ሳይዘገዩ እንዲመለሱ እርዷቸው!
ሳይዘገዩ እንዲመለሱ እርዷቸው!
“ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።” —ዮሐ. 6:68
1. ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ትተውት በሄዱ ጊዜ ጴጥሮስ ምን አለ?
በአንድ ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ብዙዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ አንዱን መቀበል ስለከበዳቸው ትተውት ሄዱ። በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱን “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት መለሰ። (ዮሐ. 6:51-69) አዎ፣ ወዴትም መሄድ አይችሉም ነበር። በዚያን ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት “የዘላለም ሕይወት ቃል” አልነበረውም፤ በዛሬው ጊዜም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የሕይወት ቃል ፈጽሞ ሊገኝ አይችልም። ከአምላክ መንጋ ወጥተው የባዘኑ ቢሆኑም ይሖዋን የማስደስት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ ‘ከእንቅልፍ የሚነቁበትና’ ወደ መንጋው የሚመለሱበት ጊዜ አሁን ነው።—ሮሜ 13:11
2. በሚስጥር ወይም በፍርድ ኮሚቴ መያዝ ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ምንድን ነው?
2 ይሖዋ ለጠፉት የእስራኤል በጎች አሳቢነት አሳይቷል። (ሕዝቅኤል 34:15, 16ን አንብብ።) በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከመንጋው ወጥቶ የባዘነን በግ መሰል ሰው የመርዳት ፍላጎት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ሽማግሌዎች እርዳታ የሚፈልግን በመንፈሳዊ የቀዘቀዘ ሰው እንዲያስጠና አንድ አስፋፊ ቢመድቡና አስጠኚው ግለሰቡ ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ቢያውቅ ምን መደረግ ይኖርበታል? አስፋፊው በፍርድ ኮሚቴ መታየት ወይም በሚስጥር መያዝ ያለበትን ጉዳይ በተመለከተ ምክር ከመስጠት ይልቅ ግለሰቡ ራሱ ሽማግሌዎችን እንዲያናግር ሐሳብ ሊያቀርብለት ይገባል። ሆኖም ግለሰቡ እንዲህ ሳያደርግ ከቀረ አስፋፊው ለሽማግሌዎች ጉዳዩን ማሳወቅ ይኖርበታል።—ዘሌ. 5:1 የ1954 ትርጉም፤ ገላ. 6:1
3. መቶ በጎች የነበሩት ሰው የጠፋበትን በግ ባገኘ ጊዜ ምን ተሰማው?
3 በፊተኛው የጥናት ርዕስ ላይ ኢየሱስ 100 በጎች ስለነበሩት ሰው የተናገረው ምሳሌ ተጠቅሶ ነበር። እረኛው ከመንጋው ውስጥ አንዱ በጠፋ ጊዜ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ የጠፋውን በግ ለመፈለግ ሄዷል። የጠፋውን በግ ባገኘ ጊዜም በጣም ተደሰተ! (ሉቃስ 15:4-7) እኛም በተመሳሳይ ከመንጋው ጠፍቶ የነበረ አንድ የአምላክ በግ ወደ መንጋው ሲመለስ በጣም እንደሰታለን። ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላት በፍቅር ተነሳስተው በመንፈሳዊ የቀዘቀዘውን ሰው ሄደው ጠይቀውት ሊሆን ይችላል። እነሱም ግለሰቡ ወደ መንጋው ተመልሶ የአምላክን ድጋፍ፣ ጥበቃና በረከት ሲያገኝ ማየት ይፈልጋሉ። (ዘዳ. 33:27፤ መዝ. 91:14፤ ምሳሌ 10:22) በዚህ ረገድ እርዳታ የመስጠት አጋጣሚ ካገኙ ምን ማድረግ ይችላሉ?
4. ከገላትያ 6:2, 5 ምን መገንዘብ እንችላለን?
