ንድፍ አውጪ ሳይኖር ንድፍ ሊኖር ይችላል?
ንድፍ አውጪ ሳይኖር ንድፍ ሊኖር ይችላል?
ቻርልስ ዳርዊን በሕያዋን ፍጥረታት ላይ ለሚታየው ውስብስብነትና ለተለያዩ የዝርያ ዓይነቶች መገኘት ምክንያት የሆነው ተፈጥሯዊ ምርጦሽ (Natural Selection) ነው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከተናገረ 150 ዓመታት ገደማ አልፈዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብም ሆነ በዘመናችን ያሉት ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች አመለካከቶች፣ በሕያዋን ፍጥረታት ላይ የሚታየው አስደናቂና እንከን የለሽ ንድፍ በዓላማ የተሠራ መሆኑን ከሚያምኑ ወገኖች ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል። ሌላው ቀርቶ እውቅ የሆኑ በርካታ ሳይንቲስቶች እንኳ በምድር ላይ ለምናያቸው የተለያዩ ዝርያዎች መገኘት ምክንያቱ ዝግመተ ለውጥ ነው የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም።
ከእነዚህ ሳይንቲስቶች መካከል አንዳንዶቹ በምድር ላይ የምናያቸው የተለያዩ ዝርያዎች ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆባቸዋል የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ። እነዚህ ሰዎች፣ ፍጥረታት ንድፍ እንዳላቸው በባዮሎጂና በሒሳብ ቀመር ማረጋገጥ እንደሚቻልና ይህንን እውነታ አንድ ሰው በቀላሉ አመዛዝኖ ሊደርስበት እንደሚችል ይናገራሉ። እንዲያውም ይህ ሐሳብ በትምህርት ቤቶች በሚሰጠው የሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ይፈልጋሉ። የዝግመተ ለውጥ ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ይህ የሐሳብ ፍጭት በዋነኛነት የሚታየው በዩናይትድ ስቴትስ ቢሆንም በሰርቢያ፣ በቱርክ፣ በእንግሊዝ፣ በኔዘርላንድስና በፓኪስታን ውስጥም እንዳለ ሪፖርት ተደርጓል።
እንቆቅልሽ የሆነ ክፍተት
ይሁን እንጂ፣ አብዛኛውን ጊዜ ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል ብለው የሚያምኑ ምሑራን የመከራከሪያ ሐሳቦቻቸውን ለመግለጽ በሚጠቀሙባቸው በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላት ውስጥ ትልቅ ክፍተት መኖሩ በጉልህ ይታያል። ይህ ክፍተት ስለ ንድፍ አውጪ የሚጠቀስ ነገር አለመኖሩ ነው። ‘ንድፍ አውጪ ሳይኖር ንድፍ ሊኖር ይችላል’ ቢባል ትስማማለህ? ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት የዚህ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች “ስለ ንድፍ አውጪው ማንነትም ሆነ ምንነት በግልጽ የሚናገሩት ነገር የለም” ብሏል። ክሎዲ ዋለስ የተባሉ አንድ ጸሐፊ ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ደጋፊዎች “በውይይታቸው ውስጥ አምላክን ላለማንሳት ይጠነቀቃሉ” ብለዋል። ኒውስዊክ መጽሔት ደግሞ “ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው ሐሳብ ስለ ንድፍ አውጪው ሕልውናም ሆነ ማንነት ምንም የሚገልጸው ነገር የለም” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ያም ሆኖ ስለ ንድፍ አውጪው ማንነት የሚነሳውን ጥያቄ ለማድበስበስ መጣር ፍሬ ቢስ መሆኑን ሳትገነዘብ አትቀርም። የንድፍ አውጪው ሕልውናም ሆነ ማንነት ከተሰወረ፣ ሌላው ቢቀር ከግምት ውስጥ የማይገባ ከሆነ በአጽናፈ ዓለምም ሆነ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ስለተንጸባረቀው ንድፍ የሚሰጠው ማብራሪያ እንዴት የተሟላ ሊሆን ይችላል?
ንድፍ አውጪ አለ ወይስ የለም የሚለው ሙግት የሚሽከረከረው በሚከተሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ነው:- ከሰው በላይ የሆነ ንድፍ አውጪ አለ ብሎ ማመን የሳይንስንና የሰዎችን የማሰብ ችሎታ እድገት ይገታዋል? ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ አካል አለ በሚለው ሐሳብ ማመን የሚኖርብን ሕይወት ከየት መጣ ለሚለው ጥያቄ ሌላ የተሻለ መልስ ካላገኘን ብቻ ነው? ንድፍ ካለ ንድፉን ያወጣ አካል መኖር አለበት የሚለው ድምዳሜ ምክንያታዊ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጨምሮ ከዚህ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ዳርዊን ውስብስብ የሆኑት ሕያዋን ፍጥረታት የተገኙት በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ነው የሚል እምነት ነበረው
[ምንጭ]
ዳርዊን፦ From a Photograph by Mrs. J. M. Cameron/U.S. National Archives photo