በሕይወታችሁ ውስጥ ትርጉም ያለው ዓላማ ይኑራችሁ
በሕይወታችሁ ውስጥ ትርጉም ያለው ዓላማ ይኑራችሁ
‘እስትንፋስ ያለው ሁሉ ይሖዋን ያመስግን።’—መዝሙር 150:6
1. አንድ ወጣት፣ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት ስላደረገው ጥረት ግለጽ።
“ሕይወቴን ሰዎችን ለመርዳት ላውለው ስለፈለግሁ የሕክምና ትምህርት አጠናሁ። ዶክተር መሆን የሚያስገኘው ክብርና ዳጎስ ያለ ደመወዝ ደስተኛ እንደሚያደርገኝ አስቤ ነበር።” ይህን የተናገረው በኮሪያ ያደገው ሰንግ ጂን ነው። a አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ዶክተሮች ሰዎችን በመርዳት ረገድ አቅማቸው ውስን እንደሆነ ስገነዘብ ግራ ተጋባሁ። ከዚያም በሥነ ጥበብ መስክ ተሰማራሁ፤ ሆኖም የሥነ ጥበብ ሥራዎቼ ሌሎችን ብዙም ስለማይጠቅሙ ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ቀጥሎ ደግሞ መምህር ሆንኩ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ለተማሪዎቼ መረጃ ከማስተላለፍ አልፌ እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝ መመሪያ ልሰጣቸው እንደማልችል ተረዳሁ።” እንደ ሌሎች በርካታ ሰዎች ሁሉ ሰንግ ጂን በሕይወቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ዓላማ እንዲኖረው ይፈልግ ነበር።
2. (ሀ) ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ፈጣሪ በምድር ላይ እንድንኖር ያደረገበት ዓላማ እንዳለው እንዴት ማወቅ እንችላለን?
2 እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት፣ ለምን እንደምንኖር ልንገነዘብ እንዲሁም በግልጽ የተቀመጠ ግብና ልንደርስበት የምንጥረው ራእይ ሊኖረን ይገባል። ታዲያ የሰው ልጆች እንዲህ ዓይነት ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል? አዎን! የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ እንዲሁም ሕሊና ኖሮን መፈጠራችን፣ ፈጣሪ በምድር ላይ እንድንኖር ያደረገበት ታላቅ ዓላማ እንዳለው ያሳያል። በመሆኑም የሕይወታችንን እውነተኛ ዓላማ በትክክል ማወቅና ዳር ማድረስ የምንችለው ከፈጣሪ ዓላማ ጋር ተስማምተን ስንኖር ብቻ ነው።
3. አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምን ነገሮችን ያካትታል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ብዙ ነገሮችን እንደሚያካትት ይናገራል። ለአብነት ያህል፣ ግሩም የሆነው አፈጣጠራችን አምላክ ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። (መዝሙር 40:5፤ 139:14) በመሆኑም ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ሲባል አምላክ እንዳደረገው ሌሎችን ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መንገድ መውደድ ማለት ነው። (1 ዮሐንስ 4:7-11) ከዚህም በላይ የአምላክን መመሪያዎች መታዘዝን የሚጨምር ሲሆን ይህ ደግሞ ፍቅር ከሚንጸባረቅበት ዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ይረዳናል።—መክብብ 12:13፤ 1 ዮሐንስ 5:3
4. (ሀ) ሕይወታችን እውነተኛ ዓላማ እንዲኖረው ምን ያስፈልጋል? (ለ) ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚችለው ከሁሉ የላቀ ዓላማ ምንድን ነው?
4 ሌላው የአምላክ ዓላማ ደግሞ የሰው ልጆች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ፍጥረታት ጋር በደስታና በሰላም እንዲኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26፤ 2:15) ሆኖም ደስታ ለማግኘት እንዲሁም ከስጋት ነጻ ሆነንና የአእምሮ ሰላም አግኝተን ለመኖር ምን ማድረግ አለብን? አንድ ልጅ፣ ወላጆቹ አጠገቡ ሲሆኑ ደስተኛ እንዲሁም ከስጋት ነጻ እንደሚሆን ሁሉ እኛም እውነተኛ ትርጉምና ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት እንድንችል በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። (ዕብራውያን 12:9) አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ በመፍቀድ ብሎም ጸሎቶቻችንን በመስማት የአባትና የልጅ ዓይነት ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችለን ዝግጅት አድርጓል። (ያዕቆብ 4:8፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15) በእምነት ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ካደረግን’ እንዲሁም የእሱ ወዳጆች ከሆንን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ማስደሰትና ማወደስ እንችላለን። (ዘፍጥረት 6:9፤ ምሳሌ 23:15, 16፤ ያዕቆብ 2:23) ይህም ማንኛውም ሰው ሊኖረው ከሚችለው ዓላማ ሁሉ የላቀ ነው። መዝሙራዊው “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 150:6
የሕይወትህ ዓላማ ምንድን ነው?
