‘ይሖዋ ፊቱን አብርቶላቸዋል’
‘ይሖዋ ፊቱን አብርቶላቸዋል’
በሰዎች ፊት ላይ ከ30 የሚበልጡ ጡንቻዎች ይገኛሉ። ፈገግ በምትልበት ጊዜ 14ቱ የፊት ጡንቻዎችህ በአንድነት ይሠራሉ! እነዚህ ጡንቻዎች ባይኖሩ ኖሮ ከሰዎች ጋር የምታደርገው ውይይት ምን ሊመስል እንደሚችል ገምት። አስደሳች የሚሆን ይመስልሃል? በጭራሽ። ይሁንና እነዚህ የፊት ጡንቻዎች መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ውይይትን አስደሳች ከማድረግ ያለፈ ጥቅም አላቸው። እነዚህ ጡንቻዎች ከሌሎች አካላዊ መግለጫዎች ጋር ተቀናጅተው በሚሠሩበት ጊዜ ሐሳብ ለማስተላለፍ የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። በርካታ ሰዎች ‘እያንዳንዱ ቃል ሊኖረው የሚችለውን የተለያየ ትርጉም ጨምሮ ውስብስብ የሆኑ ሐሳቦችን በምልክት ቋንቋ መግለጽ የሚቻለው እንዴት ነው?’ በማለት በአግራሞት ይጠይቃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሐሳብንና ስሜትን በመግለጽ ረገድ የትኛውም ሰብዓዊ ‘ፊት’ ሊወዳደረው የማይችል አንድ ‘ፊት’ ማየት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ ማየት የቻሉት ‘የይሖዋን ፊት’ ነው። (ሰቆ. 2:19) ይህ ደግሞ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይሖዋ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ታላቅ ፍቅሩን ሲያሳይ ቆይቷል። የጥንቶቹ እሥራኤላውያን በኖሩበት ዘመን ሳይቀር መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ፍቅር አሳይቷል። (ዘሌ. 19:14) በዛሬው ጊዜም ቢሆን መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ፍቅር እንዳለው በግልጽ ታይቷል። “[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) መስማት የተሳናቸው በርካታ ሰዎች፣ ስለ አምላክ የሚናገረውን ትክክለኛውን የእውነት እውቀት በማግኘታቸው በምሳሌያዊ አነጋገር ፊቱን ማየት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች መስማት ካልቻሉ ትክክለኛውን እውቀት ያገኙት እንዴት ነው? ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የምልክት ቋንቋ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
የሚሰሙት በማየት ነው
መስማት የተሳናቸውን ሰዎችና የምልክት ቋንቋን በተመለከተ በርካታ የተሳሳቱ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። ይሁንና መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በተመለከተ ያሉትን አንዳንድ እውነታዎች እስቲ እንመልከት። መስማት የተሳናቸው ሰዎች መኪና መንዳት ይችላሉ። የከንፈር እንቅስቃሴን ማንበብ በጣም ሊከብዳቸው ይችላል። የምልክት ቋንቋ ከብሬይል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ከዚህም በላይ ዝም ብሎ የሚደረግ የሰውነት መግለጫ አይደለም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት አንድ ወጥ የሆነ የምልክት ቋንቋ የለም። ከዚህም በተጨማሪ የምልክት ቋንቋ በአንድ አገር ውስጥም እንኳ ከቦታ ቦታ ይለያያል።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማንበብ ይችላሉ? አንዳንዶች በደንብ ማንበብ የሚችሉ ቢሆንም እንኳ አብዛኞቹ ማንበብ ይቸግራቸዋል። ለምን? በጽሑፍ ሰፍረው የሚገኙት ቃላት የተወሰዱት ከንግግር ቋንቋ በመሆኑ ነው። መስማት የሚችል አንድ ሕፃን፣ ቋንቋ የሚማረው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ይህ ልጅ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ በዙሪያው ያሉ ሰዎች የአካባቢውን ቋንቋ ሲናገሩ ይሰማል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ቃላትን በማቀናጀት ዓረፍተ ነገሮችን መሥራት ይችላል። ይህ ችሎታ ደግሞ ሰዎች የሚናገሩትን ቋንቋ በመስማት ብቻ የሚገኝ ነው። በመሆኑም መስማት የሚችሉ ልጆች ማንበብ በሚጀምሩበት ጊዜ እንዲማሩት የሚጠበቅባቸው ነገር ቢኖር ቀደም ሲል የሚያውቋቸውን ድምፆችና የንግግር ቃላት የሚወክሉትን ሆሄያት ማጥናት ብቻ ነው።
ወደ ባዕድ አገር እንደሄድክና ከመስታወት በተሠራ ድምፅ በማያስተላልፍ አንድ ክፍል ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። የአካባቢውን ቋንቋ ከዚህ በፊት ሰምተህ አታውቅም። የአካባቢው ሰዎች በየቀኑ እየመጡ ወደ መስታወቱ ተጠግተው ሊያነጋግሩህ ይሞክራሉ። አንተ ግን ሰዎቹ ምን እንደሚሉህ መስማት አትችልም። የሚታይህ ከንፈራቸው ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው። ሰዎቹ የሚናገሩት ነገር እንዳልገባህ ሲረዱ የተናገሯቸውን
