በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍቅር በማስተማር ኢየሱስን ምሰሉ

በፍቅር በማስተማር ኢየሱስን ምሰሉ

በፍቅር በማስተማር ኢየሱስን ምሰሉ

“ማንም እንደዚህ ሰው ተናግሮ አያውቅም።”—ዮሐ. 7:46

1. ኢየሱስ ሲያስተምር ያዳመጡት ሰዎች ስለ ትምህርት አሰጣጡ ምን ተሰምቷቸው ነበር?

ኢየሱስ ሲያስተምር ማዳመጥ ብትችል ምን ያህል እንደምትደነቅ አስበው! መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ሲያስተምር ያዳመጡት ሰዎች ምን እንደተሰማቸው ይነግረናል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ባደገባት ከተማ የነበሩት ሰዎች “ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላት [እንደተደነቁ]” የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ገልጿል። ኢየሱስ በተራራ ላይ የሰጠውን ንግግር ያዳመጡት ሰዎች “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [እንደተደነቁ]” ማቴዎስ ዘግቧል። ኢየሱስን እንዲይዙት የተላኩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች ለምን እንዳልያዙት ሲገልጹ “ማንም እንደዚህ ሰው ተናግሮ አያውቅም” እንዳሉ ዮሐንስ ጽፏል።—ሉቃስ 4:22፤ ማቴ. 7:28፤ ዮሐ. 7:46

2. ኢየሱስ የተጠቀመባቸው የማስተማር ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?

2 እነዚያ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አልተሳሳቱም። ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ግልጽ በሆነና ለመረዳት በማያስቸግር መንገድ ያስተማረ ሲሆን አሳማኝ ማስረጃ ያቀርብ ነበር። እንዲሁም ምሳሌዎችንና ጥያቄዎችን ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል። የሚያስተምራቸው ሰዎች ከፍተኛ ቦታ ያላቸውም ሆኑ ተራ ግለሰቦች ትምህርቱን ለሁሉም እንደሚስማማ አድርጎ ያቀርበው ነበር። የሚያስተምራቸው እውነቶች ለመረዳት ቀላል ቢሆኑም ትልቅ ትርጉም ነበራቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስን ታላቅ አስተማሪ እንዲሆን ያደረጉት እነዚህ ነገሮች ብቻ አልነበሩም።

ፍቅር—ቁልፍ ባሕርይ

3. ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚለየው እንዴት ነው?

3 ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን መካከል ከፍተኛ እውቀት የነበራቸውና ይህንን እውቀታቸውን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያላቸው ሰዎች እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ ከእነሱ የተለየ እንዲሆን ያደረገው ምን ነበር? በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ለተራው ሕዝብ ፍቅር አልነበራቸውም። ይልቁንም ሕዝቡን “የተረገመ” አድርገው በመመልከት ይንቁት ነበር። (ዮሐ. 7:49) ኢየሱስ ግን ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ስለነበር እጅግ አዝኖላቸዋል። (ማቴ. 9:36) ኢየሱስ አፍቃሪ፣ ርኅሩኅና ደግ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ለአምላክም እውነተኛ ፍቅር አልነበራቸውም። (ዮሐ. 5:42) በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ለአባቱ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም በላይ ፈቃዱን ማድረግ ያስደስተው ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ለራሳቸው እንዲመቻቸው ሲሉ የአምላክን ቃል ያጣምሙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን “የአምላክን ቃል” ይወድ ስለነበር ቃሉን አስተምሯል፣ አብራርቷል፣ ለአምላክ ቃል ጥብቅና ቆሟል እንዲሁም ከቃሉ ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። (ሉቃስ 11:28) በእርግጥም ክርስቶስ በመላ ሕይወቱ ፍቅርን አንጸባርቋል፤ ያስተማረው ነገር፣ ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት እንዲሁም ሰዎችን ያስተማረበት መንገድ ጥልቅ ፍቅር እንደነበረው ያሳያል።