5. ለቁሳዊ ፍላጎቶቻችን ቅድሚያ መስጠት የጥበብ አካሄድ የማይሆነው ለምንድን ነው?
5 አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን መንከባከብን ይጨምራል። ይህም ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ማሟላትን ያጠቃልላል። ይሁን እንጂ ይህን በምናደርግበት ጊዜ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንና ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ችላ እንድንል እንዳያደርጉን ሚዛናዊ መሆን ይኖርብናል። (ማቴዎስ 4:4፤ 6:33) የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች መላ ሕይወታቸው ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ነው። ይሁን እንጂ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ በቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት መሞከር ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። በቅርቡ በእስያ በሚገኙ ባለጠጋ ሰዎች ላይ የተካሄደ ጥናት፣ አብዛኞቹ “በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሀብታቸው አንድ ነገር እንዳከናወኑ እንዲሰማቸው የሚያደርጋቸው ቢሆንም እንደሚሰጉና እንደሚጨነቁ” ጠቁሟል።—መክብብ 5:11
6. ኢየሱስ ሀብት ማሳደድን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?
6 ኢየሱስ፣ ሀብት ‘አጓጊ’ ወይም አታላይ እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 4:19) ሀብት አታላይ የሆነው እንዴት ነው? ሰዎች ቁሳዊ ነገሮች ደስታ እንደሚያስገኙ ቢያስቡም ይህ ከእውነታው የራቀ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም” ብሏል። (መክብብ 5:10) ሆኖም ቁሳዊ ነገሮችን እያሳደዱ አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ይቻላል? በፍጹም አይቻልም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።” ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን በምድር ላይ ቁሳዊ ነገሮች ከማከማቸት ይልቅ ‘በሰማይ ሀብት እንዲያከማቹ’ ማለትም ‘ከመለመናቸው በፊት ምን እንደሚያስፈልጋቸው በሚያውቀው’ አምላክ ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፉ አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:8, 19-25
7. “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው ለነበረው ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በዚህ ረገድ ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቶ ነበር። ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎታል:- “ባለጠጎች የሆኑት . . . ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። . . . ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት’ ምንድን ነው?
8. (ሀ) ብዙዎች ሀብትና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከበሬታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? (ለ) እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎችስ ምን ያልተገነዘቡት ነገር አለ?
8 ብዙዎች ‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት’ ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የቅንጦትና የተድላ ሕይወት ነው። በእስያ የሚዘጋጅ አንድ የዜና መጽሔት፣ “ፊልሞችን ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን የሚመለከቱ ሰዎች የሚያዩትን ነገር መመኘት እንዲሁም ሊኖራቸው የሚችለውን ነገር ማለም ይጀምራሉ” ብሏል። በርካታ ሰዎች የሕይወታቸው ዓላማ ሀብት ማካበትና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከበሬታ ማግኘት ሆኗል። ብዙዎች እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሲሉ የወጣትነት ዕድሜያቸውን፣ ጤንነታቸውን፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውን እንዲሁም መንፈሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ያደርጋሉ። በርካታ ሰዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርበው የቅንጦትና የተድላ ሕይወትን የሚያበረታታ ሐሳብ “የዓለምን መንፈስ” የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አይገነዘቡም፤ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው ይህ መንፈስ በምድር ላይ ከሚገኙት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በአብዛኞቹ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ሲሆን አምላክ ለእኛ ካለው ዓላማ ጋር በሚጋጭ መንገድ እንዲኖሩ ይገፋፋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2) ከዚህ አንጻር በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ደስተኞች አለመሆናቸው ምንም አያስደንቅም!—ምሳሌ 18:11፤ 23:4, 5
9. የሰው ልጆች ፈጽሞ ሊያደርጉት የማይችሉት ነገር ምንድን ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?
