባልደረባህ ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖርህ ይችላል። ሆኖም እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ግለሰብ የኢየሱስን ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ነው? ግለሰቡ/ግለሰቧ ኢየሱስ እንድናመልከው ስላስተማረን ስለ ይሖዋ ለማወቅ ፈቃደኛ ነው/ናት? እንደ እኔ ዓይነት ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር አቋም አለው/አላት?’ (ማቴዎስ 4:10) ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ስትወያይና የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በጥብቅ ለመከተል ስትጥር ከላይ ላሉት ጥያቄዎች ግልጽ መልስ ታገኛለህ።

11. የአምላክ ቃል አካሄዳችንን ሊመራልን የሚገባው በየትኞቹ ሁኔታዎች እንደሆነ ጥቀስ።

11 የአምላክ ቃል ለእግራችን መብራት ሊሆን የሚችልባቸው ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥራ አጥቶ የተቸገረ አንድ ክርስቲያን ሥራ አገኘ እንበል። ይሁን እንጂ ሥራው ጊዜውንና ጉልበቱን የሚያሟጥጥበት ከመሆኑም በላይ ይህን ሥራ ለመጀመር ከተስማማ ብዙ ጊዜ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይቀራል፤ እንዲሁም ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዙ ሌሎች እንቅስቃሴዎች መካፈል አይችልም። (መዝሙር 37:25) ሌላ ክርስቲያን ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በግልጽ የሚቃረን መዝናኛ ለመመልከት ይፈተን ይሆናል። (ኤፌሶን 4:17-19) በተመሳሳይም አንድ ሌላ ክርስቲያን የእምነት አጋሮቹ ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት በሚያደርጉት ነገር በቀላሉ ይቀየም ይሆናል። (ቈላስይስ 3:13) በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሁሉ፣ የአምላክ ቃል ለእግራችን መብራት እንዲሆንልን መፍቀድ ይገባናል። በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በሙሉ በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። ቅዱሳን መጻሕፍት “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16

“ለመንገዴም ብርሃን”

12. የአምላክ ቃል ለመንገዳችን ብርሃን የሚሆነው እንዴት ነው?

12 መዝሙር 119:105 የአምላክ ቃል ከፊታችን ያለው ጎዳና በግልጽ እንዲታየን በማድረግ ለመንገዳችን ብርሃን ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ አስጨናቂ ሁኔታዎች ያሉት ለምን እንደሆነና ወደፊት ምን እንደሚመጣ ስለሚገልጽ የወደፊቱን ሁኔታ በተመለከተ በጨለማ አልተተውንም። አዎን፣ የምንኖረው በዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ እንደሆነ እናውቃለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ከፊታችን ምን እንደሚመጣ ማወቃችን በአሁኑ አኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል።”—2 ጴጥሮስ 3:11, 12

13. ወደ ሥርዓቱ መደምደሚያ መቃረባችን በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

13 አስተሳሰባችንም ሆነ አኗኗራችን “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ጽኑ እምነት እንዳለን የሚያሳይ መሆን አለበት። (1 ዮሐንስ 2:17) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል የወደፊት ግባችንን በተመለከተ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33) በርካታ ወጣቶች በዚህ የኢየሱስ ንግግር ላይ እምነት በማሳደር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈላቸው የሚያስመሰግናቸው ነው! ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች በፈቃደኝነት ተዛውረዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ቤተሰባቸውን በአጠቃላይ ይዘው ሄደዋል።

14. አንድ ቤተሰብ በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ምን አድርጓል?

14 ከዩናይትድ ስቴትስ ተነስቶ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በምትገኝ ከተማ ለማገልገል የተጓዘውን አራት አባላት ያሉት አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ እንመልከት። ከተማዋ 50,000 ሕዝብ ያላት ሲሆን በዚያ የሚገኘው ጉባኤ 130 የሚያህሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሉት። ያም ሆኖ በሚያዝያ 12, 2006 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ወደ 1,300 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተው ነበር! በአካባቢው የሚገኘው ‘አዝመራ ለመከር የደረሰ’ በመሆኑ ከአምስት ወራት በኋላ ይህ ቤተሰብ ማለትም አባት እናት ወንድ ልጃቸውና ሴት ልጃቸው 30 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑ ነበር። (ዮሐንስ 4:35) አባትየው እንዲህ ይላል:- “ጉባኤውን ለመርዳት ወደዚህ አካባቢ የመጡ 30 ወንድሞችና እህቶች አሉ። ወደ 20 የሚያህሉት ከዩናይትድ ስቴትስ፣ የቀሩት ደግሞ ከባሃማስ፣ ከካናዳ፣ ከጣሊያን፣ ከኒው ዚላንድና ከስፔን የመጡ ናቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች የመጡት በአገልግሎት ለመካፈል ጓጉተው ስለሆነ በአካባቢው ያሉት ወንድሞች በግለት እንዲያገለግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።”

15. በሕይወትህ ውስጥ ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠትህ ምን በረከት አግኝተሃል?

