ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል
ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል
‘እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁ።’—ኢሳይያስ 61:8
1, 2. (ሀ) “ፍትሕ” እና “ኢፍትሐዊነት” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና እሱ ስላለው የፍትሕ ባሕርይ ምን ይላል?
ፍትሕ፣ ‘አድልዎ የሌለበት፣ ትክክለኛ ብያኔ እንዲሁም ከሥነ ምግባር አኳያ ቀና እና መልካም የሆነውን ማድረግ’ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ኢፍትሐዊነት ደግሞ የፍርድ መዛባትን፣ ጭፍን ጥላቻን፣ ክፋትንና በሌሎች ላይ በደል መፈጸምን ያካትታል።
2 ከ3,500 ዓመታት በፊት ሙሴ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘መንገዱ ሁሉ ፍትሕ ነው፤ ፍትሕ የማያጓድል፣ ታማኝ አምላክ ነው።’ (ዘዳግም 32:4 NW) ከሰባት መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አምላክ ኢሳይያስን ‘እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁ’ ብሎ እንዲጽፍ በመንፈሱ ገፋፍቶታል። (ኢሳይያስ 61:8) ከዚያም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ “እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርግም!” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 9:14) በዚያው ዘመን የኖረው ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል።” (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) አዎን፣ ይሖዋ “ፍትሕን ይወዳል።”—መዝሙር 37:28፤ ሚልክያስ 3:6
ኢፍትሐዊነት ተስፋፍቷል
3. በምድር ላይ ኢፍትሐዊ ድርጊት መፈጸም የጀመረው እንዴት ነው?
3 በዛሬው ጊዜ ፍትሕ እምብዛም የሚታይ ባሕርይ አይደለም። በየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ብንሆን የፍትሕ መጓደል ሊደርስብን ይችላል። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ ከባለ ሥልጣናት ጋር ባለን ግንኙነትና በሌሎች መንገዶች፣ ሌላው ቀርቶ በቤተሰብ ውስጥ ኢፍትሐዊ ድርጊት ይፈጸምብን ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች መከሰታቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ኢፍትሐዊነት በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በዓመጸኛው መንፈሳዊ ፍጡር በሰይጣን ዲያብሎስ ገፋፊነት ባመጹና ሕግን በተላለፉ ጊዜ ነበር። አዳምና ሔዋን እንዲሁም ሰይጣን፣ ይሖዋ የሰጣቸውን አስደናቂ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነታቸውን ያላግባብ መጠቀማቸው ፍትሐዊ አልነበረም። የተከተሉት የተሳሳተ ጎዳና መላውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ለብዙ መከራና ለሞት ዳርጎታል።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ሮሜ 5:12፤ ዕብራውያን 2:14
4. ኢፍትሐዊነት የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ክፍል ከሆነ ምን ያህል ዘመን አስቆጥሯል?
4 በኤደን ዓመጽ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 6,000 ዓመታት ኢፍትሐዊነት የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ክፍል ሆኖ ቆይቷል። የዚህ ዓለም አምላክ ሰይጣን በመሆኑ ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን ሐሰተኛና የሐሰት አባት ከመሆኑም ሌላ ስም አጥፊና የይሖዋ ተቃዋሚ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን ለብዙ ዘመናት አስከፊ የሆኑ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ሲፈጽም ኖሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ከኖኅ የውኃ ጥፋት በፊት አምላክ “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን” ተመልክቶ ነበር። ለዚህ ሁኔታ በከፊልም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደረገው የሰይጣን መጥፎ ተጽዕኖ ነው። (ዘፍጥረት 6:5) እንዲህ ያለው ሁኔታ በኢየሱስም ዘመን ታይቷል። ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ “ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” ሲል ተናግሯል። እንዲህ ሲል ፍትሕ የጎደላቸውን ድርጊቶች የመሰሉ አስጨናቂ ችግሮች በየዕለቱ እንደሚከሰቱ መግለጹ ነው። (ማቴዎስ 6:34 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ” መናገሩ ትክክል ነው።—ሮሜ 8:22
5. በዘመናችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የተስፋፉት ለምንድን ነው?
