ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ይቻላል!
ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ይቻላል!
ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ገንዘብንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች ለማግኘት ሲሉ ነው። አንዳንዶች በዓለም ላይ ታዋቂ ለመሆን ይደክማሉ። ሌሎች ደግሞ በሥነ ጥበብ መስክ ያላቸውን ችሎታ ለማሳደግ ይጥራሉ። ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ መላ ሕይወታቸውን የሰጡም አልታጡም። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ለመድረስ የሚጣጣሩበት ግብ የሌላቸው ከመሆኑም ሌላ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነም አያውቁም።
አንተስ? የሕይወትህ ዓላማ ምን እንደሆነ በቁም ነገር አስበህ ታውቃለህ? ሰዎች የሚከታተሏቸው አብዛኞቹ ግቦች እውነተኛ ደስታና እርካታ አስገኝተውላቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመገንዘብ ለምን ጥቂቶቹን አትመረምርም? ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር ይቻላል?
ገንዘብና ደስታ በሕይወታችን ውስጥ ያላቸው ቦታ
መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 7:12 ላይ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” ይላል። አዎን፣ ገንዘብ ጥቅም አለው። ገንዘብ ለኑሮ፣ በተለይም ደግሞ ቤተሰብ የምታስተዳድር ከሆነ ኃላፊነትህን ለመወጣት ያስፈልግሃል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
ገንዘብ በሚገዛቸው ነገሮች መደሰት እንችላለን። የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ እንደሌለው የተናገረ ቢሆንም አልፎ አልፎ ጥሩ ምግብ ይበላና ወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። ከዚህም ማቴዎስ 8:20፤ ዮሐንስ 2:1-11፤ 19:23, 24
በላይ ዋጋው ውድ የሆነ ልብስ ይለብስ ነበር።—ይሁንና ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ደስታን ለማሳደድ አልነበረም። ኢየሱስ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ነበሩት። ኢየሱስ ‘የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ’ ተናግሯል። አክሎም፣ እርሻው ፍሬያማ ስለሆነለትና እንደሚከተለው ሲል ስላሰበ አንድ ባለጠጋ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ:- “ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? . . . ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፣ ‘ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ’ እላታለሁ።” የዚህ ሰው አስተሳሰብ ስህተቱ ምን ላይ ነበር? ምሳሌው በመቀጠል “እግዚአብሔር ግን፣ [ሀብታሙን ሰው] አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊወስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል? አለው” ይላል። ሰውየው ምርቱን ቢያከማችም እንኳ ከሞተ ያካበተው ሀብት የሚፈይድለት ነገር የለም። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው” በማለት ለአድማጮቹ ግሩም ትምህርት ሰጣቸው።—ሉቃስ 12:13-21
እርግጥ ነው፣ የተወሰነ ገንዘብ ያስፈልገናል፤ መዝናኛም ቢሆን የራሱ ቦታ አለው። ይሁን እንጂ ገንዘብም ሆነ ተድላ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዙ ነገሮች አይደሉም። በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ነገር በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆንን ማለትም በእሱ ዘንድ ሞገስ የሚያስገኝ ኑሮ መምራትን ነው።
ስመ ጥር ለመሆን መፈለግ ተገቢ ነው?