9 ለሌሎች ደኅንነት በማሰብ ረሃብን፣ በሽታንና የፍትሕ መጓደልን ለማስወገድ ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ስለሚለፉ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚያከናውኑት ታላቅ ሥራ ብዙዎችን ይጠቅማል። ይሁን እንጂ ምንም ያህል ቢጥሩ ይህ ሥርዓት ፍትሕና ጽድቅ የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ አይችሉም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘መላው ዓለም በክፉው [በሰይጣን] ሥር’ ነው፤ እሱ ደግሞ ሥርዓቱ እንዲለወጥ አይፈልግም።—1 ዮሐንስ 5:19
10. ታማኝ የሆኑ ሰዎች “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” የሚያገኙት መቼ ነው?
10 ሕይወት ይህ ብቻ እንደሆነ ለሚያስብ ሰው ሁኔታው እንዴት አሳዛኝ ነው! ጳውሎስ “ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን” በማለት ጽፏል። ሕይወት ይህ ብቻ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል አመለካከት አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:19, 32) ይሁን እንጂ ስለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ አለን፤ ‘ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር [በአምላክ] ተስፋ ቃል መሠረት እንጠባበቃለን።’ (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያን ወቅት ክርስቲያኖች “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም “የዘላለም ሕይወት” አግኝተውና ፍጹማን ሆነው በሰማይ አሊያም በአምላክ መንግሥት ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ይኖራሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:12
11. የአምላክን መንግሥት በመደገፍ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም ጥረት ማድረግ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?
11 የሰው ልጆችን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። በመሆኑም ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚችለው ከሁሉ የላቀ ዓላማ የአምላክን መንግሥት በመደገፍ የእሱን ፈቃድ መፈጸም ነው። (ዮሐንስ 4:34) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሰማይ ከሚገኘው አባታችን ጋር ውድ ዝምድና ይኖረናል። ከዚህም በተጨማሪ በሕይወታቸው ውስጥ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው በሚሊዮን ከሚቆጠሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን በማገልገል እንደሰታለን።
ለትክክለኛው ነገር መሥዋዕት መክፈል
12. በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሕይወት ‘እውነተኛ ከሆነው ሕይወት’ ጋር አወዳድር።
12 መጽሐፍ ቅዱስ ዓለምና ‘ምኞቱ እንደሚያልፉ’ ይናገራል። በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለውን ዝናና ሀብት ጨምሮ የትኛውም የሰይጣን ዓለም ክፍል ከጥፋት አይተርፍም፤ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:15-17) በዚህ ሥርዓት ውስጥ ካለው አስተማማኝነት የሌለው ሀብት፣ አላፊ ከሆነው ክብርና ዘላቂነት ከሌለው ደስታ በተቃራኒ ‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት’ ማለትም በአምላክ መንግሥት ሥር የሚገኘው የዘላለም ሕይወት መጨረሻ የሌለው ከመሆኑም በላይ መሥዋዕትነት ቢከፈልለት አያስቆጭም። እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት የምናገኘው ግን ለትክክለኛው ነገር መሥዋዕት ከከፈልን ነው።
13. አንድ ባልና ሚስት ለትክክለኛው ነገር መሥዋዕት የከፈሉት እንዴት ነው?
13 ሄንሪንና ሱዛንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት የሚያስቀድሙ ሁሉ የይሖዋን እርዳታ እንደሚያገኙ አምላክ በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት አላቸው። (ማቴዎስ 6:33) በመሆኑም አንዳቸው ብቻ ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት ከሁለት ሴቶች ልጆቻቸው ጋር በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ መጠነኛ ክፍያ በሚጠይቅ ቤት ውስጥ ለመኖር መርጠዋል። (ዕብራውያን 13:15, 16) አንዲት አሳቢ የሆነች ወዳጃቸው ያደረጉት ምርጫ ሊገባት ስላልቻለ ሚስትየዋን “በሚያምር ቤት ውስጥ መኖር ከፈለግሽ አንድ ነገር መሥዋዕት ማድረግ አለብሽ” አለቻት። ሄንሪና ሱዛን ግን በሕይወታቸው ውስጥ ይሖዋን ማስቀደም “ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ [እንዳለው]” ያውቁ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ ቲቶ 2:12) ልጆቻቸውም ቀናተኛ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነዋል። የቤተሰቡ አባላት ምንም ነገር እንደቀረባቸው አይሰማቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ዓላማቸው “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት በመሆኑ በእጅጉ ተጠቅመዋል።—ፊልጵስዩስ 3:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
“በዚህ ዓለም” ሙሉ በሙሉ አትጠቀሙ
14. እውነተኛውን የሕይወታችንን ዓላማ መዘንጋት ምን አሳዛኝ ውጤት ያስከትላል?