5 ስለሆነም አስከፊ የሆኑ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በታሪክ ዘመናት ሁሉ መጥፎ ውጤት ሲያስከትሉ ኖረዋል። አሁን ደግሞ ሁኔታው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የከፋ ሆኗል። ለምን? ምክንያቱም አምላክ የለሽ የሆነው ይህ ሥርዓት መጨረሻው በጣም ስለተቃረበና ከዓመት ወደ ዓመት ይበልጥ ‘አስጨናቂ’ እየሆነ ስለመጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመን ሰዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- ‘ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ ይሆናሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንደነዚህ ያሉት መጥፎ ባሕርያት የተለያዩ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ይሆናሉ።
6, 7. በዘመናችን ያለው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንዴት ባሉ ከባድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ተጠቅቷል?
6 ባለፉት መቶ ዓመታት የፍትሕ መጓደል ታይቶ በማይታወቅ መጠን ተፈጽሟል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በእነዚህ ዓመታት በጣም ብዙ ጦርነቶች መካሄዳቸው ነው። ለምሳሌ፣ አንዳንድ የታሪክ ምሑራን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው። ይህ ጦርነት ካበቃ በኋላም ቢሆን በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። አሁንም ቢሆን አብዛኞቹ ሰለባዎች ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። ሰይጣን እንዲህ ያሉ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የሚያስፋፋው፣ ይሖዋ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ድል እንደሚያደርገው ማወቁ በጣም ስላስቆጣው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ትንቢት ይዟል:- “ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።”—ራእይ 12:12
7 በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወታደራዊ ኃይል የሚውለው ገንዘብ ወደ አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይጠጋል። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሕይወት የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች የሏቸውም። በመሆኑም ይህ ሁሉ ገንዘብ ሰላማዊ የሆኑ ዓላማዎችን ለማራመድ ቢውል ምን ያህል ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አስብ! በዓለማችን አንድ ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በምግብ እጦት ሲቸገሩ ሌሎች ግን የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛሉ። ከተባበሩት መንግሥታት የተገኘ አንድ ምንጭ ከረሀብ ጋር በተያያዙ ችግሮች የተነሳ በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን የሚያህሉ ልጆች እንደሚሞቱ ገልጿል። ይህ ምንኛ ፍትሕ የጎደለው ነው! በተጨማሪም በውርጃ ምክንያት ምን ያህል ንጹሐን እንደሚሞቱ ገምት። በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ከ40 እስከ 60 ሚሊዮን ውርጃ እንደሚፈጸም ይገመታል! እንዴት ያለ ዘግናኝ ኢፍትሐዊ ድርጊት ነው!
8. ለሰው ልጅ እውነተኛ ፍትሕ ሊያመጣ የሚችለው ማን ብቻ ነው?
8 ሰብዓዊ መሪዎች በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆችን እያጠቁ ላሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ማስገኘት አልቻሉም። ሰዎች ምንም ያህል ቢጥሩ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሊሄዱ አይችሉም። የአምላክ ቃል “ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ሲል በጊዜያችን ስለሚኖረው ሁኔታ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13) የፍትሕ መጓደል እጅግ ከመንሰራፋቱ የተነሳ ሰዎች ሊያስወግዱት አይችሉም። ይህን ማድረግ የሚችለው የፍትሕ አምላክ ብቻ ነው። ሰይጣንን እና አጋንንቱን እንዲሁም ክፉ ሰዎችን ማጥፋት የሚችለው እሱ ብቻ ነው።—ኤርምያስ 10:23, 24
ኢፍትሐዊነት ሰዎችን ማሳሰቡ ምክንያታዊ ነው
9, 10. አሳፍ ተስፋ የቆረጠው ለምንድን ነው?
9 ባለፉት ዘመናት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሳይቀሩ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ፍትሕንና ጽድቅን ያላመጣበት ምክንያት ጥያቄ ፈጥሮባቸው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖረን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ ተመልከት። በመዝሙር 73 አናት ላይ ‘አሳፍ’ የሚል ስም ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን ይህም በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የኖረውን ታዋቂ ሌዋዊ ሙዚቀኛ ወይም የእሱ ቤተሰብ የሆኑትን መዘምራን ሊያመለክት ይችላል። አሳፍና የእሱ ዘሮች ሕዝቡ ለአምልኮ የሚጠቀምባቸው በርካታ ሙዚቃዎችን አቀናብረዋል። ይሁንና በአንድ ወቅት የዚህ መዝሙር ጸሐፊ ተስፋ ቆርጦ ነበር። መዝሙራዊው ክፉ ሰዎች በቁሳዊ ሲበለጽጉ ተመልክቷል። እንዲሁም እርካታ ያለው ሕይወት እንደሚመሩና ለሠሩት ክፉ ሥራ ምንም መከራ እንደማይደርስባቸው ሆኖ ተሰምቶታል።
10 በመሆኑም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣ በዐመፀኞች ቀንቼ ነበርና። አንዳች ጣር የለባቸውም፤ ሰውነታቸውም ጤናማና የተደላደለ ነው። በሰዎች የሚደርሰው ጣጣ አይደርስባቸውም፤ እንደ ማንኛውም ሰው መከራ አያገኛቸውም።” (መዝሙር 73:2-8) ይሁንና ከጊዜ በኋላ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ፣ ያደረበት አፍራሽ አመለካከት ስህተት መሆኑን ተገንዝቧል። (መዝሙር 73:15, 16) መዝሙራዊው አስተሳሰቡን ለማስተካከል የጣረ ቢሆንም ክፉዎች ለፈጸሙት መጥፎ ድርጊት የማይቀጡትና ብዙውን ጊዜ በቅኖች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ሙሉ ለሙሉ መረዳት አልቻለም።
11. መዝሙራዊው አሳፍ ምን ማስተዋል ችሎ ነበር?