4 ይሖዋ በጎቹን እንደሚወድና ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንደማይጠብቅብን በደግነት በማስገንዘብ ወደ ጉባኤ እንዲመለስ ሊያበረታቱት ይችላሉ። ይሖዋ ከሚጠብቅብን ነገሮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ይገኙበታል። ገላትያ 6:2, 5ን ማንበብና ክርስቲያኖች አንዳቸው የሌላውን ከባድ ሸክም በመጋራት መረዳዳት የሚችሉ ቢሆንም መንፈሳዊ ኃላፊነትን በተመለከተ ግን “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም” እንደሚገባው መጥቀስ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ሌላ ሰው በእኛ ምትክ ለአምላክ ታማኝ እንዲሆንልን ማድረግ አይቻልም።
‘በኑሮ ጭንቀት’ ተውጠው ነው?
5, 6. (ሀ) በመንፈሳዊ የቀዘቀዙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ሲናገሩ በጥሞና ማዳመጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ከአምላክ ሕዝብ መራቃቸው እንደጎዳቸው እንዲገነዘቡ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
5 ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የጎለመሱ አስፋፊዎች የቀዘቀዙ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዴት ሊረዷቸው እንደሚችሉ ለማወቅ እነዚህ ግለሰቦች የልባቸውን አውጥተው ሲናገሩ በጥሞና ሊያዳምጧቸው ይገባል። ‘በኑሮ ጭንቀት’ በመዋጣቸው ምክንያት ከጉባኤ የቀሩ ባልና ሚስትን እየጠየቅህ ያለህ ሽማግሌ ነህ እንበል። (ሉቃስ 21:34) ባልና ሚስቱን በመንፈሳዊ እንዲቀዘቅዙ ያደረጓቸው ነገሮች ገንዘብ ነክ ችግሮች ወይም ተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ትንሽ ፋታ ማግኘት ያስፈልገናል የሚል ስሜት አድሮባቸው ይሆናል፤ ሆኖም ራሳቸውን ማራቃቸው መፍትሔ እንደማይሆን ልትጠቁማቸው ትችላለህ። (ምሳሌ 18:1ን አንብብ።) በዘዴ እንዲህ ብለህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ፦ “ከስብሰባ ከቀራችሁ ወዲህ ይበልጥ ደስተኛ ሆናችኋል? የቤተሰብ ሕይወታችሁ ተሻሽሏል? በይሖዋ መታመን የሚያስገኘው ደስታ አሁንም አላችሁ?”—ነህ. 8:10
6 የቀዘቀዙት ሰዎች በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላቸው፣ ከጉባኤ መራቃቸው መንፈሳዊነታቸውና ደስታቸው እንዲቀንስ ማድረጉን እንዲያስተውሉ ሊረዳቸው ይችላል። (ማቴ. 5:3፤ ዕብ. 10:24, 25) ምሥራቹን መስበክ ማቆማቸው ደስታ እንዲያጡ እንዳደረጋቸው እንዲገነዘቡ መርዳት ይቻል ይሆናል። (ማቴ. 28:19, 20) ታዲያ ምን ቢያደርጉ ይሻላቸዋል?
7. ከመንጋው ወጥተው የባዘኑ ክርስቲያኖች ምን እንዲያደርጉ ማበረታታት እንችላለን?
7 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ ‘በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ፤ ከሚመጣውም ሁሉ እንድታመልጡ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።’ (ሉቃስ 21:34-36) ከመንጋው ወጥተው የባዘኑ ቢሆኑም ድሮ የነበራቸውን ደስታ መልሰው ማግኘት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስና መለኮታዊ አመራር ለማግኘት እንዲጸልዩ እንዲሁም ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታት ይቻላል።—ሉቃስ 11:13
ከመንጋው የራቁት ተደናቅፈው ነው?
8, 9. አንድ ሽማግሌ፣ ተደናቅፎ የቀዘቀዘ ሰው ቆም ብሎ እንዲያስብ ለማድረግ ምን ነገሮችን ሊጠቅስለት ይችላል?
