የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንዲት እህት በጉባኤ፣ በወረዳ፣ በልዩ ወይም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ወደ ምልክት ቋንቋ በምታስተረጉምበት ጊዜ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል?
በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ አንዲት ክርስቲያን ራሷን መሸፈን የሚገባት ባሏ ወይም በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ወንድም ሊያከናውነው የሚገባውን ሥራ ስታከናውን ነው። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራሷን ታዋርዳለች” ምክንያቱም ‘የሴት ሁሉ ራስ ወንድ ነው’ በማለት ከተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። (1 ቆሮ. 11:3-10) አንዲት እህት እንደነዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ልከኛና ተስማሚ የሆነ የራስ መሸፈኛ ማድረጓ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላለው ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት እንደምትገዛ ያሳያል።—1 ጢሞ. 2:11, 12 *
አንዲት እህት፣ አንድ ወንድም የሚሰጠውን ንግግር ወደ ምልክት ቋንቋ በምታስተረጉምበት ጊዜስ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል? እርግጥ ነው፣ በዚህ ጊዜ እህት የምታከናውነው ነገር የተናጋሪውን ሐሳብ በሌላ ቋንቋ ማስተላለፍ ብቻ ነው። በሌላ አባባል ትምህርቱን እያቀረበ ያለው የምታስተረጉምለት ወንድም እንጂ እሷ አይደለችም። ይሁንና ወደ ምልክት ቋንቋ ማስተርጎም ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ከማስተርጎም በጣም የተለየ እንደሆነ ግልጽ ነው። በንግግር ቋንቋዎች ክፍሎች በሚቀርቡበት ጊዜ አድማጮች አስተርጓሚውን እያዳመጡ ትኩረታቸውን በተናጋሪው ላይ ማድረግ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ምልክት ቋንቋ ከማስተርጎም በተለየ መልኩ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚያስተረጉሙ እህቶች የአድማጮች ትኩረት በዋነኝነት በእነሱ ላይ እንዲያርፍ በማያደርግ ቦታ ሆነው ያስተረጉማሉ። አንዳንድ ጊዜ እህቶች በሚያስተረጉሙበት ወቅት መቀመጥ ወይም ከቆሙ ደግሞ ፊታቸውን ወደ አድማጮች ሳይሆን ወደ ተናጋሪው አዙረው ማስተርጎም ይችሉ ይሆናል።
በመሆኑም ወደ ንግግር ቋንቋ የምታስተረጉም እህት ራሷን መሸፈን ላያስፈልጋት ይችላል።ከዚህም በተጨማሪ ንግግሮች ወደ ምልክት ቋንቋ በሚተረጎሙበት ወቅት በምንጠቀምበት ቴክኖሎጂ ላይ ለውጥ በመደረጉ አስተርጓሚው ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት ይበልጥ ትኩረት ሊደረግበት ይችላል። ወደ ምልክት ቋንቋ የሚያስተረጉመው ሰው አብዛኛውን ጊዜ በትልቅ ስክሪን ላይ የሚታይ ሲሆን ተናጋሪውን ግን አድማጮች አይመለከቱት ይሆናል። እነዚህን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ምልክት ቋንቋ የምታስተረጉም እህት አስተርጓሚ እንጂ ተናጋሪ እንዳልሆነች ለማሳየት ራሷን መሸፈኗ ተገቢ ይመስላል።
ይህ ለውጥ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚቀርቡ ክፍሎችና ሠርቶ ማሳያዎች እንዲሁም በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በአገልግሎት ስብሰባና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት አድማጮች የሚሰጧቸው ሐሳቦች ወደ ምልክት ቋንቋ በሚተረጎሙበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ የሚነካው እንዴት ነው? በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ወደ ምልክት ቋንቋ የምታስተረጉም እህትም ራሷን መሸፈን ይኖርባታል? ስብሰባውን የምትመራው ይህች እህት እንዳልሆነች ሁሉም አድማጮች መገንዘብ ስለሚችሉ እህት በአንዳንድ ሁኔታዎች የግድ ራሷን መሸፈን ላያስፈልጋት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አድማጮች የሚሰጧቸውን ሐሳቦች፣ እህቶች የሚያቀርቧቸውን ክፍሎች ወይም ሠርቶ ማሳያዎችን በምታስተረጉምበት ጊዜ ራሷን መሸፈን አያስፈልጋትም። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሱት ስብሰባዎች ላይ ወንድሞች የሚያቀርቧቸውን ንግግሮች ስታስተረጉም፣ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለሚመራው ወንድም ስታስተረጉም አሊያም በምልክት ቋንቋ መዝሙር ስታዘምር ራሷን መሸፈን ይገባታል። አንዲት እህት ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ ወንድሞች፣ እህቶች፣ ልጆችና ሽማግሌዎች የተናገሩትን ማስተርጎም ያስፈልጋት ይሆናል። ከዚህ አንጻር እህት ስብሰባው በሚካሄድበት ጊዜ በሙሉ ራሷን መሸፈኗ ይበልጥ አመቺ ሊሆን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን ከመሸፈናቸው ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 209 እስከ 211 ተመልከት።