4, 5. (ሀ) በፍቅር ማስተማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እውቀትና ጥሩ የማስተማር ችሎታ ማዳበራችን ለማስተማር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 እኛስ በዚህ ረገድ እንዴት ነን? የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎታችንም ሆነ በአኗኗራችን እሱን መምሰል እንፈልጋለን። (1 ጴጥ. 2:21) በመሆኑም ዓላማችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለሌሎች ማካፈል ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ባሕርያት በተለይ ደግሞ ፍቅሩን ማንጸባረቅ ነው። ከፍተኛ እውቀት እንዲሁም ጥሩ የማስተማር ችሎታ ቢኖረንም ባይኖረንም የምንሰብክላቸውን ሰዎች ልብ ለመንካት ቁልፉ ፍቅር ነው። ደቀ መዛሙርት በማድረግ ሥራችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንድንችል በፍቅር በማስተማር ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል።

5 እርግጥ ነው፣ ጥሩ አስተማሪዎች ለመሆን ስለምናስተምረው ርዕሰ ጉዳይ እውቀት ሊኖረን እንዲሁም እውቀታችንን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ጥሩ የማስተማር ችሎታ ልናዳብር ይገባል። ኢየሱስ፣ እነዚህን ሁለት ነገሮች እንዲያዳብሩ ደቀ መዛሙርቱን ረድቷቸዋል፤ እኛም እውቀትና ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንዲኖረን ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ይረዳናል። (ኢሳይያስ 54:13ን እና ሉቃስ 12:42ን አንብብ።) ያም ሆኖ ለሰዎች እውቀታችንን ለማካፈል ብቻ ሳይሆን በፍቅር ለማስተማር ጥረት ልናደርግ ይገባል። እውቀት፣ ጥሩ የማስተማር ችሎታና ፍቅር አንድ ላይ ሲጣመሩ ውጤታማ እንድንሆን ያስችሉናል። ታዲያ በምናስተምርበት ጊዜ ፍቅር ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነበር? እስቲ እነዚህን ነጥቦች እንመርምር።

ለይሖዋ ፍቅር ሊኖረን ይገባል

6. ስለምንወደው ሰው ስናወራ ምን ዓይነት ስሜት ይኖረናል?

6 ስለምንወዳቸው ነገሮች ማውራት ያስደስተናል። በጣም ስለምንወደው ነገር ስናወራ ንግግራችን ግለትና ሞቅ ያለ ስሜት የሚንጸባረቅበት ከመሆኑም ሌላ በፊታችን ላይ ደስታ ይነበባል። በተለይ ደግሞ ስለምንወደው ሰው ስንናገር እንደዚህ ዓይነት ስሜት ይታይብናል። አብዛኛውን ጊዜ ስለ ግለሰቡ የምናውቀውን ነገር ለሌሎች ለመናገር እንጓጓለን። ግለሰቡን እናሞግሰዋለን፣ እናከብረዋለን እንዲሁም ጥብቅና እንቆምለታለን። እንዲህ የምናደርገው እኛ ግለሰቡንና ባሕርይውን እንደምንወደው ሁሉ ሌሎችም ለግለሰቡ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲኖራቸው ስለምንፈልግ ነው።

7. ኢየሱስ ለአምላክ ያለው ፍቅር ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

7 ሌሎች ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖራቸው መርዳት እንድንችል እኛ ራሳችን ይሖዋን ልናውቀውና ልንወደው ይገባል። ደግሞም እውነተኛ አምልኮ ለአምላክ ባለን ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። (ማቴ. 22:36-38) ኢየሱስ በዚህ ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ይሖዋን በሙሉ ልቡ፣ በሙሉ አእምሮው፣ በሙሉ ነፍሱ እንዲሁም በሙሉ ኃይሉ ይወደው ነበር። ኢየሱስ በሰማይ ከአባቱ ጋር ለረጅም ጊዜ ምናልባትም በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት በመኖሩ አባቱን በደንብ ያውቀዋል። ከአባቱ ጋር ይህን ያህል ጊዜ መኖሩ ለአባቱ ምን ዓይነት ስሜት እንዲኖረው አድርጎታል? ኢየሱስ ‘እኔ አብን እወደዋለሁ’ ብሏል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ ለአባቱ ፍቅር እንዳለው በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አሳይቷል። ለአባቱ ያለው ፍቅር ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን እንዲያደርግ አነሳስቶታል። (ዮሐ. 8:29) ይህ ፍቅር የአምላክ ወኪል እንደሆኑ ለማስመሰል የሚሞክሩትን ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች እንዲያወግዛቸው አድርጎታል። እንዲሁም ስለ ይሖዋ ለመናገርና ሌሎችም አምላክን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ለመርዳት አነሳስቶታል።

8. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸው ነበር?