8 ሰዎች ፍጽምና ስለሚጎድላቸው አለመግባባት መፈጠሩ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ አንድን ሰው ሊያደናቅፈው ይችላል። በጉባኤ ውስጥ በአክብሮት የሚታይ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚቃረን ድርጊት በመፈጸሙ የተነሳ አንዳንዶች ተሰናክለዋል። በመንፈሳዊ የቀዘቀዘ አንድ ግለሰብ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተጎዳ ከሆነ ሊጠይቀው የሄደው ሽማግሌ ይሖዋ ማንንም እንደማያሰናክል ሊገልጽለት ይችላል። ታዲያ ማንም ሰው ቢሆን ከአምላክና ከሕዝቡ ጋር ያለው ዝምድና እንዲቋረጥበት ለምን ይፈቅዳል? ከዚህ ይልቅ “የምድር ሁሉ ዳኛ” የተከሰተውን ነገር እንደሚያውቅና ሁኔታውን በትክክለኛው መንገድ እንደሚይዝ እርግጠኛ በመሆን አምላክን ማገልገሉን መቀጠል አይኖርበትም? (ዘፍ. 18:25፤ ቈላ. 3:23-25) አንድ ሰው ቃል በቃል ተደናቅፎ ቢወድቅ ለመነሳት ምንም ጥረት ሳያደርግ እዚያው በወደቀበት አይቀርም።
9 አንድ ሽማግሌ ግለሰቡን በመንፈሳዊ ለመርዳት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት አንዳንዶች ቀደም ሲል እንዲሰናከሉ ምክንያት የሆናቸው ነገር ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ያን ያህል ክብደት የሌለው ሆኖ እንዳገኙት ሊገልጽለት ይችላል። እንዲያውም ያሰናከላቸው ነገር ተወግዶ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው በተሰጠው ተግሣጽ ምክንያት ተሰናክሎ ከሆነ በጉዳዩ ላይ በጸሎት ማሰላሰሉ እሱ ራሱ በተወሰነ መጠን ጥፋተኛ እንደሆነና በተሰጠው ተግሣጽ መሰናከል እንዳልነበረበት እንዲያስተውል ሊረዳው ይችላል።—መዝ. 119:165፤ ዕብ. 12:5-13
አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት መቀበል ተቸግረው ነው?
10, 11. ለአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የተለየ ግንዛቤ ያለውን ሰው ለመርዳት በምንጥርበት ጊዜ ምን ዓይነት አሳማኝ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል?
10 አንዳንዶች ከአምላክ መንጋ የራቁት አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን መቀበል ስለከበዳቸው ሊሆን ይችላል። ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡት እስራኤላውያን አምላክ ለእነሱ ሲል ‘ያደረገውን ረሱ’፤ “በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም።” (መዝ. 106:13) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያቀርብ ለቀዘቀዘው ሰው ማስታወሱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም) ግለሰቡም በመጀመሪያ እውነትን የተማረው ይህ ባሪያ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ነበር። ታዲያ እንደገና በእውነት መመላለሱን ለመቀጠል ለምን ቁርጥ ውሳኔ አያደርግም?—2 ዮሐ. 4
11 ሽማግሌው ከአምላክ መንጋ ወጥተው የባዘኑትን ለመርዳት በሚጥርበት ጊዜ ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱን ለመቀበል በመቸገራቸው ትተውት ስለሄዱት ደቀ መዛሙርት ሊጠቅስ ይችላል። (ዮሐ. 6:53, 66) ከክርስቶስና ከታማኝ ተከታዮቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጣቸው መንፈሳዊነታቸውንም ሆነ ደስታቸውን አጥተዋል። ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ሰዎች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብበት ሌላ ቦታ አግኝተዋል? ምንም ሌላ ቦታ ስለሌለ ሊያገኙ አይችሉም!
ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ሊሆን ይችላል?