በርካታ ሰዎች ስመ ጥር ለመሆን ሲደክሙ ይታያሉ። በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ መፈለግ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ለማለት አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል” ይላል።—መክብብ 7:1
አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ፣ ያሳለፈው የሕይወት ተሞክሮ በሙሉ በመዝገብ ላይ ተጽፏል ለማለት ይቻላል። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ መልካም ነገሮችን አድርጎ ከነበረ የሞተበት ቀን፣ ይህ ነው ተብሎ ሊነገርለት የማይችል የሕይወት ታሪክ ካልነበረበት ከተወለደበት ቀን እጅግ የተሻለ ነው።
የመክብብ መጽሐፍን የጻፈው ንጉሥ ሰሎሞን ነው። የሰሎሞን ታላቅ ወንድም የነበረው አቤሴሎም ስሙን ማስጠራት ይፈልግ ነበር። ይሁንና በመጪው ትውልድ ስሙን ሊያስጠሩለት የሚችሉት ሦስት ወንዶች ልጆቹ ገና በልጅነታቸው የሞቱበት ይመስላል። ታዲያ አቤሴሎም ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “አቤሴሎም፣ ‘ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም’ በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ” እንደነበር ይገልጻል። (2 ሳሙኤል 14:27፤ 18:18) በዛሬው ጊዜ ይህ ሐውልት በስፍራው ላይ አይገኝም። አቤሴሎምም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ የሚታወቀው የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ለመቀማት ያሴረ የወጣለት ዓመጸኛ በመሆኑ ነው።
በዛሬው ጊዜ፣ በርካታ ሰዎች ባከናወኑት ነገር ለመታወስ ይጥራሉ። ፍላጎታቸው እንደየወቅቱ በሚቀያየረው በሰው ልጆች ፊት ክብር ለማግኘት ይደክማሉ። ይሁንና የእንዲህ ዓይነቱ ዝና መጨረሻ ምንድን ነው? ክሪስቶፈር ላሽ ዘ ካልቸር ኦቭ ናርሲሲዝም (ከልክ በላይ ራስ ወዳድ የመሆን ባሕል) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “የአንድ ሰው ስኬት በአብዛኛው የሚለካው ወጣት መስሎ በመታየቱ፣ በውበቱና አዲስ
ነገር በመሥራቱ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ዝነኝነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወዲያው የሚያልፍ ነገር ሆኗል። የብዙሃኑን ቀልብ ለመሳብ የበቁ ሰዎችም ቢሆን ዝናቸውን እንዳያጡ ሁልጊዜ ይሰጋሉ።” ከዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ታዋቂ አርቲስቶች ወደ አደንዛዥ ዕፅና ወደ አልኮል መጠጥ ዞር ስለሚሉ የአብዛኞቹ ሕይወት በአጭሩ ይቀጫል። በእርግጥም ዝነኛ ለመሆን መድከም ከንቱ ነው።ታዲያ ጥሩ ስም ማትረፍ ያለብን በማን ዘንድ ነው? ይሖዋ ሕጉን ስለጠበቁ አንዳንድ ሰዎች በኢሳይያስ በኩል ሲናገር “በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 56:4, 5) ለአምላክ ታዛዥ በመሆናቸው ምክንያት በእሱ ዘንድ ሞገስ ያገኙ ሰዎች “መታሰቢያና ስም” ይሰጣቸዋል። አምላክ ስማቸውን “ለዘላለም” ስለሚያስታውስ አይጠፉም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረታታን እንዲህ ዓይነቱን ማለትም በፈጣሪያችን በይሖዋ ፊት መልካም የሆነ ስም እንድናተርፍ ነው።
ኢሳይያስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ስለሚያገኙበት ጊዜ ተንብዮአል። በዚያች ገነት ውስጥ የሚኖረው “የዘላለም ሕይወት” አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥራቸው ሊሰጣቸው አስቦት የነበረው ‘እውነተኛ ሕይወት’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ጊዜያዊና እርካታ የሌለው ሕይወት ከመምራት ይልቅ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መጣጣር አይኖርብንም?
ሥነ ጥበብ ወይም በጎ አድራጎት ብቻውን አርኪ ሕይወት አያስገኝም
በርካታ አርቲስቶች በያዙት የሥነ ጥበብ ዘርፍ አንከን የለሽ ነው ብለው ወደሚያስቡት የሥራ ውጤት ለመድረስ ሲሉ ሥራቸውን እያሻሻሉ ለመሄድ ብርቱ ፍላጎት አላቸው። ሕይወት ደግሞ ይህን ለማድረግ በጣም አጭር ነው። በመጀመሪያው ርዕስ ውስጥ የተጠቀሰው ሂዲዮ በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ የሥነ ጥበብ ችሎታውን ለማሻሻል ይጥር ነበር። አንድ አርቲስት በሥራው ለመርካት በሚችልበት ደረጃ ላይ ቢደርስም እንኳ ወጣትና ጤነኛ በነበረበት ጊዜ ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ብዙ የጥበብ ሥራዎችን መሥራት አይችል ይሆናል። ይሁንና ለዘላለም መኖር ቢችል ኖሮስ? የጥበብ ሥራውን ምን ያህል እንከን የለሽ አድርጎ ሊሠራው እንደሚችል አስብ!