ቃላት በወረቀት ላይ ጽፈው በመስታወቱ በኩል አሳዩህ። ይህንን ያደረጉት የጻፉትን ነገር መረዳት ትችላለህ ብለው ስላሰቡ ነው። አንተ ግን የጻፉትን ነገር ምን ያህል መረዳት የምትችል ይመስልሃል? በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለህ ከሰዎች ጋር መግባባት አዳጋች እንደሚሆንብህ ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም በጽሑፍ ያሳዩህ ነገር የሚወክለው ከዚህ ቀድም ፈጽሞ ሰምተኸው የማታውቀውን ቋንቋ ነው። ይህ ምሳሌ መስማት የተሳናቸው አብዛኞቹ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ነው።መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹት በምልክት ቋንቋ በመጠቀም ነው። አንድ ሰው ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሐሳብ ለመግለጽ ምልክቶችን ይጠቀማል። ጣቶቹን፣ ክንዱንና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቹን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በፊቱ ላይ የሚነበበው ስሜት የምልክት ቋንቋን የሰዋስው ሕግ የተከተሉ ናቸው። በዚህ መንገድ፣ መረጃዎችን ለዓይን ማስተላለፍ የሚችል የሚታይ ቋንቋ መፍጠር ይቻላል።
መስማት የተሳነው አንድ ሰው የምልክት ቋንቋ በሚናገርበት ጊዜ በፊቱ ላይ የሚያሳየው እያንዳንዱ መግለጫም ሆነ እጆቹንና ሌሎቹን የሰውነት ክፍሎቹን ተጠቅሞ የሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ትርጉም አለው ማለት ይቻላል። ግለሰቡ በፊቱ ላይ የሚሳያቸው መግለጫዎች ሰዎችን ለማስደመም ብሎ የሚያደርጋቸው አይደሉም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ መግለጫዎች የምልክት ቋንቋ ሰዋስው ወሳኝ ክፍል ናቸው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፦ ቅንድብን ወደላይ በማድረግ አንድን ግለሰብ መልስ የማያሻው ጥያቄ መጠየቅ አሊያም ግለሰቡ “አዎ” ወይም “አይደለም” የሚል አጭር መልስ እንዲሰጥ የሚያደርግ ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል። ቅንድብን ወደታች ማድረግ ደግሞ ማን፣ ምን፣ የት፣ መቼ፣ ለምን ወይም እንዴት የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅን ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ የአፍ እንቅስቃሴዎች የአንድን ዕቃ መጠን ወይም የአንድን ድርጊት ክብደት ሊገልጹ ይችላሉ። መስማት የተሳነው አንድ ሰው ጭንቅላቱን የሚያንቀሳቅስበት፣ ትከሻውን የሚነቀንቅበት፣ ጉንጩን የሚያንቀሳቅስበትና ዓይኑን የሚያርገበግብበት መንገድ ሊያስተላልፈው የፈለገውን ሐሳብና ስሜት በማያሻማ መንገድ እንዲገልጽ ያስችለዋል።
እነዚህ እንቅስቃሴዎች አንድ ላይ ተዳምረው የምልክት ቋንቋ የሚናገረው ግለሰብ ለሚመለከቱት ሰዎች ሐሳቡን ይበልጥ ማራኪ በሆነ መንገድ እንዲያስተላልፍ ያስችሉታል። የምልክት ቋንቋ የሚችሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዲህ ያለውን የዳበረ ቋንቋ በመጠቀም ማንኛውንም ዓይነት ሐሳብ መግለጽ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ ቅኔያዊም ሆኑ ሙያዊ ቃላትን መጠቀም፣ የፍቅር ስሜትን መግለጽም ሆነ መቀለድ እንዲሁም በዓይን የሚታዩትንም ሆነ ረቂቅ ነገሮችን መግለጽ ይችላሉ።
በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል
መስማት የተሳነው አንድ ሰው ስለ ይሖዋ የሚናገረውን እውቀት በምልክት ቋንቋ አማካኝነት ሲመለከት በምሳሌያዊ አነጋገር መልእክቱን መስማትና የመልእክቱ ባለቤት በሆነው አካል ማመን ይችላል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ለመስበክና እነሱን ለመርዳት የሚያስችሉ የማስተማሪያ መሣሪያዎችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። (ሮም 10:14) በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በ58 የምልክት ቋንቋዎች የትርጉም ሥራ የሚከናወን ሲሆን በ40 የምልክት ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በዲቪዲ ወጥተዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ጥረት ያስገኘው ጥቅም አለ?
