በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

• “ብሉይ ኪዳን” ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ብሉይ ኪዳንን ያስጻፈው ማንነቱ የማይታወቅ ጨካኝ አምላክ ሳይሆን አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው። ኢየሱስም ሆነ የጥንት ተከታዮቹ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ መጻሕፍት ለዕለታዊ ሕይወታችን የሚሆን ምክር ከመያዛቸውም ሌላ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ ይሰጣሉ።—9/1 ገጽ 4-7

• አምላክ፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ጊዜ እንዲያልፍ መፍቀዱ ምን ነገር እንዲታይ አድርጓል?

የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ባለፉት 6,000 የሚያህሉ ዓመታት አዳምና ሔዋን እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዝርያዎቻቸው መሞታቸው ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። አምላክ ጊዜ መፍቀዱ፣ ሰዎች ከእሱ ርቀው ራሳቸውን ቢመሩ የተሻለ ሕይወት እንደማይኖራቸው እንዲሁም የሰው ልጆች አካሄዳቸውን ለመምራት መብቱም ሆነ ችሎታው እንደሌላቸው አሳይቷል።—9/15 ገጽ 6-7

• ያዕቆብ፣ ዔሳውን መስሎ በመቅረቡ ያልተወገዘው ለምንድን ነው?

ያዕቆብ፣ ብኩርናውን ከዔሳው በመግዛቱ የአባቱን ምርቃት የማግኘት መብት ነበረው። ይስሐቅም ቢሆን የመረቀው ያዕቆብን እንደሆነ ሲያውቅ ሁኔታውን ለማስተካከል አልሞከረም። ከዚህም በተጨማሪ በጉዳዩ ጣልቃ መግባት ይችል የነበረው አምላክ ያዕቆብ እንዲመረቅ እንደፈለገ በግልጽ መመልከት ይቻላል።—10/1 ገጽ 31

• ሕሊና ያለን መሆናችን የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ እንዳልመጣ የሚያሳየው እንዴት ነው?

በሁሉም ዘሮችና ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፣ ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለውም እንኳ ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ አላቸው። ሰዎች፣ የተከፈለው ተከፍሎ ራሳቸውን ለማዳን እንደሚፍጨረጨሩ እንስሳት ቢሆኑ ኖሮ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ ያሳያሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም ነበር።—10/15 ገጽ 20

• አምላክ ትሑት ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይህንን ባሕርይስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

አምላክ ሉዓላዊ ገዥና ፈጣሪ በመሆኑ እንደ እኛ አቅሙ የተወሰነ አይደለም። ያም ሆኖ ግን በ2 ሳሙኤል 22:36 (NW) ላይ በተገለጸው መሠረት አምላክ፣ እሱን ለማስደሰት ለሚጥሩ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ስለሚያስብና ምሕረት ስለሚያሳያቸው ትሑት ነው። እሱን ለሚፈሩ ሰዎች ደግነት ለማሳየት ሲል በምሳሌያዊ አነጋገር ከሰማይ ራሱን ዝቅ ያደርጋል።—11/1 ገጽ 4-5

• ጥንታዊ የሸክላ ስብርባሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

አርኪኦሎጂስቶች፣ በኢያሱ 17:1-6 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የሰባት ነገዶች ስሞች የያዙ የሸክላ ስብርባሪዎች በሰማርያ አግኝተዋል። የዓራድ የሸክላ ስብርባሪዎች ደግሞ ስለ ካህናት ቤተሰብ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ መሆኑን ከማረጋገጣቸውም በላይ የአምላክን ስም ይዘዋል። በለኪሶ የተገኙት የሸክላ ስብርባሪዎች፣ ባቢሎናውያን ይሁዳን ከመያዛቸው በፊት በይሁዳ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታና አለመረጋጋት የሚገልጽ መረጃ ይዘዋል።—11/15 ገጽ 12-14

• የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ የጻፈው ሉቃስ ነው ብለን እንድንደመድም የሚያደርገን ምንድን ነው?

የሉቃስ ወንጌልም ሆነ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፉት ለቴዎፍሎስ መሆኑ እነዚህን መጻሕፍት ያጠናቀረው ሉቃስ እንደሆነ ይጠቁማል። ሉቃስ በዘገባቸው አንዳንድ ክንውኖች ላይ ተካፋይ እንደነበር የሚጠቁሙ ሐሳቦችን አስፍሯል። (የሐዋርያት ሥራ 16:8-15)—11/15 ገጽ 18

• አንድ ክርስቲያን፣ አደንንና ዓሣ ማጥመድን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል?

አምላክ፣ ከኖኅ ጊዜ አንስቶ ሰዎች እንስሳትን አርደው እንዲበሉ ፈቅዶላቸዋል። ያም ሆኖ እንስሳትን ከመብላታቸው በፊት ደሙን እንዲያፈስሱ መመሪያ መስጠቱ የሕይወት ምንጭ አምላክ በመሆኑ ለእንስሳቱ ሕይወት አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ ያጎላል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ችሎታቸውን ለማሳየት አሊያም ደግሞ እንስሳትን ማሳደዱ ወይም መግደሉ ስለሚያስደስታቸው እንስሳትን አይገድሉም። የቄሣርን ሕግ መታዘዝና ለሌሎች ሕሊና ማሰብም አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 14:13)—12/1 ገጽ 31