ሕይወትን ለበጎ አድራጎት ሥራ ስለመስጠትስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ሰው ለድሆች ትኩረት መስጠቱና ጥሪቱን በችግር ላይ ያሉትን ለመርዳት ማዋሉ የሚያስመሰግነው ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በእርግጥም ለሌሎች ደህንነት ማሰብ እርካታን ያስገኛል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለዚህ ሥራ መላ ሕይወቱን ቢሰጥ እንኳ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት ይችላል? እኛ ሰዎች የሌሎችን ችግር ለመፍታት ልናደርግ የምንችለው ነገር በጣም ውስን ነው። የትኛውንም ያህል ከፍተኛ ቁሳዊ እርዳታ ቢደረግ ብዙዎች ችላ የሚሉትን እጅግ መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። ሰዎች ደግሞ ይህ ፍላጎት ካልተሟላላቸው መቼም ቢሆን እርካታ ሊያገኙ አይችሉም። ለመሆኑ ይህ ፍላጎት ምንድን ነው?
የግድ መሟላት ያለበት ተፈጥሯዊ ፍላጎት
ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ይህን መሠረታዊ የሆነ ተፈጥሯዊ ፍላጎት አስመልክቶ ሲናገር “በመንፈሳዊ ድኾች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 NW) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እውነተኛ ደስታ ሀብትንና ዝናን በማግኘት፣ በሥነ ጥበብ ዘርፍ ስኬታማ በመሆን ወይም ለሌሎች በጎ በማድረግ ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማለትም አምላክን ለማምለክ ያለንን ውስጣዊ ስሜት በማርካት ላይ የተመካ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ፈጣሪን የማያውቁ ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉት ሲያበረታታቸው እንዲህ ብሏል:- “[አምላክ] የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው። ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤ የምንኖረውና የምንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና።”—የሐዋርያት ሥራ 17:26-28
በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ ያለንን ፍላጎት ማርካት ነው። መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካታችን ‘የእውነተኛ
ሕይወት’ ተስፋ ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ራሷ በምታዘጋጀው አንድ ሰዓት በሚፈጅ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ በመሆን በአገሯ ታዋቂነት ያተረፈችውን የተሪሳን ሁኔታ ተመልከት። ይሁንና ብዙም ሳትቆይ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጋ ተወችው። ይህን ያደረገችው ለምን ነበር? “የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር መስማት የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ስላመንኩበት ነው” ብላለች። ተሪሳ የጾታ ብልግናንና ዓመጽን የሚያበረታታ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመተወን ከአምላክ ጋር ያላትን ዝምድና ማበላሸት አልፈለገችም። ተሪሳ በሌሎች ፊት እንደ ኮከብ እንድትታይ ያደረጋትን ሥራ መሥራቷን ያቆመች ብትሆንም የአምላክ መንግሥት ምሥራች የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በመሆንና ሌሎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ በመርዳት እውነተኛ እርካታ በሚያስገኝላት የሕይወት ጎዳና ላይ መጓዝ ጀመረች።የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋ የነበረ አንድ ሰው ተሪሳ የትወና ሥራዋን ለማቆም ያደረገችውን ውሳኔ አስመልክቶ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር:- “ስኬታማ ሆናበታለች ብዬ ያሰብኩትን ሥራ እንደ ዋዛ ስትተወው ስመለከት እጅግ አዘንኩ። ይሁን እንጂ የተሻለ ነገር እንዳገኘች ግልጽ ነው።” ቆየት ብሎ፣ ተሪሳ ሕይወቷን አጣች። ከተሪሳ ሞት በኋላ፣ ይህ የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋ እንዲህ ብሏል:- “ተሪሳ ደስተኛ ነበረች። ሰው በሕይወቱ የሚፈልገው ደግሞ ይህንኑ ነው። ደስተኞች ነን ብለን መናገር የምችለው ስንቶቻችን ነን?” በሕይወታቸው ውስጥ ከአምላክ ጋር ላላቸው ዝምድና ቅድሚያ ሲሰጡ ኖረው በሞት ያንቀላፉ ሰዎች የአምላክ መንግሥት በሚገዛበት ወቅት ትንሣኤ የማግኘት አስደናቂ ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 5:28, 29
ፈጣሪ ለምድርም ሆነ በውስጧ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ዓላማ አለው። አንተም ይህን ዓላማ እንድትረዳና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ይፈልጋል። (መዝሙር 37:10, 11, 29) የሰማይና የምድር ፈጣሪ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ለመማርም ሆነ አምላክ ለአንተ ያለውን ዓላማ ለማወቅ ጊዜው አሁን ነው። በአካባቢህ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን እውቀት እንድታገኝ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ከእነሱ ጋር እንድትገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ባለጸጋ ሰው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትፈልጋለህ?