በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

• አንድ ሕፃን ከመወለዱ በፊት ቢሞት የትንሣኤ ተስፋ ሊኖረው ይችላል?

ሕይወት የሚጀምረው ፅንስ በሚፀነስበት ቅጽበት ነው። ‘በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ስለሚቻል’ ይሖዋ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ከሞት ማስነሳት ይችላል። (ማር. 10:27) ይሁንና ይሖዋ በማሕጸን ውስጥ እያለ የሞተን ሕፃን ስለማስነሳቱ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ አይናገርም።—4/15 ገጽ 12, 13

• ጉንዳንን፣ ሽኮኮን፣ አንበጣንና ጌኮ የተባለውን የእንሽላሊት ዝርያ በመመልከት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

በደመ ነፍስ የሚመሩት እነዚህ አራት ፍጥረታት ጥበብ አላቸው። በመሆኑም እነዚህ ፍጥረታት አምላክ ጥበበኛ እንደሆነ አጉልተው ያሳያሉ። (ምሳሌ 30:24-28)—4/15 ገጽ 16-19

• በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ የዛሬ መቶ ዓመት ማለትም በ1909 ምን ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነገር ተከናውኗል?

የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ (የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ድርጅት ነው) ዋና መሥሪያ ቤት ከፒትስበርግ፣ ፔንሲልቬንያ አሁን ወደሚገኝበት ወደ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የተዛወረው በ1909 ነበር።—5/1 ገጽ 22-24

• መጽሐፍ ቅዱስ ዝምታ የራሱ የሆነ ጥሩ ጎን እንዳለው የሚናገረው ከምን አንጻር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ማለት የአክብሮት መግለጫና የአስተዋይነት ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል፤ እንዲሁም ጸጥታ ለማሰላሰል እንደሚረዳ ይናገራል። (መዝ. 37:7፤ 63:6፤ ምሳሌ 11:12)—5/15 ገጽ 3-5

• ጆን ዊክሊፍን፣ ዊልያም ቲንደልን፣ ሮበርት ሞሪሰንን እና አዶናይራም ጀድሰንን የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው?

ሁሉም ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበራቸው ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ ሊያነበው በሚችለው ቋንቋ ተርጉመዋል። ዊክሊፍ እና ቲንደል በእንግሊዝኛ፣ ሞሪሰን ደግሞ በቻይንኛ እንዲሁም ጀድሰን በበርማ (ምያንማር) ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ተርጉመዋል።—6/1 ገጽ 8-11

• ለአምላክ ቤት ከፍተኛ ቅንዓት እንዳላቸው ያሳዩት የይሁዳ ነገሥታት ስንት ናቸው?

በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ላይ ከነገሡት አሥራ ዘጠኝ ነገሥታት መካከል ለአምላክ ቤት ከፍተኛ ቅንዓት እንዳላቸው ያሳዩት አራቱ ማለትም አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ናቸው።—6/15 ገጽ 7-11

• በምድር ላይ የሚገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረቡ ሥራ ይካፈላሉ?

አይካፈሉም። እርግጥ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል ናቸው፤ ይሁንና መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን ሥራ በበላይነት የሚከታተሉት የበላይ አካሉ አባላት ናቸው።—6/15 ገጽ 22-24

• የሮም ወታደሮች የኢየሱስን እጀ ጠባብ በጣም የወደዱት ለምን ነበር?

ወታደሮቹ ኢየሱስ በተገደለበት ወቅት እጀ ጠባቡን አልተከፋፈሉትም። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ልብሶች የሚሠሩት ሁለት ጨርቆችን አንድ ላይ ገጣጥሞ በመስፋት ነው፤ ይሁን እንጂ የኢየሱስ ልብስ ምንም ስፌት የሌለው መሆኑ ይበልጥ ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል።—7/1 ገጽ 22

• ኢየሱስ ሰዎችን የያዘበት መንገድ የሃይማኖት መሪዎቹ ከያዙበት መንገድ እንዲለይ ያደረገው ቁልፉ ነገር ፍቅር ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

እነዚህ መሪዎች ለተራው ሕዝብ ፍቅር ከማሳየት ይልቅ ይንቁት ነበር። ከዚህም በላይ ለአምላክ ፍቅር አልነበራቸውም። ኢየሱስ አባቱን የሚወድድ ከመሆኑም ሌላ ለሕዝቡ ያዝን ነበር። (ማቴ. 9:36) ለሰዎች ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ደግነትን አሳይቷቸዋል።—7/15 ገጽ 15

• አንድ ባልና ሚስት ገንዘብ የሚይዙበት መንገድ በትዳራቸው ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን ችግር እንዲቋቋሙስ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

አብዛኛውን ጊዜ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ችግሮች መንስኤው ገንዘቡ ሳይሆን ባልና ሚስቱ በገንዘብ አያያዝ ረገድ እርስ በርስ አለመተማመናቸው አሊያም ወደፊት ምን ያጋጥመን ይሆን የሚለው ፍርሃት ነው። በተጨማሪም የትዳር ጓደኛሞቹ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው መሆኑ ለችግሩ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ባለትዳሮች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚረዷቸው አራት ቁልፎች የሚከተሉት ናቸው፦ ስለ ገንዘብ ስትወያዩ በእርጋታ መነጋገርን ተማሩ፣ ገቢያችሁን በተመለከተ ትክክለኛው አመለካከት ይኑራችሁ፣ እቅዳችሁን በጽሑፍ አስፍሩ እንዲሁም ማን ምን ማድረግ እንዳለበት ተነጋገሩ።—8/1 ገጽ 10-12