በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲመጣ የት መገኘት ይኖርብሃል?

የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲመጣ የት መገኘት ይኖርብሃል?

የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲመጣ የት መገኘት ይኖርብሃል?

ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት በአርማጌዶን ሲያጠፋው ቅኖች ምን ይሆናሉ? ምሳሌ 2:21, 22 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”

ይሁን እንጂ ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች በምድር ላይ የሚቀሩት እንዴት ነው? ከጥፋቱ መዳን የሚችሉበት ቦታ ይዘጋጅላቸዋል? የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲመጣ ቅኖች የት መገኘት ይኖርባቸዋል? ከጥፋት ስለዳኑ የአምላክ አገልጋዮች የሚናገሩ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በዚህ ረገድ ተጨማሪ ግንዛቤ እንድናገኝ ይረዱናል።

ለመዳን ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አስፈልጓቸዋል

በጥንት ዘመን የኖሩት ኖኅና ሎጥ ከጥፋት የዳኑበትን መንገድ በተመለከተ 2 ጴጥሮስ 2:5-7 እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም። በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆን የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል። ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በሚፈጽሙት ልቅ የሆነ ብልግና እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።”

ኖኅ ከጥፋት ውኃ የዳነው እንዴት ነበር? አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በእርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። አንተ ግን በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ።” (ዘፍ. 6:13, 14) ኖኅ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት መርከብ ሠራ። የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ ከሰባት ቀናት በፊት ይሖዋ እንስሳቱንና መላውን ቤተሰቡን ይዞ ወደ መርከብ እንዲገባ አዘዘው። በሰባተኛው ቀን በሩ ተዘጋ፤ ከዚያም “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ።” (ዘፍ. 7:1-4, 11, 12, 16) ኖኅና ቤተሰቡም ‘ከውኃው ዳኑ።’ (1 ጴጥ. 3:20) በእርግጥም መዳናቸው የተመካው መርከቧ ውስጥ በመገኘታቸው ነበር። ከመርከቡ ውጪ በየትኛውም ቦታ ቢሆኑ ከጥፋቱ መዳን አይችሉም ነበር።—ዘፍ. 7:19, 20

ለሎጥ የተሰጠውን መመሪያ ከተመለከትን ደግሞ ለኖኅ ከተሰጠው ትእዛዝ ትንሽ የተለየ ነበር። ሁለት መላእክት ለሎጥ የት መገኘት እንደሌለበት ነገሩት። መላእክቱ “በከተማዋ [በሰዶም] ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች . . . ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤ ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው” አሉት። ሎጥና ቤተሰቡ ‘ወደ ተራራ መሸሽ’ ነበረባቸው።—ዘፍ. 19:12, 13, 17

የኖኅና የሎጥ ታሪክ “ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና ዓመፀኛ ሰዎችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ” የሚያውቅ መሆኑን ያረጋግጣል። (2 ጴጥ. 2:9) የኖኅም ሆነ የሎጥ መዳን የተመካው በተነገራቸው ቦታ ላይ በመገኘታቸው ነበር። ኖኅ ወደ መርከቡ መግባት ነበረበት፤ ሎጥ ደግሞ ከሰዶም መውጣት ይጠበቅበት ነበር። ይሁንና ለመዳን፣ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ የግድ ያስፈልጋል ማለት ነው? ይሖዋ፣ ጻድቃን ባሉበት ቦታ ሆነው ወይም ሌላ ቦታ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ሊያድናቸው ይችላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከጥፋት ስለዳኑ ሰዎች የሚናገሩ ሌሎች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እንመልከት።

ለመዳን ወደ ሌላ ቦታ መሄድ የግድ ያስፈልጋል?