11 የሆነ ሆኖ በጥንት ዘመን የኖረው ይህ ታማኝ ሰው የክፉዎች የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነና ይሖዋ አምላክ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ተረድቷል። (መዝሙር 73:17-19) ዳዊት “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 37:9, 11, 34
12. (ሀ) ክፋትንና የፍትሕ መጓደልን በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ኢፍትሐዊነትን በተመለከተ ይሖዋ ስለሚወስደው የመፍትሔ እርምጃ ምን ይሰማሃል?
12 ይሖዋ፣ እሱ በወሰነው ጊዜ ክፋትንና ከዚህ ጋር የተያያዙትን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ከምድር ገጽ የማስወገድ ዓላማ እንዳለው ግልጽ ነው። ሌላው ቀርቶ ታማኝ ክርስቲያኖች እንኳ ይህን ጉዳይ ዘወትር ማስታወስ ይገባቸዋል። ይሖዋ ፈቃዱን የሚቃወሙትን ሰዎች የሚያጠፋቸው ሲሆን ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው ለሚኖሩት ግን ወሮታ ይከፍላቸዋል። “ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች። እርሱ በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምና ዲን [ያዘንባል]፤ . . . የሚለበልብ ዐውሎ ነፋስ [ያመጣል]። እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፤ የጽድቅ ሥራም ይወዳል።”—መዝሙር 11:4-7
ፍትሕ የሰፈነበት አዲስ ዓለም
13, 14. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ጽድቅና ፍትሕ የሚሰፍነው ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውን ይህን ፍትሕ የጎደለው ሥርዓት ካጠፋ በኋላ በምትኩ አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም ያመጣል። ይህ አዲስ ዓለም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ባስተማረው በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሚተዳደር ይሆናል። ክፋትና ኢፍትሐዊነት በጽድቅና በፍትሕ ሲተካ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚለው ጸሎት የተሟላ ፍጻሜውን ያገኛል።—ማቴዎስ 6:10
14 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት አገዛዝ ልንጠብቅ እንደምንችል ይነግረናል። ይህ አገዛዝ በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የሚጓጉለት መስተዳድር ነው። በዚያን ጊዜ መዝሙር 145:16 በተሟላ ሁኔታ ተፈጻሚነቱን ያገኛል:- “[ይሖዋ አምላክ] አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።” በተጨማሪም ኢሳይያስ 32:1 “እነሆ፤ ንጉሥ [ክርስቶስ ኢየሱስ በሰማይ] በጽድቅ ይነግሣል፤ ገዦችም [የክርስቶስ ምድራዊ ወኪሎች] በፍትሕ ይገዛሉ” ይላል። ኢሳይያስ 9:7 ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።” አንተስ ይህ ፍትሕ የሰፈነበት አገዛዝ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ስትካፈል ይታይሃል?
15. በአዲሱ ዓለም ይሖዋ ለሰው ልጆች ምን ያደርግላቸዋል?
15 በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ በመክብብ 4:1 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት የምንናገርበት ምክንያት አይኖረንም:- “ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።” እርግጥ ነው፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚሰፍነው ጽድቅ ምን ያህል አስደናቂ እንደሚሆን ፍጹም ባልሆነው አእምሯችን መገመት ያዳግታል። ክፋት ፈጽሞ አይኖርም፤ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ቀን በመልካም ነገሮች የተሞላ ይሆናል። አዎን፣ ይሖዋ እኛ ከምንገምተው በላይ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል። ይሖዋ አምላክ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚከተሉትን ቃላት እንዲጽፍ በመንፈሱ ያነሳሳው መሆኑ ተገቢ ነው:- “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን”!—2 ጴጥሮስ 3:13
16. በአሁኑ ጊዜ “አዲስ ሰማይ” የተቋቋመው እንዴት ነው? “አዲስ ምድር” ለመገንባት የሚያስችለው መሠረት በዘመናችን መጣል ጀምሯል የምንለው ከምን አንጻር ነው?