15 ብዙዎች፣ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሁኔታቸው እንደማይፈቅድላቸው የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲህ የሚያደርጉ ወይም ሁኔታቸውን አስተካክለው ራሳቸውን ማቅረብ የሚችሉ ሁሉ፣ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ በመካፈል የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያጭዱ ምንም ጥርጥር የለውም። የምታገለግለው የትም ይሁን የት ይሖዋን በሙሉ ኃይልህ የምታገለግል ከሆነ እንዲህ በማድረግ ከሚገኘው ደስታ መቋደስ ትችላለህ። በሕይወትህ ውስጥ ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የምትሰጥ ከሆነ ይሖዋ ‘የተትረፈረፈ በረከትን ማስቀመጫ እስክታጣ ድረስ ሊያፈስልህ’ ቃል ገብቷል።—ሚልክያስ 3:10

ይሖዋ ከሚሰጠው መመሪያ ጥቅም ማግኘት

16. የአምላክ ቃል እንዲመራን በመፍቀዳችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

16 የይሖዋ ቃል ተዛማጅነት ባላቸው ሁለት መንገዶች እንደሚመራን ቀደም ብለን ተመልክተናል። ቃሉ ለእግራችን መብራት ሆኖ ያገለግላል። ይህም ሲባል፣ በትክክለኛው አቅጣጫ እንድንሄድ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ውሳኔዎችን ስናደርግ ይመራናል ማለት ነው። በተጨማሪም የአምላክ ቃል ከፊታችን ያለው ጎዳና በግልጽ እንዲታየን በማድረግ ለመንገዳችን ብርሃን ይሆንልናል። ይህ ደግሞ ጴጥሮስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል:- “ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ።”—1 ጴጥሮስ 1:13

17. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን የአምላክን መመሪያ ለመከተል የሚረዳን እንዴት ነው?

17 ይሖዋ መመሪያ እንደሚሰጠን ምንም ጥርጥር የለውም። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘አንተ ለዚህ መመሪያ ለመገዛት ፈቃደኛ ነህ?’ የሚል ነው። ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ለመረዳት እንድትችል በየቀኑ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። ያነበብከው ነገር በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ፈልግ። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ከዚያም የግል ውሳኔዎችን ስታደርግ ‘በአእምሮህ’ ወይም በማመዛዘን ችሎታህ ተጠቀም።—ሮሜ 12:1

18. የአምላክ ቃል እንዲመራን ስንፈቅድ ምን በረከት እናገኛለን?

18 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች አካሄዳችንን እንዲመሩልን ከፈቀድን መንገዳችንን ያበሩልናል፤ እንዲሁም ልንከተለው የሚገባውን ትክክለኛ ጎዳና በምንወስንበት ጊዜ መመሪያ ይሰጡናል። በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ‘አላዋቂውን ጥበበኛ እንደሚያደርግ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 19:7) መጽሐፍ ቅዱስ አካሄዳችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ ንጹህ ሕሊና ይኖረናል፤ እንዲሁም ይሖዋን በማስደሰታችን እርካታ እናገኛለን። (1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19) የአምላክ ቃል አካሄዳችንን በየዕለቱ እንዲመራልን ፈቃደኛ ከሆንን ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሽልማት በመስጠት ይባርከናል።—ዮሐንስ 17:3

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ አምላክ አካሄዳችንን እንዲመራልን መፍቀዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የአምላክ ቃል ለእግራችን መብራት መሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው?

• የአምላክ ቃል ለመንገዳችን ብርሃን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

• መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን የአምላክን መመሪያ እንድንከተል የሚረዳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እምነታችንን ከማይጋራ ሰው ጋር መወዳጀት ተገቢ የማይሆነው ምንጊዜ ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች የይሖዋን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሰዎች ነበሩ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አኗኗራችን ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እንደምንሰጥ ያሳያል?