ታማኝነት በማሳየት ኢታይን ምሰሉ
ታማኝነት በማሳየት ኢታይን ምሰሉ
“ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ሥራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው። የዘላለም ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው። ይሖዋ ሆይ፣ አንተን በእርግጥ የማይፈራና ስምህን ከፍ ከፍ የማያደርግ ማን ነው? ምክንያቱም አንተ ብቻ ታማኝ ነህ!” ይህን መዝሙር የዘመሩት በሰማይ ያሉት ‘አውሬውንና ምስሉን ድል የነሱት’ የአምላክ አገልጋዮች ሲሆኑ በመዝሙሩ ላይ የአምላክን ታማኝነት ጎላ አድርገው ገልጸዋል። (ራእይ 15:2-4) ይህን ግሩም ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ ይሖዋ አገልጋዮቹ እሱን እንዲመስሉት ይፈልጋል።—ኤፌ. 4:24
በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን ዲያብሎስ በምድር ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች ከአምላካቸው ፍቅር ለመለየት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ያም ሆኖ ብዙዎች በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያሉም እንኳ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። ይሖዋ እንዲህ ላለው ታማኝነት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥ ማወቃችን በጣም አመስጋኞች እንድንሆን ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይሖዋ ፍትሕን እንደሚወድና ታማኞቹንም እንደማይጥል’ ዋስትና ይሰጠናል። (መዝ. 37:28) ይሖዋ፣ ታማኝነታችንን ጠብቀን መኖር እንድንችል እኛን ለመርዳት በቃሉ ውስጥ የበርካታ ታማኝ ሰዎች ታሪክ እንዲጻፍ አድርጓል። ከእነዚህ ታሪኮች መካከል የጌት ሰው ስለሆነው ስለ ኢታይ የሚናገረው ታሪክ ይገኝበታል።
‘ከአገሩ ተሰዶ የመጣ እንግዳ’
ኢታይ ታዋቂ ከሆነችውና ጌት ከተባለችው የፍልስጥኤማውያን ከተማ የመጣ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ጌት፣ ግዙፍ የነበረው የጎልያድና የሌሎች የእስራኤል ጠላቶች የትውልድ ከተማ ነች። ጀግና ተዋጊ ስለነበረው ስለ ኢታይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው አቤሴሎም በንጉሥ ዳዊት ላይ ስለማመጹ በሚናገረው ዘገባ ላይ ነው። በዚያን ወቅት ኢታይና እሱን ይከተሉ የነበሩት 600 ፍልስጥኤማውያን ከአገራቸው ተሰደው በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይኖሩ ነበር።
ዳዊት፣ የኢታይንና የተከታዮቹን ሁኔታ ሲመለከት እሱ ራሱ ከ600 እስራኤላውያን ጦረኞች ጋር ሆኖ በፍልስጥኤማውያን ምድር፣ የጌት ንጉሥ በሆነው በአንኩስ ዘንድ ያሳለፈውን የስደት ኑሮ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 27:2, 3) ኢታይና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች፣ የዳዊት ልጅ አቤሴሎም በአባቱ ላይ ማመጹን ሲመለከቱ ምን ያደርጉ ይሆን? ለአቤሴሎም ይወግናሉ? ወይስ በጉዳዩ ጣልቃ ላለመግባት ይመርጣሉ? ወይስ ከዳዊትና ከሰዎቹ ጋር ለመሆን ይወስናሉ?