14 እውነተኛውን የሕይወታችንን ዓላማ ከዘነጋንና “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” አጥብቀን ካልያዝን ግን አደገኛ ነው። “በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ [ልንታነቅ]” እንችላለን። (ሉቃስ 8:14) ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ያለንን ፍላጎት ገደብ ካላበጀንለት እንዲሁም ከመጠን በላይ ‘ስለ ኑሮ የምንጨነቅ’ ከሆነ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከልክ በላይ ልንጠላለፍ እንችላለን። (ሉቃስ 21:34) የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንዶች በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚገኘው ሀብታም የመሆን ፍላጎት ስለተጠናወታቸው “ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” ሌላው ቀርቶ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ውድ ዝምድና እንኳ አጥተዋል። በእርግጥም ‘የዘላለም ሕይወትን አጥብቀው’ አለመያዛቸው ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሎባቸዋል!—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10, 12፤ ምሳሌ 28:20
15. አንድ ቤተሰብ “በዚህ ዓለም” ሙሉ በሙሉ ባለመጠቀሙ የተባረከው እንዴት ነው?
15 ጳውሎስ “በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:31) ኪትና ቦኒ ይህንን ምክር ተግባራዊ አድርገዋል። ኪት እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት በጥርስ ሕክምና መስክ ትምህርቴን ላጠናቅቅ ስቃረብ ነበር። በርካታ ሕመምተኞችን በማከም ብዙ ገንዘብ የማግኘት አጋጣሚ የነበረኝ ቢሆንም እንዲህ ማድረጌ ግን መንፈሳዊነታችንን እንደሚነካብን ተገነዘብኩ። አምስት ሴቶች ልጆቻችንን ጨምሮ የቤተሰባችንን መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለኝ የበለጠ ጊዜ ለማግኘት ስል የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሕመምተኞችን ብቻ ለማከም መረጥኩ። ትርፍ ገንዘብ የሚኖረን ከስንት አንዴ ቢሆንም በቁጠባ መኖርን ስለለመድን የሚያስፈልገንን አጥተን አናውቅም። ቤተሰባችን የተቀራረበና እርስ በርስ የሚዋደድ እንዲሁም ደስተኛ ነው። ከጊዜ በኋላ ሁላችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማራን። በአሁኑ ጊዜ ልጆቻችን አስደሳች ትዳር ያላቸው ሲሆን ሦስቱ ልጆች ወልደዋል። እነሱም በሕይወታቸው ውስጥ የይሖዋን ዓላማ በማስቀደማቸው ቤተሰባቸው ደስተኛ ነው።”
በሕይወትህ ውስጥ የአምላክን ዓላማ አስቀድም
16, 17. መጽሐፍ ቅዱስ ለየት ያለ ችሎታ ስለነበራቸው ሰዎች የሚገልጹ ምን ምሳሌዎችን ይዟል? እነዚህ ሰዎችስ የሚታወሱት በምንድን ነው?