ይሖዋ በሙሴ ዘመን፣ በግብፃውያን ላይ አሥረኛውን መቅሰፍት ከማምጣቱ በፊት እስራኤላውያንን ለፋሲካ በዓል ያረዱትን እንስሳ ደም በበራቸው ጉበንና መቃን ላይ እንዲቀቡ አዟቸው ነበር። ይህ ትእዛዝ የተሰጣቸው ለምን ነበር? ‘ይሖዋ ግብፃውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጉበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያንን ደጃፍ አልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታቸው ገብቶ እንዳይገድላቸው ይከለክለዋል።’ በዚያኑ ሌሊት ይሖዋ፣ “በግብፅ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው።” የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ግን የትም ቦታ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ከመቅሰፍቱ ድነዋል።—ዘፀ. 12:22, 23, 29

በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ጋለሞታይቱ ረዓብ የገጠማትን ሁኔታም እንመልከት። ጊዜው እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የጀመሩበት ወቅት ነበር። ረዓብ ኢያሪኮ ልትጠፋ መሆኑን ስታውቅ ለሁለቱ እስራኤላውያን ሰላዮች፣ የከተማይቱ ነዋሪዎች እየገሰገሰ የሚመጣውን የእስራኤል ሠራዊት በመፍራት እንደተሸበሩ ነገረቻቸው። ሰላዮቹን የደበቀቻቸው ከመሆኑም ሌላ ኢያሪኮ ድል በምትደረግበት ጊዜ እሷንና መላውን ቤተሰቧን ከጥፋቱ እንዲያድኗቸው ቃል እንዲገቡላት ጠየቀቻቸው። ሰላዮቹም ቤተሰቧን ይዛ ከከተማዋ ቅጥር ጋር ተያይዞ በተሠራው ቤቷ ውስጥ እንድትቀመጥ አዘዟት። በዚህ ወቅት ከቤቱ መውጣት ከከተማዋ ጋር አንድ ላይ መጥፋት ማለት ነበር። (ኢያሱ 2:8-13, 15, 18, 19) ይሁንና በኋላ ላይ ይሖዋ ‘የከተማዪቱ ቅጥር እንደሚፈርስ’ ለኢያሱ ነገረው። (ኢያሱ 6:5) ሰላዮቹ ከጥፋቱ ለመዳን ያስችላል ብለው ያሰቡት ቦታ አስጊ ሁኔታ ላይ ወደቀ። ታዲያ ረዓብና ቤተሰቧ እንዴት ይድኑ ይሆን?

ኢያሪኮ ድል የምትደረግበት ጊዜ ሲደርስ እስራኤላውያን ድምፃቸውን ከፍ አድረገው የጮኹ ከመሆኑም ሌላ መለከቶቹን ነፉ። ኢያሱ 6:20 የተከሰተውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ [የእስራኤል ሕዝብ] በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ።” የኢያሪኮን ቅጥር እንዳይፈርስ ሊያደርግ የሚችል ማንም ሰው አልነበረም። ይሁንና የከተማይቱ ቅጥር ሙሉ በሙሉ ሲፈርስ የረዓብ ቤት ብቻ በተአምር ሳይፈርስ ቀረ። ከዚያም ኢያሱ ሁለቱን ሰላዮች “ወደ ጋለሞታዪቱ ቤት ሂዱ፤ በማላችሁላትም መሠረት እርስዋንና የእርሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” በማለት አዘዛቸው። (ኢያሱ 6:22) በዚህ መንገድ በረዓብ ቤት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ዳኑ።

ለመዳናቸው በጣም አስፈላጊ የነበረው ነገር ምንድን ነው?

ኖኅ፣ ሎጥ፣ በሙሴ ጊዜ የነበሩት እስራኤላውያንና ረዓብ ከጥፋት ስለዳኑበት መንገድ ከሚናገረው ታሪክ ምን እንማራለን? እነዚህ ታሪኮች ይህ ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ የት መገኘት እንዳለብን ለመወሰን የሚረዱንስ እንዴት ነው?

እውነት ነው፣ ኖኅ የዳነው መርከብ ውስጥ በመግባቱ ነበር። ይሁንና መርከቡ ውስጥ የገባው ለምንድን ነው? ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት ስላሳደረና ታዛዥ ሰው ስለነበረ አይደለም? መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” ይላል። (ዘፍ. 6:22፤ ዕብ. 11:7) እኛስ አምላክ ያዘዘንን ሁሉ እያደረግን ነው? በተጨማሪም ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) እኛስ በክልላችን የሚገኙ ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ ባይሰጡንም እንኳ እንደ ኖኅ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እንካፈላለን?