12, 13. ከመንጋው ወጥቶ የባዘነ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ከተናገረ እንዴት ሊረዳ ይችላል?
12 አንዳንድ ግለሰቦች ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት መስበካቸውንና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ያቆማሉ። የፈጸሙትን ኃጢአት ለሽማግሌዎች ቢናገሩ እንደሚወገዱ ያስቡ ይሆናል። ሆኖም ይፈጽሙት የነበረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ድርጊት ከተዉና ልባዊ ንስሐ ከገቡ ከጉባኤ አይወገዱም። (2 ቆሮ. 7:10, 11) ከዚህ ይልቅ ጉባኤው የሚቀበላቸው ከመሆኑም ሌላ ሽማግሌዎች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ እርዳታ ይሰጧቸዋል።
13 አንድን የቀዘቀዘ ሰው እንድትረዳ የተመደብክ የጎለመስክ አስፋፊ ብትሆንና ግለሰቡ ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ቢነግርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይህን ጉዳይ በተመለከተ በራስህ አንዳንድ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ ግለሰቡ ሽማግሌዎችን ቀርቦ እንዲያነጋግር ሐሳብ አቅርብለት። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ከቀረ እንዲህ ዓይነት ዘሌዋውያን 5:1ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ሽማግሌዎች ወደ ጉባኤው ለመመለስና ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እንዴት መርዳት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ፍቅራዊ ተግሣጽ መስጠት ያስፈልግ ይሆናል። (ዕብ. 12:7-11) ግለሰቡ አምላክን መበደሉን ካመነ፣ ይፈጽመው የነበረውን መጥፎ ድርጊት ካቆመና ልባዊ ንስሐ ከገባ ሽማግሌዎቹ የሚረዱት ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ምሕረት ሊያገኝ ይችላል።—ኢሳ. 1:18፤ 55:7፤ ያዕ. 5:13-16
ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጠውን መለኮታዊ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ለይሖዋ ስምና ለጉባኤው መንፈሳዊ ደህንነት ያለህን አሳቢነት ማሳየት ይኖርብሃል። (የልጁ መመለስ ለደስታ ምክንያት ሆነ
14. ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረውን ምሳሌ በራስህ አባባል ግለጽ።
14 ከመንጋው ወጥቶ የባዘነን በግ ለመርዳት ጥረት በሚደረግበት ጊዜ ግለሰቡን እንዲረዳ የተመደበው አስፋፊ በሉቃስ 15:11-24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ምሳሌ ሊጠቅስ ይችላል። በዚህ ምሳሌ ላይ አንድ ወጣት በውርስ ያገኘውን ሀብት ልቅ በሆነ ሕይወት እንዳባከነ ተገልጿል። ከጊዜ በኋላ፣ ይከተለው የነበረው ርካሽ ሕይወት አንገሸገሸው። በረሃብ ተሠቃየ፣ ቤተሰቦቹ ናፈቁት፤ በመጨረሻም ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ! ገና ከሩቅ ሳለ አባቱ አየውና ወደ እሱ ሮጦ በመሄድ አንገቱን አቅፎ ሳመው፤ ልጁን በማግኘቱም ተደሰተ። ቀስ በቀስ ከመንጋው ርቆ የሄደው ሰው በዚህ ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ ወደ መንጋው እንዲመለስ ሊያነሳሳው ይችላል። ይህ ሥርዓት በቅርቡ ስለሚጠፋ ምንም ሳይዘገይ ‘ወደ ቤቱ መመለስ’ ይኖርበታል።
15. አንዳንዶች ቀስ በቀስ ከጉባኤ እየራቁ የሚሄዱት ለምንድን ነው?