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልክ እንደ እሱ ለይሖዋ ፍቅር የነበራቸው ሲሆን ይህም ምሥራቹን በድፍረትና በቅንዓት እንዲያውጁ ገፋፍቷቸዋል። ኃይለኛ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ቢቃወሟቸውም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው ሞልተዋት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ስላዩትና ስለ ሰሙት ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት እንደማይችሉ ገልጸዋል። (ሥራ 4:20፤ 5:28) ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንደሆነና እንደሚባርካቸው ያውቁ ነበር፤ ይሖዋም ቢሆን ባርኳቸዋል! እንዲያውም ኢየሱስ ከሞተ 30 ዓመት እንኳ ሳይሞላው ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” እንደተሰበከ ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል።—ቆላ. 1:23

9. ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 እኛም ውጤታማ አስተማሪዎች ለመሆን ከፈለግን ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በጸሎት አማካኝነት አዘውትረን ከአምላክ ጋር በመነጋገር ነው። እንዲሁም ቃሉን በማጥናት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማንበብና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ እናደርጋለን። ስለ አምላክ ያለን እውቀት እያደገ ሲሄድ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር ይሞላል። ከዚያም ለአምላክ ያለንን ፍቅር በንግግራችንና በድርጊታችን ስንገልጽ ሌሎች ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ተመልክተው ወደ እሱ ለመቅረብ ይነሳሱ ይሆናል።—መዝሙር 104:33, 34ን አንብብ።

ለምናስተምረው ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል

10. አንድ ሰው ጥሩ አስተማሪ እንዲሆን ምን ሊኖረው ይገባል?

10 አንድ ሰው ጥሩ አስተማሪ እንዲሆን ለሚያስተምረው ነገር ፍቅር ሊኖረው ይገባል። የሚያስተምረው ነገር እውነት፣ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ ሊያምንበት ይገባል። አንድ አስተማሪ የሚያስተምረውን ነገር የሚወደው ከሆነ ሐሳቡን የሚገልጸው በግለት ይሆናል፤ ይህም በሚያስተምራቸው ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በሌላ በኩል ግን አንድ አስተማሪ ለሚያስተምረው ነገር ልባዊ አድናቆት ከሌለው ተማሪዎቹ የሚሰሙትን ነገር ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት እንዴት ሊጠብቅባቸው ይችላል? የአምላክን ቃል ስታስተምር የአንተ ምሳሌነት በተማሪዎቹ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዳለ ፈጽሞ አትዘንጋ። ኢየሱስ “በሚገባ የተማረ ሁሉ . . . እንደ አስተማሪው ይሆናል” ብሏል።—ሉቃስ 6:40

11. ኢየሱስ ለሚያስተምረው ነገር ፍቅር ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ለሚያስተምረው ነገር ፍቅር ነበረው። ለሰዎች የሚያካፍለው ውድ ነገር እንዳለው ያውቅ ነበር፤ ይህ ውድ ነገር ደግሞ በሰማይ ስላለው አባቱ የሚገልጸው እውነት፣ ‘የአምላክ ቃል’ እንዲሁም “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነው። (ዮሐ. 3:34፤ 6:68) ኢየሱስ ያስተማራቸው እውነቶች፣ ብሩሕ እንደሆነ ብርሃን መጥፎ የሆነውን ነገር ከማጋለጣቸውም በተጨማሪ ጥሩ የሆነው ነገር ጎልቶ እንዲታይ አድርገዋል። እነዚህ እውነቶች ሐሰተኛ በሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ለተታለሉትና በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ለወደቁት ትሑት የሆኑ ሰዎች ተስፋና ማጽናኛ ሰጥተዋቸዋል። (ሥራ 10:38) ኢየሱስ ለእውነት ፍቅር እንደነበረው በትምህርቶቹ ብቻ ሳይሆን በድርጊቱም አሳይቷል።

12. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ምሥራቹ ምን አመለካከት ነበረው?