ሎጥ ከጥፋት ሊተርፍ የቻለው ከሰዶም ወጥቶ በመሸሹ ነበር። እንዲሁም በአምላክ ዘንድ ጻድቅ ሆኖ ስለተገኘና ለሕግ ተገዢ ባልነበሩት የሰዶምና የገሞራ ሰዎች የብልግና አኗኗር በእጅጉ ይሳቀቅ ስለነበር ነው። እኛስ፣ በዛሬው ጊዜ የሚታየው ልቅ የሆነ የብልግና አኗኗር ያስጨንቀናል? ወይስ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ማየት ከመልመዳችን የተነሳ ሕሊናችንን ምንም አይረብሸውም? በአምላክ ፊት ‘ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርብን በሰላም ለመገኘት’ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው?—2 ጴጥ. 3:14

በግብፅ የነበሩት እስራኤላውያንም ሆኑ በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ረዓብ፣ ከጥፋት መዳናቸው የተመካው ቤታቸው ውስጥ በመቆየታቸው ላይ ነበር። እንዲህ ለማድረግ ደግሞ በአምላክ ላይ እምነት ማሳደርና ታዛዥ መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። (ዕብ. 11:28, 30, 31) ከእያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት “ለቅሶና ዋይታ” ሲሰማ፣ እስራኤላውያን ቤተሰቦች የበኩር ልጃቸውን ትኩር ብለው ሲመለከቱ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ዘፀ. 12:30) የኢያሪኮ ቅጥር ሲፈርስ የሚሰማው ድምፅ እየቀረበ ሲመጣ ረዓብና ቤተሰቧ ከመፍራታቸው የተነሳ ሁሉም አንድ ጥግ ኩርምት ብለው ተቀምጠው ይታዩህ። ረዓብ በታዛዥነት ቤት ውስጥ ለመቆየት እውነተኛ እምነት አስፈልጓታል።

በቅርቡ የሰይጣን ክፉ ዓለም ይጠፋል። ይሖዋ አስፈሪ በሆነው ‘የቍጣው ቀን’ ሕዝቦቹን የሚያድነው እንዴት እንደሆነ እስካሁን የምናውቀው ነገር የለም። (ሶፎ. 2:3) ይሁን እንጂ ጥፋቱ በሚመጣበት ጊዜ የትም እንሁን የት ወይም በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንገኝ፣ መዳናችን የተመካው በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደራችንና እሱን በመታዘዛችን ላይ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን ኢሳይያስ በትንቢቱ ላይ “ቤት” በማለት ስለጠራው ነገር ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል።

“ወደ ቤትህ ግባ”

ኢሳይያስ 26:20 “ሕዝቤ ሆይ፤ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤ በርህን ከኋላህ ዝጋ፤ ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ፣ ለጥቂት ቀን ተሸሸግ” ይላል። ይህ ትንቢት መጀመሪያ የተፈጸመው ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ባቢሎንን ድል ባደረጉበት በ539 ዓ.ዓ. ሊሆን ይችላል። ፋርሳዊው ቂሮስ ባቢሎንን በተቆጣጠረበት ወቅት ወታደሮቹ ከቤት ውጭ ያገኙትን ማንኛውንም ሰው እንዲገድሉ ስለተነገራቸው ማንም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር።

በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሰው “ቤት” በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን ከ100,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ጉባኤዎች በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ‘በታላቁ መከራ’ ወቅትም ቢሆን ጉባኤዎች ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 7:14) የአምላክ ሕዝቦች ‘ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ ወደ ቤታቸው ገብተው እንዲሸሸጉ’ ታዘዋል። በመሆኑም ምንጊዜም ለጉባኤ ጥሩ አመለካከት መያዛችንና ከጉባኤው ጋር ተቀራርበን ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ልብ ልንለው ይገባል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።”—ዕብ. 10:24, 25

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በጥንት ጊዜ ሕዝቦቹን ካዳነበት መንገድ ምን እንማራለን?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቤት” የተባለው ነገር በዘመናችን ምንን ሊያመለክት ይችላል?