15 ከጉባኤ የሚርቁ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ልክ እንደ አባካኙ ልጅ ናቸው ማለት አይደለም። ወደብ ዳር ያለች አንዲት ጀልባ ከወደቡ ቀስ በቀስ እየራቀች እንደምትሄድ ሁሉ አንዳንዶችም ከጉባኤ የሚርቁት ቀስ በቀስ ነው። ሌሎች ደግሞ በኑሮ ጭንቀቶች ሲዋጡ መንፈሳዊ እይታቸው ይጠፋል። በሌላ በኩል በአንድ የጉባኤ አባል ተደናቅፈው ወይም አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት መቀበል ከብዷቸው ከጉባኤ የሚርቁም አሉ። ጥቂቶች ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ድርጊት ይፈጽማሉ። ያም ሆነ ይህ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የቀረቡት ነጥቦች በእነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከመንጋው የወጡት ሁሉ ጊዜው ሳያልፍባቸው እንዲመለሱ ለመርዳት ሊያግዟችሁ ይችላሉ።
“ልጄ፣ ወደ ቤትህ እንኳን ደህና መጣህ!”
16-18. (ሀ) አንድ ሽማግሌ ለዓመታት ቀዝቅዞ የነበረን ወንድም የረዳው እንዴት ነው? (ለ) ይህ ወንድም እንዲቀዘቅዝ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ምን እርዳታስ ተደረገለት? ጉባኤውስ እንዴት ተቀበለው?
16 አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የጉባኤያችን የሽማግሌዎች አካል የቀዘቀዙትን ለመርዳት ልዩ ትኩረት ይሰጣል። አንድ ያስጠናሁትና እውነትን እንዲያውቅ የረዳሁት ወንድም ትዝ ይለኛል። ይህ ወንድም ለ25 ዓመት ገደማ ቀዝቅዞ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ
ማዋል እንዴት ሊረዳው እንደሚችል ገለጽኩለት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ መንግሥት አዳራሽ መምጣት ጀመረ፤ እንዲሁም ወደ መንጋው ለመመለስ ያደረገውን ውሳኔ ለማጠናከር እንዲረዳው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ።”17 ይህ ወንድም የቀዘቀዘው ለምን ነበር? እንዲህ ሲል ሐቁን ተናግሯል፦ “ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለዓለማዊ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት መስጠት ጀምሬ ነበር። ከዚያም ማጥናቴን፣ ማገልገሌንና በጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘቴን አቆምኩ። ምንም ሳይታወቀኝ ከጉባኤው ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። ሆኖም ይህ ሽማግሌ ለእኔ በግል ትኩረት መስጠቱና ልባዊ አሳቢነት ማሳየቱ እንድመለስ ረዳኝ።” ይህ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ከተስማማ በኋላ የነበሩበት ችግሮች እየተቃለሉ ሄዱ። “በሕይወቴ ውስጥ የይሖዋንም ሆነ የድርጅቱን ፍቅርና አመራር አጥቼ እንደነበር ተገነዘብኩ” ሲል ተናግሯል።
18 ይህ ወንድም ወደ ጉባኤ ሲመለስ ወንድሞችና እህቶች እንዴት ተቀበሉት? እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌው ላይ እንደጠቀሰው አባካኝ ልጅ እንደሆንኩ ተሰማኝ። እንዲያውም ከ30 ዓመታት በፊት በጉባኤው የነበሩና አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ አንዲት አረጋዊት እህት ‘ልጄ፣ ወደ ቤትህ እንኳን ደህና መጣህ!’ አሉኝ። ይህን ስሰማ ልቤ በጣም ተነካ። በእርግጥም ወደ ቤቴ እንደተመለስኩ ተሰማኝ። ሽማግሌው ወንድምም ሆነ መላው ጉባኤ ላሳዩኝ ፍቅር፣ አሳቢነት፣ ትዕግሥትና ትኩረት ከልብ የመነጨ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ። ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ወደ መንጋው እንድመለስ በእርግጥ ረድቶኛል።”
ዛሬውኑ እርምጃ እንዲወስዱ አበረታቷቸው!