16 በአሁኑ ወቅት ‘አዲሱ ሰማይ’ ማለትም በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ተቋቁሟል። ‘አዲሱን ምድር’ ይኸውም ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች የሚሞላውን አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ለመገንባት መሠረት ሆነው የሚያገለግሉት ሰዎች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሰዎች በ235 አገሮችና ወደ 100,000 በሚጠጉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ቁጥራቸውም ሰባት ሚሊዮን ገደማ ሆኗል። እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን የጽድቅና የፍትሕ መንገዶች የተማሩ በመሆናቸው በክርስቲያናዊ ፍቅር የተሳሰረ ዓለም አቀፍ አንድነት ሊኖራቸው ችሏል። ይህ አንድነት የሰይጣን ተገዢዎች ካላቸው ከየትኛውም አንድነት ልቆ የሚገኝ ሲሆን በጉልህ የሚታይና ጸንቶ የሚቀጥል መሆኑ በዓለም ታሪክ ተመሥክሮለታል። እንዲህ ያለው ፍቅርና አንድነት፣ በጽድቅና በፍትሕ በሚተዳደረው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖረው አስደናቂ ጊዜ ቅምሻ ነው።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 13:34, 35፤ ቈላስይስ 3:14
የሰይጣን ጥቃት ይከሽፋል
17. ሰይጣን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው የመጨረሻ ጥቃት እንደሚከሽፍ እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው?
17 በቅርቡ ሰይጣንና ተከታዮቹ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችን ለማጥፋት ይነሳሉ። (ሕዝቅኤል 38:14-23) ይህ ሁኔታ ኢየሱስ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ” ሲል የገለጸው “ታላቅ መከራ” ክፍል ይሆናል። (ማቴዎስ 24:21) የሰይጣን ጥቃት ይሳካለታል? በፍጹም አይሳካለትም። የአምላክ ቃል የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:28, 29
18. (ሀ) ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ለሚሰነዝረው ጥቃት አምላክ ምን ምላሽ ይሰጣል? (ለ) ፍትሕ ድል እንደሚያደርግ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መከለስህ ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?
18 ሰይጣንና ጭፍሮቹ በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት በይሖዋ ላይ የሚቃጣ የመጨረሻው የድፍረት ድርጊት ይሆናል። ይሖዋ በዘካርያስ በኩል “የሚነካችሁ የዐይኑን [“የዓይኔን፣” የ1980 ትርጉም] ብሌን ይነካል” በማለት ተናግሯል። (ዘካርያስ 2:8) ይህ አንድ ሰው የይሖዋን የዓይን ብሌን ለመንካት እጁን እንደሰነዘረ ያህል ይቆጠራል። ይሖዋም ፈጣን እርምጃ በመውሰድ እንዲህ የሚያደርጉትን ያጠፋቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ እጅግ አፍቃሪዎች፣ አንድነት ያላቸው፣ ሰላማውያንና ሕግ አክባሪዎች ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት የማይገባና ኢፍትሐዊ ነው። ‘ፍትሕን የሚወደው’ ይሖዋ ዝም ብሎ አይመለከትም። ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማዳን የሚወስደው እርምጃ ጠላቶቻቸው ለዘላለም እንዲደመሰሱ፣ ፍትሕ ድል እንዲያደርግ እንዲሁም ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች መዳንን እንዲያገኙ ምክንያት ይሆናል። ከፊታችን እንዴት ያሉ አስደናቂና አስደሳች ሁኔታዎች ይጠብቁናል!—ምሳሌ 2:21, 22
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢፍትሐዊ ድርጊት የተስፋፋው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ በምድር ላይ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል የሚያስወግደው እንዴት ነው?
• ፍትሕ ድል እንደሚያደርግ በሚገልጸው በዚህ ጥናት ውስጥ ልብህን የነካው ምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጥፋት ውኃ በፊት እንደነበረው ሁሉ ክፋት በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመንም’ ተንሰራፍቶ ይገኛል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ አዲስ ዓለም ክፋት በፍትሕና በጽድቅ ይተካል