በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአረማውያን በዓል የክርስቲያን በዓል ሊደረግ ይችላል?

የአረማውያን በዓል የክርስቲያን በዓል ሊደረግ ይችላል?

የአረማውያን በዓል የክርስቲያን በዓል ሊደረግ ይችላል?

በጣሊያን በ2004 የክረምት ወቅት በገና በዓል ሰሞን የጦፈ ክርክር ተካሂዶ ነበር። አንዳንድ የትምህርት መምሪያ ባለ ሥልጣናትና መምህራን፣ ሃይማኖታዊ የገና ልማዶችን መጥቀሱ በጣም እንዲቀነስ ወይም እስከ ጭራሹ እንዲቀር የቀረበውን ሐሳብ ደግፈዋል። ይህን ያደረጉት እያደር ቁጥራቸው እየጨመረ ለመጣው ካቶሊክም ሆነ ፕሮቴስታንት ያልሆኑ ተማሪዎች በማሰብ ነው። ይሁን እንጂ በማስተማሩም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ የተለያዩ ሰዎች ባሕሉ ክብር እንዲሰጠውና እንዳለ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ።

ለመሆኑ የአብዛኞቹ የገና ልማዶች ምንጭ ምንድን ነው? ውዝግቡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘው የቫቲካን ጋዜጣ ትኩረት የሚስቡ አስተያየቶችን ሰጥቷል።

ይህ የካቶሊክ ጋዜጣ፣ ገና የሚከበርበትን ቀን አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል:- “ከታሪክ አንጻር ኢየሱስ የተወለደበት ትክክለኛ ቀን አይታወቅም፤ ምክንያቱም የሮም ታሪክ፣ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ያከናወነው የሕዝብ ቆጠራ እንዲሁም ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት የተካሄዱት ጥናቶች ትክክለኛውን ጊዜ በእርግጠኝነት አይገልጹም። . . . በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው ታኅሣሥ 25ን የመረጠችው የሮም ቤተክርስቲያን ናት። በአራተኛው መቶ ዘመን የተመረጠው ይህ ዕለት በወቅቱ ብዙ አማልክት በሚመለኩባት በሮም የፀሐይ አምላክ የሚከበርበት ቀን ነበር። . . . ምንም እንኳ ቆስጠንጢኖስ ባወጣው አዋጅ አማካኝነት ክርስትና በሮም እውቅና ቢያገኝም የፀሐይ አምላክ . . .  አፈ ታሪክ በተለይም በወታደሮች መካከል ተስፋፍቶ ይገኝ ነበር። በታኅሣሥ 25 የሚከበረው ከላይ የተጠቀሰው በዓል በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ባተረፈ ባሕል ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም የሮም ቤተ ክርስቲያን የፀሐይን አምላክ፣ የፍትሕ እውነተኛ ፀሐይ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በመተካትና ይህ ዕለት የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ቀን እንዲሆን በመምረጥ ዕለቱ በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ ፈለገች።”

በአሁኑ ጊዜ የካቶሊክ እምነት ክፍል ስለሆነው ስለ ገና ዛፍስ ምን ማለት ይቻላል?

በካቶሊክ ጋዜጣ ላይ የወጣው ርዕሰ አንቀጽ እንዳመለከተው በጥንት ዘመን “የጥድ ዝርያ የሆነ ዛፍ ቅርንጫፍ” ዓይነት ቅጠላቸው ምንጊዜም የማይረግፍ በርካታ ዕፅዋት “ሕመምን ለመከላከል የሚያስችል ምትሐታዊ ኃይል ወይም መድኃኒትነት እንዳላቸው ይታሰብ ነበር።” ጋዜጣው በመቀጠልም እንዲህ ብሏል:- “በገና በዓል ዋዜማ ማለትም ታኅሣሥ 24 ላይ ለአዳምና ለሔዋን መታሰቢያ ሲባል በምድራዊው ገነት ስለሚገኘው ዛፍ የሚያወሳ በጣም ተወዳጅ ታሪክ ይተረክ ነበር። . . . ዛፉ ፖም ሳይሆን እንደማይቀር ቢታሰብም በክረምት የፖም ዛፍ ቅጠል ስለማይኖረው በምትኩ የጥድ ዝርያ የሆነ ዛፍ መድረክ ላይ ይቆምና በቅርንጫፉ ላይ ጥቂት የፖም ፍሬዎች ይንጠለጠላሉ፤ ወይም ደግሞ የሰው ልጅ ወደፊት የሚያገኘውን መዳን ለማመልከት ከተፈጨ ብስኩት የተዘጋጀና የቁርባን ተምሳሌት የሆነ ልዩ ቅርጽ ያለው ስስ ቂጣ እንዲሁም ጣፋጭ ነገሮችና ለልጆች የሚሆኑ ስጦታዎች ይቀመጡ ነበር።” ከዚያ ዘመን በኋላስ ምን ሆነ?

ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ የተባለው ጋዜጣ የገናን ዛፍ የመጠቀም ባሕል የጀመረው በ16ኛው መቶ ዘመን በጀርመን መሆኑን ከገለጸ በኋላ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ጣሊያን የገናን ዛፍ ለመቀበል የመጨረሻ ከሆኑት አገሮች አንዷ ነበረች፤ ለዚህም በከፊል ምክንያቱ የገናን ዛፍ መጠቀም የፕሮቴስታንት ባሕል በመሆኑ [የኢየሱስን ልደትን በሚያሳይ] የሕፃን አልጋ መተካት አለበት የሚል ሐሳብ በሰፊው መሠራጨቱ ነው።” ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ “ባሕሉን የጀመሩት [በሮም ከተማ በሴይንት ጴጥሮስ አደባባይ]” ላይ የኢየሱስን ልደት በሚያሳየው ምስል አጠገብ “አንድ ትልቅ የገና ዛፍ በማቆም ነበር።”

አንድ የሃይማኖት መሪ፣ በጥንት ዘመን በነበረ አረማዊ አምልኮ ላይ ለተመሠረቱ ክንውኖችና ምልክቶች ክርስቲያናዊ ትርጉም ያላቸው እንዲመስል ማድረጉ ተቀባይነት ያለው ድርጊት ይመስልሃል? ቅዱሳን መጻሕፍት “ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” በማለት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው ትክክለኛ አካሄድ የትኛው እንደሆነ ይጠቁማሉ።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የገና ዛፍ (በፊተኛው ገጽ ላይ) እና በቫቲካን የሚገኘው የኢየሱስን ልደት የሚያሳይ ሐውልት

[ምንጭ]

© 2003 BiblePlaces.com

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፀሐይ አምላክ

[ምንጭ]

Museum Wiesbaden