19, 20. የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ መንጋው እንዲመለሱ ማበረታታትና አምላክ ከአቅማችን በላይ እንደማይጠብቅብን ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
19 የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ሲሆን የዚህ ሥርዓት ፍጻሜም በጣም ቀርቧል። ስለዚህ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ወደ ስብሰባ እንዲመጡ አበረታቷቸው። ዛሬ ነገ ሳይሉ መሰብሰብ እንዲጀምሩ አሳስቧቸው። ሰይጣን ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማበላሸት ጥረት እያደረገና እውነተኛውን አምልኮ በመተው ከኑሮ ውጥረት እፎይታ እንደሚያገኙ ሊያሳምናቸው እየሞከረ መሆኑን አስታውሷቸው። እውነተኛ እረፍት ማግኘት የሚችሉት የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች በመሆን ብቻ እንደሆነ ልታረጋግጡላቸው ትችላላችሁ።—ማቴዎስ 11:28-30ን አንብብ።
20 አምላክ እንድናደርግ የሚጠብቅብን የምንችለውን ነገር እንደሆነ ለቀዘቀዙት ክርስቲያኖች አስገንዝቧቸው። የአልዓዛር እህት ማርያም ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ውድ የሆነ ሽቶ አምጥታ ራሱ ላይ በማፍሰሷ ትችት በተሰነዘረባት ጊዜ ኢየሱስ “ተዉአት፣ . . . እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች” አለ። (ማር. 14:6-8) ኢየሱስ ለቤተ መቅደሱ በጣም አነስተኛ መዋጮ ያደረገችውን ችግረኛ መበለት አመስግኗታል። እሷም ብትሆን ያደረገችው የምትችለውን ነበር። (ሉቃስ 21:1-4) አብዛኞቻችን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ መካፈል እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ቀዝቅዘው ከሚገኙት ውስጥ አብዛኞቹ በይሖዋ እርዳታ እነዚህኑ ነገሮች ማድረግ ይችላሉ።
21, 22. ወደ ይሖዋ የሚመለሱትን ምን ነገር ልታረጋግጡላቸው ትችላላችሁ?
21 ከመንጋው ወጥቶ የባዘነ አንድ በግ መሰል ሰው ተመልሶ ሲመጣ የወንድሞቹን ፊት ማየት ከከበደው አባካኙ ልጅ ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ የተፈጠረውን ደስታ ልታስታውሱት ትችላላችሁ። የቀዘቀዙ ሰዎች ወደ ጉባኤ በሚመለሱበት ጊዜም ተመሳሳይ ደስታ ይኖራል። ዲያብሎስን ለመቃወምና ወደ አምላክ ለመቅረብ ዛሬውኑ እርምጃ እንዲወስዱ አበረታቷቸው።—ያዕ. 4:7, 8
22 ወደ ይሖዋ የሚመለሱትን ሁሉ በደስታ እንቀበላቸዋለን። (ሰቆ. 3:40) ይሖዋን ሲያገለግሉ በነበሩበት ጊዜ ያገኟቸው ተሞክሮዎች ከፍተኛ ደስታ እንዳመጡላቸው ጥርጥር የለውም። ሳይዘገዩ ወደ መንጋው የሚመለሱ ሁሉ በቃላት ሊገለጽ የማይችል በረከት ይጠብቃቸዋል!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ተደናቅፎ የቀዘቀዘን አንድ ክርስቲያን እንዴት መርዳት ትችላላችሁ?
• ስለ አንድ ትምህርት የተለየ አመለካከት በመያዙ ምክንያት ከአምላክ መንጋ የራቀን ሰው የትኞቹን አሳማኝ ነጥቦች ማንሳት ሊረዳው ይችላል?
• ወደ ጉባኤ ለመመለስ የሚያቅማማን ሰው መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ የቀዘቀዘ የእምነት ባልንጀራችሁ የልቡን አውጥቶ ሲናገር በጥሞና አዳምጡት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላቸው ወደ መንጋው ለመመለስ እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል