የይሖዋን ቀን በጽናት መጠበቅ
የይሖዋን ቀን በጽናት መጠበቅ
‘በእምነታችሁ ላይ መጽናትን ጨምሩ።’—2 ጴጥሮስ 1:5, 6
ታላቁ የይሖዋ ቀን በጣም ቀርቧል። (ኢዩኤል 1:15፤ ሶፎንያስ 1:14) ለአምላክ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ያደረግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበትን ይህን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን በእምነታችን ምክንያት ጥላቻ፣ ነቀፋ፣ ስደትና ሞት ሊያጋጥመን ይችላል። (ማቴዎስ 5:10-12፤ 10:22፤ ራእይ 2:10) ይህ ደግሞ መጽናትን ይጠይቃል። ጽናት፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የመቋቋም ችሎታ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በእምነታችን ላይ መጽናትን እንድንጨምር’ አሳስቦናል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ኢየሱስም “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ስላለ ይህ ባሕርይ ሊኖረን ይገባል።—ማቴዎስ 24:13
2 ከዚህም በተጨማሪ ሕመም፣ ሐዘንና ሌሎች ፈተናዎች ይደርሱብናል። ሰይጣን እምነታችን ሲጠፋ ከማየት የበለጠ የሚያስደስተው ነገር የለም! (ሉቃስ 22:31, 32) በይሖዋ እርዳታ የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 5:6-11) የይሖዋን ቀን እምነታችን ሳይዳከም በጽናት መጠበቅ እንደምንችል የሚያሳዩ አንዳንድ የሕይወት ታሪኮችን እንመልከት።
ሕመም እንቅፋት አልሆነባቸውም
3 አምላክ ያለብንን ሕመም በተዓምር ባይፈውስልንም በጽናት እንድንቋቋመው የሚያስችለን ጥንካሬ ይሰጠናል። (መዝሙር 41:1-3) ሻረን የተባለች አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች:- “እስከማስታውሰው ድረስ ተሽከርካሪ ወንበር ተለይቶኝ አያውቅም። ስወለድ ጀምሮ ያጋጠመኝ ሴረብረል ፖልዚ የተባለ በሽታ የልጅነት ደስታዬን ነፍጎኛል።” ሻረን ስለ ይሖዋና ወደፊት ሰዎች ፍጹም ጤንነት እንደሚኖራቸው ስለሚገልጸው ተስፋ መማሯ የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ሆኖ እንዲታያት አድርጓል። ሻረን የምትራመደውም ሆነ የምትናገረው በብዙ ችግር ቢሆንም በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈሏ ደስታ አስገኝቶላታል። ሻረን የዛሬ 15 ዓመት እንዲህ ብላ ነበር:- “የጤንነቴ ሁኔታ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል። ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ ያለኝ እምነትና ከእሱ ጋር የመሠረትኩት ዝምድና የሕይወቴ አለኝታ ሆኖልኛል። ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል በመቆጠሬና የእሱን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማግኘቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ!”