መስማት የተሳናቸው ወላጆች ያሉት ጄረሚ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ከመጠበቂያ ግንብ ላይ ጥቂት አንቀጾችን ለመረዳት በመኝታ ክፍሉ ሆኖ ረጅም ሰዓት ያጠፋበት ጊዜ ትዝ ይለኛል። ድንገት ከመኝታ ክፍሉ ወጥቶ በምልክት ቋንቋ ‘አሁን ገባኝ! አሁን ገባኝ!’ በማለት በደስታ ተናገረ።
ቀጥሎም ከጽሑፉ የተረዳውን ሐሳብ ይነግረኝ ጀመር። በዚያን ወቅት ገና 12 ዓመቴ ነበር። አንቀጾቹን ፈጠን ብዬ ካነበብኳቸው በኋላ በምልክት ቋንቋ ‘አባዬ፣ ሐሳቡን በትክክል የተረዳኸው አይመስለኝም’ አልኩት። ከዚያም ‘ሊባል የተፈለገው’ ብዬ ልቀጥልለት ስል ዝም እንድል ምልክት ከሰጠኝ በኋላ የጽሑፉን ሐሳብ በራሱ ለመረዳት ወደ መኝታ ክፍሉ ተመለሰ። በዚያን ወቅት በፊቱ ላይ ያነበብኩትን የሐዘን ስሜት እንዲሁም ወደ መኝታ ክፍሉ ተመልሶ ሲገባ ስመለከት የተሰማኝን የአድናቆት ስሜት መቼም ቢሆን አልረሳውም። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች በዲቪዲ መወጣታቸው የጽሑፎችን ሐሳብ በተሻለ መንገድ ለመረዳት አስችሎታል። ስለ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው በሚገልጽበት ጊዜ በፊቱ ላይ የሚነበበውን የደስታ ስሜት መመልከቴ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።”አንድ ባልና ሚስት፣ በቺሊ የምትኖረውን ሄሴንያ የተባለች መስማት የተሳናት አንዲት ወጣት ባነጋገሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ተሞክሮም እስቲ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በቺሊ የምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ—በዲቪዲ የተባለውን መጽሐፍ ለሄሴንያ ለማሳየት እናቷን ፈቃድ ከጠየቁ በኋላ ያጋጠማቸውን እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “ሄሴንያ ታሪኩን በምትመለከትበት ጊዜ መሳቅ ጀመረች፤ ትንሽ ቆይቶም እንባዋ ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ። እናቷ ለምን እንደምታለቅስ ስትጠይቃት የምታየውን ነገር ስለወደደችው እንደሆነ ገለጸችላት። በዚህ ጊዜ እናትየው፣ ልጅቱ በዲቪዲው ላይ ያለውን ታሪክ በሚገባ እንደተረዳችው ተገነዘበች።”
ቬነዝዌላ ውስጥ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ የምትኖር መስማት የተሳናት አንዲት ሴት አንድ ልጅ ነበራት። ሁለተኛ ልጇን ስታረግዝ እሷና ባለቤቷ ካለባቸው የኢኮኖሚ ችግር አንጻር ሁለት ልጅ ማሳደግ እንደማይችሉ ስለተሰማቸው ጽንሱን ለማስወረድ አሰቡ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ባልና ሚስቱ ስላቀዱት ሁኔታ ምንም የሚያውቁት ነገር ባይኖርም በቬነዝዌላ የምልክት ቋንቋ ከተዘጋጀው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከተባለው ብሮሹር ትምህርት 12ን በቪዲዮ አሳዩአቸው። ይህ ትምህርት አምላክ ስለ ውርጃና ሰው ስለ መግደል ያለውን አመለካከት ያብራራል። ከጊዜ በኋላ ሴትየዋ ያን ትምህርት በማጥናቷ ደስተኛ መሆኗን ለይሖዋ ምሥክሮቹ ገልጻለች። ይህንን ትምህርት ከተማሩ በኋላ ጽንሱን ላለማስወረድ እንደወሰኑ ነገረቻቸው። በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው ይህ ዲቪዲ ያልተወለደውን ልጅ ሕይወት ታደገ!
ለሬን የተባለች መስማት የተሳናት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የአንድን ትልቅ ምስል ቁርጥራጮች አንድ ላይ በመገጣጠም ምስሉን ለማምጣት ከሚደረግ ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ማለትም የምስሉን አጠቃላይ ገጽታ ለመሥራት በምጥርበት ወቅት አንዳንድ ቁርጥራጮች በመጉደላቸው ክፍተቶች ይፈጠሩብኝ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በምልክት ቋንቋ እንደ ልብ ማግኘት ስችል ግን ክፍተቶቹ መሙላት ጀመሩ።” የይሖዋ ምሥክር ከሆኑ 38 ዓመታት የሆናቸውና መስማት የተሳናቸው ጆርጅ እንዲህ ብለዋል፦ “ያለ ማንም እርዳታ አንድን ጉዳይ መረዳት መቻላችሁ ለራሳችሁ አክብሮት እንዲኖራችሁ ብሎም በራስ የመተማመን ስሜት እንዲያድርባችሁ እንደሚያደርግ ምንም ጥያቄ የለውም። በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁት ዲቪዲዎች በመንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።”
“ስብሰባው የሚደረገው በገዛ ቋንቋዬ ነው!”
የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን በምልክት ቋንቋ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን አቋቁመዋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ1,100 የሚበልጡ በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች ይገኛሉ። መስማት የተሳናቸው ሰዎች ትምህርቱ የሚቀርብላቸው በገዛ ቋንቋቸው ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የሚብራሩላቸው
የእነሱን አስተሳሰብ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በስብሰባዎቹ ላይ ትምህርቶቹ የሚቀርቡበት መንገድ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ባሕልና የሕይወት ተሞክሮ ከግምት ያስገባ ነው።በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች መቋቋማቸው ያስገኘው ጥቅም አለ? በ1955 የተጠመቁትን ሲረል የተባሉ ወንድም ተሞክሮ እንመልከት። እኚህ ወንድም በወረቀት ላይ የታተሙ ጽሑፎችን ለዓመታት የቻሉትን ያህል ለማጥናት የሞከሩ ከመሆኑም በላይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኙ ነበር። ስብሰባዎቹን በምልክት ቋንቋ የሚተረጉሙ ወንድሞች አንዳንዴ ይኖራሉ፤ አንዳንዴ ደግሞ አይኖሩም። አስተርጓሚዎች በማይኖሩበት ጊዜ አንዳንድ ወንድሞች በፍቅር ተነሳስተው ከመድረክ የሚተላለፈውን ትምህርት እየጻፉ ባያሳዩአቸው ኖሮ ሐሳቡን መረዳት የሚችሉበት ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም ነበር። ሲረል የይሖዋ ምሥክር ከሆኑ ወደ 34 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይኸውም በ1989 በኒው ዮርክ ሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ። ሲረል የዚህ ጉባኤ አባል በሆኑ ጊዜ ምን እንደተሰማቸው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ጥቅጥቅ ካለ ጫካ ወይም በጨለማ ከተዋጠ ዋሻ ወደ ብርሃን የመውጣት ያህል ነበር። ስብሰባው የሚደረገው በገዛ ቋንቋዬ ነው!”