ዳዊት ከኢየሩሳሌም ከሸሸ በኋላ “ቤትሜርሐቅም” የተባለው ቦታ ላይ ቆሞ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የዚህ ቦታ ስም ‘ሩቅ ያለው ቤት’ የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቤት አንድ ሰው፣ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ በሚወስደው አቅጣጫ ሲሄድ የቄድሮን ሸለቆን ከመሻገሩ በፊት በኢየሩሳሌም የሚያገኘው የመጨረሻው ቤት ሳይሆን አይቀርም። (2 ሳሙ. 15:17 የ1954 ትርጉም) ዳዊት እዚህ ቦታ ሆኖ ምን ያህል ሰዎች ተከትለውት እንደመጡ እየተመለከተ ነው። አብረውት የመጡት ታማኝ እስራኤላውያን ብቻ አይደሉም። ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ኢታይና እሱን ተከትለው የመጡት 600 ጌታውያን ጭምር ነበሩ።—2 ሳሙ. 15:18
ዳዊት ለኢታይ ከልቡ በማሰብ እንዲህ አለው፦ “ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ [‘ተሰደህ፣’ የ1954 ትርጉም] የመጣህ እንግዳ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ [የይሖዋ] በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋር ይሁን!”—2 ሳሙ. 15:19, 20
ኢታይ ለዳዊት ታማኝ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉን እንዲህ በማለት ገለጸ፦ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል!” (2 ሳሙ. 15:21) በዚህ ወቅት ዳዊት፣ ቅድመ አያቱ የሆነችው ሩት የተናገረችውን ተመሳሳይ ነገር ሳያስታውስ አልቀረም። (ሩት 1:16, 17) ዳዊት ኢታይ በሰጠው መልስ ልቡ ስለተነካ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” በማለት የቄድሮን ሸለቆን እንዲሻገር ነገረው። በዚህ ጊዜ “ጌታዊው ኢታይ ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ።”—2 ሳሙ. 15:22
“ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል”
ሮም 15:4 “ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል” ይላል። በመሆኑም ከኢታይ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ኢታይ ለዳዊት ታማኝ እንዲሆን ያነሳሳው ምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት። ኢታይ ከፍልስጥኤም ምድር ተሰዶ የሚኖር እንግዳ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑንና ዳዊትም በይሖዋ የተቀባ ንጉሥ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንዲሁም በእስራኤላውያንና በፍልስጥኤማውያን መካከል የነበረው ጠላትነት በአመለካከቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግበት አልፈቀደም። ኢታይ ስለ ዳዊት ሲያስብ ወደ አእምሮው የሚመጣው ፍልስጥኤማዊውን ጀግና ጎልያድን ጨምሮ በርካታ የአገሩን ሰዎች የገደለ ሰው መሆኑ ብቻ አይደለም። (1 ሳሙ. 18:6, 7) ኢታይ፣ ዳዊት ይሖዋን የሚወድና መልካም ባሕርያት ያሉት ሰው መሆኑን እንደተመለከተ ጥርጥር የለውም። ይህ አጋጣሚ ዳዊትም በምላሹ ኢታይን እንዲያከብረው አድርጎታል። ከዚህም በላይ ዳዊት፣ ከአቤሴሎም ሠራዊት ጋር ባደረገው ወሳኝ ውጊያ ላይ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የጦር ሠራዊቱን “በኢታይ አዛዥነት ሥር” እንዲሆን አድርጓል!—2 ሳሙ. 18:2
እኛም የባሕል፣ የዘር ወይም የጎሳ ልዩነት እንዲሁም በውስጣችን የቀረ ጭፍን ጥላቻ ተጽዕኖ ሳያሳድርብን የሌሎችን መልካም ባሕርይ ለመመልከት ጥረት ማድረግ አለብን። ይሖዋን ማወቃችንና እሱን መውደዳችን፣ አንዳንድ ልዩነቶች ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት መሰናክል እንዳይሆኑብን ሊረዳን እንደሚችል በዳዊትና በኢታይ መካከል ከነበረው ወዳጅነት በግልጽ ማየት ይቻላል።
በኢታይ ታሪክ ላይ ስናሰላስል ራሳችንን እንዲህ ብለን ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ‘በአስቸጋሪ ጊዜያት ታማኝ መሆኔን ለማሳየት ምን ያህል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’
ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ለታላቁ ዳዊት ለኢየሱስ ክርስቶስ ኢታይ ያሳየውን ዓይነት ታማኝነት አሳያለሁ? የአምላክን መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ታማኝነቴን አሳያለሁ?’ (የቤተሰብ ራሶችም ስለ ኢታይ ታማኝነት በሚናገረው ታሪክ ላይ በማሰላሰል ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ኢታይ ለዳዊት ታማኝ መሆኑና አምላክ ከቀባው ንጉሥ ጋር ለመሄድ መወሰኑ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች የሚነካ ጉዳይ ነበር። በተመሳሳይም የቤተሰብ ራሶች እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ሲሉ የሚያደርጉት ውሳኔ ቤተሰባቸውን ሊነካ አልፎ ተርፎም ለጊዜውም ቢሆን እንኳ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ‘[ይሖዋ] ከታማኙ ጋር ታማኝ እንደሚሆን’ ዋስትና ይሰጠናል።—መዝ. 18:25
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳዊት ከአቤሴሎም ጋር ስላደረገው ውጊያ ከተረከ በኋላ ስለ ኢታይ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ስለዚህ ሰው የሚናገረው አጭር ዘገባ፣ ዳዊት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ወቅት ኢታይ ያሳየውን ባሕርይ በተመለከተ ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ያስችለናል። የኢታይ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተቱ፣ ይሖዋ ይህን የመሰለ ታማኝነት የሚያሳዩ ሰዎችን እንደሚመለከታቸውና እንደሚክሳቸው ያረጋግጣል።—ዕብ. 6:10