4 ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” ሲል አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን የመሰሉ ሁኔታዎች አንድን ሰው ለመንፈስ ጭንቀት ሊዳርጉት ይችላሉ። ሻረን በ1993 እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ፈጽሞ የማልረባ እንደሆንኩ ይሰማኝ ስለነበር . . . ለሦስት ዓመት ያህል በከባድ የመንፈስ ጭንቀት እሠቃይ ነበር። . . . በእነዚህ ጊዜያት የጉባኤ ሽማግሌዎች ማጽናኛና ምክር ሰጥተውኛል። . . . ይሖዋ በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት ስለ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ምንነት እንድንገነዘብ ፍቅራዊ እርዳታ አድርጎልናል። አዎን፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያስባል፤ ስሜታችንንም ይረዳልናል።” (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ሻረን አሁንም አምላክን በታማኝነት እያገለገለች ታላቁን የይሖዋን ቀን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
5 አንዳንድ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ባሳለፏቸው ሁኔታዎች ምክንያት በከባድ ጭንቀት ይሠቃያሉ። ለምሳሌ ሃርሊ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ ጦርነቶችን ከመመልከቱ የተነሳ በቅዠት ይሠቃይ ነበር። በእንቅልፍ ልቡ “ተመልከት! ተጠንቀቅ!” እያለ ይጮሃል። ከዚያም በላብ ተጠምቆ ከእንቅልፉ ይባንናል። ይሁንና ሃርሊ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሕይወት መምራት የቻለ ሲሆን የሚያስጨንቀው ቅዠትም በጊዜ ሂደት ቀንሶለታል።
6ባይፖላር ዲስኦርደር በተባለ የአእምሮ በሽታ የሚሠቃይ አንድ ክርስቲያን ከቤት ወደ ቤት መስበክ አስቸጋሪ ሆኖበት ነበር። ይሁንና አገልግሎት ለእሱም ሆነ መልእክቱን ለሚሰሙ ሰዎች ሕይወት የሚያስገኝ መሆኑን ስለተገነዘበ በዚህ ሥራ ከመካፈል ወደኋላ አላለም። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) አንዳንድ ጊዜ የበሩን ደወል መጫን እንኳ ከባድ ይሆንበት ነበር። ያም ሆኖ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ትንሽ ቆም ብዬ ስሜቴን አረጋጋና ወደሚቀጥለው ቤት እሄዳለሁ። በአገልግሎት መካፈሌን በመቀጠል መንፈሳዊ ጤንነቴን መጠበቅ ችያለሁ።” በስብሰባዎች ላይ መገኘትም ቢሆን ለዚህ ወንድም ቀላል አልነበረም። ሆኖም መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር መገናኘት ያለውን ጥቅም ስለተገነዘበ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የተቻለውን ሁሉ ይጥር ነበር።—ዕብራውያን 10:24, 25
7 አንዳንድ ክርስቲያኖች ፎቢያ በመባል የሚታወቅ አንድን ሁኔታ ወይም ነገር ከልክ በላይ የመፍራት ችግር አለባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በሕዝብ ፊት መናገር፣ ሌላው ቀርቶ በስብሰባ ላይ መገኘት ሊያስፈራቸው ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ወይም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ማቅረብ ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል አስብ! ያም ሆኖ ያለባቸውን ችግር በጽናት ተቋቁመው በስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውና ተሳትፎ ማድረጋቸው እኛንም ጭምር ያበረታታናል።
8 በቂ እረፍትና እንቅልፍ ማግኘት ስሜታዊ ችግሮችን ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል። የሕክምና እርዳታ ማግኘትም ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ውጤታማ የሆነው ዘዴ ወደ አምላክ በመጸለይ ትምክህታችንን በእሱ ላይ መጣል ነው። መዝሙር 55:22 እንዲህ ይላል:- “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።” እንግዲያው “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን።”—ምሳሌ 3:5, 6
የምንወደው ሰው ሲሞት የሚደርስብንን ሐዘን መቋቋም
9 የአንድ ሰው ሞት በቤተሰቡ ላይ ጥልቅ ሐዘን ሊያስከትል ይችላል። አብርሃም የሚወዳት ሚስቱ ሣራ በሞተች ጊዜ አልቅሶላታል። (ዘፍጥረት 23:2) ሌላው ቀርቶ ፍጹም የነበረው ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) በመሆኑም የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ ማዘንህ ያለ ነገር ነው። ይሁንና ክርስቲያኖች ትንሣኤ እንደሚኖር ያውቃሉ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) በዚህም ምክንያት ‘ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አያዝኑም።’—1 ተሰሎንቄ 4:13
10 የምንወደው ሰው ሲሞት የሚደርስብንን ሐዘን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? የሚከተለውን ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አንድ ወዳጃችን ራቅ ወዳለ ቦታ ቢሄድም እንኳ ሲመለስ እንደምናገኘው እርግጠኞች ስለሆንን በአብዛኛው ሐዘናችን ለረጅም ጊዜ አይዘልቅም። ታማኝ የሆነ አንድ ክርስቲያን በሚሞትበት ጊዜም ተመሳሳይ አመለካከት መያዛችን ሐዘናችንን ሊያቀልልን ይችላል። ምክንያቱም ይህ ክርስቲያን ትንሣኤ እንደሚያገኝ እርግጠኞች ነን።—መክብብ 7:1
2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረችው መበለቲቷ ሐና ባደረገችው ነገር ላይ ማሰላሰል ጠቃሚ ነው። ሐና ባሏ የሞተው ገና በተጋቡ በሰባት ዓመታቸው ነበር። ሆኖም በ84 ዓመቷም እንኳ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረቧን አላቋረጠችም። (ሉቃስ 2:36-38) ለአምላክ ያደረች ሆና መኖሯ ሐዘኗንና የብቸኝነት ስሜቷን እንድትቋቋም እንደረዳት ጥርጥር የለውም። የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ጨምሮ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረን መካፈላችን የምንወደውን ሰው በሞት ማጣታችን ያስከተለብንን ሐዘን ለመቋቋም ይረዳናል።
11 ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ በሆነው በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ሐዘናችንን ለመቋቋም ይረዳናል። (ልዩ ልዩ ፈተናዎችን መቋቋም
12 አንዳንድ ክርስቲያኖች ከቤተሰብ ሕይወት ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን መቋቋም ግድ ሆኖባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የትዳር ጓደኛ ምንዝር ቢፈጽም ቤተሰቡ ምን ያህል ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል አስብ! በደል የተፈጸመበት የትዳር ጓደኛ በሚደርስበት ድንጋጤና ሐዘን የተነሳ እንቅልፍ ሊያጣ ብሎም ጠዋትና ማታ ሊያለቅስ ይችላል። ከዚህም ባሻገር ምግብ አልበላ ሊለው፣ ክብደት ሊቀንስና ስሜቱ ሊቃወስ ይችላል። በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈልም ይከብደው ይሆናል። በዚህ ጊዜ ልጆች ምን ያህል ሊጎዱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም!
13 እንደዚህ ያሉ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። (መዝሙር 94:19) የይሖዋ ቤተ መቅደስ በተመረቀ ጊዜ ንጉሥ ሰሎሞን ያቀረበው ጸሎት አምላክ የሕዝቡን ጸሎት እንደሚሰማ ያሳያል። ሰሎሞን ወደ አምላክ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንኛውም ሰው የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። አንተ ብቻ የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ሁሉ ክፈለው፤ ይህም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩ ነው።”—1 ነገሥት 8:38-40
ማቴዎስ 7:7-11) የመንፈስ ፍሬ ደስታና ሰላምን የመሳሰሉ ባሕርያትን ያካትታል። (ገላትያ 5:22, 23) በሰማይ የሚኖረው አባታችን ለጸሎታችን መልስ ሲሰጠን ታላቅ እፎይታ ይሰማናል፤ ሐዘን በደስታ፣ ጭንቀት ደግሞ በአእምሮ ሰላም ይተካል!
14 በተለይም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን መጸለያችን ጠቃሚ ነው። (15 ከፍተኛ ውጥረት ሲያጋጥመን የተወሰነ ጭንቀት ቢሰማን እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁንና የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት ማስታወሳችን በመጠኑም ቢሆን ጭንቀታችንን ሊቀንስልን ይችላል:- “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። . . . ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።” (ማቴዎስ 6:25, 33, 34) ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘አምላክ ስለ እኛ ስለሚያስብ የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንድንጥል’ አሳስቦናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ችግሮችን ለመፍታት መጣር ተገቢ ነው። ይሁንና የቻልነውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ስለ ጉዳዩ መጨነቅ ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ መጸለያችን ይረዳናል። መዝሙራዊው “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 37:5
16 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ፍጽምና የሚጎድላቸው የአዳም ዘሮች ሙሉ በሙሉ ከጭንቀት ነፃ ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። (ሮሜ 5:12) ኤሳው ባገባቸው ኬጢያዊያን ሚስቶቹ ምክንያት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቹ ማለትም ይስሐቅና ርብቃ ‘ልባቸው ያዝን ነበር።’ (ዘፍጥረት 26:34, 35) እንደ ጢሞቴዎስና ጥሮፊሞስ ያሉ ክርስቲያኖች የጤና እክል ሳያስጨንቃቸው አልቀረም። (1 ጢሞቴዎስ 5:23፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:20) ጳውሎስ ስለ እምነት ባልንጀሮቹ ይጨነቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:28) ይሁንና ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ መቼም ቢሆን ከሚወዱት ጎን አይለይም።—መዝሙር 65:2
17 የይሖዋን ቀን መምጣት በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት “የሰላም አምላክ” ድጋፍና ማጽናኛ ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:9) ይሖዋ ‘ሩኅሩኅና ቸር፣’ እንዲሁም ‘ጥሩና ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ ነው። “ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” (ዘፀአት 34:6፤ መዝሙር 86:5 NW፤ 103:13, 14) በመሆኑም ‘ልመናችንን በእሱ ፊት እናቅርብ።’ እንዲህ ካደረግን ‘የአምላክን ሰላም’ ይኸውም ከሰዎች የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነውን የመረጋጋት ስሜት እናገኛለን።
18 ጸሎታችን መልስ ሲያገኝ አምላክ ከእኛ ጋር መሆኑን እንረዳለን። ኢዮብ የደረሱበትን ፈተናዎች በጽናት ከተቋቋመ በኋላ “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 42:5) እኛም በማስተዋል፣ በእምነትና በአድናቆት ዓይናችን ተጠቅመን ከአምላክ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ማሰላሰልና ይሖዋን ከበፊቱ ይበልጥ ‘ማየት’ እንችላለን። እንዲህ ያለው ቅርርብ ለልባችንና ለአእምሯችን እጅግ ታላቅ ሰላም ያስገኝልናል!