በምልክት ቋንቋ የሚመሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ አምላክ የሚማሩባቸው እንዲሁም እሱን ለማምለክ ዘወትር የሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ናቸው። በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩባቸውና እርስ በርስ የሚበረታቱባቸው ቦታዎች ናቸው። በዚህ ዓለም፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር በቀላሉ መነጋገር የሚያዳግታቸው ከመሆኑም በላይ ከሌሎች የተገለሉ ናቸው፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ጉባኤዎች መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር በቀላሉ መግባባትና ወዳጅነት መመሥረት እንዲችሉ ረድተዋቸዋል። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ትምህርት መቅሰም፣ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት አንድ ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር ይችላሉ። መስማት የተሳናቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ማገልገል ችለዋል። አንዳንዶች ደግሞ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት ሲሉ ወደ ሌሎች አገሮች ሄደዋል። መስማት የተሳናቸው ክርስቲያን ወንዶች ውጤታማ አስተማሪዎችና እረኞች መሆን የቻሉ ሲሆን ጥሩ የማደራጀት ችሎታንም አዳብረዋል፤ ከዚህም በላይ በርካታ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ ሆነዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ፣ በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ከ100 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎች እንዲሁም ወደ 80 የሚጠጉ ቡድኖች አሉ። በብራዚል ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችና ከ400 በላይ ቡድኖች ይገኛሉ። በሜክሲኮ 300 የሚሆኑ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች አሉ። በሩሲያ ውስጥ በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ከ30 የሚበልጡ ጉባኤዎችና 113 ቡድኖች ይገኛሉ። እነዚህ ጉባኤዎችና ቡድኖች፣ በዓለም ዙሪያ ምን ያህል እድገት እንዳለ የሚጠቁሙ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከጉባኤ ስብሰባዎች በተጨማሪ በምልክት ቋንቋ የሚደረጉ የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብሰባዎችን አደራጅተዋል። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በተለያዩ የምልክት ቋንቋዎች የተመሩ ከ120 የሚበልጡ የአውራጃ ስብሰባዎች ተደርገዋል። እነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች መስማት የተሳናቸው የይሖዋ ምሥክሮች፣ መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ የሚያገኘው የዓለም አቀፉ የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር አካል መሆናቸውን እንዲያስተውሉ አድርገዋቸዋል።
ሌናርድ የተባለ መስማት የተሳነው ወንድም የይሖዋ ምሥክር ከሆነ 25 ዓመታት አልፈውታል። ሌናርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ለመሆኑ አንድ ጊዜም ተጠራጥሬ አላውቅም። ያም ቢሆን፣ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ግልጽ አልሆነልኝም ነበር። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በይሖዋ ላይ እንድቆጣ ያደርገኝ ነበር። ይሁን እንጂ በምልክት ቋንቋ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ንግግር አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ በግልጽ እንድገነዘብ አድርጎኛል። ንግግሩ ሲያበቃ ባለቤቴ ጎሸም አደረገችኝና ‘አሁን የሚያረካ መልስ አገኘህ?’ በማለት ጠየቀችኝ። በሙሉ ልብ አዎን ብዬ መመለስ እችል ነበር!። ከ25 ዓመት በኋላም ይኸው በይሖዋ ቤት አለሁ፤ የይሖዋን ቤት ትቼ ባለመውጣቴ አመስጋኝ ነኝ። ስለ ይሖዋ የተሟላ ግንዛቤ ያልነበረኝ ቢሆንም ሁልጊዜም እወደው ነበር። ዛሬ ግን በደንብ ስለ እሱ ማወቅ ችያለሁ!”
ከልብ አመስጋኞች ናቸው
መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ በሚማሩበት ጊዜ በእሱ ፊት ላይ የሚመለከቷቸው “መግለጫዎች” የትኞቹ ናቸው? በይሖዋ ፊት ላይ እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ፍትሕ፣ ታማኝነትና ፍቅራዊ ደግነት ያሉ በርካታ ባሕርያትን ማንበብ ይችላሉ።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙት መስማት የተሳናቸው የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን ፊት እያዩ ከመሆኑም በላይ ወደፊትም ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ያዩታል። ይሖዋ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ልባዊ ፍቅር ስላለው ‘ፊቱን አብርቶላቸዋል።’ (ዘኍ. 6:25) መስማት የተሳናቸው እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በማወቃቸው ምንኛ አመስጋኞች ናቸው!
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ ከ1,100 የሚበልጡ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች ይገኛሉ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ፊቱን አብርቶላቸዋል