12 እንደ ኢየሱስ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ይሖዋ እና ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት በጣም ይወዱት እንዲሁም ከፍ አድርገው ይመለከቱት ስለነበር ተቃዋሚዎቻቸው ይህንን እውነት ለሰዎች ከማካፈል ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጓቸው አልቻሉም። ጳውሎስ በሮም ለነበሩት የእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ምሥራቹን ለማወጅ የምጓጓው ለዚህ ነው። እኔ በምሥራቹ አላፍርም፤ እንዲያውም ምሥራቹ ለሚያምን ሁሉ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።” (ሮም 1:15, 16) ጳውሎስ እውነትን ማወጅ ትልቅ ክብር እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። “ለእኔ ይህ ጸጋ ተሰጠኝ፤ ይህም ሊደረስበት ስለማይችለው የክርስቶስ ብልጽግና የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዳውጅ [ነው]” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 3:8) ጳውሎስ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች በግለት ያስተምር እንደነበር መገመት አያዳግትም።

13. ምሥራቹን እንድንወደው የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

13 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምሥራች ፈጣሪን እንድናውቀው እንዲሁም ከእሱ ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይረዳናል። ይህ ምሥራች በሕይወት ውስጥ ለሚነሱት አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የሚሰጠን ከመሆኑም በተጨማሪ ሕይወታችንን የመለወጥ ኃይል አለው፤ ተስፋ ይሰጠናል እንዲሁም መከራ ሲያጋጥመን ያበረታናል። በተጨማሪም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራትና ለዘላለም መኖር የምንችልበትን መንገድ ይጠቁመናል። ከምሥራቹ የበለጠ ውድ ወይም ጠቃሚ የሆነ እውቀት የትም አናገኝም። ከፍተኛ ደስታ ሊያስገኝልን የሚችል በዋጋ የማይተመን ስጦታ ተሰጥቶናል። ይህንን ስጦታ ለሌሎችም ስናካፍል ተጨማሪ ደስታ እናገኛለን።—ሥራ 20:35

14. ለምናስተምረው ነገር ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ለምሥራቹ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል ስታነብ አንዳንድ ጊዜ ቆም እያልክ በምታነበው ነገር ላይ አሰላስል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን አብረኸው እንዳለህ ወይም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር እንደምትጓዝ አድርገህ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ እንዳለህ በማሰብ ሕይወት አሁን ካለው ምን ያህል የተለየ እንደሚሆን ለመገመት ሞክር። ለምሥራቹ ታዛዥ መሆንህ ባስገኘልህ በረከቶች ላይ አሰላስል። ለምሥራቹ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እያደገ እንዲሄድ ካደረግህ የምታስተምራቸው ሰዎች ይህንን ያስተውላሉ። እንግዲያው በተማርነው ነገር ላይ በጥንቃቄ ማሰላሰል እንዲሁም ለምናስተምረው ነገር ትኩረት መስጠት ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16ን አንብብ።

ለሰዎች ፍቅር ሊኖረን ይገባል

15. አንድ አስተማሪ ለተማሪዎቹ ፍቅር ሊኖረው የሚገባው ለምንድን ነው?

15 አንድ ጥሩ አስተማሪ፣ ተማሪዎቹ የሚማሩትን ነገር በጉጉት እንዲከታተሉና ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ለማስቻል ሲል ዘና እንዲሉ ያደርጋቸዋል። አፍቃሪ የሆነ አስተማሪ ለተማሪዎቹ እውቀትን የሚያካፍላቸው ከልቡ ስለሚያስብላቸው ነው። ትምህርቱን የሚያቀርበው ተማሪዎቹ ከሚያስፈልጋቸው ነገርና ከመረዳት ችሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። እንዲሁም የተማሪዎቹን ችሎታና ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ያስገባል። አስተማሪዎች ለተማሪዎቻቸው እንዲህ ያለ ፍቅር ካላቸው ተማሪዎቹ ይህን ማስተዋል ይችላሉ፤ ይህም የመማር ማስተማሩ ሂደት አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል።

16. ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16 ኢየሱስ እንዲህ ያለ ፍቅር ነበረው። ለሰዎች ያለውን ፍቅር ካሳየባቸው መንገዶች ሁሉ የላቀው፣ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መስጠቱ ሲሆን ይህም የሰው ልጆች መዳን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። (ዮሐ. 15:13) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ለሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያደርግላቸው ነበር። ሰዎች ወደ እሱ እንዲመጡ ከመጠበቅ ይልቅ እሱ ራሱ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ በመጓዝ ምሥራቹን ሰብኳል። (ማቴ. 4:23-25፤ ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ታጋሽና የሰዎችን ስሜት የሚረዳ ሰው ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ እርማት መስጠት ባስፈለገው ወቅት በፍቅር ምክር ሰጥቷቸዋል። (ማር. 9:33-37) ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪዎች መሆን እንደሚችሉ እንደሚተማመንባቸው በመግለጽ አበረታቷቸዋል። ከኢየሱስ የበለጠ አፍቃሪ የሆነ አስተማሪ በምድር ላይ ኖሮ አያውቅም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያሳያቸው ፍቅር እነሱም በምላሹ እንዲወዱትና ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ አነሳስቷቸዋል።—ዮሐንስ 14:15ን አንብብ።

17. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለሰዎች ፍቅር እንደነበራቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

17 እንደ ኢየሱስ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱም ለሚሰብኩላቸው ሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸውና እንደሚያስቡላቸው አሳይተዋል። የሚደርስባቸውን ስደት ተቋቁመውና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ሌሎችን ያገለገሉ ሲሆን ምሥራቹን በመስበኩ ረገድም ውጤታማ ሆነዋል። ደቀ መዛሙርቱ በመንፈሳዊ ለረዷቸው ሰዎች እንዴት ያለ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው! ሐዋርያው ጳውሎስ ለሰበከላቸው ሰዎች የነበረውን ጥልቅ ፍቅር ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የምታጠባ እናት ልጆቿን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በነበርንበት ጊዜ በገርነት ተንከባከብናችሁ። በመሆኑም ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ጭምር ለእናንተ ለማካፈል ዝግጁዎች ነበርን፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።”—1 ተሰ. 2:7, 8

18, 19. (ሀ) የስብከቱን ሥራ ለማከናውን ስንል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች የሆንነው ለምንድን ነው? (ለ) ሌሎች ፍቅራችንን እንደሚያስተውሉ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

18 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክን ለማወቅና ለማገልገል የሚጓጉ ሰዎችን ለማግኘት በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ይሰብካሉ። ባለፉት ተከታታይ 17 ዓመታት በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዓት አሳልፈናል፤ ወደፊትም በዚሁ ሥራ መካፈላችንን እንቀጥላለን። በስብከቱ ሥራ መካፈል ጊዜን፣ ጉልበትንና ቁሳዊ ሀብትን መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ቢሆንም ይህንን ሥራ በፈቃደኝነት እናከናውናለን። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም፣ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ እናውቃለን። (ዮሐ. 17:3፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) እኛ ይሖዋን እንደምናውቀውና እንደምንወደው ሁሉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችም እሱን እንዲያውቁትና እንዲወዱት እንድንረዳቸው ፍቅር ይገፋፋናል።

19 ፍቅር እንዳለን ሌሎች በቀላሉ ሊያስተውሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት አቅኚ የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ላጡ ግለሰቦች ደብዳቤ በመጻፍ ታጽናናቸዋለች። አንድ ሰው እንዲህ የሚል ምላሽ ጽፎላታል፦ “መጀመሪያ ላይ፣ ፈጽሞ የማታውቂውን ሰው ከደረሰበት መከራ ለማጽናናት ስትይ ደብዳቤ መጻፍሽ በጣም አስገርሞኝ ነበር። ለሰዎችም ሆነ የሰው ልጆችን በሕይወት ጎዳና ላይ ለሚመራቸው አምላክ ፍቅር እንዳለሽ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።”

20. በፍቅር ማስተማር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

20 ፍቅርና ሙያዊ ክህሎት አንድ ላይ ሲጣመሩ አስደናቂ የሆነ ነገር ማከናወን እንደሚቻል ሲነገር እንሰማለን። እኛም በማስተማሩ ሥራችን፣ ተማሪዎቻችን ይሖዋን እንዲያውቁና ለእሱ ፍቅር እንዲያዳብሩ ልንረዳቸው እንፈልጋለን። በእርግጥም ውጤታማ አስተማሪዎች ለመሆን ከፈለግን ለአምላክ፣ ለእውነትና ለሰዎች ፍቅር ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ያለ ፍቅር ስናዳብርና ይህንንም በአገልግሎታችን ላይ ስናሳይ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን፤ ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስን እንደመሰልንና ይሖዋን እንዳስደሰትን ማወቃችን እርካታ ያስገኝልናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ምሥራቹን ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ

ለአምላክ፣

ለምናስተምረው ነገር እንዲሁም

ለምናስተምራቸው ሰዎች

ፍቅር ማዳበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን የተለየ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ አስተማሪ ለመሆን እውቀትና የማስተማር ችሎታ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍቅር ያስፈልጋል