19 ‘የሚያስጨንቀንን ሁሉ በይሖዋ ላይ የምንጥል ከሆነ’ ልባችንን እና ሐሳባችንን የሚጠብቅልን ውስጣዊ የመረጋጋት ስሜት ስለምናገኝ የሚደርስብንን ፈተና በጽናት መቋቋም እንችላለን። ምሳሌያዊው ልባችን ከመረበሽ ስሜት፣ ከፍርሃትና ከስጋት ነፃ ይሆናል። ግራ ከመጋባትና ከጭንቀት ነፃ ስለምንሆን የተረጋጋ አእምሮ ይኖረናል።
20 ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ከባድ የእምነት ፈተና በደረሰበት ጊዜ የመረጋጋት መንፈስ ታይቶበታል። እስጢፋኖስ የመጨረሻውን ምሥክርነት ከመስጠቱ በፊት በሳንሄድሪን ሸንጎ ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ “ፊቱ የመልአክ ፊት መስሎ ታያቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 6:15) የፊቱ ገጽታ፣ የአምላክ መልእክተኛ እንደሆነ መልአክ ፊት ፍጹም የመረጋጋት ስሜት ይነበብበት ነበር። ከዚያም እስጢፋኖስ ለኢየሱስ ሞት ተጠያቂ መሆናቸውን ሲነግራቸው ዳኞቹ “እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።” እሱ ግን “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ።” እስጢፋኖስ ይህን ራእይ መመልከቱ ስላበረታታው እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ለመሆን ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 7:52-60) በአሁኑ ጊዜ ራእይ ባናይም ስደት ሲደርስብን አምላክ የሚሰጠው የመረጋጋት መንፈስ ይኖረናል።
21 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚዎች የተገደሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስሜታቸውን እንዴት ገልጸው እንደነበር ተመልከት። አንድ ክርስቲያን ችሎት ፊት በቀረበበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የሞት ፍርድ እንደተበየነብኝ ሲነበብ ሰማሁ። ከዚያም ‘እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን’ እንደሚለው ያሉ የጌታችንን ቃላት ከተናገርኩ በኋላ ሁሉ ነገር አበቃ። በአሁኑ ወቅት ከምትገምቱት በላይ ሰላምና የመረጋጋት ስሜት አለኝ፤ በመሆኑም ፈጽሞ አትጨነቁ!” አንገቱ ተቀልቶ እንዲሞት የተፈረደበት አንድ ወጣት ክርስቲያን ለወላጆቹ እንዲህ ሲል ጽፎላቸው ነበር:- “አሁን እኩለ ሌሊት አልፏል። ሐሳቤን ለመለወጥ የሚያስችል ጊዜ አለኝ። ሆኖም ጌታችንን ብክድ በዚህ ዓለም ደስተኛ ሆኜ መኖር እችላለሁ? እንደማልችል የታወቀ ነው! አሁን ግን የምሞተው ደስ እያለኝና ተረጋግቼ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ።” ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ ምንም ጥርጥር የለውም።
መጽናት ትችላለህ!
22 ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች አልደረሱብህ ይሆናል። ያም ሆኖ ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ ትክክል ነው። (ኢዮብ 14:1) ልጆችህን በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሠረት ለማሳደግ የምትደክም ወላጅ ልትሆን ትችላለህ። ልጆችህ በትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸውን ፈተና በጽናት መቋቋም ቢኖርባቸውም ለይሖዋና ለጽድቅ መሥፈርቶቹ ታማኝ መሆናቸውን ስትመለከት እጅግ ትደሰታለህ! ወይም ደግሞ በሥራ ቦታ አስቸጋሪ ሁኔታና ፈተና የሚያጋጥምህ ክርስቲያን ልትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ሸክምህን በየዕለቱ ስለሚሸከምልህ’ እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን በጽናት መቋቋም ትችላለህ።—መዝሙር 68:19
23 ራስህን ተራ ሰው አድርገህ ትቆጥር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሥራህንና ቅዱስ ለሆነው ስሙ ያሳየኸውን ፍቅር ፈጽሞ እንደማይረሳ አስታውስ። (ዕብራውያን 6:10) በእሱ እርዳታ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት መወጣት ትችላለህ። ስለዚህ ስትጸልይ የአምላክን ፈቃድ ስለማድረግ ጸልይ፤ እንዲሁም እቅድ ስታወጣ የአምላክን ፈቃድ ከግምት ውስጥ አስገባ። እንዲህ ካደረግህ የይሖዋን ቀን በጽናት ስትጠብቅ የእሱ በረከትና ድጋፍ እንደማይለይህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ክርስቲያኖች መጽናት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
• ሕመምንና የደረሰብንን ሐዘን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
• ጸሎት በፈተና ወቅት እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?
• የይሖዋን ቀን በጽናት መጠበቅ ይቻላል የምንለው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1, 2. ጽናት ምንድን ነው? ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ የሆነውስ ለምንድን ነው?
3, 4. የጤና ችግር ቢኖርብንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል እንደምንችል የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
5. ክርስቲያኖች ያለባቸውን ከባድ ጭንቀት መቋቋም እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
6. አንድ ክርስቲያን ስሜታዊ ችግሮቹን የተቋቋመው እንዴት ነው?
7. አንዳንዶች በሕዝብ ፊት መናገር ወይም በስብሰባ ላይ መገኘት የሚያስፈራቸው ቢሆንም ይህን ችግራቸውን በጽናት የተቋቋሙት እንዴት ነው?
8. ስሜታዊ ችግሮችን ለመቋቋም ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ምንድን ነው?
9-11. (ሀ) የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን የሚሰማንን ሐዘን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) የሐና ምሳሌ ሐዘናችንን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
12. አንዳንድ ክርስቲያኖች ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ እንዴት ያለ ፈተና መቋቋም አስፈልጓቸዋል?
13, 14. (ሀ) ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ በሚመረቅበት ወቅት ካቀረበው ጸሎት ምን ማበረታቻ ታገኛለህ? (ለ) መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
15. ጭንቀታችንን ለመቀነስ የሚረዱን የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ናቸው?
16, 17. (ሀ) ሙሉ በሙሉ ከጭንቀት ነፃ መሆን የማንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን ተግባራዊ ማድረጋችን ምን ያስገኝልናል?
18. በኢዮብ 42:5 ላይ እንደተገለጸው አምላክን ‘ማየት’ የሚቻለው እንዴት ነው?
19. ‘የሚያስጨንቀንን ሁሉ በይሖዋ ላይ መጣል’ ምን ውጤት ያስገኛል?
20, 21. (ሀ) የእስጢፋኖስ ሁኔታ በስደት ጊዜ መረጋጋት እንደሚቻል የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በፈተና ጊዜ መረጋጋት እንደሚቻል የሚያሳዩ ዘመናዊ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
22, 23. የይሖዋን ቀን በጽናት ስትጠብቅ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ መታመን የምንወደውን ሰው በሞት ማጣታችን ያስከተለብንን ሐዘን ለመቋቋም ይረዳናል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከልብ የመነጨ ጸሎት የሚደርስብንን የእምነት ፈተና ለመቋቋም ያስችለናል