16 መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ስለኖሩ ሰዎችም ሆነ እንዲህ ስላላደረጉ ግለሰቦች የሚናገሩ ምሳሌዎችን ይዟል። ከእነዚህ ምሳሌዎች የሚገኘው ትምህርት በሁሉም የዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ፣ የተለያየ ባሕልና ሁኔታ ላላቸው ሰዎች የሚጠቅም ነው። (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:6, 11) ናምሩድ ታላላቅ ከተሞችን የቆረቆረ ቢሆንም ይህን ያደረገው ይሖዋን በመቃወም ነበር። (ዘፍጥረት 10:8, 9 NW) በሌላ በኩል ግን መልካም ምሳሌ የተዉልን ሌሎች በርካታ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ፣ ሙሴ የግብፅ ልዑል ሆኖ መኖር የሕይወቱ ዓላማ እንዲሆን አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ መብቶቹን “ከግብፅ ሀብት ይልቅ . . . እጅግ የሚበልጥ ሀብት” እንደሆኑ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ዕብራውያን 11:26) ሐኪሙ ሉቃስ፣ ጳውሎስንና ሌሎች ሰዎችን ሲታመሙ ረድቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሉቃስ ለሌሎች ካደረጋቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የላቀው ወንጌላዊና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በመሆን ያከናወነው ሥራ ነው። ጳውሎስም ቢሆን የሚታወቀው “የአሕዛብ ሐዋርያ” ሆኖ በሚስዮናዊነት በማገልገሉ እንጂ የሕግ ባለሙያ በመሆኑ አይደለም።—ሮሜ 11:13
17 ዳዊት በዋነኝነት የሚታወሰው ለአምላክ ‘እንደ ልቡ የሆነ ሰው’ እንደሆነ ተደርጎ እንጂ የጦር አዛዥ፣ የሙዚቃ ባለሙያ እንዲሁም ገጣሚ በመሆኑ አይደለም። (1 ሳሙኤል 13:14) ዳንኤልን የምናውቀው የባቢሎን መንግሥት ባለ ሥልጣን ሆኖ በመሥራቱ ሳይሆን የይሖዋ ታማኝ ነቢይ በመሆኑ ነው፤ አስቴርም የምትታወሰው የድፍረትና የእምነት ምሳሌ ስለነበረች እንጂ የፋርስ ንግሥት በመሆኗ አይደለም። ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስም የሚታወቁት ጥሩ ችሎታ ያላቸው አሳ አጥማጆች ስለነበሩ ሳይሆን የኢየሱስ ሐዋርያት በመሆናቸው ነው። ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሆነውን ኢየሱስንም ቢሆን የምናስታውሰው ‘በዐናጢነቱ’ ሳይሆን “ክርስቶስ” በመሆኑ ነው። (ማርቆስ 6:3፤ ማቴዎስ 16:16) እነዚህ ሁሉ ሰዎች የቱንም ያህል ንብረት፣ ምንም ዓይነት ችሎታ ወይም ክብር ቢኖራቸውም ሕይወታቸው በሰብዓዊ ሥራቸው ላይ ሳይሆን በአምላክ አገልግሎት ላይ ማተኮር እንዳለበት በግልጽ ተገንዝበው ነበር። በሕይወታቸው ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለው ከሁሉ የላቀና ከምንም ነገር በላይ የሚክስ ዓላማ፣ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ሆኖ መኖር እንደሆነ ያውቁ ነበር።
18. አንድ ወጣት ክርስቲያን ሕይወቱን በምን መንገድ ሊጠቀምበት ወስኗል? የትኛውንስ ሐቅ ሊገነዘብ ችሏል?
18 በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ሰንግ ጂን ከጊዜ በኋላ ይህንን ሐቅ ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል:- “ያለኝን ችሎታ ሁሉ በሕክምና ወይም በሥነ ጥበብ መስክ አሊያም በመምህርነት ከማዋል ይልቅ ራሴን ለአምላክ ስወስን ከገባሁት ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወቴን ለመጠቀም ወሰንኩ። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄጄ ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ እየረዳሁ ነው። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ችሎታዬን ሙሉ በሙሉ መጠቀም የምችል አይመስለኝም ነበር። ባሕርዬንና የተለያየ ባሕል ያላቸውን ሰዎች የማስተማር ችሎታዬን ለማሻሻል ስጥር ሕይወቴ ከምንጊዜውም በላይ አስደሳች ሆኖልኛል። ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የምንችለው የይሖዋን ዓላማ ዓላማችን ካደረግነው ብቻ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።”
19. እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት ምን ይረዳናል?
19 ክርስቲያኖች፣ ሕይወት አድን የሆነ እውቀትና የመዳን ተስፋ አላቸው። (ዮሐንስ 17:3) እንግዲያው ‘የተቀበልነውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳናደርገው’ መጠንቀቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 6:1) ከዚህ ይልቅ ውድ የሆኑትን የሕይወታችንን ዘመናት ይሖዋን ለማወደስ እንጠቀምባቸው። በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ደስታ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን እውቀት ለሰዎች እናዳርስ። ይህን ስናደርግ ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን እንመለከታለን። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) እንዲሁም እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት እንመራለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• በሕይወታችን ውስጥ ሊኖረን የሚችለው ከሁሉ የላቀ ዓላማ ምንድን ነው?
• በሕይወታችን ውስጥ ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት የጥበብ አካሄድ የማይሆነው ለምንድን ነው?
• አምላክ ቃል የገባው ‘እውነተኛ የሆነው ሕይወት’ ምንድን ነው?
• ሕይወታችንን ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ለትክክለኛው ነገር መሥዋዕት መክፈል አለባቸው